>

Saturday, 17 January 2015

በእንተ ጥምቀቱ




                 እንኳን ለብርሃነ ልደቱ ወጥምቀቱ አደረሳችሁ

በእለተ ልደቱ በመላእክት ምስክርነት የታየው ጌታ በእለተ ጥምቀት ደግሞ በሰማዩ አባቱ ምስክርነት፣ በባሕርይ ሕይወቱ መንፈስቅዱስ ገላጭነት ሰማያዊ ልደቱን አስረዳ፤ እንደ ሰውነቱ ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በሔኖን ወንዝ ዳርቻ አንድ ሌሊት ቆሞ ከሕዝቡ መካከል ከዮሐንስ በቀር የሚያውቀው ሳይኖር አደረ፤ ይገርማል! ከብዙ ሺህ ዓመት በፊት ቃኤል ወንድሙን አቤልን የገደለበት ታላቁ ኃጢአት የተፈጸመበት ስፍራ ነበር ዛሬ ደግሞ ‹‹ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኩሎ ጽድቀ፤ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ማቴ 3÷15 ተብሎ ታላቁ ጽድቅ ተፈጸመበት፡፡ አመጣጡ ጥልን ለመግደል፤ የአባቶቹን ደም ለመመለስ ነውና ነፍሰ ገዳዩ ሰይጣን ደማችንን ማፍሰስ በጀመረበት ስፍራ ላይ ቆሞ ጽድቅን ሊፈጽም እንደ መጣ በግልጥ ተናገረ፡፡  
እንደ አምላክነቱ ዮርዳኖስ ሸሸችለት ከሰው ልጆች ኃጢአትን የሚያስወግደው በጥምቀት ነውና ያ እስኪሆን ድረስ ዮርዳኖስ ለጊዜው ወደ ኋላዋ ገባች፤ የሚወርደው ውሃ እንደ ድንጋይ ክምር ሆኖ ከላይ ተከመረ ከታች ያለውም ውሃ ወርዶ ሲያልቅ፣ ከላይ ያለውም ሲቆም አጥማቂው ዮሐንስና የሚጠመቀው ጌታ ወደ ባሕሩ ገባ እንዲህ በማድረጉ ካለፈውም ከሚመጣውም ትውልድ ኃጢአትን እንዳስወገደለት አስረዳን፡፡ ዮርዳኖስ በእሳት ቅጥር ተቀጠረች፤ እሳቱ የመንፈስ ቅዱስ
ምሳሌ ሲሆን ልጅነትን የሚያስገኘው ውሃ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሞላ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋራ አብ በደመና ሆኖ ሲናገር፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሲወርድ ለዘመናት ስውር ሆኖ የኖረው ሥላሴ በዚህ ጊዜ ግልጥ ሆኖ ተረዳ፡፡ ሃይማኖታችን በዮርዳኖስ ተገለጠ፤ ሰማይ ሲከፈት ታየ፤ ምድራዊው ሰው ሰማያዊ ሲሆን ሰማይም በምድር ላይ አንዳች ነገር ሳትደብቅ የሰወረችውን ምሥጢር አስረዳች፡፡
ባርነት እንኳን አይገባው የነበረ የሰው ባሕርይ ዛሬኮ ‹‹የምወደው ልጄ……….››ተብሎ ከሰማይ ድምፅ መጣለት በምድር የሚኖር ፍጥረት ሁሉ በትዕዛዙ እንዲኖር ‹‹እርሱን ስሙት›› ተብሎ ለመሬታውያኑ ፍጥረታት በሙሉ ትዛዝ ተሰጠለት፤ ‹‹አዳም ገብሩ ..ሔዋን አመቱ›› የሚለው ደብዳቤአችን መቀደዱን ለማብሰር እኮ ነው፡፡ ጥንት በአባቶቻችን ዘመን ‹‹እግዚአብሔርም ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ አዘነ›› ዘፍ 6÷6 የተባለው ቀርቶ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ………›› ተብሎ ተነገረለት በእውነት ሳይገባን ታላቁ የእግዚአብሔር ምህረት የተገለጠበት ቀን ነውና የመገለጥ ቀን እንለዋለን፡፡
            ያኔ በዚያ መገለጥ ባልነበረበት ዘመን የነበሩ የእግዚአብሔር ነቢያት አንድ ነገር እንዲህ ሲሉ ጠየቁ ‹‹አባቴ ሆይ እንጨቱና እሳቱ ይኸው፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው?