እስራኤል የሚያከብሯቸው ዘጠኝ ያክል በዓላት ያሏቸው ሲሆን በተለየ ሁኔታ ሦስት
ዐበይት በዓላት አሉ፤ እነርሱም፡- በዓለ መፀለት፣ በዓለ ፍሥሕ እና በዓለ ሰዊት፤ ናቸው ዛሬ ማየት ምፈልገው በዓለ ሰዊትን ነው፤ይህ
በዓል ፋሲካን ካከበሩ በኋላ በሃምሳኛው ቀን እንዲያከብሩት የታዘዘ በዓል ነው ‹‹ከሰንበት ማግስት ፍፁም ሰባት ሱባዔ ቁጠሩ እስከ
መጨረሻ ሰባተኛ ሰንበት ማግሥት ድረስ አምሳ ቀን ቁጠሩ አዲሱንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ›› ዘሌ 23÷16 አዲስ መሥዋዕት
ያቀርቡባት ዘንድ የተዘጋጀች አዲስ ቀን ናት ባለፈው በዓለ ፍሥሕን ሲያከብሩ ‹‹እንጀራውንም የተጠበሰውንም እሸት ለምለሙንም እሸት
የአምላካችሁን መሥዋዕት እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ›› ዘሌ 23÷14 ተብለው መታዘዛቸውን እናስታውሳለን፡፡
ከስሙም እንደምንረዳው በዓለ ሰዊት ማለት የእሸት በዓል ማለት ነው፤ አዲሱ እህል
ሲደርስ የምድሩን ፍሬ ቀዳምያት ለእግዚአብሔር የሚያስረክቡበት ቀን ነው ዓለም የሚድነው በቀዳማዊ ቃል ነውና ቀዳምያቱ ለእግዚአብሔር
ይገባ ነበር፤ ቀዳማዊ ቃል ሥጋን ለብሶ እስኪመጣ እና ቀዳማዊ ቃል የተዋሐደውን ሥጋ መሥዋዕት አድርገን በፊቱ እስክናቀርብ ድረስ
ሌላ ምን ይዘን ልንቀርብ እንችላለን፤
የምድሪቱን ፍሬ እጅ መንሻ አድርገን በፊቱ እንሠዋለት ዘንድ ስለሚገባ እሸቱ የሚቀርብበት
ይህ ቀን ለእግዚአብሔር የተለየ ቀን ነበር፡፡
ሰባት ሱባኤያትን ካከበሩ በኋላ እንዲያመጡት መታዘዙ አዲሱን ኪዳን የሚያቆምልን
መሥዋዕታችን ክርስቶስ የሱባዔ ፍጻሜ መሆኑን ለማስረዳት ነው፤ ያውም ደግሞ ሰባት ቁጥር በእብራውያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር መሆኑን
እንዳትዘነጉ፤ ‹‹እስመ ኁልቁ ሰብአቱ በኀበ እብራውያን ፍጹም ውእቱ፤ ሰባት ቁጥር በእብራውያን ዘንድ ፍጹም ቁጥር ነው›› እንዲል
(ሳዊሮስ ዘአንፆኪያ)
የክርስቶስ መምጣት በሱባኤ ደጅ ሲጠና የኖረ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ አለመሆኑን
ለመግለጥ በሱባኤያቸው መጨረሻ አዲሱን እሸት ያቀርቡ ነበር፡፡ አዲስነት ኃጢአት ያስረጀውን አዳምን አዲስ በማድረግ ነው እንጂ ያለዚያማ
እንዴት አዲስ መሥዋዕት ሊመጣ ይችላል፤ ስለዚህ አዲሱ መሥዋዕት ያለ ኃጢአት ሆኖ ስለ ኃጢአተኞች እንደ ቀድሞው በበግና በጊደር
ሥጋና ደም መሥዋዕትነት ሳይሆን ቀርቦ የማያውቀውን አዲሱን መሥዋዕት የራሱን ሥጋና ደም ከአሮን ልዩ በሆነ እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ
ሹመት ከአይሁድ ምኩራብ ውጭ ሆኖ የሚያቀርብ አዲስ ሊቀ ካህናት እንደሚመጣና አዲስ የሆነውንም መሥዋዕት ስለሁላችን እንደሚያቀርብ
የሚያሳይ በዓል ነበር፤
ሕዝቡ ሐዲሱን መሥዋዕት ማቅረብ የሚጀምሩት በዚህ ቀን ነበር ማለት ነው፤ አሮጌውን
መሥዋዕታቸውን የሚጨርሱት በፋሲካ ነው፤ አዲሱን ፋሲካ እንዳያከብሩ ፋሲካችን ክርስቶስ ገና አልተወለደላቸውም ስለዚህ እስከ በዓለ
ሰዊት ድረስ አዲሱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ይከለከሉና እንደ ገና ሰባት ሱባኤ ይገባሉ እሱን እንደጨረሱ በሃምሳኛው ቀን
(በሱባኤው ማግሥት) አዲሱን መሥዋዕት ይዘው ይታያሉ በሊቀ ካህናቸው አቅራቢነት ከአዲሱ መሥዋዕት መቅመስ የሚጀምሩት በዚህ በሃምሳኛው
ቀን ነበር ማለት ነው፤
እኛም አሮጌውን መሥዋዕት የተሰናበትነውና አዲሱን መሥዋዕት ማቅረብ የጀመርነው
ፋሲካችን ክርስቶስ በተሠዋባት በእለተ አርብ ቢሆንም ቅሉ የሐዲስ ኪዳን አገልጋዮች ሆነን የታየነው ግን በዚህ በሃምሳኛው ቀን ነው፡፡
እናም በዓለ ሰዊትን ለውጠን በዓለ ጰራቅሊጦስ ብለነዋል፤ የመንፈሱን እሸት የቀመስንበት እለት ነውና፡፡
በበዓለ መፀለት ጥምቀትን፣ በበዓለ ፍሥሕ ፋሲካን ማስገባታችንን ማስታወስ ይገባል
እነዚህ በዓላት በሐዲስ ኪዳን ለምናከብረውና ዘለዓለማዊ ዕረፍትን ለሚሰጠን በዓል ጥላ ነበሩ እንጂ እስከወዲያው ድረስ እረፍተ ሥጋን
እረፍተ ነፍስን መስጠት የሚችሉ በዓላት አልነበሩምና ፡፡
