>

Wednesday, 13 February 2019


ነፍስ የት ሀገር
ሞትና መቃብርን ማን እንዳስማማቸው አይታወቅም፤ አንዱ ከአንዱ ሳይለያዩ፤ ሳይቀዳደሙ፤ ሳይበላለጡ፤ ይሄን ሁሉ ዘመን ፊትና ኋላ ሁኖ መኖር እንዴት ይቻላል? ሞት የማረካቸውን ምርኮኞቹን ሁሉ ለመቃብር በአደራነት ይሰጣል፤ መቃብርም ተቀብሎ በጥብቅ ያስቀምጣል የሁለቱም የጋራ ጠላት ትንሣኤ ነው፤ ሞትን ድል የሚነሣው መቃብርን የሚበዘብዘው ከትንሣኤ ሌላ ማንም ስለሌለ እርሱ እንዳያገኛቸው ሞት የሰበሰባቸውን ሙታን ሁሉ መቃብር ወደ አፈርነት እየለወጠ ከአፈሩ ጋር አመሳስሎ ያኖራቸዋል፤ ሞትም ቀላል ጠላት አይደለምና ነፍስና ሥጋን ብቻ ሳይሆን አራቱ ባሕርያትንም በታትኖ ሰዉን እጅ እንዲሰጥ ያደርገዋል፤
ገና ከወዲሁ የሞት መዳፍ የሆነው ደዌ ጠበቅ ሲልባቸው ሁለቱ ቀሊላን ባሕርያት ነፋስና እሳት ስፍራቸውን ለቀው ይጠፋሉ ይህን ተከትሎ ነፍስም ሥጋዋን አውቅሃለሁም ሳትለው አንጋላው ትሄዳለች፤ አፉን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ እያየችው ሳትራራ ዝም ብላው ትሄዳለች፤ ምንም እንኳን ለውጥ ባያመጡም መሬት እና የውኃ ባሕርያት እስከ መቃብር ድረስ አብረው ከሥጋ ጋር ይቆያሉ ነገር ግን ካልተባበሩ ምን ለውጥ አለ? ሞት አስቀድሞ ደዌ በሚሉት ፖለቲካው ስለ ከፋፈላቸው ሁሉም ወደየወገኑ ተመልሷል ነፋስም ወደ ነፋስነቱ፣ እሳትም ወደ እሳትነቱ መሬትና ውኅም መቃብር ውስጥ ከገባ በኋላ ሰውየው ምን ሊያደርግላቸው ይችላል? ተስፋ ስለሌላቸው እነሱም ወደየ ወገናቸው ይጨመራሉ፡፡
የአራቱ ባሕርያት መለያየት ነፍስ የሌለው ሥጋ እንዲኖር አደረገ፤ ሰውየው ልብሱን ለብሶ፣ ወደ ልቡ ተመልሶ፣ ከመኝታው ተነሥቶ ፈቃዱን ፈጽሞ ደስስስ ብሎት እንዳይኖር ያደረገው የእነሱ አንድ አለመሆን ነው፡፡ ያላገባው ሳያገባ፣ የተመኛትን ፍቅረኛውን ከእናትና ከአባቷ ተቀብሎ ሳያስደስታት ሳይደሰትባት፣ በቅርቡ የተጋቡት ፍቅራቸው እንደደራ፣ ተማሪው ተምሮ ሳያርፍ፣ ነጋዴው ነግዶ ሳያተርፍ፣ ለሹመት የተወዳደሩት ሳይሾሙ፣ የተሾሙት ሹመታቸውን ሳይጠግቡት፣ ሁሉም የጀመረውን ሩጫ ሳያጠናቅቅ የአራቱ ባሕርያት አለመስማማት ለሞት እድል ሰጠው፡፡
ሰላዮቹን ሕማምና ደዌን ልኮ ሲሰልለው የነበረውን ሰው አራቱ ባሕርያት እንዳልተስማሙለት ይልቁንም የገዛ ወገኖቹ እንደከዱት አውቆ ገብቶ በሰውነቱ ላይ ይነግሥበታል፤ ወራሪው ሞት መምጣቱን ተከትሎ ነፍስም ስፍራዋን ለቃ ትሄዳለች፤ ነፍስ ከወጣች ምን ቀረው? አገር ይሰበስብ የነበረው ሰው እራሱን መሰብሰብ ያቅተውና ሰዎች ይሰበስቡታል ከዚያ በኋላ ቢያነሱት ቢጥሉት ቢያከብሩት ቢያዋርዱት ቢመርቁት ቢረግሙት ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ወዳጁን አይጠቅምም ጠላቱን አይጎዳ ሲሆንባቸው ሰዎችም አውጥተው ለመቃብር ይሰጡታል እሱም ዳግም እንዳይመለስ አድርጎ አጥንትና ጅማቱን፣ ቆዳና ፀጉሩን፣ እጅና እግሩን ሌሎችንም አካላቱን ለያይቶ ይጥላቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ ቀደመው ለማድረግ የፈጠረው እግዚአብሔር እስኪመጣ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
