ዓለም
ስንል ሁለት ትርጉም ይኖረዋል አንደኛው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት የሚኖርበት ዓለም ማለታችን ሲሆን ሁለተኛው ዓለም ሰው ነው፤
እነዚህ ሁለቱም ታዲያ ማለቅ የሚስማማቸው ዓለማት ናቸው፤ እስካሁን ድረስ መነሻቸውን እንጅ መጨረሻቸውን ማወቅ የተቻለው ከፍጡራን
ማንም የለም፤ የሰው እድሜ ቢበዛ ሰማንያ የዓለም እድሜ ደግሞ ስምንት ሺህ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ይሁንም እንጅ በሚያልቅ እድሜአቸው
የማያልቅ ሌላ ዓለም ተክተው እንዲያልፉ ተፈቅዶላቸዋል፤ ማለትም ይህ ዓለም የሚያልፈውን አካሉን ሠሪው እግዚአብሔር የት እንዳደረሰው
ሳይታወቅ እንዳልነበረ ያደርገውና በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር እንዲተካ ያደርገዋል፡፡ ሰውንም እንደዚያው ወደዚህ ምድር ሲመጣ
ለጊዜው በማደጉ ደስ የሚያሰኘውን ካደገ በኋላ ደግሞ በእርጅናውና በመለወጡ የሚያስከፋውን አካል ይዞ እንዲወለድ ያደርገዋል ኋላ
ግን እንደገና ሞትን እንደ ገበሬ መቃብርን እንደ እርሻ አድርጎ ይዘራውና ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ በማይፈርስና በማይበሰብስ ሰውነት
እንዲነሣ ያደርገውና ያለቀውን ዓለሙን እንደገና እንዲቀጥል ያደርገዋል ማለትነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በማንኛውም ሰው አዕምሮ ውስጥ
የሚመላለስ አንድ ጥያቄ ሁልጊዜም አለ፤ የዓለሙ መጨረሻ መቼ ነው? መቼም ልናውቀው የማንችለው ጥያቄ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል፤