>

Wednesday, 18 November 2015

ሦስቱ ስደታት

   ክፍል ሁለት
ባለፈው ክፍል እንደተመለከትነው በኃጢአቱ ምክንያት ርስቱን ተነጥቆ ስፍራውን ለቆ የመጣው የሰው ልጅ በዚህም ዓለም በልዩ ልዩ መንገድ ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወር ይኖራል፡፡ ከሀገሩ ወጥቶ ከሄደ ደግሞ በልዩ ልዩ ፀዋትዎ መከራ መፈተኑ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ስደትን ከባድ እሚያደርገው ልጅ ይዞ የሚያደርጉት ስደት ነው ልጅ ይዞ አስከትሎ የሚያደርጓት ስደት የመከራዎች ሁሉ እናት ናት፡፡ በእመቤታችን ም የሆነው ይህ ነውና በመከራ የሚተካከላት ማንም የለም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ‹‹ሐዊረ ፍኖት በእግሩ ሶበ ይስዕን ሕጻንኪ ያንቀዐዱ ኀቤኪ ወይበኪ በእግሩ መሐድን በደከመ ጊዜ ወደ አንች ቀናብሎ ያለቅሳል›› እንዳለ በነገር ሁሉ ሕጻናትን መስሏልና ሕጻናት እናቶቻቸውን የሚጠይቁትን ሁሉ ጠይቋታል፡፡ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ተብላ ነበርና በብርቱ ፈተና ውስጥ አለፈች፡፡
ሔሮድስ ግን እሷን አሰድዶ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ክብሩ ከፍ ከፍ አለ፤ የሊባኖስ ዝግባ የትኛውንስ ያክል ቢገዝፍ በቅርንጫፉ ዓለምን ቢከድን የሰማይ አዕዋፍ ቢንጠላጠሉበት፣ የምድርም እንስሳት ቢጠለሉበት ምን ቁም ነገር አለው፤ አንዲት ክብሪት እንዳልነበረ ታደርገው የለ! ይገርማል እኮ! ያ ግዙፍ ዛፍ በትንሽ ክብሪት በትንሽ ምሳር የሚጠቃ ይመስላችኋል? አንዲት ክብሪት ብዙ ደን ታጠፋለች፤ የሔሮድስም ግነት እግዚአብሔር ቁጣውን እስኪገልጥ ብቻ ነው፡፡
      እግዚአብሔር ሦስት ዓመት ከመንፈቅ የንስሐ ጊዜ ቢሰጠው አልመለስ ያለ ሔሮድስን ከስሩ ነቅሎ እንዳልነበረ አድርጎ በሞት ቀጣው፤ ያንጊዜ ‹‹ኃጥዕ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ገኖ አየሁት ስመለስ ግን አጣሁት ቦታውን ፈለግሁ አላገኘሁትም›› መዝ 36÷35-36 ብሎ ነቢዩ ዳዊት የተናገረው ደረሰ፡፡ ቀናት ሲቆጠሩ ለካ ኃጢአቱም በእግዚአብሔር ፊት እየተቆጠረበት ነበርና የዘመኑ ሳይሆን የክፋቱ ቁጥር ሲሞላ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ተፈረደበት፤ ዘመን ባይሞላም ክፋት ሲሞላ ያለ ጊዜም ሊያስነሣ ይችላል ክፉ ሰው እስከ ዕድሜው ፍጻሜ የሚኖር አይደለም፤ እንዲያው ኃጢአቱ ሲሞላ እግዚአብሔር ከተወሰነለት ዕድሜ በታች ሊያነሣው ይችላል እንጅ፡፡
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተመዘገበችው በለስ እንደ ሔሮድስ ያሉ ሰዎችን ትመስላለች፤ የእርሻው ባለቤት ለሦስተኛ ጊዜ መጥቶ አንዳች ፍሬ ያላገኘባት በዚህም ምክንያት ‹‹እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቆርጠህ ጣላት›› የተባለላት፡፡ ሉቃ 13÷6 ሔሮድስንም ጠበቀው እና በጎ ፍሬ ማፍራት አልችል ሲል አጫጆችን ልኮ አጨደው፡፡
