ያለንባት ምድር ትናንትና
ሌሎች ሰዎች ነበሩባት፤ አንዳንዶቹ ሠርተዋት አንዳንዶቹ ደግሞ አፍርሰዋት ሂደዋል፡፡ እጣ ፋንታዋ ይህ ነውና ያበቀለችውን አብልታ፣
ያፈለቀችውን አጠጥታ፣ ከሆዷ የወጣውን አልብሳ ያሳደገቻቸው ሁሉ ጥቂት ቀን አለን አለን ይሏትና ይጠፉባታል፤ ሁል ጊዜ የጋለሞታ
አይነት ሥርዓት እንዲኖራት ያደርጓታል፡፡ አንድ ወቅት ላይ የተመዘገበውን ታሪክ እናንሣና እንይ የኛም ታሪክ ያንድ ዘመን ማስታዎሻ
እንደሚሆን እርግጠኞች ነን፡፡
በእናቱ
ማኅፀን ውስጥ እንዲኖር የተፈቀደለትን ጊዜ ጨርሶ አንድ ሕጻን ወደ ዓለም እንዲመጣ ወደ እናቱ ሔዋናዊ መልእክት መጣ፤ ማለትም ሁላችንንም
ወደ ዓለም ስንመጣ የቀደመን ምጥ በእናቱ ላይ የተፈጥሮ ሕጉን ጠብቆ መጣ፡፡ ዓለምን የተቀላቀልንበት ጉዞ የሚጀምረው በእናቶቻችን
ምጥ ነው፤ ጉዟችን የሚያበቃው ደግሞ ከሞት ጋር በምናደርገው ትግል በሚፈጠር ምጥ ነው፡፡ በምጥ ጀምረን በምጥ እንጨርሳታለን፤ ዓለም
እንዲህ ናት፡፡
ታዲያ የዛሬው ባለታሪካችንም ሁላችንም በመጣንበት መንገድ ሊመጣ ግድ ነውና
እናቱን አስጨንቆ ወደ ዓለም ሊመጣ ሲቃረብ የሴቲቱን ጭንቅ ብርቱ ያደረገባት ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ? ሴቲቱ ብቻዋን የምትኖር
ሴት ነበረች፤ ከጎኗ ሆኖ ጭንቀቷን ሊጋራት የሚችል አንድም ዘመድ የላትም፤ መከራን ለብቻ መሸከም ከባድ ያደርገዋል፡፡ ለነገሩ በሰው
ሰውኛው ማለታችን ነው እንጂ ሰው ቢኖርስ ምን ያደርጋል፤ በዘመድ የከበሩ፣ በእውቀት የነጠሩ፣ በሀብት የበለጠጉ ብዙዎች ሲሞቱ እናውቅ
የለ፤ ይህች ሴት ግን ምንም እንኳን የሚታይ ምድራዊ ዘመድ ባይኖራትም እግዚአብሔር ከሰማይ ዘመድ ላከላት፡፡
ሚካኤልና
ገብርኤል የሚወለደውን ሕጻን
እንዲባርኩና እናቱን ከጭንቀቷ እንዲገላግሉ ተላኩ፤ ከጎኗ ካሉ ጎረቤቶቿ ይልቅ ከሦስተኛው ሰማይ የመጡት መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል ለእርሷ ይቀርባሉ፤ ሕጻኑ ተወለደ በመላእክቱም እጅ ተባረከ፤ የሕጻኑ መባረክ ያላስደሰተው ሰይጣን ከጎረቤት ሂዶ ጠላት ቀሰቀሰ፤ ባለጠጋው ጎረቤቷ እንደ ሔሮድስ በሽንገላ ማቴ2÷8 ላሳድገው ብሎ ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ሕጻኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ሚያሳድገው አምላክ ቤት ተዛወረ፤ ባለጠጋው ሊገለው ፈልጎ ሳያስበው ሁሉን ወደ ሚችል አምላክ እቅፍ አስጠጋው፤ እሱ በሳጥን ውስጥ አድርጎ በባሕር ጨመረው፤ እግዚአብሔር ግን በብርሃን ሠረገላ አድርጎ በመላእክቱ ክንፍ አሻገረው፤ ዮሐንስ በራእይ እንዳያት ሴት ክንፍ ተሰጠው፣ እንደ ኤልያስም ማደሪያ ዋሻ ተከፈተለት፤ 1ነገ19÷9፣ራእ 12÷14 ኅጻኑ ሳይሞት ከባሕር ወጣ እግዚአብሔር ባዘጋጀለትም መንገድ ማደጉን ቀጠለ፤ ከባሕር ተገኝቷልና ስሙ ባሕራን ተባለ፤ መከራው ስም ሆነለት፤ ሞቷል ብሎ ያሰበው ያ ባለ ጠጋ ለንግድ ሲሄድ ሕጻኑ ከሚያድግበት ስፍራ ደረሰ፤ እሱ መሆኑንም እንዳወቀ ጊዜ ሳያጠፋ እንዲገድለው ወሰነ፤ የሚሞትበትን መንገድ የሚገልጠውን ደብዳቤ ጽፎ በእጁ አስይዞ ወደ ሚገደልበት ሥፍራ ሰደደው፤ እግዚአብሔር ግን አሁንም ሞትን ከመንገዱ አራቀለትና ገዳዮቹ እልል ብለው እንዲድሩት አደረጋቸው፤ እስካሁን ድረስ የተረክሁላችሁ ሙሉ የሰውየው ታሪክ ነው
እንዲባርኩና እናቱን ከጭንቀቷ እንዲገላግሉ ተላኩ፤ ከጎኗ ካሉ ጎረቤቶቿ ይልቅ ከሦስተኛው ሰማይ የመጡት መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል ለእርሷ ይቀርባሉ፤ ሕጻኑ ተወለደ በመላእክቱም እጅ ተባረከ፤ የሕጻኑ መባረክ ያላስደሰተው ሰይጣን ከጎረቤት ሂዶ ጠላት ቀሰቀሰ፤ ባለጠጋው ጎረቤቷ እንደ ሔሮድስ በሽንገላ ማቴ2÷8 ላሳድገው ብሎ ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ሕጻኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ሚያሳድገው አምላክ ቤት ተዛወረ፤ ባለጠጋው ሊገለው ፈልጎ ሳያስበው ሁሉን ወደ ሚችል አምላክ እቅፍ አስጠጋው፤ እሱ በሳጥን ውስጥ አድርጎ በባሕር ጨመረው፤ እግዚአብሔር ግን በብርሃን ሠረገላ አድርጎ በመላእክቱ ክንፍ አሻገረው፤ ዮሐንስ በራእይ እንዳያት ሴት ክንፍ ተሰጠው፣ እንደ ኤልያስም ማደሪያ ዋሻ ተከፈተለት፤ 1ነገ19÷9፣ራእ 12÷14 ኅጻኑ ሳይሞት ከባሕር ወጣ እግዚአብሔር ባዘጋጀለትም መንገድ ማደጉን ቀጠለ፤ ከባሕር ተገኝቷልና ስሙ ባሕራን ተባለ፤ መከራው ስም ሆነለት፤ ሞቷል ብሎ ያሰበው ያ ባለ ጠጋ ለንግድ ሲሄድ ሕጻኑ ከሚያድግበት ስፍራ ደረሰ፤ እሱ መሆኑንም እንዳወቀ ጊዜ ሳያጠፋ እንዲገድለው ወሰነ፤ የሚሞትበትን መንገድ የሚገልጠውን ደብዳቤ ጽፎ በእጁ አስይዞ ወደ ሚገደልበት ሥፍራ ሰደደው፤ እግዚአብሔር ግን አሁንም ሞትን ከመንገዱ አራቀለትና ገዳዮቹ እልል ብለው እንዲድሩት አደረጋቸው፤ እስካሁን ድረስ የተረክሁላችሁ ሙሉ የሰውየው ታሪክ ነው
እኔ የነገርኳችሁን ይህን ሁሉ ታሪክ እግዚአብሔር ያውቃል እንጅ ልጁ
