ክብራችን
ወዴት ሄደ?
ከስደት
ለተመለሰ ሕዝብ፣ በፈርዖናዊ አገዛዝ ወገቡ ለጎበጠ ወገን ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ምንኛ ከባድ ነው!? ዳታን እና አቤሮንን ምድር
እንድትከዳቸው፣ ደቂቀ ቆሬን እሳት ከሰማይ ወርዳ እንድታቃጥላቸው፣ የሰማርያን ሰዎች ረሀብ እንዲፈጃቸው ምክንያት የሆነው የእግዚአብሔር
ቅያሞት ነው፤ እግዚአብሔር ሲቀየም ሥነ ፍጥረት ሁሉ ሰውን ይቀየመዋል፤ እንኳን ሌላው ፍጥረት ይቅርና ሰው በራሱ የተፈጥሮ ሕጉን
ጠብቆ መሄድ አይችልም፡፡
እስራኤል
ከፈጣሪው ጋራ በተጣላበት ወራት ለተወለደው ኅጻን እናቱ ስም ስታወጣለት ‹‹ኢካቦድ›› አለችው፡፡ በወቅቱ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ
የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለች፤ ካህናቱም አብረው ተማርከዋል፤ የእስራኤል ጎበዛዝቶች በጦርነቱ ድል ሆነው አፍረው ተመልሰዋል፤
እስራኤልን ለዓርባ ዓመታት የመገበው ካህን ዔሊ ከመንበሩ ወድቆ ተንቆጫቁጮ ሞቷል፤ የሊቀ ካህናቱ መንበር ያለ ሰው ቀርቷል፤ ስለዚህ
ልጁን ከዚህ የተሻለ ሌላ ስም ምን ብላ ልታወጣለት ትችላለች?
በእኛስ
ሀገር ዛሬ ለሚወለድ ኅጻን ስም አውጡ ብትባሉ ማን ልትሉት ትችላላችሁ?? በውኑ ክብር ከእኛ አልራቀም? በረከትስ አልጎደለንም?
ኃያላኖቻችን በመንፈሳዊ ሰልፍ ቢሰለፉ ድል መንሣት ይችላሉ? የትኛው ሕዝብ ነው በሀዘን ያልተዋጠ በእውነት ምንድነው እየሆነ ያለው
በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ማነው የእግዚአብሔር ክብር እንዲጎድለን እየሠራ ያለው? ሲጀመር አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ክብር ሊርቀው
የሚችለው ክብር ከቤተ መቅደሱ ሲጠፋ ነው፡፡ የሀገርም ሆነ የሕዝብ ክብር የሚመነጨው ከቤተ መቅደሱ ነውና፡፡
እስራኤልን
‹‹ኢካቦድ›› ያሰኘው ክብር በካህናቱ ምክንያት ከቤተ መቅደሱ በመጥፋቱ ነው፡፡
ቤተ
መቅደሱ ካልተፈራ ሀገር አትፈራም ካህናቱ ካልከበሩ የሀገር ሽማግሌዎቹ አይከብሩም፤ ካህናቱ ጽድቅን ለብሰው ኃጢአትን አሸንፈው ካልነገሡ
ንጉሥ በሀገሪቱ አይነግሥም የንጉሡ ሰራዊት አያሸንፍም፡፡
ቤተ
ክርስቲያኒቱ ክብር ከጎደላት ሀገሪቱ ክብር ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም መፈራትና መወደድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሹማምንት ዘንድ ሲኖር
በሀገሪቱም ሹማምንት ዘንድ ሊኖር ይችላል፡፡
ትውልዱ
የሚቀበለው ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት የሚችል አባት አጣን እኮ! ምንድነው እንደዚህ በሰው ድርቅ እንድንመታ ያደረገን?
