በብሉይ ኪዳን ከነቢያት አንዱ ለእግዚአብሔር ሲሳል ‹‹ኢይሁቦን ንዋመ ለአእይንትየ ወኢድቃሰ
ለቀራንብትየ፤ ለዐይኖቸ እንቅልፍን ለቅንድቦቼም ሽልብታን አልሰጣቸውም›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ እስኪያይ ድረስ ለሰውነቱ
እረፍትን እንደማይሰጥ በልቡ ጽኑ መሀላን ምሎ እንደ ነበረ ተመዝግቧል መዝ 131÷2፤ እንደ ተናገረውም ‹‹ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ
ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ እነሆ በኤፍራታ በዱር ተጥሎ እንደ ኅጻናት ሲያለቅስ ሰማነው ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ እግዚአብሔር
ማደሪያዎች እንገባለን›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ አግኝቶ እስኪመለስ ድረስ ሱባዔውን አላቋረጠም::
በሐዲስ ኪዳንም እንደዚሁ ‹‹ሊቅ አይቴ ተሐድር›› እያሉ ከሀገር ወደ ሀገር
እየተዘዋወረ ያስተምር የነበረውን ጌታ በኋላው እየተከተሉ ማደሪያውን እስኪያሳያቸው ድረስ ይጠይቁት የነበሩ ሁለት ሰዎች እንደነበሩ
ተጽፏል፡፡ ዮሐ1÷39 እርሱም ያልፈለጉትን የሰው ልጆች ሊፈልግ ነውና የመጣው የሚፈልጉትን ሰዎች ኑ ማደሪያዬን አሳያችኋለሁ ብሎ
እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ከእርሱ ጋር ውለው ማደሪያውን አይተው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡
ለቅዱሳን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ከማየት ሌላ ደስታን የሚፈጥርላቸው ምን ነገር አለ? ማደሪያውን
ፍለጋ ባሕር ያቋርጣሉ፣ በዋሻ ውስጥ መንገድ ያበጃሉ፣ ዓለም የማትገባቸው በመሆኗ የፍየል ሌጦ የበግ ለምድ ለብሰው በዋሻ በፍርኩታ
ሰዎች ሆነው ሳለ ከሰው ተለይተው ይኖራሉ፣ መንገዳቸውን ከዓለም ለይተው ወደ እግዚአብሔር ይጓዛሉ፡፡
ዛሬ ለብዙ ዘመናት የተመኘሁት ተሳክቶልኝ እኔም የእግዚአብሔርን
ማደሪያ ለማየት በጣና ባሕር ጀርባ ላይ እየተጓዝሁ ነው፤ የተጫንሁበት ጀልባ ወደፊት እየተጓዘ እኔ ግን በፍኖተ አእምሮ ወደ ኋላየ
ተመልሼ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 8÷23 አንድም እያልሁ እየተረጎምሁ በገሊላ ባሕር ላይ በመርከብ ብዙ ጊዜ ይመላለሱ የነበሩ ደቀ
መዛሙርቱን አስታወስሁ፤ኅሊናዬ በገሊላ ባሕር እንጅ በጣና ላይ የሚጓዝ አልመስለኝ አለ። መዳረሻዬም የጥብርያዶስ ማዶ ጌታ ተዓምራት
ያደርግበት የነበረው ሥፍራ የገሊላ መንደር ይመስለኝ ነበር፡፡ ከመርከብ ስወርድ የጴጥሮስን አማት በንዳድ ታማ ጌታ ሲፈውሳት እንደማገኛት
እያሰብሁ ነው የምጓዘው፡፡ እንዲያውም ባይገርማችሁ በአካል ሳይሆን በኅሊናዬ ተነሣሁና ጌታዬን እንደ ሐዋርያት ከመርከቡ ጀርባ ፈለግሁት በሥጋ ሕግ ተኝቶ የማገኘውና ዓለም
እንዲህ በጭንቀት ማዕበል ስትጠፋ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ መናፍቃን ስትዳፈን አይገድህምን? ልለው ፈለግሁ ውስጤን ፍርሃት ተሰማው፤
ያን ጊዜ በዘለዓለማዊ እንቅልፍ ውስጥ የነበርን እኛን ሊያነቃን ተኝቷል እንጅ ለባሕርዩ እንቅልፍ የሚስማማው ይመስልሃልን?ብሎ
የሚገሥጸኝ መላኩን የላከብኝ መስለኝ፡፡