>

Wednesday, 18 November 2015

ሦስቱ ስደታት

  
               ክፍል አንድ

በዚህ ምድር ላይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ እመቤታችን የከበረ ማንም የለም፤ ክብሯ ከምድራውያኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰማውያኑ ጋር ስንኳን ሊነጻጸር የማይችል ታላቅ ነው፤ ነገር ግን በዚህ ምድር እንደ እመቤታችን በመከራ የተፈተነ ደግሞ ማንም የለም፤ እንደ ሚታወቀው ይህች ዓለም ለእግዚአብሔር ሰዎች የፈተና መድረክ እንጅ የስጦታ ሰገነት አይደለችምና በነገር ሁሉ እንደ ሰማዕታት ተፈትናለች፡፡ ከልጅነቷ እስከ እለተ ሞቷ፣ ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ ዮሐንስ ሁሉም ያለፈችባቸው መንገዶች በእሾኽ የታጠሩ እንጅ የአበባ ምንጣፍ የተጎዘጎዘባቸው አልነበሩም፡፡
      በዚህ ሁሉ ፈተና በእመቤታችን ሕይወት ውስጥ አስቸጋሪው የፈተና ወቅት ያለፈው ጌታችን በተወለደ ማግስት በተነሣው ስደት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ጌታችን የመጣው ዓለምን እንደ ሰውነቱ ዞሮ ሊባርካት እንደ አምላክነቱም ሕይወትን ሊሰጣት ነውና ሰይጣን በክፉ ሀሳቡ ያረከሳትን ዓለም ለመቀደስ ኃጢአት ወደ በዛባቸውና በጣዖት በኃጢአት የተሰነካከሉትን ለማዳን ሰይጣን ሳያውቅ ባስነሣቸው ክፉ ሰዎች ምክንያት ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ግብፅ እንዲሰደድ ግድ ሆነ፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ በረከት ወደ ምድረ አፍሪቃ ተሸጋገረች፡፡
      የገሊላ ንጉሥና ሕዝብ ሳያውቁት በረከታቸውን ለሌላ ሕዝብ አሳልፈው ሰጡ፤ በነቢይ ‹‹ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱነ የተነሣ ጠፍቷል›› እንደ ተባለ የልደት እለት እነሱ ተኝተው ሳሉ በዚያች ሌሊት ከሩቅ ምሥራቅ የመጣው ሕዝብ በረከተ ልደቱን ተሳትፎ ተመለሰ፤ ዛሬ ደግሞ  እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከአህጉር ሁሉ መርጦ በመካካላቸው ቢወለድ ለተመረጡለት በረከት ብቁ ባለመሆናቸው በረከታቸውን እያሳደዱ መርገማቸውን አጨዱ፡፡ እጃችን ላይ ያሉ ግን ሳንጠቀምባቸው የሚያልፉ በረከቶች እንዳይኖሩ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡ ገሊላውያን በወቅቱ የነበራቸው ሀሳብ ከሀገር ሲያስወጡት ከሰውም ልብ የሚያስወጡት መስሏቸው ነበር፤ ውስጠ ምሥጢሩ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት፤ ያኔ ጌታ እንዲሰደድ ባይሆን ኖሮ ታላላቁን የግብፅ ገዳማት እነ ገዳመ አስቄጥስን፣ ገዳመ ሲሀትን  በሀገራችንም እነ ዋልድባን፣ ጣና ቂርቆስን ማግኘት ባልተቻለም ነበር፡፡ ይህን እግዚአብሔር እንጅ ሌላ ማን ሊያውቀው  ይችላል?
      በዚህ ወቅት ታዲያ የንጉሡ እናት የሰውና የመላዕክት እመቤት ድንግል ማርያም የደረሰባትን ፈተና ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም፤ አባቷ አዳም እናቷም ሔዋን የደረሰባቸው መከራ በሥጋም በነፍስም ከባድ ነበርና ለዚያ ማስረጃ እንዲሆን እመቤታችን ያለ ርህራሄ አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎችን አሳልፋለች የሰማዕታት እናታቸው ናትና በምትቀበለው መከራ ለሰማዕታት መንገድ ጠራጊ አደረጋት፡፡ እመ ብዙኃን የሚያሰኛትም አንዱ ይህ ነው እመ ብዙኃን የምትባለው ስለሦስት ነገር ነው:-