አላወቀም ነበር፤ ዛሬ ማድረግ ያለበትን ያደርግ ነበር እንጂ የነገውን አልያም የትናንቱን ማሰብ አይፈልግም ነበር፤ ብቻ በዛሬው
መንገዱ ላይ እግዚአብሔር እንዲጠብቀው ተስፋ ያደርግ ነበር
ወንድሜ ሆይ! በአንተ የሕይወት ጉዞ ውስጥ ብዙ ያላወቅሀቸው ፈተናዎችን
በእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳለፍካቸው ታውቃለህ? ሳታውቀው ሞትን ራሱን ተረግጠህ ያለፍክበት ቀን እንዳለ ልታምን ይገባሀል፤ ከፀናው
መሬት ይልቅ ነፋስ በሚያንገላታው ለራሱ ተረጋግቶ መኖር በማይችለው ባሕር ውስጥ ላንተ መንገድ አዘጋጅቶ ወደ ምታድግበት ሥፍራ ይወስድሀል፤ከምታውቀው
ሳይሆን ከማታውቀው ሀገርና ወገን መካከል መኖሪያህን ያዘጋጅልሀል፡፡
ሳታውቀው ከተጣልክበት ባሕር እርሱ ራሱ መውጫውን ያሳይሀል፤ የጥልቀቱ
አይነትና መጠን ይለያይ ይሆናል እንጅ በባሕር ያልተከበበ ሕይወት ይኖራል ብለህ ነው? የእያንዳንዱን ስኬታማ ሕይወት ምሥጢሩን ስትመለከት
የመከራ ድምር ውጤት ነው፡፡ አንተን ወደ ባሕሩ የጨመሩህ እንድትሞት ፈረልገው ቢሆንም እግዚአብሔር ግን አንተን በባሕሩ ላይ ወደ
ሌላ ሊያሻግርህ ፈልጎ ስትጣል ዝም አለ፤ መጣልህን ብታውቅ ኖሮ አታንጎራጉርም ነበር? እግዚአብሔር የተወህ መስሎ አይሰማህም ነበር?
ሰው ነሃ! ምን ይደረግ;; እግዚአብሔር የሚሠራውን ዝም ብለህ ተመልከት፤ አንተን ወደ ሌላ ድንቅ ሕይወት ለማሻገር መንገዱን በመከራህ
በኩል አደረገው፡፡ ምን አልባት አንተ የብሱን ልትመርጥ ትችል ይሆናል፤ ግን ታላቅ እምትሆነው በባሕሩ በኩል ያለፍህ እንደሆነ ነው፡፡
ግድ የለህም! ከውሀው ማዶ እግዚአብሔር ቤት ሠርቶ ይጠብቅሃል፤
እስከፈለገው ቀንም በዚያ ያኖርሃል፤ አሁንም አደራ እልሀለሁ፤ የነገውን
መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፤ እርሱ ይመራሀል፤ እጅህ ላይ የገባውን ነገር ሁሉ በእምነት ጨብጠው፤ በእምነት ከያዝከው አንበሳው
ይገርምልሀል፤ የሚያቃጥለው ይበርድልሀል፤ የመውጊያው ብረት ምቾትን ይሰጥሀል፤ ሞት በሕይወት ይተካልሀል፡፡ ብቻ አንተ ታምነህ ተሠማራ
እንጅ እግዚአብሔር አንተን በንሥር ክንፍ ጭኖ ይመራሀል፤ በሚያፈርሱህ
እጆች ይገነባሃል፡፡
አንድ ወዳጄ ጋር ከተለያየን ብዙ ዘመናችን ነበርና ልጠይቀው ስሄድ የሰው
በማይመስል ሥራ ተሠርቶ አገኘሁትና እንዲህ አድርጎ የሠራው እግዚአብሔር እንጅ ሰው አይደለምና ብየ ደፍሬ ጠየቅሁት እንዲህም አልኩት
