>

Thursday, 19 March 2015

የዓለም መጨረሻ



ዓለም ስንል ሁለት ትርጉም ይኖረዋል አንደኛው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት የሚኖርበት ዓለም ማለታችን ሲሆን ሁለተኛው ዓለም ሰው ነው፤ እነዚህ ሁለቱም ታዲያ ማለቅ የሚስማማቸው ዓለማት ናቸው፤ እስካሁን ድረስ መነሻቸውን እንጅ መጨረሻቸውን ማወቅ የተቻለው ከፍጡራን ማንም የለም፤ የሰው እድሜ ቢበዛ ሰማንያ የዓለም እድሜ ደግሞ ስምንት ሺህ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ይሁንም እንጅ በሚያልቅ እድሜአቸው የማያልቅ ሌላ ዓለም ተክተው እንዲያልፉ ተፈቅዶላቸዋል፤ ማለትም ይህ ዓለም የሚያልፈውን አካሉን ሠሪው እግዚአብሔር የት እንዳደረሰው ሳይታወቅ እንዳልነበረ ያደርገውና በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር እንዲተካ ያደርገዋል፡፡ ሰውንም እንደዚያው ወደዚህ ምድር ሲመጣ ለጊዜው በማደጉ ደስ የሚያሰኘውን ካደገ በኋላ ደግሞ በእርጅናውና በመለወጡ የሚያስከፋውን አካል ይዞ እንዲወለድ ያደርገዋል ኋላ ግን እንደገና ሞትን እንደ ገበሬ መቃብርን እንደ እርሻ አድርጎ ይዘራውና ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ በማይፈርስና በማይበሰብስ ሰውነት እንዲነሣ ያደርገውና ያለቀውን ዓለሙን እንደገና እንዲቀጥል ያደርገዋል ማለትነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በማንኛውም ሰው አዕምሮ ውስጥ የሚመላለስ አንድ ጥያቄ ሁልጊዜም አለ፤ የዓለሙ መጨረሻ መቼ ነው? መቼም ልናውቀው የማንችለው ጥያቄ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል፤
ምክንያቱም ይህ ዓለም ሲመጣ ከእኛ መካከል ከእግዚአብሔር ጋር የተማከረ ማን ነው? መፈጠሩን በዚህ ዘመን አድርገው አሠራሩን እንዲህ አድርገው ያለስ ማን አለ? እኛ ይህን ዓለም ያወቅነው ከተፈጠረ ከብዙ ቀናት በኋላ ነው፤ እንደዚህ ሁሉ ማለፉንስ እናውቀው ዘንድ እንዴት እንችላለን? የሚመጣውንስ አዲሱን ዓለም መቼ እንደሚመጣ ምን እናውቃለን? ምን አልባት እንዲህ ስላችሁ ዓለም ሲፈጠርማ ስላልነበርን ነው ሳናውቅ የቀረን አሁን ግን እንዴት እያለን ሳናውቅ እንቀራለን እንዳትሉኝ፤ አደራ! ምክንያቱም ያንጊዜም አንኖርምና፡፡ ሁላችንም በሞት እንወሰዳለን ዓለም ከእኛ አስቀድማ እንደተገኘች አሁንም ወደኋላ ትቀራለች ለአንድ ሱባዔ ብቻዋን ተራራው ኰረብታው ተንዶላት፣ ጎድጓዳው ሞልቶላት ትሰነብታለች፤ ፈጣኖቹ የነፋስ እግሮች ይረማመዱባታል ያልተስተካከለችውን ዓለም ያስተካክሏታል፤ ከነፋስ በስተቀር ሕይወት ያለው ፍጥረት ይታጣባታል ነፋሱም የመዓት ነፋስ ስለሆነ ሕያዋን ለሆኑ ፍጥረታት የሚስማማ ነፋስ አይደለም፡፡ በምድር የነበሩ ምድራውያን ፍጥረታት በሞትና በመቃብር ውስጥ ሆነው፣ ነፍሳተ ጻድቃን በገነት፣ መላዕክት በሰማያት፣ ሆነው የሰንበት ጌታ በሰንበት መጥቶ ምህረትን እስኪያደርግላቸው ድረስ እለተ ሰንበትን ይጠባበቃሉ፡፡ ዛሬ በመዝሙራችን ያከብርዋ ለሰንበት…. ብለን መዘመራችን እኮ ሁሉም ፍጥረት ደጅ የሚጠናት ቀን መሆኗን ለመግለጥ ነው እንጅ ሌላ ምንድነው፡፡ መጀመሪያም ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የመጣባት፣ ኋላም ከመኖር ወደ አለመኖር የሚሸጋገርባት እለት ስለሆነች ሁሉም በተስፋ ይጠብቃታል፡፡ ይህችኛዋ ዓለም ተስፋ የሌላት ዓለም ስለሆነች ያለተስፋ ያለደጅ ጥናት የተሰጠችን ዓለም ናት ያችኛዋ ዓለም ግን ከታላቅነቷ የተነሣ በተስፋ የተሞላች የፍጥረት ሁሉ ተስፋ ፍጻሜ ናት፡፡ እንዲያውም አንድ ሱባዔ በመቃብር ተዘግቶብን በመቆየታችን የምናገኛት የሱባዔ ውጤት ናት- ያችኛዋ ዓለም፡፡ ቢሆንም ግን ይህን መጨረስ ካልቻልን ያኛውን ዓለም መጀመር አንችልም፤ በዚህኛው ዓለም በኵል ካልሆነ ወደዚያኛው ዓለም መሸጋገር አንችልም፤ እንደዚያ ከሆነ የዚህ ዓለም መጨረሻው መቼ ይሆን? ቶሎ ቢያልቅ አይሻልም? ምክንያቱም ይህ ዓለም ሲያልቅ ነውና ጌታችን ዳግመኛ መጥቶ ሊወስደን ቃል የገባልን፡፡‹‹እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትኖሩ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ›› ዮሐ 14÷3፡፡ ደስስስስ የሚል የተስፋቃል ነው፤ ዳሩግን ምን ይሆናል የዓለሙ ፍጻሜ ካልደረሰ አይመጣም፤የዚህን መጽሐፍ ቃል የምታምን ነፍስ ሁላ ‹‹አሜን ጌታ ሆይ ቶሎ ና››ራእ22÷20 ስትል ትኖራለች፡፡
      እኛ ለዓለም የምንሰጠው እስከ አርባና ሰማንያ ቀን ብቻ ነው እንጅ ከዚያ በኋላ ከዓለም አይደለንም፤ ዓለማችን ያንጊዜ ታልፋለች፤ ምክንያቱም ክርስቶስን በሞቱ እንመስለው ዘንድ ወደ ጥልቁ የምንወርድበት ቀን ስለሆነ ነው ሮሜ 6÷3 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኛ በዓለም ዘንድ የሞትን፣ ዓለምም ደግሞ በእኛ ዘንድ የሞተች ትሆናለች፤ ባለቤቱ ክርስቶስም እንደ ተናገረው እኛ ከዓለም ሳንወጣ በዓለም እንኖራለን እንጅ ከዓለም አይደለንም ዮሐ 17÷14 ስለዚህ በምድር ላይ የምንኖረው ኑሮ ለወዲያኛው ዓለም የምንዘጋጅበት የዝግጅት ጊዜ መሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ማለቅ ከሚስማማቸው አራት ባሕርያት ተሠርተን፣ የሚያልቅ ምግብ ተመግበን፣ የሚያልቅ ልብስ ለብሰን ምን አይነት ተስፋ ሊኖረን ይችል ነበር ብላችሁ ታስባላችሁ? እንዳለ እንደ ቆምን እኮ ነው ሰውነታችን የተገኘባቸው አራቱ ባሕርያት የሚያልቁት፤ የነፋስ ባሕርያችን እያለቀ ሲሄድ እንደ ልብ ሩጦ መቅደም አይቻልም፤ ወገብ ይተሳሰራል፣ጉልበት