እድሜ ሰጥቶኝ ኃጢአትን በጠገብኋት የሚል እንጅ እድሜ ሰጥቶኝ ንስሐ በገባሁ የሚል አይደለምና እንደ ናቡከደነፆር በብረትና በነሐስ ማሰሪያ የታሰረ ጉቶ በምድር ላይ ሊተውለት አልፈለገም፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው የተመዘገበላቸው አራት ነገሥታት ሁልጊዜ ያሳዝኑኛል፤ መንግሥታቸውን ለማስፋት ፀሐይ ወጥታ እስከምትገባበት ድረስ ዙፋናቸውን ለመዘርጋት ያላደረጉት አንዳች ነገር የለም፡፡ ናቡከደነፆር፣ጺሩጻይዳል፣ ሰናክሬምና ሔሮድስ ናቸው፡፡ አራቱም የተሰጣቸውን ዘመን ኃጢአትን አልጠግብ ብለው ሲያሳድዱ የጨረሱት ዘመን ነው ያላቸው፡፡ ከነዚህ የንስሐ እድሜ የተሰጠው ናቡከደነፆር ብቻ ነው፤ ከሰባት ዓመት የምድረ በዳ ቅጣት በኋላ ‹‹ናሁ አእመርኩ ከመ ልዑል ይኴንን መንግሥተ አሕዛብ›› መንግሥቱኒ መንግሥት ዘለዓለም ወምኩናኑኒ ለትውልደ ትውልድ፤እነሆ ልዑል አምላክ የአሕዛብን መንግሥት እንዲገዛ ለወደደውም እንዲሰጥ አሁን አወቅሁ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ዘመን ነው›› ዳን 4÷34 ብሎ ወደ ሰማይ ዐይኑን አንስቶ በቃል ሰብአዊ መናገር ባይችል በልቡ ንስሐ ሲገባ እግዚአብሔር መንግሥቱንና ግርማውን መልሶለት እንዲያውም ለወርቅ ምስል ካልሰገዳችሁ ብሎ ወደ ዕቶነ እሳት ከጨመራቸው ከሠለስቱ ደቂቅ ለዘለዓለም እንዳይለዩት ‹‹ይኩን መቃብርየ ምስለ መቃብረ ሲድራቅ ሚሳቅ ወአብደናጎ፤ መቃብሬ ከሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ጋር ይሁን›› ብሎ ተናዘዘ፡፡ ሌሎቹ ግን መንግሥታቸውን ለማስፋት ሲሮጡ ወደ ተከፈተ ቤተ መንግሥት ሳይሆን ወደ ተከፈተ መቃብር ገቡ፡፡
      ኃይልን በድካም የሚለውጥ እግዚአብሔር ናቡከደነፆርን በእነ ዳንኤል፣ ጺሩጻይዳልን በመቃብያን፣ ሰናክሬምን በሕዝቅያስ ጸሎት ድል እንድነሳ እመቤታችንም በሰይፋቸው የሚመኩ፣ በሰራዊታቸው ብዛት ዓለምን የሚያንበረክኩ እነ ሔሮድስን በመከራዋ ድል አድርጋ ኢየሩሳሌምን ወርሳ ልትኖር ቀኑ ደረሰ፡፡
      ነገሩ እንዲህ ነው የመከራው ወራት በተፈፀመ ጊዜ አስቀድሞ ወደ ግብጽ እንድትሄድ የነገራት የእግዚአብሔር መላክ ተገልጦ ‹‹የሕጻኑን ነፍስ የሚሻት ሞተዋልና ወደ ምድረ እስራኤል ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ተመለስ›› ማቴ 2÷20 አላቸው፤ ይህን የምሥራች በሰሙበት ወቅት ደብረ ቁስቋም ከምትባል ተራራ ላይ ወጥተው ተቀመጡ፡፡ ደብረ ቁስቋም በግብጽ ከሚገኙት ታላላቅ ተራሮች አንዷ ናት፡፡ እመቤታችን የምሥራቹን በሰማችበት ዕለት ወጥታ ያረፈችበት ቦታ ስለሆነ መካነ ዕረፍት እንለዋለን፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ኃዘን እንጅ ደስታ ሰምታ አታውቅም፤ ለቅሶ እንጅ ሳቅ አጋጥሟት አያውቅም፡፡ ዛሬ ግን እግዚአብሔር መከራዋን በደስታ፣ ኃዘኗን በሳቅ ለወጠላት፡፡
      በብርቱ ውጣ ውረድ የደከመ ጉልበቷን ያሳረፈችበት ቦታ በመሆኑ በሀገራችን ተራራው ለእመቤታችን እንደ መጠሪያ ስም ሆኖ ሲያገለግል እንመለከተዋለን፡፡ አዳሪ በማደሪያው ሊጠራ ይችላልና ነው እንጅ ቁስቋም ለእመቤታችን መጠሪያ ሊሆን አይችልም፤ በስሟ የሚማጸንም ሰው ቢኖር የቁስቋሟ እመቤት ስሚኝ ሊል ይገባዋል እንጅ ቁስቋም ስሚኝ ብሎ ሊማጸን፣ ስለ ቁስቋም ብሎ ምጽዋት ሊሰጥ አይችልም፡፡
ለምን ተመለሰች?
