>

Thursday, 26 February 2015

ነገረ ቤተ ክርስቲያን--ክፍል ሁለት



ምዕራፍ
የቤተ ክርስቲያንን የሥራ ሁኔታ የምናይበት ምዕራፍ ሲሆን ሠለስቱ ምዕት በፍትሐ ነገሥታቸው እንደ ጠቀሱት ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቅዶ ካልሆነ እንዳትሠራ እና አገልግሎት እንዳይሰጥባት ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ በዘጠና አራተኛው አንቀጽ ላይ የተመዘገበውን ጠቅሰው እነሱም ተስማምተው አጽድቀውታል፤ አባቶቻችን ሐዋርያትም እንደዚሁ ዲድስቅልያ በተሰኘው ትምህርታቸው 15ኛውና 30ኛው ክፍል ላይ እንዳስተማሩት ቤተ ክርስቲያንን የሚሠራ ሰው ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ሠርቷት ቢገኝ እንደ በረት ልትቆጠር ይገባታል እንጅ ቅዱስ ቁርባንን ሊያቀብሉባት አይገባም ብለዋል፤
ምክንያቱም አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትሠራ ሊሟሉላት የሚገቡ ነገሮች ያሉ ስለሆነ ነው፡፡
1.     የሚያገለግሏት ልዑካን ሊሟሉላት ይገባል፡- የልዑካኑ ብዛት ትንሹ ቁጥር ሰባት ሲሆን ትልቁ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐቅም ነው፡፡ ይህም አስቀድሞ በነቢይ እንደተጻፈው ‹‹ጥበብ ሐነፀት ቤተ ወአቀመት ላቲ ሰባተ አዕማደ፤ ጥበብ ቤትን ሠራች ሰባት ምሰሶዎችንም አቆመች›› ምሳ 9÷1 ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡
ጥበብ የተባለችው በነቢዩ ዘንድ ወልድ ናት፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጥበብ ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ጥበብ››1ቆሮ 1÷24 በማለት የነቢዩን ቃለ ትንቢት ይተረጉምለታል ሌላው ሊቅ ቅዱስ ኢጲፋንዮስም በቅዳሴው ‹‹ጥበብሰ መድኃኒነ ውዕቱ ዘቤዘዎነ በጥብሐ ሥጋሁ ወተሳየጠነ በንዝኃተ ደሙ፤ ጥበብስ ማነው ትሉኝ እንደሆነ በደሙ መፍሰስ፣ በሥጋው መቆረስ ያዳነን መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው›› ብሏል፡፡ በሥጋ ተገልጦ ዓለሙ የተሠራበት ጥበብ ስለሆነ ነው፡፡
ቤት የተባለችውም በጥበበ እግዚአብሔር በክርስቶስ የተሠራችው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ሰባት ምሰሶዎች የተባሉትም ሰባቱ ልዑካኖቿ (ሰባቱ መዓርጋቶቿ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ፣ቆሞስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ንፍቀ ዲያቆን) ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን በነዚህ ምሰሶነት እንጂ ያለነዚህ የተሠራች ስላልሆነች ምሰሶዎቿ ተባሉላት፤ በመጽሐፍም ስለ መጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ልዑካን የተጻፈው ‹‹አዕማድ መስለው የሚታዩ..›› ገላ 2÷9 በማለት የአገልጋዮቿን የቤተ ክርስቲያን አዕማድነታቸውን ያስረግጥልናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን መሰብሰቢያ የምትሆነው እነዚህ ምሰሶዎቿ ጥሩ ተሸካሚ ሆነው የተገኙ እንደሆነ ነው፤ ያለ በለዚያ ግን ‹‹ዝናም ዘነመ ነፋስ ነፈሰ…….አወዳደቁም ታላቅ ሆነ›› ማቴ 7÷27 እንደ ተባለው ቤት ጽኑዕ አወዳደቅን ትወድቃለች፡፡ ባለቤቱ ክርስቶስም ቤተ ክርስቲያንን ሲመሠርታት ምሰሶዎቿ የሚሆኑ ሐዋርያትን አቆመላት ከዚያ በኋላ ያለውን ሐዋርያት እንዲሠሩ አዝዞ ነው ወደ ሰማይ ያረገው ማቴ 28÷19