ይብረከረካል፤ የእሳት ባሕርያችን እያለቀ ሲሄድ ደግሞ ሰውነታችን ይቀዘቅዛል፣ ሙቀትና ውበት ይርቀዋል፤ የውኃ ባሕርያችን እያለቀ ሲሄድ የመሬት ባሕርይ ይሠለጥንበትና ምድር ተደግፎ እንዲነሣ የምድር ባሕርዩ ከባድ ስለሆነ እንደ ልቡ እንዳይንቀሳቀስ ያደርገዋል፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የሚበላው የሚጠጣው እንዳይስማማው ያደርገዋል፤ ምክንያቱም በሰውነታችን ውስጥ የእሳት ባሕርያችን ካላበሰለ፣ የውኃ ባሕርያችን ካላረጠበ፣ የነፋስ ባሕርያችን ጠቃሚ ጠቃሚውን እየለየ ለደም ስሮቻችን ካላቀበለ የመሬት ባሕርይ ተግባሩ መሸከም ብቻ ነው የሚሆን ስለዚህ የጤና ችግር ሊፈጠር ግድ ይሆናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ደግሞ በሚያልቁ ነገሮች የተሠራ ሥጋን የለበስን የሚያልቀው ዓለም ነዋሪዎች መሆናችን ነው፡፡
      እኔን በጣም የሚያስገርመኝ ግን እያንዳንዱ ባሕርያችን እንዲህ ቀስ እያለ እንደሚያልቀው ሁሉ የምንኖርባት ዓለማችንም እንዲሁ ቀስ እያለች የምታልቅ ዓለም ናት፤ ስለዓለም ስናወራ ሁለት አይነት አጨራረስ አላት አንዱ ማለቅ ሲሆን ሌላው ደግሞ ማለፍ ነው፤ ሁለቱም ይከናወንባታል አሁን እያደረገች ያለችው ቀስ እያለች ማለቅ ነው፡፡ አሁን ዛሬ በአባቶቻችን ዘመን የነበረው በረከት አለ? በነ አቡነ ፊልጶስ ዘመንኮ ደብረ ሊባኖስ ላይ አንድ ጽዋ ውኃ የብዙ መነኮሳትን ጥም ይቆርጥ ነበር፤ዛሬ በየቤታችን ውኃ ገብቶም ገና ጠጥተን አልረካንም፡፡ የቀደመው ፍቅርስ አለ? ስለወንድም ተላልፎ እንዲሞቱ የሚያደርገው፤ ለኔ ይድላኝ የማይለው፤ ባዕድና ዘመድ የማይለየው፤የቀድሞው ትዳርስ አለ? ጌታዬ፣ እህቴ የሚያባብለው፤ በማይታየው የፍቅር ሰንሰለት ልብን የሚያስተሳስረው፡፡ እንደ ቀድሞውስ ያለ ደግ ሰው አለ? እንኳን ለሰው ለእንስሳ የሚራራ እንደ አጼ ዮሐንስ ያለ፤ አጼ ዮሐንስ የጎንደሩ የሚነገርላቸው ታሪክ አለ ከእለታት አንድ ቀን ከቤተ መንግሥታቸው ያልተለመደ እንግዳ ዘበኞችን ሳያስፈቅድ ዘው ብሎ ይገባል፤ የተበደለ አህያ ነው፤ ንጉሡ ገርሟቸው ሲመለከቱ ሳሉ ያለ ርህራሄ ሲጭኑት በመኖራቸው ምክንያት ጀርባው ቆሳስሎ አዩትና ባለ አህያውን ቀጥተው አህያውን ነጻ ሆኖ እንዲኖር ፈረዱለት ይባላል፤ እንደዚህ ያሉ ርህሩሃን ኢትዮጵያውያን ነበሩን ዛሬ የት ሄዱ? መልሱ አለቁ ነው፤ ነቢዩ ይህ ታይቶት ነው አስቀድሞ ‹‹አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና አድነኝ›› መዝ 11÷1 ሲል የጸለየው፡፡ እንግዲያውስ ዓለም በማለቅ ላይ ናት ማለት ነው፡፡ የሚቀራት ቢኖር ማለፍ ነውና ሳታልፍብን የማያልፍ ሥራ ልንሠራባት ይገባናል፡፡  

 

1 comment:

Anonymous said...

ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