>

Sunday, 27 July 2014

ዓለም ትዞራለች!?




ይህ ጉዳይ ለብዙ ዘመናት አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል፤ አንዳንዶችን እስከመቃብር ድረስ እንዲሸኙም ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ ይህች ዓለም የራሷ እንኳ ጉዳይ ሲነገራት ቶሎ መረዳት የማትችል ስለሆነች ስለ ራሷ ሰዎች የደረሱበትን ቢነግሯት አይሆንም ብላ ገደለቻቸው፤ ለነገሩ ስለዝግመተ ለውጥ እያወሩ አዝጋሚ ሳያደርጓት የቀሩ አይመስለኝም፤ ነገሮች ሁሉ ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ከዞረች በኋላ ነው የሚዞሩላት ይህም ማለት አንድ ዓመት ሙሉ ፊቷን የማታሳያቸው ፍጥረታት አሉ ማለት ነው፤ ነገር ግን የምትፈልገውን እስክታገኝ ድረስ በቀን አንድ ጊዜ በፀሐይ ፊት ሳትዞር ውላ አታውቅም፤ የምትፈልገውን ቀላውጣ፣ ለፀሐይ ፊቷን አስመትታ ሌሊቱን ደግሞ ከሌላው ወዳጇ ከጨለማ ጋር ታድራለች፤
የሚገርመው! ቀን እኮ በፀሐይ ፍቅር ተቃጥላ፣ የቁንጅናዋን  ጉንጮች ተራሮቿን አክስላ ስትመለከቷት ከፀሐይ ጉያ መውጣት የማትችል የፀሐይ ፍቅረኛ ትመስላለች፤ ወዲያውኑ እጆቿን ለጨለማ ስትዘረጋ ደግሞ ጊዜ አይወስድባትም ጨለማው ሲመጣም ሁለንተናዋን ለጨለማ አስገዝታ በፀሐይ ፍቅር መቃጠሏን ረስታ ፍፁም ጨለማውን መስላ ዓለሟን ስትቀጭ ታነጋለች፤
አይገርማችሁም! ፀሐይ ዘወር ብሎ እስኪመለስ እንዴት ፈጥና ቀዘቀዘች?
ውሃ ተኝቶባት፣ ጭቃነት ሠልጥኖባት እንዳይኖር ምክንያት የሆናት፣ ከላይዋ የነገሠውን ውሃ በነፋስ ጭኖ ፣በሙቀት አትንኖ ድራሹን ያጠፋላት ብቸኛ ወዳጇ ፀሐይ ነበር ጨለማ ምን አደረገልሽ ብትባል ምን ልትል ትችላለች፤
እኔ ግን እላችኋለሁ! ነገሩእንጅ እንዲህ አይደለም፤ በዚህ ሁሉ መለዋወጧ ዘወርዋራነቷን እረዳለሁ፤ አብራ ብትውል እንጅ አብራ የማታድር መሆኗን፣ አብራ ብታድር ቀን ከሌላው ጋር መቀላወጧን አወቅሁላት፤ እስኪ ንገሩኝ ከማን ጋር ነው አብራ የኖረችው? ማንንስ ነው እስከ መቃብር የተከተለችው? አንድ ወዳጅ ብቻ እንዲኖራት አትፈልግም፤ ቀን ፊቷን የሰጠችውን ማታ ጀርባዋን የምትሰጥ ዘማ ልብ ናት፤ ማር ይስሐቅ ዓለምን በገለጠበት አንቀጽ ‹‹ዓለምሰ ዘማ ይዕቲ ዘወትር›› ይላታል፤ ግብሯን ያወቀባት ያለ አይመስለኝም፤
