ክፍል ሁለት
ባለፈው ክፍል እንደተመለከትነው በኃጢአቱ ምክንያት ርስቱን ተነጥቆ
ስፍራውን ለቆ የመጣው የሰው ልጅ በዚህም ዓለም በልዩ ልዩ መንገድ ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወር ይኖራል፡፡ ከሀገሩ ወጥቶ ከሄደ
ደግሞ በልዩ ልዩ ፀዋትዎ መከራ መፈተኑ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ስደትን ከባድ እሚያደርገው ልጅ ይዞ የሚያደርጉት
ስደት ነው ልጅ ይዞ አስከትሎ የሚያደርጓት ስደት የመከራዎች ሁሉ እናት ናት፡፡ በእመቤታችን ም የሆነው ይህ ነውና በመከራ የሚተካከላት
ማንም የለም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ‹‹ሐዊረ ፍኖት በእግሩ ሶበ ይስዕን ሕጻንኪ ያንቀዐዱ ኀቤኪ ወይበኪ በእግሩ መሐድን
በደከመ ጊዜ ወደ አንች ቀናብሎ ያለቅሳል›› እንዳለ በነገር ሁሉ ሕጻናትን መስሏልና ሕጻናት እናቶቻቸውን የሚጠይቁትን ሁሉ ጠይቋታል፡፡
በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ተብላ ነበርና በብርቱ ፈተና ውስጥ አለፈች፡፡
ሔሮድስ ግን እሷን አሰድዶ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ክብሩ ከፍ ከፍ
አለ፤ የሊባኖስ ዝግባ የትኛውንስ ያክል ቢገዝፍ በቅርንጫፉ ዓለምን ቢከድን የሰማይ አዕዋፍ ቢንጠላጠሉበት፣ የምድርም እንስሳት ቢጠለሉበት
ምን ቁም ነገር አለው፤ አንዲት ክብሪት እንዳልነበረ ታደርገው የለ! ይገርማል እኮ! ያ ግዙፍ ዛፍ በትንሽ ክብሪት በትንሽ ምሳር
የሚጠቃ ይመስላችኋል? አንዲት ክብሪት ብዙ ደን ታጠፋለች፤ የሔሮድስም ግነት እግዚአብሔር ቁጣውን እስኪገልጥ ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሦስት ዓመት ከመንፈቅ የንስሐ ጊዜ ቢሰጠው አልመለስ ያለ
ሔሮድስን ከስሩ ነቅሎ እንዳልነበረ አድርጎ በሞት ቀጣው፤ ያንጊዜ ‹‹ኃጥዕ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ገኖ አየሁት ስመለስ ግን አጣሁት
ቦታውን ፈለግሁ አላገኘሁትም›› መዝ 36÷35-36 ብሎ ነቢዩ ዳዊት የተናገረው ደረሰ፡፡ ቀናት ሲቆጠሩ ለካ ኃጢአቱም በእግዚአብሔር
ፊት እየተቆጠረበት ነበርና የዘመኑ ሳይሆን የክፋቱ ቁጥር ሲሞላ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ተፈረደበት፤ ዘመን ባይሞላም ክፋት ሲሞላ
ያለ ጊዜም ሊያስነሣ ይችላል ክፉ ሰው እስከ ዕድሜው ፍጻሜ የሚኖር አይደለም፤ እንዲያው ኃጢአቱ ሲሞላ እግዚአብሔር ከተወሰነለት
ዕድሜ በታች ሊያነሣው ይችላል እንጅ፡፡
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተመዘገበችው በለስ እንደ ሔሮድስ ያሉ
ሰዎችን ትመስላለች፤ የእርሻው ባለቤት ለሦስተኛ ጊዜ መጥቶ አንዳች ፍሬ ያላገኘባት በዚህም ምክንያት ‹‹እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን
ቆርጠህ ጣላት›› የተባለላት፡፡ ሉቃ 13÷6 ሔሮድስንም ጠበቀው እና በጎ ፍሬ ማፍራት አልችል ሲል አጫጆችን ልኮ አጨደው፡፡