>

Thursday, 9 June 2016

እርገት

የዛሬው እርገት በሥጋ የተደረገ እርገት እንጅ እግዚአብሔር በባሕርዩ ከዚህ ያለ ከዚያ የሌለ ሆኖ ከዚህ ወደዚያ ሄደ ማለታችን አይደለም፤ ሰው በሆነ ጊዜ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ማለታችን ከዚህ የሌለ በዚያ ብቻ ያለ ነው ማለታችን ሳይሆን ምድራዊነትን ገንዘብ አደረገ ማለታችን እንደሆነ ሁሉ አሁንም ወደ ሰማይ ወጣ ስንል በሥጋ ግብር መናገራችን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ ልንረሳው እማይገባ ዋናው ነገር የሥጋ እርገት የቃል ርደት የተፈጸመው በማኅፀነ ማርያም መሆኑን ነው ለዚህ ነው ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ ‹‹ ምዕራግ እምድር እስከ ሰማይ፤ ከምድር ወደ ሰማይ መውጫ መሰላል ሆይ..›› ብሎ ማመስገኑ፡፡ ጌታችንም ከእርገት አስቀድሞ በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ፤ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም›› ዮሐ 3÷13 ብሎ ያስተማረው እርገት በማኅፀነ ማርያም ስለተፈፀመ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ከሆነ የዛሬው እርገት ምንድነው? ብሎ የሚጠይቅ ቢኖር