እመ መናንያን

እመ ሐዋርያት

እመ ሰማእታት በመሆኗ ነው።
የመናንያን እናት የምንላት በሦስት ዓመት እድሜዋ ወገኖቿን የአባቷንም ቤት ረስታ በቤተ መቅደስ ስለኖረች ነው አባቷ ዳዊት እንደተናገረ መዝ 44 ከቤተ መቅደስ በአስራ ሁለት ዐመቷ እንድትወጣ የተደረገ ቢሆንም እንኳን ወደ ወገኗቿ ለመሄድ አላሰበችም ንጉሡ እግዚአብሔር ውበቷን የወደደላት መናኒተ ዓለም ናትና፡፡
በቤተ መቅደስ እነ ሳሙኤልም ያደጉ ሲሆን የሷ ግን ይለያል ወደ ቤተ መቅደስ ከመጣች በኋላ እናትና አባቷ እግዚአብሐየር እንጅ ሰው አይደለምና በምናንያን ሕግ በእናትና በአባቷ አልተጎበኘችም፡፡ ታዲያ በዚህ ግብሯ እመ መናንያን እንላታለን፡፡
-እመ ሐዋርያትም የተባለች፡- ሐዋርያት ወንጌልን ተምረው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ወደ ዓለም ወጥተው እስከ ጽንፈ ምድር ሳይሰብኩ እሷ ግን ‹‹መንፈስ ቅዱስ ወደ አንች ይመጣል የልዑል ኃይል ይጸልልሻል ›› ተብላ ወንጌል ክርስቶስን በጀርባዋ አዝላ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ሀገራችን ድረስ ተጓዘች፡፡
- የሰማእታት እናት የምንላትም፡- ስደትን የጀመረች እሷ ስለሆነች ነው ስደት በተሳለ ስለት ተቀልቶ በነደደ እሳት ገብቶ መሞት ብቻ አይደለም ስደትም ሰማእትነት ነው እንጅ፤ በዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ የነበሩ ሰማእታት ሁለት አይነት ነበሩ አንዳንዶቹ ሃይማኖታቸውን እንዳያስክዳቸው እንዳይገላቸውም ሲሰደዱ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹በሥጋችሁ የሚገሏችሁን አትፍሯቸው›› ማቴ 10 የተባለውን ይዘው ‹‹ታበጽኃኒኑ ዛቲ ፍኖት ኀበ ዲዮቅልጥያኖስ፤ በውኑ ይህች መንገድ ወደ ዲዎቅልጥያኖስ ታደርሰኛለችን›› እያሉ ለመታረድ ይገሠግሱ ነበር፡፡ በእርግጥ ትልቁ ሰማእትነት ራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው ከዚህ ሁሉ ጋራ በስደት ሰማእትነትን ተቀበለች፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ስታመሰግናት ‹‹እመ ሰማእታት መዋእያን፤ የአሸናፊዎች የሰማእታት እናት›› ብላ ታመሰግናታለች፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት እመቤታችን እመ ብዙኃን እየተባለች ስትጠራ ትኖራለች፡፡
 ይልቁንም በስደቷ ወቅት የገጠማት ፈተና ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ተራበች ፣ ተጠማች፣ ሌሊትና ቀን እንቅልፍ በማጣት ተፈተነች፣ ማረፊያ እንደ ሌላት ዖፍ በዛፍ ስር ተጠግታ አደረች፣ በዘመድ የከበሩ የኢያቄምና የሐና ልጅ የሚያውቃት ሰው አጥታ እፍኝ ውኃ ለልጇ መስጠት ተሳናት፤
      ይገርማችኋል! ምድርን መጠኑ በማይታወቅ ውኃ ላይ ያጸና ውቅያኖሳትን በእፍኙ የሚሰፍራቸው እርሱ ውኃ እንድታጠጣው እናቱን ተማፀናት፤ አባቱ አዳምና እናቱ ሔዋን በነፍስም በሥጋም ጥማት ነበረባቸውና ያን ለማራቅ እንደ መጣ ለማጠየቅ ውሃ ተጠማ፡፡ ሁሉን የሚያፅናና እርሱን ማን ሊያፅናናው ይችላል፤ ስለዚህ ማንም ቢሆን ኃዘኗን የተካፈላት የለም ምን አልባት አብረዋት ከተሰደዱት ከዮሴፍና ከሰሎሜ በስተቀር፡፡ እርሷ እመቤታችን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማለቷ አልቀረም‹‹አይቴኑ መልአክ ዘአብሠረኒ ብካይየ ይርአይ ወይርድአኒ፤ መከራዬን አይቶ ይካፈለኝ ዘንድ ያበሠረኝ መላክ ወዴት አለ›› ብላ ሙሾ እያወጣች እንባዋን ሽቅብ የረጨችበት ጊዜ ነበራት፤ ሊቃውንቱም የደረሰባትን መከራ ታላቅ መሆኑን ለመግለጥ‹‹ ነዓ ኤርምያስ እምአናቶት ለወለተ ዳዊት ታስቆቅዋ፤ የዳዊት ልጅ ድንግል ማርያምን እንደ ጥንቱ ሙሾ እያወጣህ ታላቅሳት ዘንድ ኤርምያስ ሆይ ከአናቶት እባክህ ና›› ብለው ይማፀኑላታል፡፡ኃዘኗ ከባድ፣ መከራዋ የማይለመድ ነበር፤ መከራን ያልለመደች፣ በቤተ መቅደስ በካህናቱና በሊቃነ መላዕክቱ ምስጋና ያደገች የነገሥታት ልጅ ስትሆን መከራውን እንዴት ልታውቀው ትችላለች፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተናገረው  ከፈተናው ጋር አብሮ መውጫውን ይሰጣልና መከራዋን ሲያበዛው ትዕግሥቷንም አበዛላትና በድል እንድትወጣው አደረጋት፤
      በተለይም በዚያ ወቅት ከሁለት መንገድ የሚመጣ ስጋት ነበረባት፤ አንደኛው ከሄሮድሳውያን በኵል ያለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሄሮድስ ልጆቻቸውን ያስፈጀባቸው ሰዎች ተከታትለው መጥተው ልጀን ይገሉብኛል ብላ ትፈራ ነበር፤ የልጇ ደም ያለ ዕለተ ዓርብ እንደማይፈስ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ ቢሆንም ቅሉ እሷ እንዴት ልታውቅ ትችላለች፤ ይልቁንም ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት ካደረችበት እንዳትውል፣ ከዋለችበትም እንዳታድር በሚያስቸኩል ክፉ ስደት ሌሊትና ቀን እናቱ ድንግል ማርያም እግሯን የምታሳርፍበት እንዳጣች ዖፍ ዕረፍት በማይሰጡት የግብጽ በረሃዎች ተንገላታች፡፡ እንዲህ ሆና ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አስቆጠረች፤
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት አስቸጋሪ ወቅቶች አሉ፤ ሁሉም ተመሳሳይ ዕድሜ ነው ያላቸው አርባ ሁለት ወራት ናቸው በሰው ሕይወት ውስጥ ሁሉም የፈተና ወቅቶች ናቸው፡፡ ሁለቱ አልፈዋል አንዱ ገና ወደፊት የሚጠብቀን አስቸጋሪ የመቅሰፍት ወራት ነው፡፡
Ø  ዘመነ ኤልያስ 1ነገ 18÷2
Ø  ዘመነ ስደታ ለማርያም ማቴ 2÷13-23
Ø  ሐሳዊ መሢሕ የሚነግሥበት ዘመን ናቸው፡፡ራእ 13÷5-18
 