  1. የነቢያት ትንቢታቸው እንዲፈጸም፡-
ነቢያት የመሰደዷን ነገር ‹‹ወናሁ ይወርድ እግዚአነ ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል፤እነሆ ጌታ በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብጽ ምድር ይወርዳል›› ኢሳ 19÷1 ብለው ተናግረዋል፤ ስደቷ እንደ አብርሃም ያለ ስደት አልነበረምና የመመለሷንም ነገር መላልሰው ብዙ ነቢያት ተናግረውታል፤ ‹‹ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ፤ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ›› መኃ 7÷1 ስሙ በመጻሕፍተ ነቢያት ያልታወቀ አንድ ነቢይም ‹‹እምግብጽ ጸዋዕክዎ ለወልድየ፤ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት›› ማቴ 2÷23 ብሎ ከግብጽ የመመለሱን ነገር ተናግሯል፡፡ ንጉሡ ሰሎሞን ‹‹ሰላምን እናይብሽ ዘንድ ተመለሺ›› ብሎ እንደ ተናገረው ዓለም ሰላም እንዲያይ እርሷ ልትመለስ ይገባታል፡፡ ርግቧ ሰላሙን ይዛው ካልተመለሰች በሞት ጥላ ሥር ላሉ ሕዝቦች ምን ሰላም ሊኖራቸው፤
      አባቶቿ ነቢያት በመቃብር ውስጥ በተስፋ የመመለሷን ነገር እየተጠባበቁ ‹‹እናይሽ ዘንድ ተመለሽ›› እያሏት እንዴት ልትቀር ትችላለች፡፡ ደጅ ወደ ሚጠኗት አባቶቿ ከተማ ተመለሰች፡፡ በዚያውም ላይ ይዛው ካልተመለሰች ‹‹ከመ ናዝራዊ ይሰመይ ወልድየ፤ ልጄ ናዝራዊ ይባል ዘንድ›› የተባለው ትንቢት እንዴት ሊፈጸም ይችላል፡፡
  1. አይሁድን ምክንያት ለማሳጣት፡-
 አይሁድ የክርስቶስን ሰው መሆን ከሌላው ዓለም ተለይተው ደጅ ሲጠኑ የኖሩ የነቢያት ልጆች ናቸው፡፡ የዛሬዎቹ ልጆቻቸው ግን ከነዚያ ቅዱሳን አባቶቻቸው የተለዩ የክፋት ልጆች ሆነዋል፤ ለዚህም የምድረ በዳው ሰባኪ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኦ ትውልደ አራዊተ ምድር፤ እናንተ የእፉኝት እባብ ልጆች…..››እያለ በሥጋ ቢወልዳቸውም በክፉ ግብራቸው የአብርሃም ልጆች መባል እንደማይገባቸው ‹‹ሶበሰ ውሉደ አብርሃም አንትሙ ግብረ አብርሃም እምገበርክሙ፤ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ›› እያለ ይዘልፋቸው የነበረ፡፡ ማቴ 3÷7 ሱባኤውን ከሚቆጥሩበት መንገድ አንዱ ትውልደ አበው ስለነበረ ከአዳም አራተኛ የሆነውን ዓመተ ቃይናንን ፍቀው ከኦሪታቸው ፍቀው ለሕዝቡ መሢሑ የሚመጣበት ዘመን አልደረሰም እያሉ ደርሶ ሳለ እንዳልደረሰ ተወልዶ ሳለ እንዳልተወለደ አድርገው ያስተምሩ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሪታቸው ኦሪተ አይሁድ ብጡል ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህን ክፋታቸውን ሊገልጥ ሁለት ምስክሮችን አቁሞባቸዋል፤ ኦሪተ ሣምራውያንን እና የሰባ ሊቃናትን ትርጉም ኦሪት ነው፤
