ከትንሣኤ በኋላ የምናሳልፈው ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ስያሜ ማዕዶት ተብሎ ይጠራል፤
መሸጋገሪያ ማለት ነው፤ ሳይሻገሩ የተስፋይቱን ምድር መውረስ እንዴት ይቻላል! ያልተሻገረ ሕዝብ ባሪያ ነው ዘፀ 5÷2 ያልተሻገረ
ሕዝብ እረፍት የለውም ዘፀ 5÷17 ያልተሻገረ ሕዝብ ከዓለም አስጨናቂነት የተነሣ ነፍሱ ተጨንቃ የእግዚአብሔርን ቃል እንዳይሰማ
ታደርገዋለች ዘፀ 6÷9 ያልተሻገረ ሕዝብ ነፍሱን ከገዳየቹ እጅ ማዳን አይችልም፤ ከሞትም ጋር ተስማምቶ ይኖራል ዘጸ 1÷16 ያልተሻገረ
ሕዝብ የሰው ከተማ ይገነባል ዘፀ 1÷11 ብቻ ያልተሻገረ ሕዝብ ነጻነቱን፣ ክብሩን፣ ማንነቱን፣ ሀገሩን፣ ሃይማኖቱን እና ሌሎችንም
አጥቶ ከተስፋ ርቆ ይኖራል፡፡
ይህ ሁሉ ችግር ወደ ነበረበት
ሕዝብ ነው ክርስቶስ የመጣው፤ ቀድሞ ዮርዳኖስን መሻገር አልችል ብሎ በባርነት ይኖር ወደ ነበረው ሕዝብ ሙሴ እንደተላከ ዛሬ ደግሞ
ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ወደዚህ ሕዝብ ተላከ፡፡ ከዚያ በፊት ኃጢአት፣ ሞት፣ ፍዳ ነግሠውበት የእነዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ
ሠልጥኖበት ክብረ ሥጋን፣ ክብረ ነፍስን፣ ነጻነትን፣ ሰማያዊት ርስትን ተነጥቆ ከሞት ጋር ተላምዶ መቃብር የመጨረሻ ዕጣ ፋንታው
ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል፡፡
ነገር ግን አሻጋሪያችን
ክርስቶስ በእለተ ጽንስ ቁራኝነትን፣ በእለተ ልደት መርገምን፣ በእለተ ስቅለት ኃጢአትን ሞትን ፍዳን አጥፍቶ ወደ መቃብር ወርዶ
በመቃብር ባደረባቸው ሌሊቶች ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን ተነሥቷል፡፡ የሰው ልጅ ከሀሳር ወደ ክብር፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣
ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገሩን ያረጋገጥነው በዚሁ እለት ነው፤
በመቃብር ፈርሶ በስብሶ
ቀርቷል እንዳንል መቃብሩ ባዶ ሆኗል፤ ማቴ 28÷5፣ ሞት ሠልጥኖበታል እንዳንል መግነዙ ተፈቷል፤ የአይሁድን ቃል ሰምተን ደቀ መዛሙርቱ
ሰርቀው ወስደውታል እንዳንል ‹‹ተነሥቷል በዚህ የለም›› ማር 16÷5 የሚለው የመላእክት ምስክርነት ተሰምቶለታል፡፡ ሁሉም ነገር
በዚህ ቀን አዲስ ነው፤ እንደ አይሁድ ሥርዓት ሴቶቹ ይዘውት የመጡትን ሽቱ የሚቀቡት ሬሳ በመቃብር ውስጥ ማግኘት አይቻልም፤
እሱማ የኦሪት ሕግ ስለ
ነበረ ኦሪት በተፈጸመችበት ወንጌል በተጀመረችበት እለት ኃጢአተኛዋ ሴት ማርያም ባደረገችው ሽቱ የመቅባት ሥርዓት ተጠናቋል፡፡ ይሁዳን
ምን አስቆጣው ይመስላችኋል ይህ ቀን ሽቱ የመቅባት ሥርዓት ፍጻሜ ቀን ስለሆነ ነው እንጅ ሌላ ምንድነው! ብልቃጡ ተከፈተ ሽቱው
በሙሉ በአንድ በክርስቶስ ላይ ተፈጸመ ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውለት ሳይጨርሱ የተውት ሽቱ ከክርስቶስ ማለፍ ሳይችል ቀረ፤ የሽቱው
ማለቅ ይሁዳን ያስቆጣው በምን ምክንያት እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ የተቀመጠ ቢሆንም ዮሐ 12÷6 ሌላው ምክንያት ሬሳ ማሸት ከእንግዲህ
እንደ ማይኖር የሚገልጥ ምሥጢር ያለው ስለሆነ እንዲህ ያስቀጣዋል፡፡ እንዲያውም የይሁዳ ንግግር የሚያስረዳልን ይህንኑ ነው ‹‹ለምንት
ዘመጠነዝ እፍረተ አሕጎለት ዛቲ ብእሲት ይህች ሴት ይህን ያክል ሽቱ ስለምን ታጠፋለች›› ማቴ 26÷8 ብሏል እንጅ ዋጋውን አይናገርም፤
ሽቱው አለቀ ክርስቶስም
በሕይወት ሳለ የተቀባውን ይህን ሽቱ ‹‹ዘንተሰ ለቀበርየ ገብረት፤ ይህንን ለመቃብሬ አደረገችልኝ›› ብሎ ሴቲቱን አመሰገናት፤ አሁን
ከዚህ ለሥጋ መዓዛን ከሚያመጣው ምድራዊ ሽቱ ወደ መዓዛ ነፍስ የምንሸጋገርበት ጊዜ ላይ ነን ይህ መዓዛ ሳይመጣ ሰይጣን በአስቆሮቱ