ከነዚህ አስቸጋሪ ዘመናት የደረሰ ሰው ሁለት ነገር ይጠብቀዋል፤ አንድ ክህደት፣ ሁለት ሰማዕትነት ነው፤ ከነዚህ አንዱን መቀበል ግድ ሳይሆንበት አይቀርም፡፡ እመቤታችንም በዚህ ጉዞዋ የደረሰባት ይሄው ነው፤
በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡ ብዙ የስደት ታሪኮች አሉ አብርሃም ከካራን ወደ ከነዓን ከከነዓን ወደ ግብጽ ያደረገው ስደት፣ ይስሐቅም ያዕቆብም ወደ ግብጽ ያደረጉት ስደት ጎልቶ የሚጠቀስ ስደት ነው ዘፍ 12÷1፣13፤           ሁሉም የተሰደዱበት ምክንያት ረሀብ ነበር፤ ነገር ግን ከላይ የጠቐስናቸው ሦስቱ ስደቶች ከነዚህ የተለዩ ናቸው በረሀብ ምክንያት የተደረጉ ስደቶች ስላልሆኑ ነው፡፡ ሦስቱም ስደቶች ስለ እግዚአብሔር ክብር እና እውነትን ለትውልድ ለማትረፍ የተደረጉ ስደቶች ናቸው፡፡
ሦስቱን ስደቶች የሚያመሳስሏቸው ዐበይት ነጥቦች፡-
1.እውነትን ለማትረፍ የሚደረጉና የተደረጉ ስደቶች ናቸው፤ ኤልያስ ኤልዛቤል ያጠፋችውን እውነት ለማስመለስ አስምቶ ጮኸ ማስመለስ ባይችል እስከ ጊዜው ድረስ እውነቱን እንደያዘ ተሰደደ፤ ኤልዛቤል በሦስት መንገድ እውነትን ገፋች፤
Fባሏን አክዓብንና ሌሎችንም ጣዖት እንዲያመልኩ ትገፋፋቸው ነበር በተለይም አክዓብ ጣዖት እንዲያመልክና ናቡቴንም እንዲያስገድል ክፋትንም እንዲያደርግ ምክንያት የሖነችው እርሷ ነበርች 1 ነገ20÷25፣16÷32
F ካህናተ ጣዖቱን እየቀለበች የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ግን ታሳድዳቸው ነበር ከእግዚአብሔር ነቢያት በግልጥ የሚታይ ኤልያስ ብቻ እስኪቀር ድረስ (እግዚአብሔር በድብቅ ያስቀመጣቸው አምስት ሺህ በኣልን ያልተከተሉ ነቢያት ሳይጨምር ማለት ነው( እሷ ግን በየእለቱ የምትቀልባቸው አራት መቶ ሃምሳ የጣዖት ካህናት ነበሯት፤ 1ነገ 18÷4-19
F የሀሰት መሳክርትን በማስነሣት ሰው ናቡቴን አስገድላለች የሀሰት ደብዳቤ ጽፋ ሽማግሌወቹን ሳይቀር አሳስታለች፤ 1ነገ 20÷5 በዚህ ምክንያት እንዲያውም ስሟ የክፉ ነገር ምሳሌ ሆኖ ቀረ፤ ራእ 2÷20 በነዚህ ሁሉ ነገሮች ያጠፋችውን እውነት ለማስ\ተበቅ የሚተጋው ኤልያስ በውስጡ የያዘው እውነት ከዐመጸና ሕዝብ ጋር እንዲኖር ባያደርገው ከከተማ ወጥቶ ተሰደደ ከነ እውነቱ የተወሰነለት ጊዜ እስኪደርስ በተራሮች ንቃቃት ውስጥ ተደብቆ ቆየ፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ከተማን ለቀው ሲሰደዱ ሀገር በረከትን ታጣለች በመጽሐፍ እንደተባለው በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነውና እነርሱን ተከትላ በረከታቸው ትሄዳለች በእርግጥ ኤልዛቤልና አክዓብ በኤልያስ በረከት የመባረክ እድል የሌላቸው በመሆናቸው እንዲሰደድ አድርጎታል ደብቆ ካኖራቸው አምስት ሺህ ነቢያት ጋር አድርጎ ባላተረፈውም ነበር? ቁም ነገሩ በኤልያስ በረከት ሊባረኩ የሚገባቸው ሌሎች ሰዎች ስለነበሩ ነው ኤልያስ ባይሰደድ የሰራፕታዋ መበለት እንዴት በእግዚአብሔር መጽሐፍ ልትመዘገብ ትችላለች? በእግዚአብሔር መጽፍ ካለመመዝገብስ በላይ ምን የሚያስቆጭ ነገር አለ? አንዳንድ ጊዜ ያንዱ ጉዳት አንዱን ሊጠቅም ይችላል የእርሱ ስደት ለዚች ሴት በረከት ሆኗታል፤ ሙት የሚያነሣውን እውነት ይዞ ነውና ወደ ቤቷ የተሰደደው የሞተ ልጇን ከሞት ጉያ ነጥቆ በማውጣት በአክዓብ ከተማ በሰማርያ እንኳን ያላደረገውን ድንቅ ተዓምር አደረገ በጠቅላላው እሷ እሱን በመቀበሏ ተባርካለች እሱም ወደ እርሷ ቤት በመግባቱ ከዚያ በፊት ያላደረገውን ከዚያም በኋላ የማይደግመውን ሥራ እንዲሠራ አድርጎታል፡፡