እነዚህ ኦሪቶች ከአይሁድ ኦሪት የተለዩ ናቸው ምክንያቱም አይሁድ ኦሪቱን ሳይቆነጽሉት አስቀድመው ለምስክርነት በባዕድ ምድር ተዘጋጅተው የተቀመጡ ስለነበሩ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋራ በመካከላቸው ባያድግ ኖሮ እንዴት አይተነው እንመንበት ባሉና ምክንያት መፍጠር በቻሉ ነበርና ለበደላቸው ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡ እሱ ራሱ ሲናገር ‹‹ሶበሰ ኢመጻእኩ አነ ወኢነገርክዎሙ እምኢኮኖሙ ጌጋየ ወይእዜሰ አልቦሙ ምክንያት ለጌጋዮሙ፤ እኔ ወደ እነሳቸው ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ እዳ በደል ባልሆነባቸውም ነበር አሁን ግን ለበደላቸው ምክንያት የላቸውም››  ዮሐ 15÷22፡፡
 ቤተ አይሁድ የሠራችውን ሸማ ትጎናጸፈው ዘንድ የጠመቀችውን ወይን ትጠጣው ዘንድ በማካከሏ እየተመላለሰ በሚያደርገው ተዓምራት በሚያስተምረው ትምህርት ከከንቱ ምክንያት ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንድትመለስ አስጠነቀቃት እሷ ግን አፈ ወርቅ ቅዱስ የሐንስ ‹‹ምኩራብ አነመት ፀምረ ወቤተ ክርስቲያን ተአጽፈቶ እንታክቲ አፀረት አስካለ ወይን ወአህዛብ ሰትዩ ስቴ ምሥጢር፤ ምኩራብ ፀምረ ትንቢትን አዘጋጀች ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው ቤተ አይሁድ የወይን ጠጅን ጠመቀች ቤተ አሕዛብ ምሥጢሩን ጠጣችው›› ብሎ እንደተናገረው ላትጠጣው ጠምቃ ላትለብሰው ፈትላ ለአሕዛብ አበረከተች ሆኖም አላየሁም እንዳትል በመካከሏ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ተመላለሰ እሷ በከንቱ ጠላችው ‹‹ጸልዑኒ በከንቱ፤ በከንቱ ጠሉኝ›› ዮሐ 15÷25፡፡ የተባለውም ተፈጸመ፡፡
  1. ›መንገዱን ከአጋንንት ለመሠወር፡-
 ይመጣል ተብሎ የተነገረለትን መሢህ የሚጠባበቁ ሁሉ የሚጠብቁት ከገሊላና ከናዝሬት አልነበረም፤ ከዳዊት ወገን ከቤተ ልሔም ነበር እንጅ፡፡ ለዚህ ነው ለሐዋርያነት ከተመረጡት አንዱ ‹‹ቦኑ ይትከሐል እምናዝሬት ከመ ይጻዕ ብእሲ ሔር፤ በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይችላልን›› ዮሐ 1÷47፡፡ ብሎ መጠየቁ፡፡ ምናምንቴ ሰዎች ይኖሩባቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩት እነዚህ መንደሮች አምላክን ለመውለድ የተመረጠችው እመቤታችንን ያስገኛሉ ተብሎ እንዴት ይታሰባሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሰው የሆነው በኃጥአን መካከል ተገኝቶ የኃጥአን ቤዛ ሊሆን ነውና ደዌ ኃጢአት በጸናባቸው መንደሮች መካከል ሊያድግ ከስደት ሲመለሱ ወደ ገሊላ ገቡ፡፡