በየመንገዱ
ድንጋይ መወራወር በዝቶ ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያዊው ደምቶ እያየን ስናዝን በዓየር ካልሆነ በምድር መጓዝ አልችል ብለን እየተቸገርን
ሰንብተን የዚህን መፍትሔ አምጣልን ብለን ጸሎታችንን ሳንጨርስ ቅዱሱ ጉባኤያችን ድንጋይ መወራወር በዝቶበት ስናየው በጣም ያሳዝናል፡፡
አንድ
ሲኖዶስ መፈራትን፣ መወደድን፣ ባለሟልነትን ገንዘብ ማድረግ አለበት፤ በመናፍቃን ዘንድ መፈራትን፣ በምዕመናን ዘንድ መወደድን፣ በእግዚአብሔር
ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት አለበት፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን እውነት እውነቱን ስንነጋገር ማኅበረ ቅዱሳንን እንጅ ሲኖዶሱን የሚፈራ
መናፍቅ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ታላቁ የሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሊቃውንት ጉባኤ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ ያላገኘውን
መፈራት እና መወደድ አንድ የወጣት ጉባኤ ሲያገኝ ክብራችን ወዴት ሄደ ተብሎ ክብራችንን ፍለጋ መሄድ ያለብን ይመስለኛል እንጅ አሁን
ያለንን ጉልበትና ሥልጣን ተጠቅመን ክብራችንን ማስመለስ የምንችል አይመስለኝም፤ ክብር ከሰማይ ነውና፡፡
ብፁዓን
አባቶቻችን ሆይ! ይሄን ትውልድ ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት መርታችሁ የምታስገቡበት ቁልፉ ያለው በእጃችሁ ነው፤ መግቢያው ጠፍቶበት
የሚባዝነውን ሕዝባችሁን እናንተው ራሳችሁን ሳታጠሩ ቀርታችሁ መግቢያ ብታሳጡት ፍርድ ከሰማይ ይጠብቃችኋል፡፡ እናንተ የረገጣችሁትን
መሬት ስሞ የጨበጣችሁትን መስቀል ተሳልሞ በደስታ የሚኖር ሕዝብ ነበራችሁ አሁን ግን ነገሩ እየተለወጠ ነው፤ በየቦታው በእናንተ
ላይ ምሬት የሚያሰማ፣ በየቤቱ እናንተን የሚያማ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡
እውነት
የሚነግረው፣ ክርስትናን በተግባር የሚያሳየው፣ ተሻግሮ የሚያሻግረው መሪ ይፈልጋል፡፡ እንደምታዩት መሻገሪያው ሁሉ ታጥሮ በብዙ ነገሮች
ተከቦ ነው የሚኖረው ቀድማችሁ ስለሕዝቡ መጸለይ ያስፈልጋል፤ ሁሉም በእናንተ ጸሎት እንደሚከናወንለት ያምናል፡፡
የሊቃነ
ጳጳሳት የኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ ማለት የኒቅያ የኤፌሶን ጉባኤ ነው፤ ርዕዮተ ዓለም በተቀየረ ቁጥር የማይቀየር ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ
ጉባኤ በመሆኑ በሽህ የሚቆጠሩ ዓመታትን በሕያውነት መቆየት ይችላል፡፡
እኔ
አሁንም እኛ እናንተን እንናገር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራውም ጉባኤ ሀሳብ እንሰጥ ዘንድ አግባብ አይደለም፤ ነገር ግን ሕዝቡ
ከመንሾካሾክ አልፎ ስለእናንተ በጩኸት እያወራ ነው እናንተ ግን በዓመት ሁለት ጊዜ የምታነሡት አጀንዳ ሁልጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን
ጉዳይ ነው፤ እናንተ ሙሴ ለመሆን ከበቃችሁ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እጃችሁን የሚደግፍ እንደ አሮንና ሖር
ያለ ትውልድ ነው፡፡
ቤተ
ክርስቲያናችን ብዙ ወቅታዊ ጉዳዮች እያሉባት ከሃይማኖት የወጡ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ፣ የምዕመኑ ቁጥር እየተመናመነ፣ በአንድ
በኩል አክራሪ እስልምና በሌላ በኩል ፕሮቴስታንት ተሐድሶ በሚል ስም ገብቶ እየገዘገዛት አሁንም የቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ ማኅበረ
ቅዱሳን ላይ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡
የእናንተን ውሳኔ የሚሹ ብዙ ዘመኑ የወለዳቸው ችግሮች አሉ እኮ! ስደተኛና
መደበኛ የሚባል ሲኖዶስ የተፈጠረው፣ በቦርድ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት የተፈጠሩ፣ አብነት ትምህርት ቤቶች የተመናመኑ፣ ገዳማቱ
የመናንንያን እጥረት ገጥሟቸው ራሳቸው ከሰው ተለይተው የመነኑ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ በብዛት የተሰረቁ፣ ምዕመናን ከሥጋው ከደሙ የራቁ
በዚሁ እናንተ ቤተ ክርስቲያኒቱን በኃላፊነት በተረከባችሁበት ዘመን ነው፡፡
ብፁዓን
አባቶቻችን ሆይ! ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በእጃችሁ ነው ያለው አንድ ሁኑና ትውልዱን አድኑት የቅዱስ ሲኖዶስ አለመስማማት
በሀገር ላይ አለመስማማትን ያመጣል፤ የአባቶቻችን ክብር በትውልዱ ልብ ውስጥ መቀነስ የሀገርን ክብር ይቀንሳል፡፡
መናፍቃንን
ስትገሥፁ እንጅ እርስ በእርሳችሁ መሰዳደባችሁን ልጆቻችሁ መስማት የለብንም፤ ነውርና ነቀፋ የሌለባት ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን
መትጋት ያስፈልጋችኋል፡፡
ክብራችን
ይመለስልን!፡፡
No comments:
Post a Comment