አሥሩ ደናግል ክፍል ፪
አሥር መሆናቸው ለምን ይመስልሃል? የሰው ልጅ የሚጸድቀውም የሚኮነነውም በአሥሩ ኅዋሳት በኩል መሆኑን ለማመልከት
ነው፤ አምስቱ ጠባባት የተባሉት ጌታ ይመጣል ብለው በማሰብ አምስቱንም የስሜት ኅዋሳቶቻቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሚኖሩ ናቸው፡፡
§ ማየት
§ መስማት
§ መቅመስ
§ ማሽተት
§ መዳሰስ፡- እነዚህ አምስቱ ሰዉን
ለሞትም ለሕይወትም የሚያበቁት መንገዶች ናቸው፡፡
ቅዱሳን ለእግዚአብሔር መንግሥት ከታጩበት ጊዜ ጀምሮ የዓለምን መልኳን አይተው፣ መዓዛዋን አሽትተው፣
ጣዕሟን ቀምሰው፣ በእጃቸውም ዳስሰው እንዳያዩአት ሰውነታቸውን ወስነው ይኖራሉ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችን በምንታጭበት ቀን (ክርስትና
በምንነሣበት ቀን) እነዚህን ኅዋሳቶቻችንን በቅብዐ ሜሮን ታትማቸዋለች፤ በመጀመሪያ ግምባራችን ላይ በመስቀል ምልክት ይታተምብናል
ቅብዓ መንግሥተ ክርስቶስን ተቀብተናልና ከዓለም ተለይተን በአጋንንት ዘንድ ተፈርተን እምንኖረው በዚህ ቅዱስ ቅብዓት ነው፡፡ ሙሴ
ከፈርዖን ሞት ያመለጠው በግብጻውያን አዋላጆች ዘንድ ሞገስን ያገኘው ግምባሩ ላይ በነበረው የመዳን ምልክት እንደነበረ ልብ ይሏል፡፡
ዐይን፣ ጆሮ፣
አፍ፣ አፍንጫ፣ እጅ እነዚህ ሁሉ ጽድቅም ሆነ ኃጢአት ያለ እነዚህ መሣሪያነት አይሠራምና አስቀድመው ይታተማሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ
ወንጌላዊ ‹‹አንትሙሰ ቅብዓት ብክሙ እምነ መንፈስ ቅዱስ፤ እናንተስ በቅዱሱ ቅብዓት ታትማችኋል›› 1ዮሐ 2፥21 የሚለውም ይህንኑ
ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሆኑ ሌሎች ሠለሳ ስድስት አዕዋዳት መኖራቸውንም በዚሁ አጋጣሚ እገልጣለሁ ፍት. መን. አን. 3
በአንጻሩ ከዚህ የሚልቀውን መልክዓ
መለኮቱን አይተው፣ መዓዛ መለኮቱን አሽትተው፣ የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም ቀምሰው፣ የሚመጣውን ዓለም በተስፋ ዳስሰው፣ ቃለ ወንጌሉን
ሰምተው ይኖራሉ፡፡ የታጨላት ባል እስኪመጣ ድረስ ተዘጋጅታ እንደምትጠብቅ ሙሽራ ነፍሳቸውን በንስሐ እንባ አጥበው፣ የጽድቅ ካባ
አልብሰው ለሰማያዊው ሙሽራ እንደሚገባ ሁነው ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡
የውስጥና የውጭ ኅዋሳቶቻችን ሲቆጠሩ
አሥር ይሆናሉ እነዚህን አስተባብረው አሳምነው ለነፍሳቸው አስገዝተው የሚኖሩ ጻድቃን በቅዱስ ወንጌል የተጠቀሱት አሥር ዓይነት ናቸው
ለዚህ ነው ጌታ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ሙሽራቸውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ደናግልን ትመስላለች›› ያለው፡፡ እነዚህም፡- ነቢያት፣ ሐዋርያት
(መምህራን)፣ ነገሥታት፣ ደናግል፣ መዐስባን፣ ሰማዕታት፣ ምዕመናን፣ መነኮሳት፣ ባሕታውያን እና መላእክት ናቸው፡፡ ከነዚህ የወጣ
ጻድቅ በቤተ ክርስቲያን አይገኝም፤ በሰማይም በምድርም ያሉ የታላቋ የክርስቶስ ማኅበር የቤተ ክርስቲያን አባላት እነዚህ ናቸው፡፡
እነዚህ በጠቅላላው ‹‹ፍጽምት ምዕመን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› ተብለው ይጠራሉ፤ ሊቀ ማኅበሩም ክርስቶስ ነው፡፡ እግዚአብሔር
የሰማያውያኑን መላእክት እና ምድራውያኑን ጻድቃን ይኖሩበት ዘንድ አሥር ከተሞችን በሰማይ አዘጋጅቷል፤ እናታችን ሔዋን አሥሩን ኅዋሳት
ድንግልናቸውን ባሳጣቻቸው ጊዜ ከአሥረኛው ከተማ ወደዚህ ምድር የመጣነው በስደት ነው፡፡