ቅድስት ሀገሬ ኢትዮጵያም እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠራት ዓለም በክርስትና ሳይፈጠር የተፈጠረች ሀገር ናት፡፡ ሲፈጥራትም እንደ ሰው ተፈጥሮ ሁሉ ከብዙ ባሕርያት አንድ አድርጎ ፈጥሯታል እንጅ ከአንድ ባሕርይ አይደለም እንደ መላዕክት ተፈጥሮ እምኃበ አልቦ አልፈጠራትም ብዙ ቋንቋዎችን፣ ባሕሎችን፣ ነገዶችን አዋሕዶ ከአራቱም አቅጣጫ ሰዎችን አምጥቶ አስማምቶ አንድ ሀገር አድረጎ ፈጠራት፡፡
ሰው ሲሞት አራቱ ባሕርያት ወደየወገናቸው እንደሚመለሱት ሁሉ ኢትዮጵያ የተፈጠረችባቸው ነገዶች፣ ቋንቋዎች ሕዝቦች ወደየወገናቸው መመልከት ጀምረዋል፤ እነዚህ ከተበታተኑ ሀገሪቱ ትሞታለች ነፍሷንም ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ብላ እስከምትጸልይ አይጠብቋትም የሰይጣን ማኅበር ተቀራምተው ይወስዷታል፡፡አንዲትን ሀገር የምትፈጠረው ከብዙ ባሕርያት ነው፤ እነዚህ መለያየት ሲጀምሩ ነፍሷን መነጠቋ የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የዚች ሀገር ነፍሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ነፍሷን ሊነጥቋት የተሰለፉት የሞት አይነቶች ብዙ ናቸው፤ ሀገር አንድ ሞት አትሞትም አንዴ መሞት ከጀመረች ደግማ ደጋግማ ስትሞት ነው የምትኖረው፡፡ የባሕል መበረዝ፣ የዕውቀት መጥፋት፣ የብዙ አይነት ፖለቲካ ማራገፊያ ወደብ መሆን እነዚህ በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ለሀገር ሕመም መቀስቀስ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ በወቅቱ ካልታከሙ የተፈጠረችባቸው ባሕርያቶቿ መለያየት እንዲጀምሩ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የሚኖራት ትውልድ ልብሱን መልበስ የማይችል፣ አከናውኖ የማይናገር፣ ጠላት ቢመጣ የማይመክት ይሆናል፡፡ አውጥተው ይቀብሩትና ርስቱን ይካፈሉታል፤
የዚህን ዘመን ኢትዮጵያዊ ትውልድም አውጥተው ቀብረው ርስቱን ሊወርሱበት የተማማሉ ይመስላል እንደሞተ ሰው ሆነን እራሳችን የማንሰበስብ በሕይወት ያለ ሰው እንደ ወደደ የሚያደርገን እንድንሆን እያደረጉን ነው፤ እነሱ በሠሩልን መኪና ተጉዘን፣ በፈጠሩልን አውሮፕላን በርረን፣ በቀየሱልን መንገድ ተጉዘን፣ በሠሩልን ድልድይ ተሻግረን፣ እነሱ ባዘጋጁልን ዌብሳይት ምሥጢራችንን አስቀምጠን ባጠቃላይ እነሱ ባወጡልን ንድፍ ተመርተን እኛ ስናሰምር፣ እነሱ የረገጡትን እየረገጥን፣ ያተረፉትን እየበላን እንድንኖር አመቻችተው በአርዓያቸውና በምሳሌአቸው እየሠሩን ነው ያሉት፡፡
ያለ እነሱ የሠራነው ሥራ የትኛው ነው፤ ያለ እነሱ ግድብ አንገድብ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል አናመነጭ፣ ነዳጅ አንቆፍር፣ አስፋልት አንሠራ በጠቅላላው ትልቅ ሥራ ለመሥራት እነሱን ማማከር ግዴታችን እየሆነ ነው፡፡ የዕውቀት ባንካችን googl ነው፣ መገናኛችን facebook፣ whatsap፣ messenger ሁሉም የእነሱ ነው፡፡ ሁላችንም ከጭንቅላታችን download የምናደርገው እውቀት እያጣን ነው በዚህ ሁሉ ጥገኛ እንድንሆን የሚደረገው ለሚመጣው የአውሬው መንግሥት ቶሎ እጅ እንድንሰጥ ለማድረግ ነው፡፡   ከዚህም አልፎ ራዕይ ያዩልናል ሕልም ያልሙልናል ንጉሥ ይሾሙልናል ፓርቲ ያጀግኑልናል ሁሉ ይባላል፡፡ ለማንኛውም ነፍስ የሌላት ሀገር እንዳትኖረን መጠንቀቅ የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