ጰራቅሊጦስ
ለዚህ ግሪክኛ ቃል መጽንኢ፣ መንጽሒ፣ ናዛዚ፣ ከሣቲ መሥተፍስሒ የሚል የግእዝ
ቃል አቻ ትርጉም ተሰጥቶታል፤ የሚያጸና የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋ፣ የተሠወረውን የሚገልጥ፣ ለነፍስ ደስታዋን የሚመልስ ማለት ነው፡፡
ይሄ ሁሉም በቅዱስ ወንጌል ስለ እርሱ የተባለውን መነሻ በማድረግ የተሰጠ ትርጓሜ ነው፤ ስለዚህ ስም አስቀድሞ በቅዱስ ወንጌል የነገረን
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስሙን በገለጠልን ጊዜ ስለ እርሱ የነገረን ግብሩ እንዲሁ እንደተረጎምነው ነው፤
በዚህ እለት ቤተ ክርስቲያን በእለተ ዕርገት ክርስቶስ ተስፋ ያስደረገላት መንፈስ
ቅዱስን ተቀብላ ደስታዋን ፍፁም አድርጋለች፤ እንደሰማነው ወደ ሰማይ ባረገበት እለት ‹‹አባቴ ተስፋ ያስደረገላችሁን አጽናኙን መንፈስ
እስከምልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ›› ሉቃ 24÷51 የሚል የተስፋ ቃል ሰጥቷቸው ነበርና ያን የተስፋ ቃል ለመፈጸም በአንድ
ቤት በአንድነት ሳሉ የተስፋውን ቃል ፈጸመላቸው፡፡ ጸጋውን ዐይናቸው እንድትመለከተው በእያንዳንዳቸው ራስ ላይ እንደ እሳት ላንቃ
እየሆነ የተከፋፈለ ልሳን ሲያርፍባቸው ይታያቸው ነበረ፡፡
የዚህ ቀን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምን ይመስላችኋል! ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው
በእለተ ዐርብ ሆኖ ሳለ ያለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነበር የተመሠረተችው ማለት ይቻላል? እስከዚህ ቀን ድረስ መንፈስ ቅዱስ የሌላት
ቤተ ክርስቲያን ነበረች ማለት ነው?
ነገሩ እንደዚያ አይደለም መንፈስ ቅዱስ የሌላት ሆና ለሃምሳ ቀናት የቆየች አይደለችም፤
መሠረቷም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንዲት ፈቃድ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሰው ልጆች የመጣባት እለት
ታስታውሳላችሁ አይደል፤ የእግዚአብሔር መላክ ወደ እኛ ተልኮ የመጣባት ች የምሕረት መጀመሪያ እለት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሰው ባሕርይ
መጥቶ የተሰጠባት እለት ናት ሉቃ 1÷28
በዚያውስ ላይ ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ውስጥ ሳሉ ገብቶ እፍ ካለባቸው በኋላ
በእስትንፋሱ ‹‹ንሥኡ መንፈሰ ቅዱሰ›› ብሎ መንፈስ ቅዱስን አልሰጣቸውምን? እውነት ነው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት
ጊዜ ጀምሮ ያለ መንፈስ ቅዱስ የቆየችበት ጊዜ የላትም ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሲሆን ጸጋው ብዙ ነውና በመጀመሪያ
(በምሴተ ሐሙስ) መንፈሰ ልደትን ሰጣቸው ማለትም ሥጋውና ደሙ ሳይሰዋ እንደተሰዋ አድርጎ ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋየ ነው ከዚህ
ጽዋዕ ጠጡ ይህ ስለ ሐዲስ ኪዳን የሚፈሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› ማቴ 26÷26 ብሎ እንደሰጣቸው ማየ ገቦንም ሳይፈስ እንደ
ፈሰሰ አድርጎ ከእርሱ ጋር እድልፋንታ እንዲኖራቸው የሚያደርገውን ህጽበተ እግር በፈጸመላቸው ጊዜ ‹‹አባ አባት ሆይ›› ብለው የሚጣሩበትን
የልጅነትን መንፈስ ሰጥቷቸዋል፡፡
በዝግ ቤት ውስጥ ገብቶ ‹‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ›› ባላቸው ጊዜ ኃጢአትን
ይቅር የሚሉበትን ለመላእክት እንኳን ያልተቻለውን ኀብተ ክህነትን ሰጣቸው፤ ለዚህም ነው ‹‹መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ
የሾመባት….›› ሥራ 20÷28 ተብሎ የተጻፈው፡፡
ዛሬ ደግሞ የአገልግሎት መንፈስን ሰጣቸው፤
No comments:
Post a Comment