>

Saturday, 15 July 2017

ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ



ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ
በዘመነ ክርስቶስ ከዘመነ ነቢያት ይልቅ ስለ ክርስቶስ ብዙ ጥያቄዎች ይቀርቡበት የነበረው ዘመን ነው፤ ተዓምራቱን ያዩ፣ ትምህርቱን የሰሙ፣ በመልኩ የተማረኩ፤ በቃሉ የረኩ ሁሉም የየራሳቸውን ጥያቄ አንሥተው ለራሳቸው መልስ ሰጥተው ያልፋሉ፤ በተዓምራቱ የተደነቁት ሙሴ ነው ይሉታል፤ ንጽሕናውን ድንግልናውን ያወቁ፣ ሕብስት ሲያበረክት ያዩት ደግሞ ኤልያስ ነው ይሉታል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጠሯቸው ነቢያት ሁሉ የሚበልጠውን ተዓምራት ሲያደርግ ያዩት እንደሆነ የሚሉትን ያጡና ብቻ ከነቢያት አንዱ ነው ብለው ያልፉት ነበር ማቴ 16÷14

 እንደ ሚያውቋቸው መምሕራን ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና ለዚህ መልስ ቢያጡ አድንቀው ዝም ይሉ ነበሩ እንጅ አንዱም እንኳን ከነሳቸው ማን እንደሆነ ጠይቆ ሊያውቅ የደፈረ ሰው የለም ማቴ 13÷54 ምን አልባትም ከዮሐንስ መጥምቅ በቀር አንተ ማን ነህ ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ ሰው ላይኖር ይችላል፤

ከሦስት ዓመት ከሦስት ወር ባስተማረባቸውም ጊዜያት ከሰማይ ተልኮ ስለ መምጣቱ ቢነግራቸው ‹‹ዘለሊነ ነአምር አባሁ ወእሞ እፎ እንከ ይብለነ እምሰማይ ወረድኩ፤ እኛ አባትና እናቱን እያወቅናቸው እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል›› ዮሐ 6÷42 ብለው ይነቅፉት ነበር እንጅ ትምህርቱን ሊቀበሉት አልተቻላቸውም፤ እንዲያውም መነቀፍና መሰደብ በሚገባው ሥጋ ከመምጣቱም በላይ ከነገሥታቱ ቤት ሳይሆን ንቀው አጥቅተው በሚመለከቱት በድሀው በዮሴፍ ቤት በመወለዱ ምክንያት ‹‹አኮኑ ዝንቱ ወልዱ ለፀራቢ ይህ የእንጨት ጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን!?›› ማቴ 13÷55 ብለው ይጠይቁም ነበር፡፡

 የዮሴፍ ድህነቱ የዳዊት ልጅነቱን በአይሁድ ዘንድ አስረስቶበት ነው እንጅ በዘር ሐረጉ ቢቆጠር የዳዊት ልጅ ሆኖ ባገኙት ነበር፤ አይሁድ ግን ይህን አላወቁም፤ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ማቴዎስ ተናዶ ተነሥቶ ወንጌሉን ወልደ ዳዊት ብሎ የሚጀምረው የዳዊትን አባትነት በዮሴፍ በኩል አድርጎ ወደ እመቤታችን ወደ ክርስቶስ ለማድረስ፡፡ 

አይሁድ ባለማወቃቸው ሲሳለቁ ‹‹የጠራቢው ልጅ አይደለምን!›› ብለዋል እንጅ እሱስ እውነት ነው ሰማይና ምድሩን ጠርቦ ያስማማ የአብ የባሕርይ ልጁ ነው እንደ እግዚአብሔር ጠራቢ ማነው? የጠራቢ ግብሩ ያልተስማማውን ማስማማት የማይዋሐደውን ጠርቦ አስተካክሎ ማስማማት አይደለምን!? እንኪያስ ሰማይን ከምድርጋር በአድማስ ያስማማ አባቱ ነውና ‹‹የጠራቢው ልጅ›› ማለታቸው እውነታቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከስላቅ ውስጥ ቁም ነገርን ለሚድኑ ሰዎች ያዘጋጃል በእመቤታችን ፊት ውኃ ሲቀዱ የነበሩ ሴቶች አስቧቸው  ‹‹…እኛስ ለባሎቻችን ስራ አለብን እንዳንች ሥራ ፈት አይደለንም ወይም እንጅ ክርስቶስ ይወለዳል እሚባለው ካንች ይሆናል›› ብለው የዘበቱባትን መዘባበት ለእመቤታችን እውነት አድርጎላት ወላዲተ አምላክ ሆነች፤ እውነታቸውን ነው እሷ ለሰማዩ ንጉሥ የታጨች ሙሽራ ናት ከእርሱ ‹‹ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና›› ከተባለችለት ከእርሱ በቀር ለማንም ሥራ ሊኖርባት አይችልም፡፡ 

