>

Wednesday, 27 March 2019


መጻጉዕ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ተሰቅሎ ዓለምን ከማዳኑ አስቀድሞ በለመለመ ሳር ትምህርቱ በጠራ ውኃ ተዓምራቱ ሰዎችን እየፈወሰ የባሕርይ አምላክነቱን በሥራው እያስመሰከረ ምድርን ዞረ፤ በተለይም የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ካስመሰከረ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ ድል የነሳውን ሰይጣን በከተሞችም እያሳደደው ማዳኑን ቀጠለ፤ በዚህ ሰዓት ከፈወሳቸው ሕሙማን መካከል እንደ መጻጉዕ ደዌ የፀናበት ሰው በቅዱስ ወንጌል አልተመዘገበልንም፤ ይህ ሰው እንደ ሌሎቹ በሽተኞች ከባለመድኃኒቶች ዘንድ ስለመሄዱ አልተነገረለትም፣ የጉባኤው ቦታ በሰዎች በመጨናነቁ ምክንያት መግቢያ እንኳን ቢያጡ ጣራውን አንሥተው ወደ ክርስቶስ ፊት የሚያቀርቡ ወዳጆችም አልነበሩትም እሱ እራሱ እንደገለጠው ሰው ባጠገቡ አልነበረምና ዮሐ 5፥5

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማን የእግዚአብሔርን ምሕረት ደጅ በሚጠኑባት ቤተ ሳይዳ ተገኘ፤ ቤተ ሳይዳ አምስት መመላለሻ የነበራት የሕሙማን ስፍራ ናት፤ ታመው ይመጡባታል እንጅ ታመው የማይመለሱባት፤ እየተጨነቁ መጥተው እየተደሰቱ የሚመለሱባት፤ በልመና ገብተው በምስጋና የሚመለሱባት፤ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚገለጥባት ናት- ቤተ ሳይዳ፡፡ በዚህ ስፍራ የሚድኑ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ ውኃውን በባረከው ጊዜ ቀድሞ የሚገባ አንድ ድውይ ብቻ ነው የሚድነው፤ ለመዳን ጥቂት ጉልበት እና የሚያግዝ ሰው ያለው ቀድሞ ይፈወስ ነበር፤

 ዮሐንስ ወንጌላዊ ግብሩን እንጅ ስሙን ያልገለጠው ሕሙም ለብዙ ቀናት በዚህ የምሕረት ስፍራ ተኝቶ ቆይቷል ሌሎቹ እየተፈወሱ ሲመለሱ እያየ ከነደዌው ዘመናትን አስቆጠረ፤ ቀድሞ እንዳይገባ ጉልበቱን ደዌ አድቅቆታል፤ ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመቱ ነውና መዳን እያማረው ሳይድን ዘገየ፡፡

በዚህ ሁኔታ ሳለ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው፤ እስኪያነጋረው ድረስ አዳኙ እንደመጣለት አላወቀም፤ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ሲጠይቀውም ለመዳን የሚያበቃውን ሁኔታ እንዲያመቻችለት ይመስላል እስካሁን ያልዳነበትን ምክንያት እየዘረዘረ መዳን የሚፈልግ መሆኑን አስረዳ፤ ምን ያድርግ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበርና ከነዚህ አንዱን ቢያዝዝልኝ አንሥቶ ወደ ባሕሩ ያስገባኝ እና እድናለሁ አለበለዚያም ደግሞ ጎልማሳ ነውና አንስቶ ወደ መጠመቂያው ያደርሰኛል ብሎ ጎመጀ እንጅ ድምፁን ሰምቶ የሚያድነው እርሱ እንደሆነ ማወቅ አልቻለም፡፡ እርሱ ግን መን እንደሚፈልግ ካረጋገጠ በኋላ ‹‹ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው በቅጽበትም ተረፈ ደዌ ሳይኖርበት ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ ወጣ፡፡

ይህ ሰው የሁላችንም አባት አዳም ነው፤ ወንጌላዊው ግብሩን እንጅ ስሙን ያልጠራው ለምን ይመስላችኋል? ደዌ የፀናበት አዳማዊ ሕይወትን የሚወክል ስለሆነ ነው፡፡ የመጠመቂያው ስፍራ ጵሩጳጥቄ (የመዋኛ ስፍራ) የተባለችው ኦሪት ናት፤ አምስት መመላለሻ ነበራት ማለት አምስት ክፍል ሁና መሠራቷን ያስረዳል

