ደብረ ቁስቋም
ደብረ
ቁስቋም ማለት ደብረ ምዕራፍ ማለት ነው፤ ከእመቤታችን ክብረ በዓላት መካከል አንዱ በዚህ ስም ይጠራል፤ ለቤተ ክርስቲያን ከሚደረግላት
የመዳን ታሪክ ጋር ስለተገናኘ እንጅ ከግብፅ ተራሮች አንዱን መጥራት ስላስፈለገን አይደለም፤ ዛሬ አግዚአብሔር ታላቅ የሆነውን ፍርዱን
በምድር ላይ ማድረጉን ለዮሴፍ በሕልም የታየው መላክ አስረድቶታል፤ ‹‹እስመ ሞቱ እለ የሐስስዋ ለነፍሰዝ ሕጻን፤ የዚህን ሕጻን
ነፍስ ሊገሏት የሚሷት ሁሉ ሞተዋልና›› ማቴ 2 20 ከዚህ በፊት የተደረገው እንዲህ አልነበረም በልደተ ክርስቶስ ያልተደሰተው ሰይጣን
በሔሮድሳውያን አድሮ ስደት የሚገባቸው ግፈኞች አርፈው ተቀምጠው ስደት የማይገኝባት እመ አምላክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም
ተሰደደች የእግዚአብሔር መላክ የቀኑን ልክ ሳይናገር ‹‹እስክነግርህ ድረስ በዚያ ተቀመጥ›› ብሎ ዮሴፍን ወደ ግብፅ እንዲወርድ
አዘዘው፡፡ የመከራ ጫፉ አይነገርም የእስራኤልን የግብጽ ኑሮ መጀመሪያውን እንጅ መጨረሻውን ከእግዚአብሔር በቀር ማን ያውቀው ነበር፤
የዚህ ዓለምም ጉዞ መጨረሻው በኛ ዘንድ አልተነገረንም
ነገር
ግን እግዚአብሔር ማንንም በስደት ምድር አይረሳምና ከሦስት ዓመት ከስድስት ወራት በኋላ ዛሬ ስደተኞችን በምሕረት አሰበ ይህ አርባ
ሁለት ወር ለእመቤታችን የስደት ወቅት ይሁን እንጅ ለሔሮድሳውያን ደሞ የንሥሐ ጊዜ ነበር ታዲያ ሔሮድስ ንስሐ ባለመግባቱ ዛሬ ተቀስፎ
ሞተ፤ ስደተኛዋእመቤታችን ወደ ናዝሬት ስትመለስ አሳዳጁ ሔሮድስ ከእግዚአብሔር መንግሥት ለዘለዓለም ተሰደደ፤ ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ
ሽሽ ብሎ ስደቱን የነገረው መላክ ዛሬ ደግሞ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ ብሎ ነገረው፤ በዚሁ ዕለት ደብረ ቁስቋም ገብተው አድረዋልና
ደብረ ምዕራፍ ተብሎ ተተረጎመ፡፡
የምድረ
በዳው ጉዞ፣ የበረኃው ስቃይ፣ የግብፅ ዋዕይ፣ የሽፍቶቹ ማንገላታት፣ የሔሮድስ ሰራዊት ከበባ፣ የሦስት ዓመት ረሀብና ጥም፣ የነኮቲባ
ክፉ ወሬ፣ ይሄ ሁሉ መከራ ዛሬ ተጠናቀቀ፤ ማደሪያ የሌላት ዖፍ ብሎ ቅዱስ ዳዊት የዘመረላት ፀዓዳ ዖፍ ድንግል ማርያም ዛሬ ማረፊያ
አገኘች ይህችውም ደብረ ቁስቋም ናት፡፡ እንዴት ደስ ይላል ከረጅም የመከራ ወራት በኋላ የተሰማ የምሥራች ነው ደሞ የምሥራቹን ታላቅ
የሚያደርገው የሕጻኑን ነፍስ የሚሹት መሞታቸው ነው፡፡ የገደላቸው ሕጻናት ብዙ ናቸው በእናታቸው እቅፍ ላይ እያሉ አንቀው የገደሏቸው
አሉ ጡት እየጠቡ ሳሉ ነጥቀው በሰይፍ የቀሏቸው አሉ፤ ተኝተው ሳሉ ከእናቶቻቸው ጀርባ እያወረዱ የጨፈጨፏቸውም ብዙ ናቸው፤ የእናቶቻቸው
ልብስ በደም ተነከረ ዓይናቸው በእንባ ተሞላ ቤተ ልሔምና አካባቢዋ በጩኸት ተሞላች፤ አስቀድሞ በነቢይ እንደተባለ ‹‹ራሔል ስለልጆቿ
አለቀሰች›› በራሔል ልጆች ርስት ላይ የተፈፀመ ጭፍጨፋ ስለሆነና የራሔልም መቃብር በገሊላ አውራጃ ውስጥ ስለነበረ ነው ከአራቱ
