>

Friday, 14 November 2014

መልክ የሌለው ውብ፣ ጣዕም የሌለው ጥዑም



አንዳንድ ጊዜ ሁሉን ነገር በትኩረት ለመመልከት ሞክሩ በተለይ አምላካችን እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታትን በአንክሮ ብትመለከቷቸው መልካም ነው፤ ምክንያቱም ከልባችሁ እየተቀበለ አፋችሁ የሚናገራቸው ውድ ቃላት ሊገልጡት የማይቻላቸው ውበት አላቸውና፡፡ የሥነ ፍጥረትን ነገር አስብና በሰማይና በምድር የሞላውን ፍጥረት እመለከትና መገረም ይይዘኛል፤ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹የፍጥረታትን አነዋወራቸውን፣ የሰማይን ምጥቀቱን፣ የምድርን ስፋቱን ሊያይ ህሊናየ በነፋሳት ትከሻ ላይ ሆኖ ምሥራቅና ምዕራብን፣ ሰሜንና ደቡብን ይበራል ነገር ግን የሥነ ፍጥረት አኗኗር አልመረመረው ብሎ ህሊናዬ ወደ አለመመርመር ይመለሳል›› ብሎ የተናገረው የሥነ ፍጥረት ጉዳይ አስደናቂ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ 
የትኛዉም ዐይነት ፍጥረት ያለ አንዳች ፍጥረት እንዳልተፈጠረ እርግጠኛ ሆኘ እነግራችሁ አለሁ፤ ቢሆንም ግን የአንዱ ውበት ከሌላው የተለየ መሆኑ ደግሞ የበለጠ እንድንደነቅ የሚያደርገን ሲሆን ምድራዊውን ኑሯችንን እንዳይሰለችና ምቾት ያለው እንዲሆን ያደረገልን ይህ የሥነ ፍጥረት ውበት እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ለማንኛውም
ዛሬ የምነግራችሁ ከነዚህ አንዱ ስለሆነው የውሃ ውበት ነው ሌላውን ደግሞ ይህ ከተመቻችሁ ሌላ ጊዜ አወራችኋለሁ፡፡ ውሀ በሕይወታችን ውስጥ ዘወትራዊ ከሆኑ አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ የሚመደብ የሕይወታችን መሠረት ነው፡፡ ለነገሩ አካላችንም ቢሆን የተገነባው ከብዙ ውሃ ነው ስለዚህም ለአንድ ቀንም ቢሆን ከውሀ መለየት የማንችል የውሀ ጥገኞች ነን፤
እንግዲህ ሳይንሱም እንደሚያምነው ውሀ የሀይድሮጅንና የኦክስጅን የተዋሕዶ ውጤት ነው፤ በተዋሕዶ አብዛኛውን ድርሻ ሀይድሮጅን የወሰደ ሲሆን ኦክስጅን ዝቅተኛውን ሥፍራ ይይዛል ማለትም አንድ እጅ ኦክስጅን፣ ሁለት እጅ ሀይድሮጅን ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ሆነው ያለ መቀናናት በፍቅር ይኖራሉ እንጅ አንድም ቀን ታናሹን ድርሻ የያዘው ታላቁን ድርሻ በያዘው አይቀናም እኛ ብንሆን ስንት ጊዜ በተካሰስን ነበር፤ ታናሽነትን በታላቅነት ከለወጥን በኋላ የበላይነት ያምረናል፤ በነርሱ ዘንድ ግን እንዲህ የለም አሁንም በፍቅር ይኖራሉ፡፡ ይህም ይሁን ሌሎችም ሊያደርጉት ይችላሉ እግዚአብሔር ጥበበኛ አምላክ ነውና እርሱ ከወደደ እሳትና ውሃንም አስማምቶ ማኖር የማይሳነው አምላክ እንደሆነ እናምናለን፡፡
እኔን በጣም የሚያስገርመኝ ውሃ ጣዕም አልባ፣ ሽታ አልባ፣ መልክ አልባ ነው ተብሎ ይነገርለታል፤ እነዚህ ሦስት ነገሮች ናቸው እያንዳንዱን ፍጥረት ውብና አስደናቂ አድርገውት የሚኖሩት እንጅ ያለ እነዚህ ምን ውበት፣ምን መወደድ፣ ምን መፈለግ ሊኖር ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? ከእናንተ መካከል ማንም ቢሆን ስለእያንዳንዱ ፍጥረት ምኑን ትወደዋለህ ተብሎ ቢጠየቅ መዓዛውን፣ መልኩን፣ ጣዕሙን ሊል እንደሚችል  አልጠራጠርም፤ ውሀ ግን ከነዚህ ሁሉ ውጭ ሆኖ ሳለ ፍጥረት ሁሉ በየጊዜው የሚፈልገው እጅግ ተወዳጅ ፍጥረት ነው፡፡ የውሀ መወደዱ ከግብሩ የተነሣ ነው እንጅ ከላዩ ላይ ባሉ አስደሳች ነገሮች አይደለም፤
ለነገሩ እኔ ውሃ መልክ፣ ሽታ፣ ጣዕም የለውም በሚለው አልስማማም በእርግጥ በአንድ ነገር እስማማለሁ፤ ለመልኩ፣ ለሽታውና ለጣዕሙ ስም አልተሰጣቸውም፤ እናንተ ከምታውቁት አንድ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ ሰማይ በራሱ መልኩ ስም የለውም፤ ነገርግን በስምምነት ሰማያዊ የሚል የመልክ ስም አውጥተናል በሚገባ ካያችሁት ግን ሰማያዊ ማለት ሰማይ የሚመስል ማለት እንጅ የሰማይ መልክ ምን አይነት እንደሆነ የሚያስረዳ ስም አይደለም፡፡ እኛ ግን በትርጓሜ ትምህርታችን ሰማይ ማለት ስዕለ ማይ ማለት ስለሆነ የውሃ መልክ ያለው ነው ብለን ነው የምናምነው፤