1.     ዘፍጥረት                                       4. ዘኁልቁ                       

2.    ዘፀአት                                         5. ዘዳግም ናቸው፡፡

3.    ዘሌዋውያን

እነዚህ አምስቱ ሕግጋት አምስት የመሥዋዕት ዓይነቶች ነበሯቸው፤

1.     የሚቃጠል መሥዋዕት                          4. የበደል መሥዋዕት

2.    የደኅንነት መሥዋዕት                           5. የእህል ቁርባን የሚባሉት ናቸው፡፡

3.    የኃጢአት ማሥተስረያ መሥዋዕት

በዚህ ሁሉ ሥርዓቷ ሕጓ አንዱን አዳምን ማዳን አለመቻሏን ተመልከቱልኝ፡፡ ነገር ግን በውኃው ዳር ለተቀመጡ በሽተኞች አንዳንድ ሰው ይፈወስ እንደነበረ መነገሩ በኦሪት ፍፁም መዳን ባይሰጥም በመልእክተኞች የሚደረግ ጥቂት ጥቂት የእግዚአብሔር ምሕረት ይታይ ነበር መካኖች ወልደዋ፣ ሕዝቡ ከባርነት ቤት ወጥቷል፣ ባሕር ተከፍሏል፣ ከነዘር እባብ መርዝ ድኗል እንዲህ የመሳሰሉ ትንንሽ ተዓምራቶች አለመከልከላቸውን መናገር ነው ነገር ግን የአዳምን ባሕርይ መፈወስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ካህና በሹመታቸው በሚያቀርቡት መሥዋዕታቸው ነቢያቱ በሚፀልዩት ጸሎታቸው አዳምን ማስታረቅ አልቻሉም ለዚህ ነው መጻጉዕ - አዳም  ‹‹ሰው የለኝም›› ብሎ የተናገረው እውነቱን ነው! ተስፋ ያደረጋቸው ጻድቃን ልጆቹ ባሕርዩን ከመርገም አላዳኑለትም ሁሉንም ሞት ገዛቸው እንጅ ሮሜ 5 ለአዳም ሰው ቢኖረው ኖሮ እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ? እግዚአብሔርም እንደ ቀድሞው በመልአክ ሊያድነው አልፈለገም እራሱ ሰው ሁኖ ወደ እርሱ በሥጋ መጣ፡፡

ይገርማል! አምስት እርከኖች ወደነበሯት የመጠመቂያ ስፍራ መጣ የታመመውን ሰውም ቀርቦ ‹‹ልትድን ትወዳለህን›› ብሎ ጠየቀው መባሉ ለምን ይመስልሃል? አባታችን አዳም ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ አምስቱም ኅዋሳቱ በድለዋል፤ በዚህ ሰዓት እግዚአብሔር የኃጢአት ደዌ ወደ ፀናበት አዳም መጥቶ ‹‹አይቴ  ሀሎከ አዳም›› ማለቱ እና ዛሬ በመጻጉዕ ታሪክ ላይ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ የጠየቀው ጥያቄ ተነጻጻሪ ነው፤ ሁለቱም ሰውን ለማዳን ካለው ጥልቅ ፍላጎት የተነሣ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሰውን የሚያድነው ለመዳን ያለውን ፍላጎት አይቶ እንጅ ሁሉን ቻይነቱ የሰውን ፈቃድ አትከለክልበትም ሰው ባለ አዕምሮ ፍጡር ነውና ሞትንም ሆነ ሕይወትን የመምረጥ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ ቀርቦ ጠየቀው ማለት ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ሰውን በባሕርይ መሰለው ማለት ነው፤ መጻጉዕ የሚያድነውን ጌታ አለማወቁ ስለምን ነው ቢሉ ለጊዜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ ከሰዎች እንዳንዱ ሆኖ በእለተ ዐርብ ተሰቅሎ እስኪያድነን ድረስ አይሁድ ዕሩቅ ብዕሲ ወልደ ዮሴፍ (ሎቱ ስብሐት) ሲሉት የነበሩ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡

በፈወሰውም ጊዜ ፈውሱ ከባለ መድኃኒቶች ልዩ ነው ብለናል ምክንያቱም ባለ መድኃኒቶች የፈወሱት ሰው በዕለቱ ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ የሚያስኬድ ዐቅም አያገኝም በዚያውም ላይ ባለመ ድኃኒቶች የጠጣበትን ጽዋዕ የተኛበትን አልጋ የእኛ ይገባል እያሉ ያስቸግራሉ እሱ ግን እንዲህ አይደለም፤ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው እንጅ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን እስኪያድነው ድረስ ብዙ ዘመናትን በደዌ ሥጋ በደዌ ነፍስ እንደተያዘ መቆየቱ ግልጽ ነው ነገር ግን በእለተ ዐርብ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ፈጥኖ የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ነፍሳትን ወደ መዳን ጠራቸው እንጅ ከማዳን አልዘገየም አንድ ጊዜ ተወለደ፣ አንድ ጊዜ ሞተ፣ አንድ ጊዜ ወደ ሲኦል ወረደ ለዘለዓለም ነፍሳትን ሁሉ ወደ ገነት መለሰ የሰውን ባሕርይ ወደ የማነ እግዚአብሔር አሳረገ፡፡

መጻጉዕ መዳኑን ሳያዩ በሰንበት ስለመዳኑ ይካሰሱ የነበሩ አይሁድ እንደነበሩ ሁሉ በአዳም መዳንም የተቃወሙ አጋንንት ነበሩ፡፡

መልካም የመዳን ሳንምንት 


Thursday, 7 March 2019


የተወደደ ፆም የትኛው ነው?

በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ፆም እንዳለ ሁሉ የተነቀፈ ፆምም አለ፤ የሚያድን ፆም እንዳለ ሁሉ የማያድን የማይረዳ ፆምም አለ፤ በዚህ ምድር በሥጋም ሆነ በነፍስ የሚያድኑ ነገሮች ሁሉ ሊያድኑ የሚችሉት የሚቀበሏቸው ሰዎች ለመዳን ካላቸው ፍላጎት የተነሣ በሚያደርጉት ዝግጅት ነው፤ ማንኛውም መድኃኒት ከመወሰዱም በፊትም ሆነ በኋላ የአጠቃቀም መመሪያ አለው ያንን ሳያሟሉ ቢወስዱት ሌላ ጉዳት ሌላ በሽታ ሊያስከትል ይችላል፡፡

በሐኪሙ ትዕዛዝ የማይስማማ ሰው ከበሽታው ጋር ተስማምቶ መተኛት ይገባዋል እንጅ እሱም ሰው እኔም ሰው ብሎ ያለ አግባብ የወሰደው እንደሆነ ያለ ፈቃዱ ለመታከም የሚያስችል ከባድ ደዌ ያድርበትና አንደበቱን ዘግቶ ዐይኑን ጨፍኖ በሰዎች እርዳታ ውስጥ እንዲወድቅ ያስገድደዋል፡፡

በመንፈሳዊውም እንዲሁ ነው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተሾሙ መምህራን ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን መድኃኒት እያዘጋጁ የሚያቀብሉ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ቁርባኑ ያድናል፤ ፆሙ ጸሎቱ ይታደጋል፤ ጠበሉ ይፈውሳል፤ መስቀሉ አጋንንትን ያርቃል፤ የቤተ ክርስቲያኑ መዓዛ ዕጣን የነፍሳችንን መዓዛ ብቻ ሳይሆን የዓለማችንንም መዓዛ መለወጥ የሚችል ሱራፊ መልአክ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር የሚያሳርገው መሥዋዕት ነው ራዕ 8፥3  ነገር ግን ከመቀበላችን አስቀድሞ ከዚያም በኋላ ልናከብረው የሚገባ ትዕዛዝ አለው እንዲሁ አይደለም ያድናል ያልነው፡፡ አሁን ስለ ፆም ስለሆነ ያነሣነው እሱን ለይተን እናያለን እንድንበት ዘንድ የሚያስችለን ፆም የትኛው ነው?

1.     ፍቅር ያለው ፆም ሲሆን ነው

ለማንኛውም መንፈሳዊ ነገር ሕይወቱ ፍቅር ነው፤ ፍቅር የሌበት መንፈሳዊ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመድረስ ዐቅም የለውም፤ በተለይ ደግሞ ፆም ያለ ፍቅር እንዳይቀርብ ተከልክሏል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወሶበሂ ትጸውሙ ቅብዑ ርዕሰክሙ፤ በምትፆሙበት ጊዜ ራሳችሁን ተቀቡ›› ማቴ 6፥17ብሎ አስተምሯልና፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ‹‹ተቀቡ›› የተባለው ፍቅርን እንጅ ሌላ ቅብዓት አይደለም በትርጓሜ ወንጌልም የተቀመጠው ‹‹ቅብዕ ኢይርሀቀ ቅብዕሰ ፍቅረ ደቂቀ እጓለ እመሕያው፤ ቅቤ አይራቅህ ቅቤም የተባለው የሰው ልጅ ፍቅር ነው›› ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