እመቤታችን እውነት ክርስቶስን ከገሊላዊው ንጉሥ ፊት ማስቀመጥ አይገባምና ብላ ይዛው ተሰደደች፤ እንቁን በእሪያዎች ፊት ማስቀመጥ ይሰብሩት ካልሆነ ሌላ ምን ያደርጉታል ብላ ይዛው ሄደች፤ እውነትን የያዘ ሰው ከዐመጸኞች ጋር ካልሆነ ከሁሉም ፍጥረት ጋር ተስማምቶ ይኖራልና ከእንስሳት እስከ እጸዋት ድረስ ግዕዛን የሌላቸው ሥነ ፍጥረታት ሳይቀር በየ መንገዱ አስተናግደዋታል፤ የሔሮድስ ጭፍሮች በደረሱባት ጊዜ በሆዱ የሸሸጋትን ሾላ፣ በድርሳነ ዑራኤል እንደ ተመዘገበው አገልጋዩአ ዮሴፍን የተሸከመላት የምድረ በዳ ግሩም አንበሳ፣ በጣና ባሕር ላይ ጀልባ ሆኖ ያገለገላት ድንጋይ (ዛሬም በጣና ቂርቆስ ገዳም የሚገኝ ድንጋይ ነው እነዚህ ሁሉ አከበሯት ሰዎች ብቻ ያሳድዷት ነበር፤ እነሩ ለበረከት አልታደሉምና ነው እንጅ የእመቤታችን መሰደድስ ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ውኃን አስገኝቷል፤ ድውያን እንዲፈወሱ አድርጓል፤ ጣዖታተ ግብጽን አስደንግጧል፤ እነሱ እንቢ ያሉትን በረከት እነ ገዳመ አስቄጥስ፣ እነ ጣና ቂርቆስ፣ እነ ገዳመ ዋልድባ ተካፈሉት በረከታቸውን እንደወሰዱባቸው ይታወቅ ዘንድ ዛሬ እንደነዚህ የቅዱሳን መናኸሪያ የሆኑ ታላላቅ ገዳማት በኢየሩሳሌም አይገኙም፤ ምን አልባትም ጌታችን እየተመላለሰ ካስተማረባቸው ጥቂት ቦታዎች በስተቀር፡፡ ጌታችን በእናቱ ጀርባ ሆኖ ባይሰደድ ኖሮ ሀገራችን በኪደተ እግሩ እንዴት ልትባረክልን ትችል ነበር? እንደ መላው ዓለም በደመ መለኮት ከመቀደሷ በተጨማሪ የእመቤታችን የቃል ኪዳን ምድር የሆነችውም አምላካችን ክርስቶስ ክብር ይግባውና በስደት ወደዚህ በመጣ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ከመስቀሉ ሥር የእናትነት ቃል ኪዳን እስቀድሞ ድንግል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የቃል ኪዳን እናታችን ነበረች፡፡
አረጋዊ መንፈሳዊ ‹‹ንዑ ንርዓዮ ለወልደ መንክራት፤ አስደናቂ ነገሮች የሚታዩበትን ልጇን ኑ እንየው›› አሉ ብሎ የተናገረው ለኢትዮጵያ ሰዎች ሳይሆን አይቀርም ምክንያቱም በሄደችበት አካባቢ ሰዎቹ ተሰብስበው እያት እያት ለማለት በግእዝ ቋንቋ ረአያ ረአያ ተባብለው ነበርና የሀገሩም ስም እስከ ዛሬ ራያ ተብሎ ቀረ ብለው አበው ይተርካሉ፡፡ ድርሳነ ዑራኤልም እንደመዘገበው በንጉሥ ባዚን ዘመነ መንግሥት ንጉሡና ሊቀ ጳጳሱ ከነ ሰራዊታቸው በታቦተ ጽዮን ፊት ቆመው መጽሐፈ ኢሳይያስን ሲያነቡ በእለቱ የተነበበው ‹‹ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ›› ኢሳ 7÷14 የሚለው ነበር እመቤታችንም በስደት ወደዚህ ቅዱስ ሥፍራ ገብታ በልጇ የባሕርዩ መሠወሪያነት ተሠውራ በቤተ መቅደስ ተቀምጣ ትሰማቸው ነበርና አንብበው ሲጨርሱ መላኩ ዑራኤልን ልካላቸው ያነበቡት የነቢይ ቃል እንደተፈጸመ አስረድቷቸዋል፡፡ በዚያች እለትም ለንጉሡና ለሰራዊቱ ለጳጳሱና ለሊቃውንቱ ብዙ በረከትን ሰጥታ ነው የሄደችው፡፡ የስደቷ ተቀዳሚ ምክንያት እውነትን ከሞት ለማትረፍ ነውና የያዘችውን እውነት የመላክ ሰባኪ እያስነሣች ለሚገባቸው ሰዎች እያስረዳች ስደቷን ቀጠለች፡፡
