>

Friday, 26 December 2014

ነገረ ቤተ ክርስቲያን-- ክፍል አንድ



 ነገር የሚለው ቃል ሲተረጎም - ወግ፣ ታሪክ፣ መልዕክት፣ ሥርዓት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፤  ነገረ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የቤተ ክርስቲያንን ጉዞ የሚገልጽ ወግ፣ ታሪክ፣ መልዕክት፣ ሥርዓት፣ ሕግ የሚነገርበት ትምሕርት ማለታችን ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለሦስት ነገሮች እንነጋገራለን፤ ስለሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ካሕናት አገልግሎትና ስለ ምዕመናን እንመለከትበታለን፤ ቤተ ክርስቲያን የሚለውንም ቃል ስንተረጉመው እነዚህን ሦስት ትርጉሞች ነውና የሚሰጠን፡፡
      በዚህም ርዕሰ ጉዳይ ውስጥ ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አተካከል ጀምሮ ምዕመናንና ካህናት አንድ ሆነው የሚወርሷት፣ እኛ ሁላችንም ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት እስክትሰጠን ድረስ ያለውን የሰው ልጆች ሥርዓተ አምልኮ አፈጻፀም በተመለከተ አባቶቻችን የነገሩንን፣ በመጻሕፍት ጉያ ውስጥ የተደበቀውን መንፈሰ እግዚአብሔርን ገላጭ በማድረግ እያወጣን እንነጋገራለን፤
      ለዚህም ጽሑፋችን በዋናነት ፍትሐ ነገሥትን ቋሚ ምስክር የምናደርግ ሲሆን ፈውስ መንፈሳዊንና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት በምንጭነት እንጠቀማለን፤ መልካም ንባብ፡፡
በእንተ ሕንጼሃ ለቤተ ክርስቲያን
በዚህ ንዑስ ርዕስ ውስጥ ማየት የምፈልገው የቤተ ክርስቲያንን የአተካከል ነገር ነው፤
መምህራችን ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ጊዜ ፍጹም አንድነቷ ከሁሉ በላይ የሆነች ምዕመንን ከተበተነችበት ሰብስቦ አንድ መንጋ እንዳደረጋት እናውቃለን ምዕመናን ከመሰብሰብ አስቀድሞ የሠራው ሌላ የቤተ ክርስቲያን ሥራ የለም፤ ከሰማያዊነት ወደ ምድራዊነት ያመጣውም የምዕመናን ከልጅነት በረት ወጥቶ በምድረ በዳ እረኛ እንደሌላቸው መንጋዎች ተበትነው የአራዊት ንጥቂያ የጠላት መሳለቂያ መሆናቸው ነውና፤ ስለዚህም የመጀመሪያውን ሥራውን የጠፉትን በጎች ፍለጋ አደረገ፡፡ በዚህ የጠፉትን የመፈለግ ወቅት የሰበሰባቸውን ምዕመናን የሚያከማችበት ስፍራ አልነበረውም፤ ምክንያቱም ለዚህ ለእግዚአብሔር መንጋ የሚሆን ንጹሕ ስፍራ ባለመኖሩ ነው፡፡

      ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ፣ እንደ ሰው በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በሰው መካከል እየተመላለሰ የሚሠራቸው ሥራዎችን ጨርሶ ወደ ቀደመ አነዋወሩ የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ ለምዕመናን መሰብሰቢያ የሚሆን ቤትን አሳይቷቸው መሄድ ስለነበረበት ያደረገውን ተመልከቱ፤ አይሑድ ለገዛ ራሳቸው ጥቅም የማይገባ ሥራ እየሠሩበት ወደ ሚገኘው ቤተ መቅደስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን አስተካከለ፤ ከዚህ አስቀድሞ ጌታችን በተወለደበት ዕለት ለማደሪያ የሚሆን ቦታ የላቸውምና ድንግል የበኵር ልጇ ክርስቶስን የወለደችው በከብቶች በረት ነው ሉቃ 2÷7 የአባቱን ቤት ወንበዴዎች ወርሰውት የውንብድና ሥራ እየሠሩበት ነበርና በዚያ እንዳይወለድ ሥራቸውን ስለተጸየፈ ለመወለጃው የከብቶችን በረት መረጠ፤ እንደእውነቱማ ከሆነኮ በመለኮቱ፡- ሰማያዊ አባቱ የሚመሰገንበት በዚያም ተገኝቶ የሰው ልጆችን ጸሎት ሊቀበል ቃል የገባበት ቅዱስ ቦታ ነው  1ነገ 7÷16 በምድርም አባቱ ሰሎሞን የሠራው በሰማይም በምድርም የአባቱ ቤት ነው በዚህ ሊወለድ በተገባ ነበር፤ ዳሩ ግን ምን ይሆናል የአባቱን ቤት የያዙት ሌሎች ናቸውና ያንን ስፍራ ለመወለድ አልመረጠውም፡፡