ምንም ይሁን ምን መወደድ የመልክና የጣዕም ጉዳይ አይደለም፤ እንዲያው የፈጠረን መወደዱን ከሰጠን ከላይ በተሰጠን ስጦታ ነው ነገሮች ሁሉ የሚወሰኑት ማለት ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ከሆነ ለምትወዱት ነገር ለምን መልክ ትሰጡታላችሁ? እኔ ስሰማ ብዙ ጊዜ ባል ለሚስቱ፣ ጎረምሳ ለፍቅረኛው፣ ወዳጅ ለወዳጁ የሎሚ ሽታ፣ የብርቱካን ጣዕም፣ የጽጌ ረዳ መልክ ሲሰጡ ነፍሳቸው በወደደችው ውብና ጣፋጭ ነገር ሲመስሉ፣ የሌላትን ስም ሲሰይሙ እሰማለሁ፤ እስኪ ልብ ብላችሁ ተመልከቱት፤ የሎሚ ሽታም የሚበልጠው ሌላ ሽታ አለ፣ የብርቱካን ጣዕምም ይሰለቻል፣ የጽጌረዳ ውበትም ይጠወልጋል፣ ከዚህም አስበልጣችሁ መንደሪን፣ ትርንጎ፣ አቡካዶ፣ ፓፓያ ብትሉም አንዱ ካንዱ ይበልጣል፣ አንዱ ከሌላው ያንሳል፣ ነገር ግን በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባው ፍቅር ይህ ሁሉ ሊኖርበት የማይገባው ዘለዓለማዊ ፍቅር ነው፤ እና እንዴት ሆኖ ነው ከዚህ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው፤ ምን አልባት በዚህ ምድር በስፋት እየታየ ለመጣው በተለይም ደግሞ አሁን አሁን እየተባባሰ ለመጣው የፍቅር መጥፋት፣ የፍቅረኛሞች መሰለቻቸት፣ የወዳጅ አለመተማመን ምክንያት ይህ ይሆን እንዴ ብየ አስባለሁ፤
ዘወትር እንደ ማይሰለቸው የውሃ ጣዕም ሁልጊዜ የሚጣፍጥ ፍቅር እንዲኖረን ያስፈልጋል ፍቅር እኮ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ የሕሊና ቀለብ ነው፤ ስለዚህ ሳንሰለቸው እንደምንመገበው ውሃ ዘወትር በቀላሉ ሳንጨነቅ ደጃችን ላይ ልናገኘው ይገባናል፡፡ ሰው የውሃን ቀለብነት ከቁጥር ሳያስገባው እንደሚኖረው ሁሉ ፍቅርን ቁጥር አልሰጠው ይሆናል እንጅ ያለ ፍቅር በምድር እና በሰማይ ያለውን ኑሮ መኖር አይቻልም፡፡ በሌላ አነጋገር ፍቅር የሰማያዊውና የምድራዊዉ ኑሮ ሕይወት ነው ማለት ነው፤
የሕይወት ምን መልክ አላት፣ ጣዕሟንስ በምን ስም እንጠራዋለን፣ ሽታዋንስ ከየትኛው በጎ መዓዛ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን? እንዲያው ዝም ብለን የመንፈስ ቅዱስ መዓዛ እንላታለን እንጅ ሌላ ምን ስም ልናገኝላት እንችላለን፡፡ ውሃም የሥጋ ሕይወት ሆኖ ሳለ መልክ፣ ጣዕም፣ ሽታ የለውም፡፡ ከኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን እንደምታውቁት ሲያገቡና ሲጋቡ የኖሩትና ምድርንም በትውልድ እንድትሞላ ያደረጓት፣ መልኩ፣ ጣዕሙ፣ ሽታው ምን እንደሆነ ሳያውቁ በጀመሩት የፍቅር ሕይወት ነው፤ ይገርማችኋል እንዲህ ሆኖ የተጀመረው የፍቅር ጉዞ ብዙ ዓመታትን ተጉዞ የትዳር ኢዮቤልዩ ሲከበር አይተናል አሁን ግን ያለው ትውልድ ለዚህ የታደለ አይመስልም፤ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ኢዮቤልዩ ሲያከብሩ የምንመለከተው፤ ልጅ የሚወልድ ሰው አስቀድሞ መልኩን አይቶ፣ ድምጹን ሰምቶ የሚወልደው አይደለም እንዲያው ምንም ይሁን ምን ገና ወደ ዓለም ሳይመጣ ጀምሮ ይወደዋል፤ በመልክና በድምጽ የሚሆን ፍቅር ለጥቂት ጊዜ ብቻ የሚቆይ ሲሆን እግዚአብሔር የሠራውን ሁሉ አስተካክሎ መውደድ በሚለው ቃል ኪዳን መሠረት የሚሆነው ፍቅር ግን ማለቂያ የሌለው ፍቅር ነው፡፡
እግዚአብሔር የባረከው ሰው ስም ባይኖረውም ይወደዳል፤እግዚአብሔር ስም ሳይሰጥ ያከበራቸው ብዙ ናቸው በታላቁ መጽሐፍ ውስጥ ዕገሌ ተብሎ የተጠራ የግል ስሙ የሌለ ሰው ታገኛላችሁ ነገር ግን እግዚአብሔርን በቤቱ ማስተናገድ የቻለ ታላቀ ሰው ነው፡፡ የመጨረሻውን የፋሲካ ራት ያደረገው በዚህ ሰው ቤት ነው፤ ዓለም ሲጠብቀው የነበረውን የመዳን ድምጽ ክርስቶስ የተናገረው በዚህ ሰው ቤት ነው፡፡ ‹‹ይሕ ስለ ብዙዎች የሐጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› በዚህ ሰው ቤት የተሰጠ መግለጫ ፡፡ ሥጋውና ደሙን ክርስቶስ የሠራው ለደቀ መዛሙርቱም የሰጠው በዚሁ ሥፍራ ነው
እንግዲያውስ ስምያለው ነገር ሳይሆን መወደድ ያለውን በጎ ነገር እንዲሰጣችሁ ለምኑ፤ ስም፣ መልክ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛችሁ አይደለምና፡፡