የእስራኤል ልጆች እናቶች መካከል ራሔልን ለይቶ ይጠራታል፡፡
ሞትን
በሰው ልጆች ላይ የፈረደው ንጉሡ ሔሮድስ እሱም በሰማዩ ንጉሥ ሞት ተፈርዶበት መቃብር ወረደ፡፡ እገለዋለሁ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በኃጢአት የሞተውን ዓለም ለማዳን
ኃጢአት ወደ በዛባቸው ሰዎች ሂዶ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ጎበኛቸው፤ ከዚህም በኋላ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ለመግባት ያሰበ
አይደለም፤ ኃጢአት ወደፀናባት ከተማ ወደ ናዝሬት ተመለሰ፡፡
በእርግጥ
የመጨረሻ ድል አይደለምና በክፉው ሔሮድስ ፋንታ ልጁ ነው የነገሠው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ኃጥዕ ሔሮድስን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ
ዝግባም ለምልሞ አየሁት ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም›› መዝ 36÷35 የሚለውን የአባቷን መዝሙር እየዘመረች
ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
ደብረ
ቁስቋም የመንግሥተ ሰማይ ምሳሌ ነው፡፡ እመቤታችንና አብረዋት የተሰደዱት ሰዎች የምዕመናን ምሳሌዎች ናቸው፤ ምዕመናን የሰማይና
የምድር ፈጣሪ ከነእርሱ ጋር እያለ በክፉዎች ምክንያት ይሰደዳሉ፤ እውነትን ይዘው ከሀገር ሀገር ይንገላታሉ፤ በምድረ በዳ ማደሪያ
በማጣት፣ በረሀብ በጥምና በእርዛት ይፈተናሉ ነገር ግን ለነፍሳቸው የሚሆን ማረፊያን ፍለጋ እየተጓዙ እንደሆኑ በማሰብ ይፀናሉ፤
በመጨረሻም የጠላታቸውን የዲያብሎስን መሞት ይሰማሉ፤ ለቤተ ክርስቲያን ታላቁ የምሥራች የዲያብሎስ ድል መነሣት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን
ዲያብሎስን በሃይማትና በምግባር ገድላ ራሷን ወደ ማረፊያው ተራራ ወደ ደብረ ጽዮን ታስጠጋለች፡፡
የዛሬው
በዓል ቤት አልባ የነበረችው የሰው ልጆች ሕይወት ማረፊያ ያገኘችበት ቀን ነው፤ ስደቱ ቤተ ክርስቲያን በሐሳዊ መሢህ ዘመን የሚደርስባት
ስደት መነሻ ነውና የተደረገውም ዕረፍት ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር መንግሥት ለምታገኘው ዕረፍት ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ እኮነው
መላዕክትም በልጇና በእርሷ ላይ ክንፋቸውን እየጋረዱ ምስጋን ያቀረቡት ቅዱስ ያሬድም ‹‹ዮም ፀለሉ መላዕክት ላዕለ ማርያም ወላዕለ
ወልዳ ክርስቶስ በደብረ ቁስቋም፤ መላዕክት በልጇና በእርሷ ላይ ክንፋቸውን እየጋረዱ አመሰገኑ›› ብሎ ይናገራል፡፡ መላዕክትን ሳይቀር
ያስደሰተ ታላቅ ዕረፍት፡፡
እግዚአብሔር
ዕረፍት በሌለባት ዓለም ውስጥ ስንኖር ዕረፍትን ለሁላንም ያድለን፡፡