ሰው ልብ ውስጥ አድሮ ይቃወማል፤ ለዚህ ነው ሴቶቹ በኦሪታቸው ልማድ ሽቱ ሊቀቡ ሲገሠግሱ ቢመጡ ሊያገኙት አለመቻላቸው፡፡
መቃብሩ በመንፈስ ቅዱስ
መዓዛ ተሞልቷል፤ የእኛን ባሕርይ ከእኛ የነሣው ክርስቶስ አይሁድ በእለተ አርብ ልብሱን ተካፍለው ወስደውታልና ባለጠጋው ዮሴፍ ባዘጋጀው
መግነዝ ተጠቅሎ ወደ መቃብር ወረደ ማቴ 27÷59 ሲነሣ ግን ለእርቃኑ መሸፈኛ ያንኑ ለብሶ እንዳልተነሣ ቅዱስ ወንጌል መሰከረልን፤
ለዓይን የሚበዘብዝ የብርሃን ልብስ ለብሶ ለሴቶቹ ታይቶ ነበር፡፡ ይሄ ነው መሻገር፤
ይህ ሁሉ ነገር በምድር
ላይ ከመገለጡ አስቀድሞ መሻገር በእለተ ዐርብ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ተፈጽሞላቸዋል፤ እለተ ዐርብ የእኛ ትንሣኤ የክርስቶስ ሞት
የታየባት እለት ናት በሞቱ ተነሥተናል በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አረጋግጠናል፤ ለዚህም ማስረጃችን እርሱ በመስቀል ላይ ‹‹አባት
ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ›› ብሎ ነፍሱን ሲሰጥ ምድር ተነዋወጠች፣ መቃብራት ተከፈቱ የሰማይ ኃይላት ተናወጡ ከጻድቃን
ወገን ብዙዎች ከመቃብር ወጡ
ሽግግሩ በዚህ ዓለም የተዘጋ
መቃብርን ከፍቶ እስከመውጣት ድረስ ነው በወዲያው ደግሞ የእሳትን ባሕር አቋርጦ እስከማለፍ ድረስ መሻገር ለሰው ልጀች ተፈቅዷል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችንም አሻጋሪዋን ክርስቶስን ‹‹ሐዳፌ ነፍሳት›› ስትለው ይህንንም የተሻገርንበትን ሳምንት ማዕዶት ብላ ታከብረዋለች፡፡
ስለ ቅዱስ ቁርባን የሚደረገውን የቅዳሴ ጸሎትም የምታደማድመው ሐዳፌ ነፍስ በተባለ ጸሎት ነው የተሻገርንበት መሥዋዕታችን ይህ ነው
ለማለት ነው፡፡
ከእሑድ እስከ እሑድ ስምንቱን
እለታት ስለ ክብረ ትንሣኤ ሰንበት አድርገን እናከብራለን በዓል እናውጃለን፡፡
1. ሁሉም ደቀ መዛሙርት በመነሣቱ
አላመኑም ነበርና መቶ ሃያው ቤተ ሰብእ ለሃይማኖታችን መሠረተች ስለሆኑ እስኪያምኑ መጠበቃችን ነው፡፡ እንዲያውም መጨረሻውን እሑድ
ዳግም ትንሣኤ ብለን እናስታውሰዋለን ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ የጌታን መነሣት ያመኑበት ቀን ስለሆነ ነው ዮሐ 20÷27-29 የመጀመሪያው
ቀን ላይ ‹‹ወመንፈቆሙ ናፈቁ፤ እኩሌቶቹ ግን ተጠራጠሩ›› ማቴ 28÷17 ተብሎ መጻፉን እናስታውሳለን፡፡
2. ከእለተ ዐርብ እስከ ትንሣኤ
ሥራ የሠሩ ሰዎችና አንዳንድ ታሪኮች የሚታወሱበት ሰሙን ስለሆነ ነው፡፡
- ሰኞ ነፍሳት፣ (ከሲኦል መውጣታቸው)
-ማክሰኞ መላእክት (በእለተ ትንሣኤ መቃብሩ ላይ የተገለጡ ድንጋዩን ያንከባለሉ)
-ረቡዕ አልዓዛር (በትንሣኤው)
-ሐሙስ አዳም (ከገነት ወጥቶ አልቀረም ለማለት)
- ዐርብ ቤተ ክርስቲያን(ምዕመን) (በሞተ ክርስቶስ መመሥረቷን)
- ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት (ትንሣኤውን ያበሠሩ)
የሚታሰቡበት ሳምንት ስለሆነ ነው፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሁሉ
ከጌታችን ትንሣኤ ቀድመው የተደረጉ ነገሮች እንደሆኑ ግልጥ ነው፤ ነገር ግን የጌታችንን ትንሣኤ ሳናከብር ሌላ ማክበር ስለሌብን
ነው፡፡
ተሻግረናል፡፡
የግብጽን ባርነት በነጻነት፣
የፈርኦንን ትእቢት በፈርኦን ሞት ተክተን ንሴብሆ ብለን የተሸጋሪዎችን መዝሙር ዘምረናል ዘፀ 16÷1፤ ሀገራችንን ወርሰን ‹‹ከቅዱሳን
ጋር አብረን ባላገሮች ነን እንጅ እንግዶችና መጻተኞች አይደለንም›› ብለን ተናግረል ኤፌ2÷19፤ አክሊለ ሦኩ ለጽድቅ አክሊል አብቅቶናል
2ጢሞ 4÷7፤ የእለተ ዐርብ ድካሙ ወደ ዘለዓለም እረፍት አሻግሮናል ማቴ 26÷45
ምስጋና ለእግዚአብሔር
ይሁን
ሚያዝያ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ
No comments:
Post a Comment