5 comments:

Teshome Ayele said...

It is good article please abatachin yitsafu... post more preaching and tegsats.....

Haftamu said...

ቃለ ሕወይት ያሰማለን፡፡

Anonymous said...

ቃለ ሕይወት ያሰማልን

Yohannes Mengistu said...

እግዚአብሔር የባረከው ሰው ስም ባይኖረውም ይወደዳል፤እግዚአብሔር ስም ሳይሰጥ ያከበራቸው ብዙ ናቸው በታላቁ መጽሐፍ ውስጥ ዕገሌ ተብሎ የተጠራ የግል ስሙ የሌለ ሰው ታገኛላችሁ ነገር ግን እግዚአብሔርን በቤቱ ማስተናገድ የቻለ ታላቀ ሰው ነው፡፡ የመጨረሻውን የፋሲካ ራት ያደረገው በዚህ ሰው ቤት ነው፤ ዓለም ሲጠብቀው የነበረውን የመዳን ድምጽ ክርስቶስ የተናገረው በዚህ ሰው ቤት ነው፡፡ ‹‹ይሕ ስለ ብዙዎች የሐጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› በዚህ ሰው ቤት የተሰጠ መግለጫ ፡፡ ሥጋውና ደሙን ክርስቶስ የሠራው ለደቀ መዛሙርቱም የሰጠው በዚሁ ሥፍራ ነው

Unknown said...

tmchetonal....ቃለ ሕወይት ያሰማለን፡፡