>

Friday, 11 October 2019




የነፍሴ ጥያቄ
በእርግጥም የሆነውን ሁሉ እንዲህ ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በቀር ማን ነበር የሚያውቀው? ይህን ሁሉ ሲያደርግ ማን ነበር ከእርሱ ጋር የነበረ? ለመባርቅት ነጎድጓድን፣ ለክረምት ዝናምን ባደረገ ጊዜ ያማከረው አለ? የምድር መሠረት በተጣለ ጊዜ፣ የሰማይም ዐምድ በቆመ ጊዜ የማዕዘኑን ድንጋይ ያዘጋጀ ማን ነው? ባሕርን በመዝጊያ በዘጋት ጊዜ ነፋስንም በልክ በልክ አድርጎ ወደ ዓለም በላከው ጊዜ ደመናን ለሰማይ ልብስ አድርጎ ባዘጋጀ ጊዜ ከእርሱ ጋር ማን ነበረ?
መጽሐፍ ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ግን የሆነ ምንም ነገር የለም›› ዮሐ 1÷3 ያለው ለዚህ ነው አግዚአብሔር ሳይፈጥረን ገና በተለይም ለእኛ ለሰው ልጆች የሚያሻንን ሁሉ አዘጋጅቶ አከናውኖ ፈጠረልን፡፡
ነገር ግን ባለፈው በጥያቄ አንድ ላይ እንዳነሣነው ‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል ፈልጉ  ታገኛላችሁ›› የሚለውን ትምህርት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ስብከቱ አስተምሮታል፤ በዚህ ትምህርት ምክንያት የሚሰናከሉ ብዙ ናቸው ሳንለምነው የፈጠረን እርሱ አይደለምን? ስለምንድነው ለምኑ የሚለን? ወይስ እንደ ክፉ ባለጠጋ ባደረገው ነገር የሚመጻደቅ ጌታ ነው እግዚአብሔር? የሚሉ ብዙ ናቸው የኔም ነፍስ ይህን ጥያቄ መልሳ መላልሳ ይህን ትጠይቀኛለች፡፡
ከእለታት በአንድ ቀን ነፍሴ በዚህ ጥያቄ ባሕር ላይ ስትንሳፈፍ የምትሳፈርበት የመልስ ታንኳ አጥታ ስትጨነቅ ከዓዜብ በኩል የመጣው ነፋስ ባሕሩን እያናወጠ ለነፍሴ ግን ጥያቄዋን ይመልስላት ጀመረ፤
እንዲህም ሲል ነገር ጀመረ፡- እግዚአብሔር አዳምን እንደ ረዓይት ሳያስረዝመው ዘፍ 6÷4 እንደ ድንክ ሳያሳጥረው እጥር ምጥን ያለ ጥሩ ፍጥረት አደርጎ ፈጠረው፡፡
ይህም አልበቃ ብሎ ከእንስሳት ይለይ ዘንድ ከመለኮታዊ ባሕርዩ የተገኘች ሕያዊት ነፍስን ሰጠው፤ መች ይሄ ብቻ ሆነና በነፍስ በሥጋ ያከበረውን አዳምን እንደ ገና በአርባኛው ቀን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ረቂቅ ልደትን እንዲወለድ ፈቀደለት፡፡ በምድር ካሉት ዓራት ጠባይዓት ተገኝቶ ከሰማያውያን መላእክት ጋር የሚመሳሰልበት መንፈሳዊ ባሕርይ የተሰጠው ከአዳም በቀር በምድር ላይ ማን አለ? በተፈጥሮ እንስሳትንም መላእክትንም ይመስላል፤ በሥራ እንስሳትንም መላእክትንም ይጋራቸዋል፤ ከእንስሳት መብል መጠጥን ከመላእክት ቅዳሴን፣ የዘለዓለም ሕይወትን ይካፈላል፡፡
ከእግዚአብሔር ተወልዷልና የእግዚአብሔር ገንዘብ በሆነው ሁሉ ላይ ተሾመበት፤ ‹‹በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት›› መዝ 8÷6 እንዲል፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም ያልሰጠው ምንም ነገር እንደሌለ ተመልከቺ፡፡ ያውም ሁሉ የእርሱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሁሉ የሚገዛለት መሆኑ ባለጠግነቱን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሁሉ እያላቸው ሁሉን ነገር መጠቀም የማይችሉ ባለጠጎች አሉና፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆንለት ጠይቆ የተደረገለት ምን አለ? ከምድራውያን ፍጥረታት ተለይቶ የሚቆም የሚቀመጥ፤ የሚተኛ የሚነሣ ሁኖ ይፈጠር ዘንድ ጠይቆ ነበር? በሥጋ እና በደም አከናውኖ ቢፈጥረው ነፍስ ያስፈልገኛል ብሎ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ነፍስን የተቀበለ ይመስልሻል? ዓለምን ይገዛ ዘንድ በሁሉ ላይ እንዲያሰለጥነው ስጠኝ ብሎ ለምኖ ነበር? እስኪ መልሽልኝ?