ሦስተኛውም ስደት ቤተ ክርስቲያን በሀሳዊ መሲህ ምክንያት የምታደርገው ስደት ሲሆን እውነትን ጠብቆ እውነተኛውን ዓለም መንግሥተ ሰማያትን ፍለጋ የሚደረግ ስደት ነው፡፡ ያን ጊዜ የሚሰደዱ ምእመናን በሚሄዱበት ሁሉ በረከትን እየሰጡ ይሄዳሉ፡፡
2. ሦስቱም ስደቶች በግፈኛ ነገሥታት ክፉ ፍርድ ምክንያት የተደረጉ ናቸው፡- ብዙ ዐመጸኛ ነገሥታት በዓለም ላይ ነበሩ እነ ናቡከደነ ፆር፣እነ ፈርዖን እነ ስልምናሶር ነገር ግን ሁሉም ከሄሮድስና ከአክዓብ ተለዩ ናቸው እነዚያ ሰውን ሰብስበው ወደ ሀገራቸው የሚወስዱ ናቸው እንዲያውም ፈርዖን ስደተኞችን እስራኤልን አልለቅም በማለት ነው የሚታወቀው፤ እነዚህ ደግሞ በተቃራኒው ሰውን ከሀገራቸው አስወጥተው የሚያሳድዱ ናቸው፡፡ እውነትን የያዘ ዳኛ በመጥፋቱ እነሱ ሊሰደዱ ሲገባቸው በአክዓብ ኤልያስ በሔሮድስ እመቤታችን ተሰደዱ፤ በመጨረሻም በሀሳዊ መሲህ ቤተ ክርስቲያን ትሰደዳለች፤ 
በዘመነ ስደቷ ሊቃውንቱ እመቤታችንን በሚያመሰግኑበት ሰቆቃዎ ድንግል ‹‹ሶበ ኮነ ፍትሕ በዝ ዓለም ዘከማኪ ስደት እምደለዎ ለሔሮድስ ከዐዌ ደም ወለኪሰ ነቢር ከማሁ ዘመኮንነ ጽድቅ እም፤ በዚህ ዓለም እውነተኛ ፍርድ ቢኖርስ ኖሮ ለደም አፍሳሹ ሔሮድስ እንዳንች ስደት ለአንች ደግሞ እንደ እርሱ በዙፋን መቀመጥ በተገባ ነበር›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዓለም እውነትን ባለማወቋ ፍርድ ሲዘዋወር ይታያል፤ አለቃ ገብረ ሐና አንድ ነገር ተናግረዋል ይባላል አንድ ሊቅ ካህንና ሌላ ቀለም የሸሸው ካህን አንድ ላይ ሲኖሩ አንድ ቀን ይጣላሉ ታዲያ ይሄ ቀለም ያላራሰው ሰው አንደበቱ ለስድብ ፈጣን ነውና ቶሎ ብሎ ሳይቀድመው ደንቆሮ ብሎ ብሎ ሊቁን ሲሰድበው ይሰማሉ አለቃ በመካከል ገብተው ሲገላግሉ አንድ ሰው ያያቸውና አለቃ ምን እያደረረጉ ነው ሲላቸው ‹‹ስም ተዘዋውሮ ወደ ቦታው እየመለስሁ ነው›› ብለዋል ይባላል፡፡ እና አንዳንድ ጊዜ ፍርድም ቢዘዋወር መልካም ነበር፡፡
3. የሦስቱም ስደታት እድሜ ተመሳሳይ መሆኑ፡- እነዚህ ስደታ ሁሉም ለሰባት መንፈቅ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሔር ሰዎች ሰባት የቀኖና መንፈቅ ናቸው፤ በዚያ በቀደመው ዘመን ኤልያስ የፈረሰውን የእግዚአብሔር መሰዊያ መልሶ የሠራው ሰባት መንፈቅ በስደት ቀኖናን ተቀብሎ፤ ለካ የኤልያስ ስደት ሞትን በመፍራት ከኤልዛቤል ፊት ለመሠወር የተደረገ አይደለም፤ አባቶቹ የሠሩት የእግዚአብሔር መሰዊያ ስለፈረሰ ነው እንጅ፡፡ ያ የሰባት መንፈቅ ቀኖናው ነው የኤልዛቤልን ጣዖት የቀጠቀተው አራት መቶ ሃምሳ ካህናቶጨዋን ያሳፈረው ቀኖናው አርባ ቀን ሳይበሉ ሳይጠጡ መጓዝንም የሚያካትት ነበረ፤ 1ነገ 19÷5 ይህን አድርጎ ሲመለስ ነው በከተማ ውስጥ ያለውን ሰይጣን የሚያሸንፍበት ኃይል ያገኘው፡፡ የተሰደደው ኤልያስ ዛሬ ደግሞ አጋንንትን የሚያሳድድ ሆነ፡፡