ለጊዜው በምትሰጣቸው ፍቅር ልባቸውን አሳብዳ፣ ፈጣሪያቸውን አስክዳ ግብሯን እንዳይረዱባት፣ ኅልፈቷን እንዳያውቁባትታደርጋለች፤ ከፍቅሯ ፅናት የተነሣ ራሷ ላይ ያወጣቻቸው፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ መቃብር እንዲወርዱ ያደረገቻቸው ምንኛ ብዙ ናቸው፤ ቀኑን ከፈርዖን ጋር አሳልፋ ሌሊቱን ከእስራኤል ጋር ታድራለች፤ ግብጽን ስትለቅ ፍቅሯን ለስደተኛው እስራኤል አደረገች፤ ከሠረገላ አውርዳ ፈርዖንን ወደ መቃብር፣ ሙሴን ደግሞ ወደ ከነዓን በክብር ሸኘቻቸው፤ ዓለም ትዞራለች አላልኋችሁም? ሙሽርነትን በኃዘን፣ ደስታን በመከራ፣ ጥጋብን በረሀብ፣ ሹመትን በሽረት፣ ሕይወትን በሞት፣ ንጉሥነትን በሬሳነት፣ ክብርን በውርደት፣ ነጻነትን በእንግልት፣ ባለጠግነትን በድህነት፣ ስትለውጥ ማን ይቀድማታል፤ የነበረውን እንዳልነበር ማድረግ ትችልበታለች፤ የዞረችለትን ስትዞርበት፣ የሳቀችለትን ስታስቅበት፣ ደጅ የጠናችውን ደጅ ስታስጠናው፣የረገጣትን ስትረግጠው፣ የሰቀለችውን ስታወርደው፣ ኣላያችኋትም? ከእነ ሔሮድስ ጋር ሆና የትናንትናውን ቀን አሳለፈች፤ በእነ ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቷን መለሰች  የሐዋ. 12÷23 ዛሬ ግን እንደዚያ አይደለም እነ ሔሮድስን በሞት ሽራለች፤
አሁንማ ሲገባኝ ለካ ጨለማ የሚፈጠረው ዓለም ጥላዋን ስትጥልብን ነው፤ በፀሐይ ፊት እንዳንሆን ምድር ስትዞርብን ዓለም ፊቷን ስትመልስብን ያን ጊዜ እኛ ሁላችን መሬታውያኑ በጨለማ ውስጥ እንድንርመሰመስ እንገደዳለን፤ እርስ በእርስ እንዳንተያይ እንሆናለን፤
እንኪያማ በሕይወታችን የተፈጠረው ጨለማ ከዓለም ግርዶሽ የተነሣ ነው ማለት ነው፤ እርስ በእርሳችን በፍቅር ዐይን እንዳንተያይ፣ በፀሐይ ክርስቶስ ዙፋን ፊት በድፍረት እንዳንቆም ጥላዋን የጣለችብን እርሷ ናት ዓለም መካከል የገባችበት ሕይወት ሁል ጊዜም ጨለማ ነው፤ ተስፋ መቁረጡ፣እንደ ልቤ የሚሉት ወዳጅ ማጣቱ፣ ፍትሕ መጉደሉ፣ የሰው ልጅ እርስ በእርስ መገዳደሉ፣ መልካሙ ኑሮ መጥፋቱ፣ ሰላም ከምድር ላይ መታጣቱ ሕይወት በጨለማ ውስጥ እንድትኖር ያደርጋታል፤ ይህን ሁሉ ያመጣው የዓለም ዘዋሪነት እኮ ነው፤ ዓለምማ ባትዞር ሁልጊዜ በፀሐይ ፊት የምንሆንም አይደለን? ጨለማን እንዴት እናውቀዋለን፤
እኔ ግን ዛሬ በዓለም ፊት ላላችሁ ሁሉ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤ ማንኛውም ፍጥረት ከዓለም ፊት ለፊት ሆኖ የተፈጠረ ነው፤ ከዓለም ጀርባ የሆነው ከዓለም መዞር የተነሣ ነው፤ እውነት ነው! ዛሬ እንደ ምታዩት የዓለምን ፊት ያገኙ ሰዎች ከዓለም ጋር ይጫወታሉ፤ ዓለም ትዞራለች ቢባሉ እንኳን ማመን ያቅታቸዋል፤ እስኪ ጠይቁልኝ! ከሹመት ወደ ሽረት፣ ከባለጠግነት ወደ ድህነት፣ ከዙፋን ቤት ወደ ወኅኒ ቤት፣ ከፈራጅነት ወደ ተከሳሽነት፣ ከመጽዋችነት ወደ ለማኝነት፣ ስለተለወጡ ሰዎች ምን ይሏችኋል፤ በእውነት በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለችው ዓለም የምትዞር ባትሆን ኖሮ እንዲህ ይደረግ ነበር ብላችሁ ታስባላችሁ?