››  አባት ከልጁ እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲመጣበት ጥያቄውን በጥያቄ እንዲህ ሲል ይመልስለታል ‹‹ልጄ ሆይ! የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ዘፍ 22÷7-8 አለው ይላል፤ ከዚህ በላይ ሌላ ምን ብሎ ሊመልስለት ይችላል፤ ይሄኮ ዘመኑ ሲደርስ የሚመለስ ጥያቄ እንጅ በዚያ ዘመን የሚኖር ሰው የሚመልሰው ጥያቄ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በዘመናቸው የነበራቸው እንጨቱና እሳቱ እንጅ የመሥዋዕቱ በግ ግን አልነበራቸውምና ነው፡፡ መሥዋዕት ሊሠዋ የሚሄድ አባት ሲሆን መሥዋዕቱን ግን ገና እግዚአብሔር ያዘጋጃል ብሎ የሚያስብ ነበር፤ ምን ያድርግ! ዘመኑ የመገለጥ ዘመን አልነበረምና የመሥዋዕቱን በግ ጠቁሞ ማሳየት ሳይችል ቀረ፡፡ ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ ዛሬ በዮርዳኖስ ፈጣሪውን ሊያጠምቅ የተገባው ቅዱስ ነቢይ ዮሐንስ ሲያጠምቀው ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየዐትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያሥተሰርይ የእግዚአብሔር በግ›› እያለ በማጥመቁ መገለጥ ባልነበረበት ዘመን የተነሣውን ጥያቄ ሲመልሰው እናያለን፡፡ ዘመኑ የመገለጥ ነውና የመሥዋዕቱን በግ ጠቁሞ ማሳየት ችሏል፡፡
            ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰውን እንዴት እንዳከበረ የተረዳንበት ቀንም ነው፤ ከዮሐንስ ዘንድ ቀራጮችና ክፉ ጭፍሮች እየመጡ ይጠመቁ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል ሉቃ 3÷10-14 እኒህ ሁሉ ተጠምቀው ሲጨርሱ ነው ጌታችን ወደ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቀኝ ያለው፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረው ቀዳማዊ ቃል ደኀራዊ ሥጋን እንደተዋሀደ ለማጠየቅ ከሁሉ በኋላ ወደ ውሃው መጣ፤ ከሁሉ በኋላ ቢመጣም ከሁሉ አስቀድሞ ወደ ዮርዳኖስ የገባ ግን ከእርሱ በስተቀር ሌላ ማንም የለም፡፡ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ መንገዱ በዮርዳኖስ በኩል እኮ ነው፤ ኢያሱ ሕዝቡን የመራቸው የዮርዳኖስን ውሃ አቋርጠው በሚያልፉበት መንገድ በኩል ነበር፤ ሀገሪቱ ያለችው ከዮርዳኖስ ማዶ ነውና ፤ ኢያ 3÷1
            የድንግል ማርያም ልጅ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስም ህዝቡን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊመራ የመጣ የተስፋይቱ ምድር የመንግሥተ ሰማያት አዲስ ኢያሱ ነውና ሕዝቡን ወደ ጽድቅ ሊመራ የዮርዳኖስን መንገድ ይዞ ተጓዘ ‹‹ኅድግ ምዕረሰ እስመ ይደልወነ ከመ ንፈጽም ኩሎ ጽድቀ፤ አንድ ጊዜስ ተው ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› ማቴ 3÷15 ባለው ቅዱስ ቃሉ ይታወቃል፡፡ የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ ኢያሱም የመረጠው ዮርዳኖስን እንጅ ሔኖንን አልነበረም ስለዚህም መድኃኒታችን ክርስቶስ በነገር ሁሉ አባቶቹን ሊመስል ይገባዋልና ደጋጎቹ አባቶቹ የተጓዙበትን ተከትሎ ሄደ፡፡
            በሌላም ስፍራ የተመዘገበው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስረዳን ኤልያስ ወደ ሰማይ የተነጠቀው ዮርዳኖስን ተሸግሮ ሲሄድ ነው፡፡ የእሳት ሰረገሎችና ፈረሶች በእርሱና በደቀ መዝሙሩ በኤልሳዕ መካከል ገብተው የከፈሏቸው ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የተነጠቀው በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ላይ ነበር ‹‹እነዚህም ሁለቱ (ኤልያስና ኤልሳዕ) በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ቆመው ነበር ኤልያስም መጎናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው ውሃውንም መታ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ ከተሻገሩም በኋላ ……….