ይህ ጉዳይ ለብዙ ዘመናት አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል፤ አንዳንዶችን እስከመቃብር ድረስ እንዲሸኙም ምክንያት
ሳይሆን እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ ይህች ዓለም የራሷ እንኳ ጉዳይ ሲነገራት ቶሎ መረዳት የማትችል ስለሆነች ስለ ራሷ
ሰዎች የደረሱበትን ቢነግሯት አይሆንም ብላ ገደለቻቸው፤ ለነገሩ ስለዝግመተ ለውጥ እያወሩ አዝጋሚ ሳያደርጓት የቀሩ
አይመስለኝም፤ ነገሮች ሁሉ ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ከዞረች በኋላ ነው የሚዞሩላት ይህም ማለት አንድ ዓመት ሙሉ ፊቷን
የማታሳያቸው ፍጥረታት አሉ ማለት ነው፤ ነገር ግን የምትፈልገውን እስክታገኝ ድረስ በቀን አንድ ጊዜ በፀሐይ ፊት ሳትዞር ውላ
አታውቅም፤ የምትፈልገውን ቀላውጣ፣ ለፀሐይ ፊቷን አስመትታ ሌሊቱን ደግሞ ከሌላው ወዳጇ ከጨለማ ጋር ታድራለች፤
የሚገርመው! ቀን እኮ በፀሐይ ፍቅር ተቃጥላ፣ የቁንጅናዋን ጉንጮች ተራሮቿን አክስላ ስትመለከቷት ከፀሐይ ጉያ መውጣት የማትችል
የፀሐይ ፍቅረኛ ትመስላለች፤ ወዲያውኑ እጆቿን ለጨለማ ስትዘረጋ ደግሞ ጊዜ አይወስድባትም ጨለማው ሲመጣም ሁለንተናዋን ለጨለማ
አስገዝታ በፀሐይ ፍቅር መቃጠሏን ረስታ ፍፁም ጨለማውን መስላ ዓለሟን ስትቀጭ ታነጋለች፤
አይገርማችሁም! ፀሐይ ዘወር ብሎ እስኪመለስ እንዴት ፈጥና ቀዘቀዘች?