>

Wednesday, 18 November 2015

ሦስቱ ስደታት

   ክፍል ሁለት
ባለፈው ክፍል እንደተመለከትነው በኃጢአቱ ምክንያት ርስቱን ተነጥቆ ስፍራውን ለቆ የመጣው የሰው ልጅ በዚህም ዓለም በልዩ ልዩ መንገድ ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወር ይኖራል፡፡ ከሀገሩ ወጥቶ ከሄደ ደግሞ በልዩ ልዩ ፀዋትዎ መከራ መፈተኑ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ስደትን ከባድ እሚያደርገው ልጅ ይዞ የሚያደርጉት ስደት ነው ልጅ ይዞ አስከትሎ የሚያደርጓት ስደት የመከራዎች ሁሉ እናት ናት፡፡ በእመቤታችን ም የሆነው ይህ ነውና በመከራ የሚተካከላት ማንም የለም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ‹‹ሐዊረ ፍኖት በእግሩ ሶበ ይስዕን ሕጻንኪ ያንቀዐዱ ኀቤኪ ወይበኪ በእግሩ መሐድን በደከመ ጊዜ ወደ አንች ቀናብሎ ያለቅሳል›› እንዳለ በነገር ሁሉ ሕጻናትን መስሏልና ሕጻናት እናቶቻቸውን የሚጠይቁትን ሁሉ ጠይቋታል፡፡ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ተብላ ነበርና በብርቱ ፈተና ውስጥ አለፈች፡፡
ሔሮድስ ግን እሷን አሰድዶ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ክብሩ ከፍ ከፍ አለ፤ የሊባኖስ ዝግባ የትኛውንስ ያክል ቢገዝፍ በቅርንጫፉ ዓለምን ቢከድን የሰማይ አዕዋፍ ቢንጠላጠሉበት፣ የምድርም እንስሳት ቢጠለሉበት ምን ቁም ነገር አለው፤ አንዲት ክብሪት እንዳልነበረ ታደርገው የለ! ይገርማል እኮ! ያ ግዙፍ ዛፍ በትንሽ ክብሪት በትንሽ ምሳር የሚጠቃ ይመስላችኋል? አንዲት ክብሪት ብዙ ደን ታጠፋለች፤ የሔሮድስም ግነት እግዚአብሔር ቁጣውን እስኪገልጥ ብቻ ነው፡፡
      እግዚአብሔር ሦስት ዓመት ከመንፈቅ የንስሐ ጊዜ ቢሰጠው አልመለስ ያለ ሔሮድስን ከስሩ ነቅሎ እንዳልነበረ አድርጎ በሞት ቀጣው፤ ያንጊዜ ‹‹ኃጥዕ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ገኖ አየሁት ስመለስ ግን አጣሁት ቦታውን ፈለግሁ አላገኘሁትም›› መዝ 36÷35-36 ብሎ ነቢዩ ዳዊት የተናገረው ደረሰ፡፡ ቀናት ሲቆጠሩ ለካ ኃጢአቱም በእግዚአብሔር ፊት እየተቆጠረበት ነበርና የዘመኑ ሳይሆን የክፋቱ ቁጥር ሲሞላ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ተፈረደበት፤ ዘመን ባይሞላም ክፋት ሲሞላ ያለ ጊዜም ሊያስነሣ ይችላል ክፉ ሰው እስከ ዕድሜው ፍጻሜ የሚኖር አይደለም፤ እንዲያው ኃጢአቱ ሲሞላ እግዚአብሔር ከተወሰነለት ዕድሜ በታች ሊያነሣው ይችላል እንጅ፡፡
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተመዘገበችው በለስ እንደ ሔሮድስ ያሉ ሰዎችን ትመስላለች፤ የእርሻው ባለቤት ለሦስተኛ ጊዜ መጥቶ አንዳች ፍሬ ያላገኘባት በዚህም ምክንያት ‹‹እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቆርጠህ ጣላት›› የተባለላት፡፡ ሉቃ 13÷6 ሔሮድስንም ጠበቀው እና በጎ ፍሬ ማፍራት አልችል ሲል አጫጆችን ልኮ አጨደው፡፡