በዐይኖቿ እባብን አይታ በጆሮዋ ምክረ ሰይጣንን ሰምታ በእጇ እፀ በለስን ቆርጣ
በእግሯ ወደ ዕፀ በለስ ተጉዛ በአፏ ዕፀ በለስን በልታ እግዚአብሔርን አሳዘነች፤ ለእነዚህ ለአምስቱ አምስት ውስጣዊ ኅዋሳት አሏቸው
እነዚህ ሁሉ ረከሱብን፡፡ ነገር ግን እመቤታችን በዚህ ሁሉ የታመነች ሁና ስለተገኘች በምድር ላይ ለእግዚአብሔር መንግሥት የታጩ
አሥር ደናግል እንዲኖሩ ተደረገ፤ ለዚህም ማሳያ እንዲሆን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጌታን እንደምትፀንስ ባበሠራት ጊዜ አሥር ቃላትን
አነጋገራት 1. ፀጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፣ 2. እግዚአብሔር
ካንች ጋር ነው፣ 3. ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ፣ 4. በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሸልና አትፍሪ፣ 5. እነሆ
ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፣ 6. እርሱም ታላቅ ነው፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፣
7. በያዕቆብ ቤት ለዘለዓለም ይነግሣል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፣ 9. መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፣ የልዑል ኀይልም ይፀልልሻል
10. ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የሚሉት ናቸው፡፡
በዚህ አንጻር አሥሩ ማኅበረ ቤተ
ክርስቲያን ተመሠረቱ ማለት ነው፡፡ እነዚህም በዐሥር መዐርጋት መሰላልነት ወደ ላይ እየወጡ መንግሥተ ሰማያትን እዲወርሱ አድርጓቸዋል፡፡ ሙሴ ሕዝቡን በአሥሩ ቃላት እየተመሩ
ምድረ ርስትን እንዲወርሱ አደረጋቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አሥሩ ማኅበረ ቤተ ክርስቲያ በአሥሩ መዐርጋት ልዕልና ነፍስን አግኝተው
አሥረኛዋን ከተማ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ አደረጋቸው፡፡
እነዚህ አሥሩም የሰው ልጅ የሕይወት
መስመሮች በቅዱስ ወንጌል ተጽፈው ይገኛሉ፤ አምላካችን ክርስቶስ በምድር ላይ እየተመላለሰ በሚያስተምርበት ወቅት አንዳንዶችን በአኗኗሩ
መሰላቸው ሌሎችን ደግሞ በየቦታቸው እየገባ ጎበኛቸው ከእርሱ ጋር ሊኖሩ የተፈቀደላቸውን እንዲኖሩ አደረጋቸው፡፡ እነዚህ ሐምስ ጠባባት
ተብለው በቅዱስ ወንጌል ተጠርተዋል፤ መንግሥተ ሰማያትን ደጅ ሲጠኑ የሚኖሩ የሙሽራውን መምጣት ሲጠብቁ በሙሽራው መዘግየት ምክንያት
በሞት ከማንቀላፋታቸው በቀር ድካመ - ኃጢአት ያልተገኘባቸው ናቸው፤ ሙሽራው ክርስቶስ በመጣ ጊዜም ከጽድቃቸው የተነሣ ኅዋሳቶቻቸው
ሁሉ እንደ ፋና እያበሩ ከመቃብር ወጥተው ይቀበሉታል፤ ቅዱስ እንጦንስ ከአባ ጳውሊ ዘንድ በሄደ ጊዜ አባ ጳውሊ ለጸሎት ሲቆም አሥሩ
ጣቶቹ እንደ ፋና ሲያበሩ ያያቸው ነበር፤ ሰውነታችንን ከኃጢአት ስንጠብቀው እንዲሁ ይሆናል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው አሥሩም ኅዋሳቶቻቸው
የነፍሳቸውን ቅድስና ላለማስነጠቅ የሚተጉ ወታደሮች ይሆኑላቸዋል፡፡ የነፍሳችንን ድንግልና የሚያሳጣን ኃጢአት በነዚህ ካልሆነ በሌላ
ምንም መግቢያ የለውምና ኃጢአትን መግቢያ አሳጥተው ልባቸውን ንጹሕ አድርገው እግዚአብሔርን ሲያዩት ይኖራሉ ‹‹እግዚአብሔርን ያዩታልና››
ማቴ 5፥8 ተብሎ ስለነእርሱ የተጻፈው ቃል ምንኛ ድንቅ ነው!?
ለምን ጠባባት ተባሉ…….ይቀጥላል