አገልግሎታቸው
ሦስቱም ክፍላት የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው፤ እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ለማየት ያክል፡-
1. ቤተ መቅደስ፡- መቅደሱ ካህናቱ ህብስቱን ሥጋ አምላክ፣ ወይኑን ደመ መለኮት አድርገው የሚለውጡበት ውስጠኛው ክፍል ነው፡፡
ወደ ቤተ መቅደስ መግባት የሚፈቀድለት ማነው?
በዚህ ክፍል ሥልጣነ ክህነት ካላቸው ሰዎች በስተቀር ማንም እንዲገባ አልተፈቀደም፤ ከሊቃነ ጳጳሳት እስከ ዲያቆናት ድረስ ባሉ መዐርጋት ውስጥ ያሉ አገልጋዮች ገብተው ያገለግሉበታል፤ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ(ኤጲስ ቆጶስ)፣ ቆሞስ፣ ካህን፣ ዲያቆን፤ እነዚህ አምስቱ መዐርጋት ያሏቸው እንደ ጥንቱ ቢሆን ኖሮ ነገሥታቱም ክህነትን ከመንግሥ አንድ አድርገው የያዙ ስለነበሩ የእነርሱም መቆሚያ በዚህ ክፍል ነበር፡፡ (በሀገራችን ታሪክ ታቦት የሚሸከሙ ነገሥታት እንደነ አጼ ኢያሱ አድያም ሰገድ ያሉ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናልና፤ ከእሳቸው በፊትም ሌላ ካህን ንጉሥ መኖሩን አዝማሪው በገጠመው ግጥም መረዳት እንችላለን የተገለጠውን የአባቱን ቅስና ኢያሱ ገለጠው ታቦት አነሣና በማለት ከእሱ በፊት የነበረውን የአባቱን ቅስና ይገልጣል) ከዚህ በታች ያሉ ምንም እንኳን በእኛ ቤተ ክርስቲያን የተለመዱ ባይሆኑም በአንብሮተ እድ ሳይሆን በቃል ቡራኬ ብቻ የሚሰጡ የቤተ ክርስቲያን መዐርጋት አሉ ከቤተ መቅደስ ውጭ ባለው ተልዕኮ ካልሆነ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው መጸለይም ሆነ አገልግሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ለምን ከተባለ ይህ ስለክብረ ክህነት ነው፡፡ አምላካችን በዳግም ምጽአቱ የሚያደርገውም ይህንኑ ነው፤ አትናቴዎስ በቅዳሴው እንደተናገረው
በቤተ መቅደስ ውጥ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት
ሥርዓተ አምልኮ ከምንፈጽምባቸው ንዋያተ ቅድሳት ዋኖቹ የሚገኙት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው፤ ታቦት፣ መንበር እነዚህ ሁለቱ መሠዊያ ናቸው፤ ጻሕል፣ ጽዋዕ፣ እርፈ መስቀል፣ማኅፈድ፣ አውድ፣ አጎበር፣ እነዚህ ደግሞ የሥጋው የደሙ ማቅረቢያዎች ናቸው፡፡ ጽና፣ መስቀል፣ ልብሰ ተክህኖ እና እነዚህን የመሳሰሉት ሥጋውና ደሙን በማቅረብ ጊዜ የምን ገለገልባቸው ንዋያተ ቅድሳት ናቸው፡፡ (የእያንዳንዳቸውን ምሥጢራዊ ትርጓሜ ስለንዋያተ ቅድሳት በሚናገረው ክፍል እንነጋገራለን)
በቤተ መቅደስ የሚፈጸመው አገልግሎት
በዚህ ክፍል ውስጥ ለጸሎት ብቻ ካልሆነ በስተቀር መግባት እንዳይቻል የሥርዓት መጽሐፋችን ይከለክላል፡፡ ቤተ መቅደሱ የቀራንዮ ምሳሌ ነው፤ በቤተ ልሔም ዲያቀኑ ያዘጋጀው ህብስት ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል፤ በዚህም ክርስቶስ በቤተ ልሔም ተወልዶ በቀራንዮ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡን ቤተ ክርስቲያን ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የምታስተምርበት ነው፡፡