ጌታም በእናቱ በእመቤታችን ጀርባ ሆኖ ባደረገው የሰባት መንፈቅ ስደት በመሥዋዕተ ኦሪት ፋንታ መሥዋዕተ ወንጌልን ተክቶ ቤተ ክርስቲያን ከምኩራበ አይሁድ ልቃ በመላው ዓለም እንድትታይ አደረጋት ሰይጣንን ከሰውልጆች ልብ ለማሰደድ የተደረገ ስደት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በሰው ልብ ውስጥ እንድትኖር ያደረጋት ያንጊዜ ነው፤ በሰባት መንፈቅ ስደት የተሠራችው የእግዚአብ\ሔር ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዓለም ጉዞዋን የምታጠናቅቀውም በሀሳዊ መሢህ ምክንያት በሚመጣባት የመጨረሻ የሰባት መንፈቅ ስደት ነው፤ በምድር ያለችው የእግዚአብሔር መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ከሰባት መንፈቅ ስደት በኋላ እንደ ተገኘች ፍጥረት በተስፋ እያንጋጠጠ ‹‹ትምጻዕ መንግሥትከ›› የሚላት ሰማያዊቷ የእግዚአብሔር መንግሥትም የምትመጣው ከሰባት መንፈቅ ስደት በኋላ ነው፤ ከዓለም የተሰደደ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳል፡፡

6 comments:

Anonymous said...

እግዚአብሄር ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሰማልን በህይወት በፀጋ ይጠብቅልን!

ytamene said...

ቃለ ህይዎት ያሰማልን። በርቲ አባታችን።

Unknown said...

ቃለ ህይወት ያሰማልን

Getaneh Kassie said...

ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።

Anonymous said...

በዚህ የማያውቁት እየጻፉ የሚያውቁት ሳይጽፉ ቀርተው እውነት በተጣመመበት ዘመን እንደ እርሶ አውቆና ጠንቅቆ የሚጽፍ ሊቅ ማግኘት መታደልም ጭምር ነውና ይበርቱ እንላለን። በተረፈ ከዚህ ገጾት በተጨማሪ በየአውደምህረቱ የሚያስተምሯቸው አንጀት አርስ ትምህርቶት በመጽሐፍ መልክ ቢያስቀሯቸው ክዛሬ አልፈው የነገውን ትውልድ ለማነጽ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸል ብዬ አምናለሁ። ፈጣሪ እረጅም እድሜ ከበለጠ ጸጋ ጋር ያድልልን።

Unknown said...

ቃለ ህይወት ያሠማልን