      በእርግጥ ዮሴፍም ሆነ እመቤታችን የዳዊት ዘር እንደ መሆናቸው መጠን ርስታቸው ያለው በዳዊት ሐገር በቤተ ልሔም ነው ለዚህም ነው ከአውግስጦስ ቄሳር በወጣው የቆጠራ ትእዛዝ መሠረት ሊቆጠሩ ወደ ቤተ ልሔም የሔዱት ርስታቸው ያለው በቤተ ልሔም ስለሆነ ነው፤ ሰው ሁሉ የሚቆጠረው በየርስቱ ነበርና፡፡ ታዲያ ይህ በሰዎች ዘንድ ምሥጢር ሆኖባቸው ‹‹ህሡ ውስተ መጻሕፍት ከመ እምገሊላ ኢይትነሣዕ ነቢይ፤ ከገሊላ ነቢይ እንደ ማይነሣ መጻሕፍትን መርምሩ›› ዮሐ 7÷52 እያሉ ይከራከሩ ነበር፡፡ ከክፉዎች ሰዎችና ከአጋንንት ራሱን ሰውሮ ከምናምንቴ ሰዎች እንዳንዱ ሆኖ በኃጢአቱ ምክንያት ምናምንቴ ሆኖ ወደ ምድረ ፋይድ የተጣለ አባቱ አዳምን ነጻ አወጣው፡፡
      አባቱ አዳም በፍርድ የወደቀባት ገሐነም ከሁሉም የተናቀች የክፉዎች መናፍስት ማኅደር ናት ጌታችንም የመጣው በመዋረዱ ውርደታችንን ሊያስወግድ ነውና ሁሉም በናቋት በገሊላ ሊኖር ወዶ ከግብጽ ሲመለስ ወደ ገሊላ ገባ ተብሎ ተጻፈለት፡፡
  1. ጉዞዋ ከጥንት በምሳሌ የተገለጠ መሆኑን ለመግለጥ፡-
የቀደመው ፍኖተ አበው በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ለሚጀመረው የሕይወት መንገድ ጥላ ነው፤ እስራኤል ወደ ግብጽ መውረዳቸው ወለተ እስራኤል እመቤታችን ተሰዳ ግብጽ ለመውረዷ ምሳሌ ነበር፤ እስራኤል ቀኑ እስኪደርስ በዚያው የቆዩ ቢሆንም ቀኑ ሲደርስ ግን የሞቱትን ሳይቀር ለግብጽ ሊተውላት አልፈለጉም መቃብራቸውን እየፈነቀሉ ይዘዋቸው ተመልሰዋል እንጅ፡፤ እመቤታችንም የእግዚአብሔር መላክ ‹‹ወሐሉ ሕየ እስከ አመ እነግረከ፤ እኔ እስክነግርህ ድረስ በዚያ ተቀመጥ›› ማቴ 2÷13 ብሎ የተናገረው መላክ ቀኑን እስኪያስረዳት በዚያው ነበረች፡፡
      እስራኤል ሲወርዱ በረሀብ ምክንያት እያዘኑ ወረዱ እንዲያውም ያዕቆብ በወቅቱ የተናገረው የምሬት ቃል ‹‹መዋዕልየሰ ምዕት ወሠላሳ ወባሕቱ እኩያተ ኮናኒ፤ ዘመኔስ መቶ ሠላሳ ነው ነገር ግን ክፉ ሆኑብኝ›› ዘፍ 47÷9 የሚል ነበር በከነዓን የደረሰባቸው ረኀብ ጽኑዕ ነበርና አስጨናቂ ቃልን ይናገራል፡፡ ሲመለሱ ግን መና እየዘነመላቸው ጠላት ጠፍቶላቸው ጠኣምራት እየተደረገላቸው በደስታ ነው የተመለሱት፡፡ እመቤታችንም ወደ ግብጽ ስትወርድ በለቅሶ በኃዘን በጽኑዕ ረሀብና ጥም ነበር፤ ስትመለስ ግን የሔሮድስን ሞት ሰምታ ወደ አባቶቿ ቤት ደስ እያላት ነው የተመለሰች፡፡ አባቷ ዳዊት ዖፍኒ ረከበት ላቲ ቤተ ወማዕነቅኒ ኀበ ታነብር እጎሊሐ፤ ወፊቱ ቤትን ለራሷ አገኘች ዋኖስም ገላግልቶቿን የምታኖርበት››መዝ 83÷3 ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጽሞላት ደስ እያላት ተመለሰች፡፡ ልጇ ክርስቶስ አባቶቹ የደረሰባቸውን ጭንቅ ሁሉንም በሔዱበት ሒዶ በገቡበት ገብቶ በመከራቸው ሁሉ ተፍትኖ አባቶቹን ከሞት ጻዕረኝነት ያድን ዘንድ መጥቷልና በስደት እነሱን እንደ መሰለ በእናቱ ጀርባ ሆኖ ባደረገው ወደ ገሊላ መልስ እስራኤልን መሰለ፡፡
  1. በመመለሷ መመለሳችንን ሊያስረዳን ነው፡-