የሚያይበት ዐይን፣ የሚራመድበት እግር፣ የሚዳዳስስበት እጅ የሚያስብበት አዕምሮ እንደሚያስፈልገው አስቦ የሰጠው እርሱ አይደለም? የሚበቃውን አካል ያልከለከለው፣ የማያስፈልገውን ያልሰጠው፣ ይህንንም አካል የሚያስተዳድርበትን እውቀት ሳይነፍግ በልግስና የሰጠው እርሱ ነው፡፡ በደመ ነፍሳዊ ዕውቀት ብቻ ቢተወው እንደ እንስሳት ካልሰበሰቡት የማይሰበሰብ፣ ከመብላት፣ ከመጠጣት እና ከመሞት ውጭ ሌላ ምንም ዕጣ ፋንታ የሌለው እንዲሆን አድርጎ ቢተወው ይችል አልነበረምን? በእውነት እግዚአብሔር ንፍገት የሌለበት ሁሉን ይሰጠን ዘንድ አስቦ የፈጠረን አምላክ መሆኑን ማወቅ አለብሽ፡፡
በዚህ ጥያቄ ውስጥ ያላችሁ ወገኖቼ ሆይ! አዳም በራሱ ድህነትን አመጣ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን አዳም ሳይለምን ሁሉ ያለው ባለጠጋ ሁኖ እንዲኖር ነበር፡፡ ሳያስብ ሁሉን አገኘ፤ አስቦ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ሁሉን አጣ፡፡ ሊቁ አትናቴዎስ በቅዳሴው ዕርቃንን፣ ባዶነትን፣ ባርነትን ረሀብን ጥምን፣ የመሳሰሉትን ሁሉ በፈቃዱ እንዳመጣቸው ይናገራል፡፡ ዕፀ በለስን ሰርቆ በመብላቱ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ለሌባ አይሞላለትምና ክርስቶስ እስኪወለድ ድረስ ሁሉን ሲለምን ኖረ፡፡
 ከኃጢአቱ ባይካፈልም ‹‹የኃጥዕ ዳፋ ጻድቅ ያዳፋ›› እንዲሉ የእሱ ዳፋ ለክርስቶስም ደርሶት ድሀ ሆነ ተራበ ተጠማ ለመነ፡፡ ከዚህ በኋላ እንደገና አሁንም ክርስቶስ ሳንለምነው የሚያስፈልገንን አውቆ ሥጋውን ደሙን እንበላው እንጠጣው ዘንድ ሰጠን አሁንም የሚገርም ሌላ ስጦታ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ እንዲያውም ቀድሞ በምድር ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንበላ እንድንጠጣ  ሰጠን አሁን ግን እራሱን ሰጠን ታዲያ ‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል…..›› ማለቱ እንደማይከለክለው እያወቀ የአባቱን ፈቃድ መጠየቅ እንደሚወድ ልጅ፤ አባትም እንደማይነሣው እያወቀ ልጁ ፈቃዱን ሲጠይቀው ደስ እንደሚለው ያለ ነው፡፡
 ባለጠግነት በእግዚአብሔር ፈቃድ ድህነት በእኛ ፈቃድ ተሰጠን፡፡