አሥሩ የማሕሌት ደረጃዎች
(ከባለፈው የቀጠለ…. )
4.
ማንሳት፡-
ማንሳት እምንለው መሪው ከመራ በኋላ በቀኝና በግራ ያሉ ሌሎች መምህራን ያንኑ እርሱ ያለውን ቃለ እግዚአብሔር ደግመው እንዲያነሡት ይደረጋል፡፡ ከመሪው ጋር ሦስት መሆናቸው ነው፡፡
ይህም፡-
4.1 ክርስቶስ የሞተው በሦስቱ (በጲላጦስ፣ በሔሮድስ፣ በቀያፋ) ፈቃድ መሆኑን የምንገልጥበት ምሥጢር ነው፡፡
አይሁድ ከሀና ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ ሲያመላልሱት አድረው እንደነበረ ለማስታዎስ ሊቃውንቱ ለእለቱ ተስማሚ የሆነውን ቀለም መርጠው በቀኝና በግራ እየተቀባበሉ ያነሡታል፡፡ በአንዳንድ ታላላቅ ቦታዎች ደግሞ ምልጣን ሲመራ መሪውና በቀኝ በግራ ያሉ አንሽዎች መስቀል እንዲይዙ ይደረጋል ይህም የሚሆነው መካከሉ የጌታችን ምሳሌ ስለሆነ በቀኝና በግራው አብረውት የተሰቀሉ ወንበዴዎችን ለማሳየት ነው፡፡
በቀኝና በግራ ያሉት እንዲያነሱት መደረጉ ጌታችን በተሰቀለበት እለት የሚያልፉት ህዝቡ ሁሉ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን እያዩ ይህ ምንድነው? ይህስ ምንድነው? እያሉ ይጠይቁ ስለነበር ነው፡፡ በመካከላቸው ያለው ክርስቶስም እንደነ እርሱ ወንበዴ የሚል ስም ወጥቶለት ነበርና ሊቃውንቱ ያንን ለመግለጥ አንዱን ቃለ እግዚአብሔር እየተቀባበሉ ያዜሙታል፡፡
4.2
የዳግም ምጽዓቱን ፍርድ ለማሳየት፡-
የጌታችን ዳግም ምጽዓት ቤተ ክርስቲያን የማያልፈውን ዓለም የምትቀበልበት እለት ስለሆነ በተስፋ ስትጠብቀው የምትኖር የተስፋ ቀኗ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በቃልና በተግባር ስትሰብከው ትኖራለች፡፡ በቅኔ ማኅሌት ያሉመምህራንም ጌታ ሲመጣ ያለውን የፍርድ ሂደት ለመግለጥ መሪው መርቶ እስኪጨርስ ድረስ ዝም ይላሉ ከዚያ በኋላ በቀኝና በግራ ያሉት መምህራን በየተራቸው እንዲያነሡ ይደጋል፡፡
በፍርድ ቀንም ይህ ሊሆን ግድ ነው፤
ማለትም በመላእክት አለቃ አዋጅ፣ በመለከትና በነጋሪትም ድምጽ የሞቱት ሁሉ ተነሥተው በማኅሌት እንዳሉ ሰዎች ሁሉ የትንሣኤያችን መሪ የሆነውን የክርስቶስን ድምጽ እየሰሙ ዝም ብለው ይቆያሉ ከእርሱ ቀጥለው በቀኝና በግራው ለፍርድ የተሰበሰቡ ሕዝቡ ይናገራሉ እሱ የሚናገራቸው በማቴ 25÷34-45 ያሉትን ቃላት ነው፤ እነርሱም ያንኑ መልሰው ለጻድቃንና ለኃጥአን እንደሚገባ አድርገው ይናገሩታል፡፡