የሰው ልጆች አባት አዳም ከተፈጠረ በስምንተኛው
ቀን ላይ ከባድ እንቅልፍ ውስጥ እንደነበረ በታላቁ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ እናነባለን፤ በተፈጠረ ማግስት የነበረውን
ታላቁን ሰንበት ካከበረ በኋላ እንዲሠራ የታዘዘውን ሠርቶ ሲጨርስ አዳም ብቻውን እንዳይሆን የፈለገው አምላክ ‹‹ሰው ብቻውን ይሆን
ዘንድ መልካም አይደለም …›› በማለት ብቻውን ዓለምን እንደ ማይሠራት አስቦ የምትረዳውን ሔዋንን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ሳለ ፈጠረለት፡፡
እንቅልፍ ምሳሌው የሆነ ሞትን የምታመጣ ሔዋን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ከነበረው አዳም ጎን እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ተፈጠረች፡፡
የእንቅልፍን ታሪክ ያወቅነው ከዚህ ጀምሮ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለባሕርያችን የሚስማማ ሆኖ እንድናርፍ በተሰጠን ሌሊት
ውስጥ እንቅልፍን ከዚህ ክፉ ዓለም ወጥተን ሌሎች በልባችን ያሰብናቸውንም ሆነ ያላሰብናቸውን የምናይበት አንዳንድ ጊዜም ያላወቅነውን
የምናውቅበት ሌላ ጊዜም ወደ ፊት በሕይወታችን ውስጥ ሊሆን በእግዚአብሔር የታሰበልንን ከመሆኑ አስቀድሞ የምናይበት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ነውና የምንወደውን ብርሃን ወስዶ በጨለማ ያሳርፈናል፤ እያየን እየሰማን ሊያደርግ
ያልፈለገውን ነገር በእንቅልፍ ውስጥ ሳለን ያደርግልናል፤ በሌላ አነጋገር ሌሊት ቀን የምንሠራውን የምናቅድበት እንቅልፍም የሕይወታችንን
መስመር የምናይበት የሕይወታችን አንድ ጠቃሚ ክፍል ነው ማለት ነው፤ የቀደሙት አባቶቻችን ታላቁን የክርስቶስን ሰው የመሆኑን ነገር
ያዩት በሦስት መንገድ ነው፡-
§ በራእይ
§ በሕልም
§ ግልጥ
ሆኖ ከእግዚአብሔር በሚመጣ መልእክት ነው
ያለ እንቅልፍ ሕልም የለም፤ ያዕቆብ በፍኖተ
ሎዛ ባያንቀላፋ ኖሮ ከምድር እስከ ሰማይ በተዘረጋው መሰላል ላይ የተቀመጠውን ንጉሥ እንዴት ማየት ይችል ነበር፤ ‹‹ዛቲ ይእቲ
ሆኅታ ለሰማይ ዝዬ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር፤ ይህች የሰማይ ደጅ ናት በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ይሠራል›› ብሎ መናገርን
እንዴት ሊያገኝ ይችላል፤ በእንቅልፉ ውስጥ ያዕቆብ ወደ ፊት የሚሆነውን አይቶ ተናገረ ከአርባ ስምንቱ የአይሁድ ምኩራባት አንዱ
እሱ በተኛባት ስፍራ በቤቴል እንደሚሠራ መሰከረ፤ ነቢይነቱ ከእንቅልፍ በኋላ ተጀመረ፤