እኔ የማውቅህ በጥቂቱ ተዘርተህ ነበር፤ እንዲህ ባንድ ጊዜ የሰማይ ወፎች እስኪጠለሉበት ድረስ ቅርንጫፍህን ያሰፋው፣ ምድርን ለቀህ
ሰማዩን ተጠግተህ እንድትኖር ያደረገህ ምንድነው? አልሁት አንድ ቃል ብቻ መለሰልኝ ‹‹ ሊያፈርሱኝ በተዘረጉ እጆች ገነባኝ ››
አለኝ፡፡
እናፈርስሀለን
ብለው የገነቡህ፣ እንነቅልሀለን ብለው የተከሉህ ስንቶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጉዟችን እንደ ቁልቋል ያለ ነው፤ ቁልቋል በተፈጥሮው
ቆራጮች ካልቆረጡት አንድ ላይ እንደ ቆመ ሳይበዛ መቅረቱ ነው፡፡ ቆራጮቹ ቆርጠው ሲጥሉት ግን እየበዛ ሥር እየሰደደ ምድርን ይሞላታል፤
አየህ መቆረጥም አንዳንዴ ለበጎ ይሆናል ማለት ነው፤ ከቅርንጫፍነት አውጥቶ ግንድ ያደርጋል፤ ከጥገኝነት ለይቶ ዋና ያደርጋል፡፡
ትዝ
አይልህም ቆራጮች ሳይቆርጡህ ድሮ ሥሩ አንተን ይሸከምሀል እንጅ አንተ ሥሩን አትሸከመውም ነበር ዛሬ ግን ቆርጠው የጣሉህ ሲያልፉ
አንተን ተሸካሚ አደረገህ፡፡ ሲቆርጡህ እና ሲጥሉህ እንደነሱ አደርጋለሁ አትበል፤ እዚያው ባለህበት ስር እንድትሆን ጸልይ እንጅ፡፡
አባ ተክለ ሃይማኖት ከደብረ ዳሞ በገመድ ሲወርዱ ሰይጣን ገመዱን የቆረጠው ወድቀው ይሞታሉ ብሎ ነበር፤ ገመዱን ሲቆርጠው እድሜያቸውንም
አብሮ የቆረጠው መስሎት ነበር፤ ነገሩ ግን እንደዚያ ሳይሆን ቀረ፤ ያለ ገመድ በረው የሚሄዱበት የንስር ክንፍ አገኙ እንጅ፡፡
አንተም የታሰርህበት ገመድ ሲበጠስብህ እምታንጎራጉር ከሆነ የምታምነውን አምላክ
ከገመዱ አሳንሰኸዋል ማለት ነው፡፡ ገመዱን ይቁረጡት፣ ደብዳቤውንም ለሞት አድርገው ይጻፉት፣ የተከፈተልህንም በር ይዝጉት፤ የቀረበልህን
ማእድ ያንሱት፤ የገነባኸውን ያፍርሱት፤ አንተ ሳታውቅ መቃብርህን ይቆፍሩት፤ መንገድህን በሾህ ይጠሩት፤ ሀሳብህን በእጅ ብልጫ ይሻሩት፤
አንተ ግን እመን በየዋህነት እንደ ርግብ ተጠበቅ፤ ያኔ የምታምነው አምላክ በጠላት እጅ ይገነባሀል በእሾሁ ላይ ያስኬድሃል በተዘጋ
በር ያስገባሀል፤
ገነት
ውስጥ ስላሉ ነፍሳት ሰምተህ ትቀና ይሆናል አይደል? ይገርምሀል እያንዳንዳቸውን ብትጠይቃቸው ዓለም እየገፋች እዚህ እንዳደረሰቻቸው
ይነግሩሀል፡፡ ዓለምን እና ክፋቷን ለመሸሽ ሲጓዙ ገነት ደረሱ፤ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የሚነገርለት ሕጻኑ ዮሐኒ ያደገው ከአንድ ባሕታዊ
ጋር ስለነበረ ዓለም ምን አይነት መልክ እንዳላት አያውቅም ነበር፤ ባሕታዊው አንድ ጠላት አለን ሰይጣን የሚባል ይለዋል መልኩ ምን