አሁን ከተለመደውና ዓለም ስለራሷ ከምታወራው ወጥታችሁ አስቡ፤ እኔ እያልኋችሁ ያለሁት መሬት በፀሐይ ፊት ስለምታደርገው እሽክርክሪት አይደለም፤ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ስላለችው ዓለም እንጅ፤ መቸም ቢሆን እግዚአብሔር በፈጠራት ክብ ዓለም ውስጥ ስንኖር በራሳችን ውስጥ እምናስቀምጣት ሌላ ክብ ዓለም ደግሞ በውስጣችን እንደምትኖር የተረጋገጠ ነው፤ ክብ ከመሆኗ የተነሣ ይዘናታል ስንል ታመልጣለች ምክንያቱም ማንጠልጠያ የሌላት ክብ ስለሆነች እኮ ነው፤ እሷ እንደ ኳስ ያለች ናት፤ ያገኛት እስከ ጎል ድረስ የሚያንከባልላት ያላገኛት ደግሞ እስኪያገኛት ቆሞ የሚጠብቃት ናት፤ መቸም ቢሆን አንድ ነገር አንረሳም በኳስ ዓለም ተጫዋች ሁሉ ኳስ የማግኘት እድል ይኖረው እንደሆነ እንጅ ሁሉም ሰው ለጎል የታደለ እግር ሊኖረው አይችልም፤ ሁላችን እንጫወታለን ነገር ግን ጎል በማግባት ጥቂት ሰዎችን ብቻ አድንቀን እንለያያለን፤
እንዲህ ያለች ክብ ዓለም ላይ እምንኖር ሰዎች ነን፤ ዛሬ ወደ እኛ ዙራ ከሆነም እንኳን ትናንት ከፊቷ የነበሩ፣ ዛሬ ደግሞ ከጀርባዋ ያደረገቻቸው በዚህም ምክንያት ጨለማ ውስጥ የከተተቻቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ልንዘነጋ አይገባም፤ በእርግጥም እኮ ስናየው ትናንት እኛ የነበርነው ከጀርባዋ ነው ዛሬ ነው ፊቷን የዞረችልን፤ ነገ ደግሞ ተራው ለሌላ ነውና መዞሯ አይቀርም፤ እንደ ማጅላን እንኳን አብረናት ብንዞር ቀድማን እንደምትዞርብን ሳልጠራጠር እነግራችኋለሁ፤ ማጅላን ዛሬ የት አለ? ዓለምን እንዳልዞረ ሁሉ ዛሬ ዓለም ዞረችበትና ከመቃብር ጓዳ ውስጥ ገብቶ ተሰወረ፤ ብታምኑም ባታምኑም ዓለምና ማጅላን ዛሬ ፊት ተዟዙረዋል፤ ምን አልባት ማጅላን በዓለም ላይ የዞረበትን ጊዜ እንጅ ዓለም በማጅላን ላይ የዞረችበትን ጊዜ ማወቅ ሊከብደን ይችል ይሆናል፤ ምክንያቱም በሰዎች ላይ የምትዞርበት ጊዜ ተለይቶ ስለማይታወቅ ነው፤
አሁንም ስሙኝ ሰዎች! እኛ በዓለም ውስጥ የተሠራን ሌላ ዓለሞች ነን፤ በነቢያት በተነገረለት እውነተኛ ፀሐይ በክርስቶስ ፊት እንዞራለን፤ሚል4÷2 እንደ ሉል ያለን ዓለሞች አይደለንምና አንድ ጎናችንን ደብቀን አንድ ጎናችንን የምንሰጠው አይደለንም፤ እርሱ በውስጥም በውጭም የሚኖር ፀሐይ በመሆኑ ውስጣችንም ሆነ ውስጣችን ሳይሰወረው ያበራልናል፤ ይህች ዓለም ግብሯ እኛ እንድንዞርባት የተሠራች ናት እንጅ እርሷ እንድትዞርብን አይደለም፤ ሳትዞርባችሁ ዙሩባት አለበለዚያ ዓለም ትዞራለች፡፡
እንዲህ እንደምትዞር አውቀው አስቀድመው የዞሩባት ሰዎች ምንኛ ብጹዐን ናቸው!
                          ጅማ፣ ኢትዮጵያ