ይሄም እንደዚያ ያለ ነው እነሱ ሊሳለቁ የተናገሩትን መንፈስ ቅዱስ በአባቶቻችን ላይ አድሮ እንዲህ አስተረጎመ፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ እንዴት የዮሴፍን ስም ሳይጠሩ የቀሩ ይመስላችኋል? መንፈስ ቅዱስ ከልክሏቸው እኮ ነው፡፡
ታዲያ የሚንቁት ስለሚንቁት የሚጠሉትም ስለሚጠሉት ስለ ክርስቶስ መልስ አጥተው ለሚጨነቁት አይሁድ እነሱ መልስ ለማግኘት በቅንነት አልጠየቁምና እሱ ‹‹ምንተ ትብሉ በእንተ ክርስቶስ ወልደ መኑ ውዕቱ፤ ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡
 ይህ ጥያቄ ለተራው አይሁዳዊ ሕዝብ የቀረበ እንዳይመስላችሁ! አወቅን መጠቅን ለሚሉትና መዓርጋችን ረቂቅ አእምሯችን ምጡቅ ለሚሉ ፈሪሳውያን ነው- ጥያቄው የቀረበው፡፡ እነ ገማልያልን ያኽል ምሁር የሚገኝበት ጉባኤ ነው - የፈሪሳውያን ጉባኤ፡፡ በወቅቱ የታወቀው አንጋፋ የብሉይ ትርጓሜ ትምህርት ቤትም ያለው በነሱ እጅ ነበር- እንደነ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ንቁ ደቀ መዛሙርትን የያዘው ጉባኤ፡፡

 ግን ምን ይሆናል! የነቢያት ልጆች መሆናቸው የነቢያትን ሱባኤ ማወቃቸው ትንቢተ ነቢያትን ሲሰሙ ማደጋቸው ክርስቶስን ይመጣ ዘንድ ያለው መሢሕ እንደሆነ ሊያውቁ አላስቻላቸውም፤ በፊደል እንጅ በመንፈስ የሚመሩ አልነበሩምና፡፡ ለዚህም ነው ‹‹የዳዊት ልጅ ነው›› ማቴ 22÷41 ብለው የሰጡት መልስ በሌላ ምዕራፍ ስለ እርሱ ማንነት ጠይቆ ማቴ 16÷16 ደቀ መዛሙርቱ ለመለሱለት መልስ የሰጠውን ብፅዓን ሳይሰጣቸው የቀረው፡፡ መልሳቸው ከፊደል እንጅ ከመንፈስ ቅዱስ ያልተገኘ ነውና ‹‹ዘለሊሁ እንከ ዳዊት እግዚእየ ይብሎ እፎ እንከ ይከውን ወልዶ፤ እሱ ራሱ ዳዊት ጌታየ እያለው እንደምን ልጁ ይሆናል›› የሚለውን ጥያቄ አስከተለባቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ክርስቶስ አሁን ዓለማችን ምን ትላለች? የዓለም ጥበበኞች (ፈላስፎች ሳይንቲስቶች..) ምን ይላሉ? መናፍቃንስ? በተለይም በኛ አውደ ምሕረት ሳንዘራቸው የበቀሉት የተሐድሶ መናፍቃን ኢየሱስ ኢየሱስ ብሎ ያልዘመረ ያልሰበከ ሁሉ አልዳነም እያሉ በማሸማቀቅ አባቶቻችን ከተጓዙበት መንገድ ሊያወጡን እየታገሉን ነውና ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክርስቶስ ምን ትላለች? በተከታታይ እናያለን፡፡