አይነት ነው ሲለው ፀጉሩ ከትክሻው ላይ የወደቀ፣ ከደረቱ ላይ ጡት ያለው …እያለ ሴት አስመስሎ ይነግረዋል፤
እንዲህ አይነት ሰው ካየህ ጠላታችን ስለሆነ ገደልም ቢሆን ገብተህ አምልጥ
ብሎት ነበርና ከእለታት በአንድ ቀን እናቱ ልጇ በዚያ ገዳም እንዳለ ትሰማ ነበር እንጂ ከተወለደባት ቀን በስተቀር አይታው አታውቅ
ስለነበር ልታየው ስትመጣ ከሩቅ አይቷት አባቱ እንደነገረው የጠላቱን መልክ ይዛ ስላያት ወደ ኋላ ዞሮ ሲሮጥ በጥልቅ ገደል ውስጥ
ተወረወረ፤ ወዲያውኑ ስለ ቁርጥ ውሳኔው ክንፍ ተሰጥቶት በዚያው ወደ ብሔር ሕያዋን በረረ፤ እስካሁንም ከነሔኖክና ኤልያስ ጋር የጌታን
መምጣት በሕይወት ሆነው ከሚጠብቁት እንዳንዱ ሆኖ ይኖራል፡፡
ብዙዎቹ
ዓለምን ለመሸሽ በሚያደርጉት ሩጫ ሳያስቡት ከክርስቶስ መንግሥት ገቡ፤ ፈርዖን ክንዱን ባያበረታበት እስራኤል እንዴት የቃልኪዳኑን
ምድር ሊያስብ ይችላል፤ እንዴት ባርነቱን ያመልጠዋል፤ ከሰማይ የሚዘንብ መና የሚመገብ እስራኤል የግብጽን ዱባና ሽንኩርት እንደተመገበ
ሊቀር ነበር፤ ፈርዖንን ለማምለጥ፣ ግብጽን ላለማየት በሚደረግ ሩጫ ውስጥ ባሕር መክፈል፣ ከዓለት ላይ ውሃን ማስገኘት፣ ልብስ እንኳን
ባይኖር በደመና መሸፈን፣ እግዚአብሔር ከሚያነጋግራቸው ሰዎች ጋር መጓዝ ከዚህም በላይ ሌሎች ነገሮችን ማድረግ ይቻላል፡፡
10 comments:
Qale hiywet yasemawo memhir...
ቃለ ህይወት ያሰማልን!
kale hiwot yasemalin mengste semayatn yawrselin
Kalehiwet yasemaln tsegawn yabzalot timhrton ayleyen.
Kalehiwet yasemaln tsegawn yabzalot timhrton ayleyen.
Kale hiwet yasemaln !!!
Kale hiwet yasemaln !!!
Kale hiwot yasemalin
arif new gin leande rese ande tarik bicha bihon melekam new
ስማኮነ መላክ ቃል ሕይወት ያሰማልኝ ያገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልኝ
አንድ ጥያቄ ልጠይቅ? አመሰግናለው
ስማኮነ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ምን ማለት ነው?
መህር መላክ ያባቶት ስም ነው ወይስ ወጥ
ስማኮነ መላክ ከሆነስ ትርጉሙ ያስረዱኛ? ምክኒያቱም እንዲ ያለ ስሞች ለኢትዮጲያኖች ማስለመድ መልካም ነው ሀገራች ስንት መልካም ነገር እያላት ስም ሳይቀር ከውጭ ነው የምን
ዋሰው
Post a Comment