6 comments:

Unknown said...

እንዲህ እንደምትዞር አውቀው አስቀድመው የዞሩባት ሰዎች ምንኛ ብጹዐን ናቸው!

Unknown said...

very good beginning

Unknown said...

ውድ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ፣
ብሎግህን አነበብኩትና አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጠይቅህ አሰብኩ። የዓለምን መዞር ለምሳሌነት ተጠቅመህ ነው ያስተማርከው፣የኔ ጥያቄ ግን ቀጥታ የመሬትን መዞር የተመለከተ ነው።
፩.''ነገሮች ሁሉ ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ከዞረች በኋላ ነው የሚዞሩላት ይህም ማለት አንድ ዓመት ሙሉ ፊቷን የማታሳያቸው ፍጥረታት አሉ ማለት ነው።''ብለሃል
ሳይንስ እንደሚለው ከሆነ መሬት በራሷ ዛቢያ ዙሪያ በ 24 ሰአት ዉስጥ አንድ ሙሉ ሽክርክሪት(ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ) እየተሽከረከረች ነው በፀሐይ ዙርያ ባላት መስመር(ምህዋር)የምትዞረው። ስለዚህ በ24 ሰአት ዉስጥ ሁሉም መሬት ላይ ያሉ ነገሮች ለ 12 ሰአታት አካባቢ የፀሐይ ብርሀን ያገኛሉ(በርግጥ እንደየወቅቱና እንደየአካባቢው ልዩነት አለው)። የመሬት በፀሐይ ዙርያ መዞር የሚያመታው የወቅቶችን መለዋወጥ ነው።

፪. ሌላው ደግሞ ''...ወዲያውኑ እጆቿን ለጨለማ ስትዘረጋ ደግሞ ጊዜ አይወስድባትም...'' ካልን በመሬት የተለያዩ ቦታወች ላይ የሚታየዉን የሰሰአታት ልዩነት እንዴት ታየዋለህ? እንደሚታወቀው ለምሳሌ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ከ6 እስከ 8 ሰአታት የሚደርስ ልዩነት አለ።

Unknown said...

ውድ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ፣
ብሎግህን አነበብኩትና አንዳንድ ጥያቄዎችን ልጠይቅህ አሰብኩ። የዓለምን መዞር ለምሳሌነት ተጠቅመህ ነው ያስተማርከው፣የኔ ጥያቄ ግን ቀጥታ የመሬትን መዞር የተመለከተ ነው።
፩. ''ነገሮች ሁሉ ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ከዞረች በኋላ ነው የሚዞሩላት ይህም ማለት አንድ ዓመት ሙሉ ፊቷን የማታሳያቸው ፍጥረታት አሉ ማለት ነው።''ብለሃል
ሳይንስ እንደሚለው ከሆነ መሬት በራሷ ዛቢያ ዙሪያ በ 24 ሰአት ዉስጥ አንድ ሙሉ ሽክርክሪት(ሦስት መቶ ስልሳ ዲግሪ) እየተሽከረከረች ነው በፀሐይ ዙርያ ባላት መስመር(ምህዋር)የምትዞረው። ስለዚህ በ24 ሰአት ዉስጥ ሁሉም መሬት ላይ ያሉ ነገሮች ለ 12 ሰአታት አካባቢ የፀሐይ ብርሀን ያገኛሉ(በርግጥ እንደየወቅቱና እንደየአካባቢው ልዩነት አለው)። የመሬት በፀሐይ ዙርያ መዞር የሚያመታው የወቅቶችን መለዋወጥ ነው።

፪. ሌላው ደግሞ ''...ወዲያውኑ እጆቿን ለጨለማ ስትዘረጋ ደግሞ ጊዜ አይወስድባትም...'' ካልን በመሬት የተለያዩ ቦታወች ላይ የሚታየዉን የሰሰአታት ልዩነት እንዴት ታየዋለህ?እንደሚታወቀው ለምሳሌ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ከ6 እስከ 8 ሰአታት የሚደርስ ልዩነት አለ።

Unknown said...

ደስ የሚል እይታ ነው የምንማርበት ብቻ ሳይሆን የምንለወጥበት ያድርግልን

Unknown said...

Nice beginning! This is what, I feel, is expected of Church fathers as it is good to address scholars through such theological and philosophical views.

Having said this, may you reflect on the time gap between our calendar and the archaeological calendar (ours is 7008 since creation but archaeological findings indicate beyond that). I think it would be invaluable if addressed.
Remain Blessed!