ሦስቱ ስደታት

  
               ክፍል አንድ

በዚህ ምድር ላይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ እመቤታችን የከበረ ማንም የለም፤ ክብሯ ከምድራውያኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰማውያኑ ጋር ስንኳን ሊነጻጸር የማይችል ታላቅ ነው፤ ነገር ግን በዚህ ምድር እንደ እመቤታችን በመከራ የተፈተነ ደግሞ ማንም የለም፤ እንደ ሚታወቀው ይህች ዓለም ለእግዚአብሔር ሰዎች የፈተና መድረክ እንጅ የስጦታ ሰገነት አይደለችምና በነገር ሁሉ እንደ ሰማዕታት ተፈትናለች፡፡ ከልጅነቷ እስከ እለተ ሞቷ፣ ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ ዮሐንስ ሁሉም ያለፈችባቸው መንገዶች በእሾኽ የታጠሩ እንጅ የአበባ ምንጣፍ የተጎዘጎዘባቸው አልነበሩም፡፡
      በዚህ ሁሉ ፈተና በእመቤታችን ሕይወት ውስጥ አስቸጋሪው የፈተና ወቅት ያለፈው ጌታችን በተወለደ ማግስት በተነሣው ስደት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ጌታችን የመጣው ዓለምን እንደ ሰውነቱ ዞሮ ሊባርካት እንደ አምላክነቱም ሕይወትን ሊሰጣት ነውና ሰይጣን በክፉ ሀሳቡ ያረከሳትን ዓለም ለመቀደስ ኃጢአት ወደ በዛባቸውና በጣዖት በኃጢአት የተሰነካከሉትን ለማዳን ሰይጣን ሳያውቅ ባስነሣቸው ክፉ ሰዎች ምክንያት ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ግብፅ እንዲሰደድ ግድ ሆነ፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ በረከት ወደ ምድረ አፍሪቃ ተሸጋገረች፡፡
      የገሊላ ንጉሥና ሕዝብ ሳያውቁት በረከታቸውን ለሌላ ሕዝብ አሳልፈው ሰጡ፤ በነቢይ ‹‹ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱነ የተነሣ ጠፍቷል›› እንደ ተባለ የልደት እለት እነሱ ተኝተው ሳሉ በዚያች ሌሊት ከሩቅ ምሥራቅ የመጣው ሕዝብ በረከተ ልደቱን ተሳትፎ ተመለሰ፤ ዛሬ ደግሞ  እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከአህጉር ሁሉ መርጦ በመካካላቸው ቢወለድ ለተመረጡለት በረከት ብቁ ባለመሆናቸው በረከታቸውን እያሳደዱ መርገማቸውን አጨዱ፡፡ እጃችን ላይ ያሉ ግን ሳንጠቀምባቸው የሚያልፉ በረከቶች እንዳይኖሩ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡ ገሊላውያን በወቅቱ የነበራቸው ሀሳብ ከሀገር ሲያስወጡት ከሰውም ልብ የሚያስወጡት መስሏቸው ነበር፤ ውስጠ ምሥጢሩ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት፤ ያኔ ጌታ እንዲሰደድ ባይሆን ኖሮ ታላላቁን የግብፅ ገዳማት እነ ገዳመ አስቄጥስን፣ ገዳመ ሲሀትን  በሀገራችንም እነ ዋልድባን፣ ጣና ቂርቆስን ማግኘት ባልተቻለም ነበር፡፡ ይህን እግዚአብሔር እንጅ ሌላ ማን ሊያውቀው  ይችላል?
      በዚህ ወቅት ታዲያ የንጉሡ እናት የሰውና የመላዕክት እመቤት ድንግል ማርያም የደረሰባትን ፈተና ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም፤ አባቷ አዳም እናቷም ሔዋን የደረሰባቸው መከራ በሥጋም በነፍስም ከባድ ነበርና ለዚያ ማስረጃ እንዲሆን እመቤታችን ያለ ርህራሄ አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎችን አሳልፋለች የሰማዕታት እናታቸው ናትና በምትቀበለው መከራ ለሰማዕታት መንገድ ጠራጊ አደረጋት፡፡ እመ ብዙኃን የሚያሰኛትም አንዱ ይህ ነው እመ ብዙኃን የምትባለው ስለሦስት ነገር ነው:-

እመ መናንያን

እመ ሐዋርያት

እመ ሰማእታት በመሆኗ ነው።
የመናንያን እናት የምንላት በሦስት ዓመት እድሜዋ ወገኖቿን የአባቷንም ቤት ረስታ በቤተ መቅደስ ስለኖረች ነው አባቷ ዳዊት እንደተናገረ መዝ 44 ከቤተ መቅደስ በአስራ ሁለት ዐመቷ እንድትወጣ የተደረገ ቢሆንም እንኳን ወደ ወገኗቿ ለመሄድ አላሰበችም ንጉሡ እግዚአብሔር ውበቷን የወደደላት መናኒተ ዓለም ናትና፡፡

