እንኳን ለብርሃነ ልደቱ ወጥምቀቱ አደረሳችሁ
በእለተ
ልደቱ በመላእክት ምስክርነት የታየው ጌታ በእለተ ጥምቀት ደግሞ በሰማዩ አባቱ ምስክርነት፣ በባሕርይ ሕይወቱ መንፈስቅዱስ ገላጭነት
ሰማያዊ ልደቱን አስረዳ፤ እንደ ሰውነቱ ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በሔኖን ወንዝ ዳርቻ አንድ ሌሊት ቆሞ ከሕዝቡ መካከል ከዮሐንስ በቀር
የሚያውቀው ሳይኖር አደረ፤ ይገርማል! ከብዙ ሺህ ዓመት በፊት ቃኤል ወንድሙን አቤልን የገደለበት ታላቁ ኃጢአት የተፈጸመበት ስፍራ
ነበር ዛሬ ደግሞ ‹‹ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኩሎ ጽድቀ፤ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ማቴ 3÷15 ተብሎ ታላቁ
ጽድቅ ተፈጸመበት፡፡ አመጣጡ ጥልን ለመግደል፤ የአባቶቹን ደም ለመመለስ ነውና ነፍሰ ገዳዩ ሰይጣን ደማችንን ማፍሰስ በጀመረበት
ስፍራ ላይ ቆሞ ጽድቅን ሊፈጽም እንደ መጣ በግልጥ ተናገረ፡፡
እንደ
አምላክነቱ ዮርዳኖስ ሸሸችለት ከሰው ልጆች ኃጢአትን የሚያስወግደው በጥምቀት ነውና ያ እስኪሆን ድረስ ዮርዳኖስ ለጊዜው ወደ ኋላዋ
ገባች፤ የሚወርደው ውሃ እንደ ድንጋይ ክምር ሆኖ ከላይ ተከመረ ከታች ያለውም ውሃ ወርዶ ሲያልቅ፣ ከላይ ያለውም ሲቆም አጥማቂው
ዮሐንስና የሚጠመቀው ጌታ ወደ ባሕሩ ገባ እንዲህ በማድረጉ ካለፈውም ከሚመጣውም ትውልድ ኃጢአትን እንዳስወገደለት አስረዳን፡፡ ዮርዳኖስ
በእሳት ቅጥር ተቀጠረች፤ እሳቱ የመንፈስ ቅዱስ
ምሳሌ ሲሆን ልጅነትን የሚያስገኘው ውሃ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሞላ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋራ አብ በደመና ሆኖ ሲናገር፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሲወርድ ለዘመናት ስውር ሆኖ የኖረው ሥላሴ በዚህ ጊዜ ግልጥ ሆኖ ተረዳ፡፡ ሃይማኖታችን በዮርዳኖስ ተገለጠ፤ ሰማይ ሲከፈት ታየ፤ ምድራዊው ሰው ሰማያዊ ሲሆን ሰማይም በምድር ላይ አንዳች ነገር ሳትደብቅ የሰወረችውን ምሥጢር አስረዳች፡፡
ምሳሌ ሲሆን ልጅነትን የሚያስገኘው ውሃ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሞላ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋራ አብ በደመና ሆኖ ሲናገር፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሲወርድ ለዘመናት ስውር ሆኖ የኖረው ሥላሴ በዚህ ጊዜ ግልጥ ሆኖ ተረዳ፡፡ ሃይማኖታችን በዮርዳኖስ ተገለጠ፤ ሰማይ ሲከፈት ታየ፤ ምድራዊው ሰው ሰማያዊ ሲሆን ሰማይም በምድር ላይ አንዳች ነገር ሳትደብቅ የሰወረችውን ምሥጢር አስረዳች፡፡
ባርነት
እንኳን አይገባው የነበረ የሰው ባሕርይ ዛሬኮ ‹‹የምወደው ልጄ……….››ተብሎ ከሰማይ ድምፅ መጣለት በምድር የሚኖር ፍጥረት ሁሉ
በትዕዛዙ እንዲኖር ‹‹እርሱን ስሙት›› ተብሎ ለመሬታውያኑ ፍጥረታት በሙሉ ትዛዝ ተሰጠለት፤ ‹‹አዳም ገብሩ ..ሔዋን አመቱ››
የሚለው ደብዳቤአችን መቀደዱን ለማብሰር እኮ ነው፡፡ ጥንት በአባቶቻችን ዘመን ‹‹እግዚአብሔርም ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ አዘነ››
ዘፍ 6÷6 የተባለው ቀርቶ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ………›› ተብሎ ተነገረለት በእውነት ሳይገባን ታላቁ የእግዚአብሔር ምህረት የተገለጠበት
ቀን ነውና የመገለጥ ቀን እንለዋለን፡፡