መኪና ያለው ሰው ያለ ዘይት እንዴት ሊነዳው ይችላል? ነገሥታቱስ ያለ ቅብዓ ዘይት እንዴት ሊነግሡ ይችላሉ? 1ሳሙ 15፥13 ነፍሳችንም እንዲሁ ናት በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር ትደርስ ዘንድ ሰማያዊት መንግሥትንም ትቀበል ዘንድ ቅብዓ ዘይቱ ፍቅር ነው፡፡ ሴት በባሏ ዘንድ የተወደደች ትሆን ዘንድ የምትቀባ ከሆነ ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ መወደድን እንድታገኝ ልትቀባ አይገባትምን? ያለ ፍቅር ፆም የለም፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው ‹‹እነሆ ለጥልና ለክርክር ትፆማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ…… እኔ የመረጥሁት ፆም ይህ ነውን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቁ ዘንድ የተገፉትንስ ነጻነት ትሰጡ ዘንድ አይደለምን? እንጀራን ለተራበ ትቆርሱ ዘንድ ስደተኛዎቹን ድሀውን ብታገኝ ወደ ቤትህ ታስገባው ዘንድ እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ የተራቆተውንም ታለብሰው ዘንድ አይደለምን?›› ኢሳ 58፥4-7 በዚህ ንባብ ውስጥ ሁሉም የፍቅር መልዕክት ያላቸው ናቸው ስለዚህ ጾም ያለ ፍቅር ከንቱ ነው ማለት ነው፡፡

 አስተውሉ! አሞራ ክንፉን አጥፎ መብረር አያምረውም፤ ፍቅር የሌላት ነፍስም ይህን ዓለም ለቆ ወደ ሰማይ የሚመሰጥ ልብ ሊኖራ አይችልም እና ማስተካከል ይገባናል፡፡

2.    ግብዝነት የሌለበት ፆም መሆን አለበት

የግብዞች ፆም በሰዎች ዘንድ እንዲታወቅ እንጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ምንም ይሁን ምን የማይጨነቁለት ፆም ነው፡፡ ፊታቸውን ቋጥረው አጠውልገው ይታያሉ፤ ራሳቸውን አጽድቀው ሌላውን ይነቅፋሉ፤ ሕግ መፈጸማቸውን እንጅ ለእግዚአብሔር የተመቸ ፆም መሆኑን አያዩትም እየሰረቁ እያጭበረበሩ ግብር እንደሚከፍሉ ነጋዴዎች ያሉ ናቸው፤ ግብር በመክፈል በመንግሥት ዘንድ የሚወደሱ የማይገባ ዕቃ ለሕዝብ የሚያቀርቡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የተጭበረበረ የፆም ግብር ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ፡፡ ይሄ ግብዝነት ነው፤

ቅዱስ ሉቃስ እንደመዘገበው ግብዝ ፈሪሳዊ ያለ ፆመኛ ሰው በሚፆመው ፆም አንዳች የሚያተርፍ እንዳይመስለው ይልቁንም ባልእንጀራው ጸድቆ ሲመለስ ባዶውን ይመለሳል እንጅ ሉቃ 18፥10-14 በሥውር ለሚያየን አባት ሰማያዊ ዋጋ እንድንቀበልበት ሁነን መፆም ያስፈልገናል፤ ፆም ምድራዊ ዋጋ ሊያሰጥ የሚችለው እንደ አስቴር አስ 4፥13 እንደ ነነዌ ሰዎች ዮና 3፥1-9 አደጋ በታዘዘበት ወቅት ሊሆን ይችላል እንጅ የምንፆመው በባሕርያቸው መብል መጠጥ የማይስማማቸው መላዕክትን መስለን መንግሥቱን ለመውረስ ነው፡፡ ለምድራዊ ሀሳባችን መሳካት ብቻ ፆምን የምንጠቀምበት ከሆነ ወደ ግብዝነት ሕይወት ተሸጋግረናል ማለት ነው፡፡

3.    ንስሐ፣ ትሕትና፣ ፈቃደ ሥጋን መተው በፆማችን ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው፤ የነነዌ ሰዎች ንስሐ ዮና 3፥1-9 የነቢዩ ዳንኤል ኑዛዜ ዳን 9፥1  የሠለስቱ ደቂቅ ፈቃደ ሥጋን መተው ዳን 1፥8-16 እነሱንም ሕዝቡንም ለመዳን አብቅቷቸዋል፤ እኛም ስንፆም በተሰበረ ልብ፣ በተዋረደ መንፈስ ሁነን ልንፆም ይገባናል፡፡

እንዲህ ያደረግን እንደሆነ ፆማችን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ይሆናል፤ ምድራችንን ያድናታል፣ ጠበብቶቻችን ጥበብን ያፈልቃሉ ገዥዎቻችን ሁሉን በሰላም ይመራሉ ሕዝቡ ከሚያስገብሩት ክፉ መሪዎች እጅ ነጻ ይወጣል ቤተ ክርስቲያን ክብሯን እንደ ጠበቀች ትኖራለች መንፈስ ቅዱስ በሚፆምና በሚጸልይ ሰውነት እንጅ ለመብል ለመጠጥ በሚጎመጁ ሰዎች ላይ አያድርም፡፡