ዛሬ ስለሁለት ነገር ቤተ ክርስቲያናችን የእርገትን በዓል ታከብራለች፡-
1.     በሥውር የተፈፀመውን እርገት በግልጥ ለማሳየት ነው
በማፀነ ማርያም የተፈጸመውን ምሥጢር ከእናቱ በስተቀር ሌላ ማን ሊያውቀው ይችላል፤ ይሄ ከሁሉም ፍጡራን የራቀ የረቀቀ ምሥጢር ነበር እንዲያውም ቅዱስ አትናቴዎስ ‹‹ወአልቦ ዘአእመረ ምጽዓቶ ለቃል እምእለ ሀለው ይቀውሙ በአርያም፤ በሰማዩ ቤተ መቅደስ ከሚያገለግሉ ባለሟሎቹ የጌታን ወደ ዓለም መምጣት ያወቀ ማንም አልነበረም›› ብሎ ነው የሚገልጠው፡፡
ነገር ግን ዛሬ ወደ ሰማይ ያረገውን ጌታ ‹‹ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ እግዚአብሔር በእልልታና በመለከት ድምጽ ዐረገ›› መዝ 46÷5 ተብሎ በይባቤ መላእክት ማረጉ እንደተነገረለት ሁሉ በማኅፀነ ማርያም ባደረም ጊዜ ሰው ለሆነው አምላክ ምስጋና ከሰማያውያንና ከመሬታውያን ቀርቦለታል፡፡
2.     ዳግም ተዋርዶ በሌለበት ዘለዓለማዊ ክብር የሚኖርበት ጊዜ እንደደረሰ ለማስረዳት ነው
በዚህ ዓለም ሳለ ጲላጦስ ፈረደበት፣ ሊቃነ ካህና ዘበቱበት፣ የአይሁድ ጭፍሮች ምራቃቸውን ተፉበት፣ በጠቅላላው እስከ መስቀል ሞት ድረስ የታዘዘ ሆነ ከእንግዲህ ግን እንዲህ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ገብአ ኀበ ስብሐቲሁ ወክብሩ፤ ወደ ቀደመ አነዋወሩ ተመለሰ›› ትለዋለች መሞት መታመም መራብ መጠማት መድከም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሉበትም ማለቷ ነው፡፡ እኛ በዚህ ምድር ሳለን ያለንበት ዓለም ዓለመ ሥጋ ስለሆነ ነፍሳችን ሥጋን መስላ ትኖራለች በወዲያው ግን ዓለመ ነፍስ ስለሆነ ሥጋችን ነፍሳችንን መስላ እንድትኖር የጌታችንም በዚህ ዓለም ሳለ መለኮቱ ሥጋውን መስሎ የባሪያውን መልክ ይዞ አየነው በወዲያው ግን ሥጋ የጌታውን መልክ ይዞ በፍጹም ባሕርያዊ ጌትነት እናየዋለን እንጅ ከእንግዲህ በትህትና ወደ እኛ አይመለስም ስትል ነው፡፡
በእውነት ይህ ቀን የቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ የተስፋ ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም እኛም እሱ ወዳለበት እንደምንሄድ እናምናለንና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እምነታችንን አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ነን›› እብ 3÷14 እንዳለ የእርሱን መንግሥት ለመውረስ ወደዚያ እሱ ወዳለበት እንሄዳለን፡፡ በዚያውስ ላይ ‹‹መዝገብህ ባለበት ልብህ በዚያ ይኖራል›› ማቴ 6÷21 አይደል የተባለው የቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ በስተቀር ሌላ ምን መዝገብ አላት፤ አባ ጊዮርጊስ ስለዚህ የተናገረው በእውነት ድንቅ ነው ‹‹መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ፤ ሌባ የማያገኘው መዝገባችን›› ብሎ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን መዝገብ እንደሆነ ይናገራል፤
እናም ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ልቧን መዝገቧ ክርስቶስ ባለበት ታኖረው ዘንድ ‹‹በሰማይ የሀሉ ልብክሙ ልባችሁ በሰማይ ይሁን›› የሚለውን ቃል እየነገራችው እጁንም አንሥቶ እየባረካቸው ወደ ሰማይ ሲወጣ ተመለከትነው አባቶቻችንም ሐዋርያት ‹‹እወ የሀሉ በሰማይ ልብነ አወን እውነት ነው ልባችን ባንተ ዘንድ በሰማይ ይሁን›› እያሉ አሻቅበው በትኩረት ተመለከቱት ፡፡ ሥራ 1÷11
ከዚህ ቀን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ዓለምን ድል ነሥታ መኖሪያዋ በሰማይ እንደሆነ ተረጋገጠ ያውም ደሞ በአርባኛው ቀን ማድረጉ በአርባ ቀን በሚገኝ ጥምቀት ሰማያዊነትን ገንዘብ ታደርጋላችሁ ማለቱ ነበር፡፡ የቀድሞው ጸጋ በድካም የሚወረስ ስለነበረ አባቶቻን የተስፋይቱን ምድር የወረሱት በአርባ ዓመት ነበር እኛ ግን በአርባ ቀን ሆኖልናል፡፡
ጌታ ዛሬ አሳልፎ የሰጠው ሰው ይሁዳ በሀፍረት እየተመለከተው በክብር በሐዋርያት ጉባኤ መካከል ብርህት ደመና ተቀብላው ወደ ሰማይ ዐረገ ቤተ ክርስቲያንም ራሷ ክርስቶስ ባለበት በዚያ ልትኖር ጠላቶቿ አጋንንት በሀፍረት እየተመለከቷት በክብር ታርጋለች፤ ከዚያ በፊት ግን ቤተ ክርስቲያን በሁለት መንገድ ክርስቶስን መምሰል ይገባታል - በስቅለተ ልቡና እና በትንሣኤ ልቡና ነው፡፡ ስቅለተ ኅሊናና ትንሣኤ ኅሊና የሌለው ክርስቲያን ዕርገተ ኅሊና ላይ መድረስ አይችልም፡፡
ከከተማ ውጭ ማድረጉስ ስለምን ነው ካላችሁኝ ከዓለም ተለይታችሁ ብትፈልጉኝ እባርካችኋለሁ ማለቱ ነበር ይህን ምሥጢር ያየንባት የእጁን በረከት የተቀበልንባት ቢታንያ የተባረከች ትሁን፡፡ መጀመሪያም የትንሣኤን ምሥጢር ያንባት የአልዓዛር መንደር ናት አሁንም እርገቱን ያየንባት፡፡
እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ አደረሳችሁ!

1 comment: