እስራኤል የሚያከብሯቸው ዘጠኝ ያክል በዓላት ያሏቸው ሲሆን በተለየ ሁኔታ ሦስት
ዐበይት በዓላት አሉ፤ እነርሱም፡- በዓለ መፀለት፣ በዓለ ፍሥሕ እና በዓለ ሰዊት፤ ናቸው ዛሬ ማየት ምፈልገው በዓለ ሰዊትን ነው፤ይህ
በዓል ፋሲካን ካከበሩ በኋላ በሃምሳኛው ቀን እንዲያከብሩት የታዘዘ በዓል ነው ‹‹ከሰንበት ማግስት ፍፁም ሰባት ሱባዔ ቁጠሩ እስከ
መጨረሻ ሰባተኛ ሰንበት ማግሥት ድረስ አምሳ ቀን ቁጠሩ አዲሱንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ›› ዘሌ 23÷16 አዲስ መሥዋዕት
ያቀርቡባት ዘንድ የተዘጋጀች አዲስ ቀን ናት ባለፈው በዓለ ፍሥሕን ሲያከብሩ ‹‹እንጀራውንም የተጠበሰውንም እሸት ለምለሙንም እሸት
የአምላካችሁን መሥዋዕት እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ›› ዘሌ 23÷14 ተብለው መታዘዛቸውን እናስታውሳለን፡፡
ከስሙም እንደምንረዳው በዓለ ሰዊት ማለት የእሸት በዓል ማለት ነው፤ አዲሱ እህል
ሲደርስ የምድሩን ፍሬ ቀዳምያት ለእግዚአብሔር የሚያስረክቡበት ቀን ነው ዓለም የሚድነው በቀዳማዊ ቃል ነውና ቀዳምያቱ ለእግዚአብሔር
ይገባ ነበር፤ ቀዳማዊ ቃል ሥጋን ለብሶ እስኪመጣ እና ቀዳማዊ ቃል የተዋሐደውን ሥጋ መሥዋዕት አድርገን በፊቱ እስክናቀርብ ድረስ
ሌላ ምን ይዘን ልንቀርብ እንችላለን፤