እነሆ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሏቸው ኤልያስም  በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ›› 2ነገ 2÷7-14 እንዲል፡፡ ዮርዳኖስን ሳይሻገሩ በእሳት ሰረገላና በእሳት ፈረስ ላይ መቀመጥ እንዴት ይቻላል በዐውሎ ነፋስ መነጠቅስ ለማን ይሆናል፤ ሁሉም ዮርዳኖስን ለተሸገረች ነፍስ የተሰጡ ጸጋዎች ናቸው፡፡ ኤልሳዕ የአባቱን በረከት የወረሰው፣ እንደ አባቱ ሆኖ በእስራኤል ላይ ሊፈርድ የተመለሰው ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲመለስ ነው፤ የነቢያት ልጆች ሁሉ በፊቱ ትይዩ ቆመው ‹‹የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ አድሯል ›› እስኪሉ ድረስ ተገልጦ የሚታይ የአባቱ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ነበረ፣
እኛም የአባታችን የእግዚአብሔርን መልክ የምንመስለው፣ በረከቱን የምንወርሰው ዮርዳኖስን (ጥምቀትን) የተሻገርን እንደሆነ ነው፡፡ ከዚያ በኋላማ ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስን ተክቶ እንዳይሠራ የሚከለክለው ማነው? በሥራው ሁሉ ‹‹የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው›› እያለ ከመምህሩ የሚበልጥ እጥፍ ድርብ ተዓምራትን ማድረጉ አይቀርም፤ በጥምቀት ክርስቶስን የመሰሉ ሐዋርያትስ መምህራቸው ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከተነጠቀ በኋላ መምህራቸው ክርስቶስን መስለው ድንቃ ድንቅ ነገሮችን እንዳያደርጉ ማን ይከለክላቸዋል፤ እንዲያው እርሱ ባለቤቱ ክርስቶስ ቃል ሲገባላቸው ‹‹ኩሉ ዘየአምን ብየ ግብረ ዘአነ እገብር ውዕቱኒ ይገብር ወዘ የዐቢ እምኔሁ ይገብር፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል ከዚያም የሚበልጥ ያደርጋል›› ዮሐ14÷12 ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፤ ይህ የዮርዳኖስ (የጥምቀት) በረከት ነው፡፡
ኤልያስም ደቀ መዝሙሩን ‹‹እኔ ካንተ በምወሰድበት ጊዜ ወደ ላይ ቀና ብለህ ብትመለከተኝ ይደረግልሀል አለዚያ ግን አይሆንልህም›› አለው 2ነገ 2÷10 የሐዲስ ኪዳኑ መምህራችን ክርስቶስም ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ አንጋጠው ይመለከቱት ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ከሰማይ ጸጋውን  ልኮላቸዋል ሥራ 1÷11፣ 2÷2 እስከ ዮርዳኖስ ተከትሎ ያለ በረከት የተመለሰ ማነው! እንዲያውም የክርስቶስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ያዘጋጀልን ሰማያዊቷን ከተማ መውረስ የሚቻለው ከዮርዳኖስ በኋላ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም ዕብ 11÷16
አስቀድሞ በትንቢት ብዙ ነቢያት ያነሣሱት የነበረው ታላቁ ውሃ ዮርዳኖስ እንዲህ ያለ የብዙ ቅዱሳን መመላለሻ የእግዚአብሔር ታቦትና ሕዝብ መሸጋገሪያ፣ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመድረሳቸው ማስታዎሻ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ክርስቶስ መምጣቱንና የነቢያተም ትንቢት መፈጸሙን ሊያስረዳ መጥምቁ ዮሐንስ ጌታውን ተከትሎ ሲመጣ ሲያየው ጌታዬ ወደኔ ይመጣ ዘንድ እኔ ምንድነኝ? እያለ ወደኋላው ሸሸ፤ ‹‹ባሕርኒ ርዕየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ ባሕር አየች ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላዋ ተመለሰች›› ተብሎ የተዘመረው መዝሙር ሰለዚህ ቀን እንደሆነ እኛም አወቅን መዝ 113÷3 ጭንጫውን ወደ ውሃ ምንጭነት፣ ዐለቱንም ወደ እርጥብነት የሚለውጠው የያዕቆብ አምላክ ፊት ሆና ዮርዳኖስ ወደ ኋላዋ ብትመለስ ውሃ ሽቅብ አይፈስም ብሎ ማን ይከሳታል፤ ‹‹አንች ባሕር የሸሸሽው አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽው ምን ሆነሻል? ብለን እንጠይቃት ዘንድ እንዴት እንችላለን፤ ይልቁንስ ታችኛው የሰው ልጅ ባሕርይ ወደ ላይ ወጥቶ፣ ከሥላሴ አንዱ ሆኖ የባሕርይ ምስጋና ሲቀርብለት፣ የባሕርይ ስግደት ሲሰገድለት ማየት አይከብድም፤
ታችኛው የሰው ልጅ ላይኛውን አምላክ፣ ላይኛውም አምላክ ታችኛውን የሰውን ልጅ ሆኗልና ያ ምሥጢር እንዲገለጥ ዮሐንስ በልዕልና ‹‹መጥምቀ መለኮት›› ተብሎ፣ ጌታችን ደግሞ በትህትና በባሪያው እጅ ተጠመቀ ተብሎ ሊነገርለት ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ አብረው ገቡ፡፡ ቀኑ ልዑሉ አምላክ ትሑት፣ ትሑቱ ዮሐንስ ልዑል የሆኑበት ቀን በመሆኑ ዮርዳኖስም በመደነቅ መንገዱን ለወጠ፤ ኋላ ለነፍሳችን ተድላ ደስታን የሚፈጥርላት ከሴቶች ማኅፀን መውጣቷ ሳይሆን ከዮርዳኖስ ማኅፀን፣ ከመንፈስ ቅዱስ አብራክ መውጣቷ ነውና ለዚያ የምሥራች እንደ ማለት ዮርዳኖስ ሽቅብ ዘለለች፡፡
ከዚህ ቀን ጀምሮ ዮርዳኖስ የተቀደሰች ማኅፀን ሆነች፤ እስካሁን ድረስ በነቢያቱ ቃል ደዌ ሥጋን ታርቅ ነበር እንደ ኢዮብ እንደ ንዕማን ላሉት አማኞች ፈውስን ትሰጥ ነበር 2ነገ5÷14 ዛሬ ግን ከአካላዊው ቃለ እግዚአብሔር ከክርስቶስ የተነሣ ቅድስት ሆና ለሁሉም ፍጥረት ደዌ ነፍስን ልታርቅ ተባረከች፡፡ የጥንቱን ፍቅሩን እንደ መለሰልን እንድናውቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ክንፉን ዘርግቶ ረቦ ታየ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ‹‹ወመንፈሰ እግዚአብሔር ይጼልል መልዕልተ ውዕቱ ማይ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃው ላይ ሰፎ ይኖር ነበር›› ዘፍ 1÷2 ሰውና እግዚአብሔር ከመጣላታቸው በፊት የነበረው እንዲህ ነበር ከዚያ በኋላ ግን ውሃ የጥፋት መሣሪያ ሆኖ ምድርን የሬሳ ማደሪያ አደረጋት ዘፍ 7÷17 እንደገና ዕርቅ እንደ ተፈጸመ ለማጠየቅ የእግዚአብሔር መንፈስ በዚህ እለት ረቦ ታየ ጥንት በውሃ ያጠፋውን ዓለም በውሃ መልሶ ሊያድነው ቅዱስ መንፈሱን በውሃ ዳር ገለጠው፤
ቅዱስ ጴጥሮስ በቀደሙት ሰዎች ላይ ስለወረደው የጥፋት ውሃ በተናገረበት አንቀጹ ‹‹ይህ ውሃ ደግሞ ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል›› 1ጴጥ 3÷21 ይላል፤ ሐዋርያው እንደ ተናገረው ምድርን ያጠራት ይህ ውሃ ለክፉዎች ለጥፋት የዘነመ ቢሆንም ቅሉ በክፉዎች ክፋት የተበላሸችውን ምድር ግን አጥርቷታል፡፡ ጥምቀትም የሥጋን ፈቃድ ገሎ የነፍስን ሕይወት የሚያለመልም የአጋንንትን ተስፋ የሚያጨልም ነው፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ዳዊት ‹‹አንተ ሰበርከ ርእሰ ከይሲ በውስተ ማይ ወአንተ ቀጥቀጥከ አርእስቲሁ ለከይሲ፤ የእባቡን ራስ በውሃ ውስጥ አንተ ሰበርህ ዳግመኛም የእባቡን ራስ አንተ ቀጠቀጥህ›› መዝ 73÷13 በውሃ በሚደረግ ጥምቀት የጠላትን ሀሳብ እንደሚሽር፣ የሰው ልጆችን የባርነት ቀንበር እንደሚሰብር አስረግጦ ይናገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን የዳዊትን መዝሙር በተረጎሙበት ድርሳናቸው ‹‹ወቅጥቃጤሁሰ ለርእሰ ከይሲ ከመ ኢይትነሣእ ዳግመ ………ነኀልዮ ከመ ዘሞተ ወኢንዝክሮ ከመ ዘሀሎ፤ የእባቡን ራስ ቀጠቀጥህ ተብሎ መጻፉ ዳግመኛ እንዳይነሣ ሆኖ በጥምቀት መሞቱን ለመናገር ሲሆን እኛም እንደ ሞተ እንጅ በሕይወት እንዳለ አናስበው›› በማለት ይተረጉማሉ፡፡
