>

Tuesday, 5 January 2016

ነገረ ቤተ ክርስቲያን-- ክፍል ሰባት



ያልጠበቅናቸው ሦስቱ ቦታዎች

ባለፈው ክፍለ ትምህርታችን ነገረ ማኅሌትን አንስተን ቤተ ክርስቲያናችን በቅኔ ማኅሌት ውስጥ የክርስቶስን የእለተ ዓርብ ስቃይ በአገልግሎቷ እንዴት እንደምትገልጥ አይተን ነበር በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ከመስቀሉ በቀር ሌላ አጀንዳ እንደሌላት ግንዛቤ ወስዳችኋል ብየ አስባለሁ፡፡ ለዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ነገር ግን ያልጠበቅናቸው ሦስት ቦታዎችን እናያለን ረድኤተ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ትሁን፡፡

ሦስቱ ቦታዎች ያልናቸው የዘወትር አገልግሎታችን የሚፈፀምባቸው ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ደጅ የምንጠናባቸው ቦታዎች ናቸው እነርሱም፡-
Ø  መካነ ጸሎት
Ø  መካነ ተግሣጽ
Ø  መካነ ምጽዋት ናቸው
፠ መካነ ጸሎት:-  የምንለው ከቤተ መቅደስ እስከ ቅኔ ማኅሌት ያለውን ነው፡፡ በፍት. መን. አን. 13 እንደ ተደነገገው በቤተ መቅደስ ውስጥ ከዲቁና እስከ ፕትርክና ድረስ መዓርገ ክህነት ያላቸው አበው ለጸሎት ይቆሙበታል፡፡ ነገሥታቱም መዓርገ ክህነት ያላቸው ከሆኑ በዚህ ሥፍራ እንዲጸልዩ ተፈቅዷል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሥፍራ ለጸሎት ብቻ ካልሆነ ለሌላ ለምንም ነገር መግባት አልተፈቀደም ገብቶ መቀመጥ ዋዘዛ ፈዛዛ ማውራት እንዳይገባ ተጽፏል፡፡ ምክንያቱም ቦታው አትናቴዎስ በቅዳሴው እንደ ተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባበት በበጎ አገልግሎት ያገለገሉትን ካህናቱን እና ዲያቆናቱን በቀኝ እና በግራ አድርጎ ምሥጢር የሚያሳይበት የደብተራ ብርሃን ምሳሌ ነውና፡፡ ያን ጊዜ ዋዛ ፈዛዛ መች አለና! ያንጊዜ መቀመጥ ማንቀላፋት መቸ አለና! ስለዚህ በዚህ ሥፍራ የምንቆም ሁላችን መጠንቀቅ እና የቆምንበትን ቦታ ማስተዋል ይገባል፡፡
ከቤተ መቅደስ ቀጥሎ ባለው ክፍል ለሥጋው ለደሙ የተዘጋጁ ምዕመናን የሚቆሙበት ሲሆን ወንዶችም ሴቶችም በየነገዳቸው ለጊዜው የሥጋው የደሙን መድረስ ፍጻሜው ግን የክርስቶስን መምጣት ተስፋ እያደረጉ ደጅ የሚጠኑበት ቦታ ነው፡፡ እስከ ቅዳሴው መጀመር ድረስ የግል ጸሎታቸውን የሚያደርሱትም በዚህ ሥፍራ ነው፡፡
ከዚህ ሥፍራ በኋላ የምናገኘው ቅኔ ማኅሌቱን ሲሆን የዚህ ሥፍራ ባለቤት የለውም ማለትም እስካሁን ያልናቸው ካህናትና ምእመናን ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚቆሙበት አንጅ ከነዚህ የተለየ ፆታ ምእመናን ስለሌለ ነው፡፡