የምንኖርባት ምድር የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ናት እንጅ የሰው ልጅ መኖሪያ ሰገነት አይደለችም፤ መጽሐፍ እንደ ተናገረው ሀገራችን በሰማይ ነውና፡፡ ዛሬ በዚህ የምንኖር ሁላችንም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተዘጋጅታ የምትወርደውን አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን በተስፋ ‹‹ትምጻዕ መንግሥትከ›. እያልን እንጠባበቃለን ምክንያቱም ፊተኛው ሰማይና ምድር ሊያልፍ ተወስኖበታልና ራእ 21÷1-3 ታዲያ ይህን ስደታችን ለመግለጥ የወገኖቹን ስደት ሊካፈል ከስደተኛው ከአብርሃም ቤት ተወልዶ ሰይጣንን ከሰው ልብ እስኪያሰድደው ድረስ ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡
 በስደቱ ስደታችንን እንደሻረልን በመመለሱ ደግሞ መመለሳችንን ሊያስረዳን ስደቱን በሌሊት መጥቶ ለዮሴፍ የነገረው መላክ አሁንም ‹‹ተንሥእ ወንሳዕ ሕጻነ ወእሞ ወሑር ውስተ ምድረ እስራኤል፤ ተነሥ ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ሂድ›› እንዲነግረው አደረገ፡፡ ይህ ለጊዜው ወደ ገነት ፍጻሜው ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት የመመለሳችንን ምሥጢር የያዘ ነበር፡፡  ምክንያቱም ደብረ ቁስቋም የደብረ ጽዮን ራእ 14÷1 ምሳሌ ስትሆን እመቤታችን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናትና፡፡ እመቤታችን በሌሊት ወጥታ እንደተሰደደች ጌታም የሚመጣውና ለቤተ ክርስቲያን  በደብረ ጽዮን የቆመው በግ መስሎ የሚታያት በሌሊት ነው፡፡ ሌሊት የመከራ ምልክት ነው ቤተ ክርስቲያንም ከሐሳዊ መሢህ በሚመጣ ጽኑዕ መከራ ውስጥ ሳለች ነው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ከወኅኒ የሚያወጣ መላክ አይልክላትም በጠቅላላው ከሥጋ እስራት የሚላግላት ጌታ መጥቶ መከራ ወደ ሌለበት ዐለም እንድትዛወር ያደርጋታል እንጅ፡፡

 እመቤታችን ከአርባ ሁለት ወራት ስደት በኋላ የመጀመሪያውን የዕረፍት ቀን በዚያ እንዳከበረች ቤተ ክርስቲያንም ከአርባ ሁለት የመከራ ወራት በኋላ  የጠላቷን የዲያብሎስን መሞት ሰምታ  የመጀመሪያውን ዕረፍት የምታከብረው በደብረ ጽዮን ነው፡፡  እመቤታችን ወደ አባቶቿ ከተማ ለመመለስ ጉዞዋን የጀመረችው በደብረ ቁስቋም እንደሆነ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም የአባቶቿን የቃል ኪዳን ምድር መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ጉዞዋን የምትጀምረው በደብረ ጽዮን ነው ራእ 14÷1 በነገራችን ላይ ይህን ስል የእመቤታችን ስደት የቤተ ክርስቲያንን በሀሳዊ መሢህ የሚደርስባትን መሰደድ የሚያመለክት ስለሆነ ነው፡፡ የግብጹ መከራ ደብረ ቁስቋም ላይ ያበቃል፤የቤተ ክርስቲያንም ድካም ደብረ ጽዮን ላይ ይፈጸማል፡፡

1 comment:

Anonymous said...

ቃለ ህይወት ያሰማልን