Thursday, 29 October 2015

ማደሪያውን አይቸዋለሁ

በብሉይ ኪዳን ከነቢያት አንዱ ለእግዚአብሔር ሲሳል ‹‹ኢይሁቦን ንዋመ ለአእይንትየ ወኢድቃሰ ለቀራንብትየ፤ ለዐይኖቸ እንቅልፍን ለቅንድቦቼም ሽልብታን አልሰጣቸውም›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ እስኪያይ ድረስ ለሰውነቱ እረፍትን እንደማይሰጥ በልቡ ጽኑ መሀላን ምሎ እንደ ነበረ ተመዝግቧል መዝ 131÷2፤ እንደ ተናገረውም ‹‹ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ እነሆ በኤፍራታ በዱር ተጥሎ እንደ ኅጻናት ሲያለቅስ ሰማነው ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን›› ብሎ የእግዚአብሔርን ማደሪያ አግኝቶ እስኪመለስ ድረስ ሱባዔውን አላቋረጠም::

 በሐዲስ ኪዳንም እንደዚሁ ‹‹ሊቅ አይቴ ተሐድር›› እያሉ ከሀገር ወደ ሀገር እየተዘዋወረ ያስተምር የነበረውን ጌታ በኋላው እየተከተሉ ማደሪያውን እስኪያሳያቸው ድረስ ይጠይቁት የነበሩ ሁለት ሰዎች እንደነበሩ ተጽፏል፡፡ ዮሐ1÷39 እርሱም ያልፈለጉትን የሰው ልጆች ሊፈልግ ነውና የመጣው የሚፈልጉትን ሰዎች ኑ ማደሪያዬን አሳያችኋለሁ ብሎ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ከእርሱ ጋር ውለው ማደሪያውን አይተው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡

ለቅዱሳን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ከማየት ሌላ ደስታን የሚፈጥርላቸው ምን ነገር አለ? ማደሪያውን ፍለጋ ባሕር ያቋርጣሉ፣ በዋሻ ውስጥ መንገድ ያበጃሉ፣ ዓለም የማትገባቸው በመሆኗ የፍየል ሌጦ የበግ ለምድ ለብሰው በዋሻ በፍርኩታ ሰዎች ሆነው ሳለ ከሰው ተለይተው ይኖራሉ፣ መንገዳቸውን ከዓለም ለይተው ወደ እግዚአብሔር ይጓዛሉ፡፡

ዛሬ ለብዙ ዘመናት የተመኘሁት ተሳክቶልኝ እኔም የእግዚአብሔርን ማደሪያ ለማየት በጣና ባሕር ጀርባ ላይ እየተጓዝሁ ነው፤ የተጫንሁበት ጀልባ ወደፊት እየተጓዘ እኔ ግን በፍኖተ አእምሮ ወደ ኋላየ ተመልሼ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 8÷23 አንድም እያልሁ እየተረጎምሁ በገሊላ ባሕር ላይ በመርከብ ብዙ ጊዜ ይመላለሱ የነበሩ ደቀ መዛሙርቱን አስታወስሁ፤ኅሊናዬ በገሊላ ባሕር እንጅ በጣና ላይ የሚጓዝ አልመስለኝ አለ። መዳረሻዬም የጥብርያዶስ ማዶ ጌታ ተዓምራት ያደርግበት የነበረው ሥፍራ የገሊላ መንደር ይመስለኝ ነበር፡፡ ከመርከብ ስወርድ የጴጥሮስን አማት በንዳድ ታማ ጌታ ሲፈውሳት እንደማገኛት እያሰብሁ ነው የምጓዘው፡፡ እንዲያውም ባይገርማችሁ በአካል ሳይሆን በኅሊናዬ ተነሣሁና ጌታዬን  እንደ ሐዋርያት ከመርከቡ ጀርባ ፈለግሁት በሥጋ ሕግ ተኝቶ የማገኘውና ዓለም እንዲህ በጭንቀት ማዕበል ስትጠፋ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ መናፍቃን ስትዳፈን አይገድህምን? ልለው ፈለግሁ ውስጤን ፍርሃት ተሰማው፤ ያን ጊዜ በዘለዓለማዊ እንቅልፍ ውስጥ የነበርን እኛን ሊያነቃን ተኝቷል እንጅ ለባሕርዩ እንቅልፍ የሚስማማው ይመስልሃልን?ብሎ የሚገሥጸኝ መላኩን የላከብኝ መስለኝ፡፡