ሸክላ ሠሪ የሠራችው ሸክላ ቢሰነጠቅባት እንደገና ከስክሳ፣ በውሃ ለውሳ፣ በእሳት ተኩሳ ወደ ቀደመው ክብሩ ትመልሰዋለች እንጅ አውጥታ የምትጥለው አይደለችም እንደዚሁ እግዚአብሔር በእጁ የቀረፀው፣ በመዳፉ ያበጃጀው ሸክላ የሰው ዘር በኃጢአት ነቅቶ የማይጠቅም ሆኖ ቢያገኘው እንደገና እንዲፈርስ ፈረደበት ነገር ግን እንደፈረሰ እንዲቀር ፈቃዱ አይደለምና ዳግም በጥምቀት አረስርሶ፣ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ተኩሶ አዲስ አድርጎ ሠራው፡፡ አዲሱን ሰው እንደ ገና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ዳግም ሲወልደው የሚበላው ምግቡን (ሥጋው ደሙን) አዘጋጅቶ ነው የሚጠብቀው፡፡ እናት ለልጇ እንደ ተወለደ የሚጠባው ጡቷን እንድታቀርብለት በፊቱ እንደ ሕጻናት የሚያየን እግዚአብሔርም በዐይን የማይታይ ሰማያዊ ልብስን አልብሶ ሥጋውና ደሙን መግቦ ሰውን ያሳድጋል፡፡ እስከ ተፈቀደልን ድረስ እንዲህ አድርጎ የሚያኖረን ቢሆንም እንኳን ሞት የማይቀር በመሆኑ እንደገና በክብር አንሥቶ በወዲያኛው ዓለም መንፈሳዊ ምግብን ለዘለዓለም ሲመግበን ይኖራል፡፡   
በጥምቀት የተወለዳችሁ ዉድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ታላቅ የሆነውን ፍቅሩን እንዲህ አድርጎ ሲገልጥልን እኛም በመብልና በመጠጥ፣ ዋጋው ብዙ የሆነ ልብስ በመልበስ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳችን በመዋደድ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት በአል ሊሆን ይገባል፤ በእግዚአብሔር በረከት የተሞላ ዕድሜ እንዲኖራችሁ አጥብቃችሁ ወደ እርሱ ልትቀርቡ፣ ሃይማኖታችሁንም ልትጠብቁ ይገባል፤ እግዚአብሔር ለመንግሥቱ የተመረጣችሁ ሰዎች ያደርጋችሁ ዘንድ በዓለም ሳላችሁ እርሱ የሚወደውን ብቻ እየመረጣችሁ እንድትሠሩ እናታችሁ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላችኋለች፡፡
 ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን በሰማያውያንና በምድራውያን በረከት ይባርክ!
በድጋሜ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ፣ ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
    የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
               ፍኖተ ሰላም                                                        
                                                                                                 ጥር  2007

4 comments:

simakonemelak.blogspot.com said...

qale hiwot yasemalin

Teshome Ayele said...

KaleHiwot yasemalin Memhir. Egziabher betena behiwot Yitebikilin!

Unknown said...

ቃለ ህይወት ያሰማልን!
እንኳን አብሮ አደረሰን!

Anonymous said...


የበለጠ ምስጢራትን ለማስተማር ትጉ፣ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፤ አሜን
በድጋሜ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ፣ ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