ያኔ በዚያ መገለጥ ባልነበረበት ዘመን የነበሩ የእግዚአብሔር ነቢያት አንድ ነገር እንዲህ ሲሉ
ጠየቁ ‹‹አባቴ ሆይ እንጨቱና እሳቱ ይኸው፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው?›› አባት ከልጁ እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲመጣበት ጥያቄውን በጥያቄ እንዲህ ሲል
ይመልስለታል ‹‹ልጄ ሆይ! የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ዘፍ 22÷7-8 አለው ይላል፤ ከዚህ በላይ ሌላ ምን ብሎ
ሊመልስለት ይችላል፤ ይሄኮ ዘመኑ ሲደርስ የሚመለስ ጥያቄ እንጅ በዚያ ዘመን የሚኖር ሰው የሚመልሰው ጥያቄ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም
በዘመናቸው የነበራቸው እንጨቱና እሳቱ እንጅ የመሥዋዕቱ በግ ግን አልነበራቸውምና ነው፡፡ መሥዋዕት ሊሠዋ የሚሄድ አባት ሲሆን መሥዋዕቱን
ግን ገና እግዚአብሔር ያዘጋጃል ብሎ የሚያስብ ነበር፤ ምን ያድርግ! ዘመኑ የመገለጥ ዘመን አልነበረምና የመሥዋዕቱን በግ ጠቁሞ
ማሳየት ሳይችል ቀረ፡፡ ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ ዛሬ በዮርዳኖስ ፈጣሪውን ሊያጠምቅ የተገባው ቅዱስ ነቢይ ዮሐንስ ሲያጠምቀው
‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየዐትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያሥተሰርይ የእግዚአብሔር በግ›› እያለ በማጥመቁ
መገለጥ ባልነበረበት ዘመን የተነሣውን ጥያቄ ሲመልሰው እናያለን፡፡ ዘመኑ የመገለጥ ነውና የመሥዋዕቱን በግ ጠቁሞ ማሳየት ችሏል፡፡
ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰውን እንዴት እንዳከበረ የተረዳንበት ቀንም ነው፤
ከዮሐንስ ዘንድ ቀራጮችና ክፉ ጭፍሮች እየመጡ ይጠመቁ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል ሉቃ 3÷10-14 እኒህ ሁሉ ተጠምቀው
ሲጨርሱ ነው ጌታችን ወደ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቀኝ ያለው፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረው ቀዳማዊ ቃል ደኀራዊ ሥጋን እንደተዋሀደ ለማጠየቅ
ከሁሉ በኋላ ወደ ውሃው መጣ፤ ከሁሉ በኋላ ቢመጣም ከሁሉ አስቀድሞ ወደ ዮርዳኖስ የገባ ግን ከእርሱ በስተቀር ሌላ ማንም የለም፡፡
ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ መንገዱ በዮርዳኖስ በኩል እኮ ነው፤ ኢያሱ ሕዝቡን የመራቸው የዮርዳኖስን ውሃ አቋርጠው በሚያልፉበት
መንገድ በኩል ነበር፤ ሀገሪቱ ያለችው ከዮርዳኖስ ማዶ ነውና ፤ ኢያ 3÷1
የድንግል ማርያም ልጅ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስም ህዝቡን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊመራ የመጣ የተስፋይቱ
ምድር የመንግሥተ ሰማያት አዲስ ኢያሱ ነውና ሕዝቡን ወደ ጽድቅ ሊመራ የዮርዳኖስን መንገድ ይዞ ተጓዘ ‹‹ኅድግ ምዕረሰ እስመ ይደልወነ
ከመ ንፈጽም ኩሎ ጽድቀ፤ አንድ ጊዜስ ተው ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› ማቴ 3÷15 ባለው ቅዱስ ቃሉ ይታወቃል፡፡ የተስፋይቱን
ምድር ለመውረስ ኢያሱም የመረጠው ዮርዳኖስን እንጅ ሔኖንን አልነበረም ስለዚህም መድኃኒታችን ክርስቶስ በነገር ሁሉ አባቶቹን ሊመስል
ይገባዋልና ደጋጎቹ አባቶቹ የተጓዙበትን ተከትሎ ሄደ፡፡