Monday, 19 October 2015

ነገረ ቤተ ክርስቲያን-- ክፍል ስድስት


አሥሩ የማሕሌት ደረጃዎች

( ከባለፈው የቀጠለ……)
6.   ቁም
በቤተ ክርስቲያናችን ቁም ንባብ፣ ቁም ዜማ ቁም ጸናጽል ያለ ሲሆን ሁሉም ትርጉማቸው ተመሳሳይ ነው፤አሁን ግን የምናየው ቁም ጸናጽልን ነው፡፡ በንዋያተ ቅድሳት ክፍል የምናየው ስሆነ ነው እንጅ ጸናጽ በራሱ የክርስቶስን መከራ የአበውን ተስፋ ፍጻሜ የሚያሳይ ነው- አሠራሩ፡፡ በጸናጽል ከምናቀርባቸው አንልግሎቶች አንዱ ይህ የቁም ጸናጽል ሁለት ነገሮችን የሚያሳይ ነው

6.1   የመጨረሻዋን ቀን ለማስታወስ:-

በእግዚአብሔር  ፊት የምንቆምባት የመጨረሻቱ የፍርድ ቀን በሁችንም ሕይወት የምትታወስ ቀን ናት ኃጥአንም ሆነ ጻድቃን የማትቀር በመሆኗ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ሀለወነ ኩነ ንቁም ቅድመ ምኩናኑ ለክርስቶስ ሁላችንም በክርስቶስ ፊት እንቆም ዘንድ አለንና›› እያለ ያችን ቀን ያስታውሳታል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ስዚች ቀን ሲናገር ከምፈራቸው ሦስት ቀኖች አንዷ ናት ብሏታል፤እንኳን በፈጣሪ ፊት መቆም በንጉሥ ፊት መቆም እንኳን ምንኛ ያስፈራል፡፡ ይህች ቀን ግን የመጨረሻውን ፍርድ መስማት በቅድመ እግዚአብሔር የምንቆምባት ሰዓት ስለሆነች የምታስፈራ እንላታለን፡፡
ታዲያ ሊቃውንቱ ያንጊዜ ማረን ራራልን ለማለት ዛሬ እንደነቢዩ ዳዊት ‹‹በጽባሕ እቀውም ቅድሜከ ወአስተርኢ ለከ፤ በማለዳ በፊትህ ቆሜ እታይልሀለሁ›› መዝ 63  እያሉ በቁም ጸናጽል ፈጣሪያቸው ፊት ቆመው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ ምንጊዜም ቢሆን ማኅታውያኑ በእጃቸው በጨበጡት ጸናጽል ቁም ዜማውን እየጸነጸሉ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ሀወነ ኩልነ ንቁም ቅድመ ምኩናኑ ለክርስቶስ›› እያሉ ማሰብ ይገባቸዋል

6.2 ክርስቶስ በዐውደ ፍትሕ መቆሙን ለማስታዎስ፡-

ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነት የተሸሙ ሹማምንት ሁሉ ፍርድ እንዲሰጡ ተጠይቀው በአንድ ወንጀለኛ ላይ ተስማምተው የፈረዱበት ጊዜ በታሪክ ከዚህ ቀን በስተቀር ይገኛል ብየ አላስብም፤
ከነም እንኳን በቅዱስ ጳውሎስ ላይ እንደተደረገው በወንጀለኛው ላይ ይግባኝ ተጠይቆበት የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ የዛሬው ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው፤ የሹመት ዘመኑን የጨረሰው ሀና በዚያው ዘመን ባለሥልጣን የነበረው ቀያፋ ሌሊቱን ሙሉ ሲያዩት ካደሩ በኋላ ሲነጋ ደግሞ ወደ ቤተ መንግሥት ሹማምት ነገሩ ተመልሶ ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ እየተመላለሰ የክስ ሂደቱ ሲታይ አረፈደ፤ በእርግጥ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰበው ክርስቶስ የሚሞትባት ቀትረ ዐርብ እስክትደርስ እንጅ ፍርዱ እንደማይቀየር በእርሱ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ዝም ብሎ ፍርዱን ተቀበለ፡፡
      ፍርዱን ከሰውልጆች ያስወግድ ዘንድ በፍርድ ዐደባባይ ቆሞ ፍርድ ተቀበለ፤ ‹‹አዳም ሆይ ቀድሞ መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ትመለሳለህ……..›› በፈራጁ ላይ ካልፈረዱበት ፍርዱ ከሰው ልጆች እንዴት ሊወገድ ይችላል፡፡ ኢሳ 53÷6 በነገር ሁሉ የተፈረረደበትንአዳምን መስሎ በመምጣቱ ሰራዊተ መላእክት በፊቱ ቆመው ማገልገል የማይቻላችው የሰራዊት ጌታ በዳኞች ፊት ቆሞ የሞት ፍርዱን ሰማ፡፡