>

Wednesday, 4 May 2016

ማዕዶት



ከትንሣኤ  በኋላ የምናሳልፈው ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ስያሜ ማዕዶት ተብሎ ይጠራል፤ መሸጋገሪያ ማለት ነው፤ ሳይሻገሩ የተስፋይቱን ምድር መውረስ እንዴት ይቻላል! ያልተሻገረ ሕዝብ ባሪያ ነው ዘፀ 5÷2 ያልተሻገረ ሕዝብ እረፍት የለውም ዘፀ 5÷17 ያልተሻገረ ሕዝብ ከዓለም አስጨናቂነት የተነሣ ነፍሱ ተጨንቃ የእግዚአብሔርን ቃል እንዳይሰማ ታደርገዋለች ዘፀ 6÷9 ያልተሻገረ ሕዝብ ነፍሱን ከገዳየቹ እጅ ማዳን አይችልም፤ ከሞትም ጋር ተስማምቶ ይኖራል ዘጸ 1÷16 ያልተሻገረ ሕዝብ የሰው ከተማ ይገነባል ዘፀ 1÷11 ብቻ ያልተሻገረ ሕዝብ ነጻነቱን፣ ክብሩን፣ ማንነቱን፣ ሀገሩን፣ ሃይማኖቱን እና ሌሎችንም አጥቶ ከተስፋ ርቆ ይኖራል፡፡
ይህ ሁሉ ችግር ወደ ነበረበት ሕዝብ ነው ክርስቶስ የመጣው፤ ቀድሞ ዮርዳኖስን መሻገር አልችል ብሎ በባርነት ይኖር ወደ ነበረው ሕዝብ ሙሴ እንደተላከ ዛሬ ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ወደዚህ ሕዝብ ተላከ፡፡ ከዚያ በፊት ኃጢአት፣ ሞት፣ ፍዳ ነግሠውበት የእነዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ ሠልጥኖበት ክብረ ሥጋን፣ ክብረ ነፍስን፣ ነጻነትን፣ ሰማያዊት ርስትን ተነጥቆ ከሞት ጋር ተላምዶ መቃብር የመጨረሻ ዕጣ ፋንታው ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል፡፡
ነገር ግን አሻጋሪያችን ክርስቶስ በእለተ ጽንስ ቁራኝነትን፣ በእለተ ልደት መርገምን፣ በእለተ ስቅለት ኃጢአትን ሞትን ፍዳን አጥፍቶ ወደ መቃብር ወርዶ በመቃብር ባደረባቸው ሌሊቶች ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን ተነሥቷል፡፡ የሰው ልጅ ከሀሳር ወደ ክብር፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገሩን ያረጋገጥነው በዚሁ እለት ነው፤
በመቃብር ፈርሶ በስብሶ ቀርቷል እንዳንል መቃብሩ ባዶ ሆኗል፤ ማቴ 28÷5፣ ሞት ሠልጥኖበታል እንዳንል መግነዙ ተፈቷል፤ የአይሁድን ቃል ሰምተን ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ወስደውታል እንዳንል ‹‹ተነሥቷል በዚህ የለም›› ማር 16÷5 የሚለው የመላእክት ምስክርነት ተሰምቶለታል፡፡ ሁሉም ነገር በዚህ ቀን አዲስ ነው፤ እንደ አይሁድ ሥርዓት ሴቶቹ ይዘውት የመጡትን ሽቱ የሚቀቡት ሬሳ በመቃብር ውስጥ ማግኘት አይቻልም፤