የተወደደ ፆም የትኛው ነው?
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በእግዚአብሔር
ዘንድ የተወደደ ፆም እንዳለ ሁሉ የተነቀፈ ፆምም አለ፤ የሚያድን ፆም እንዳለ ሁሉ የማያድን የማይረዳ ፆምም አለ፤ በዚህ ምድር
በሥጋም ሆነ በነፍስ የሚያድኑ ነገሮች ሁሉ ሊያድኑ የሚችሉት የሚቀበሏቸው ሰዎች ለመዳን ካላቸው ፍላጎት የተነሣ በሚያደርጉት ዝግጅት
ነው፤ ማንኛውም መድኃኒት ከመወሰዱም በፊትም ሆነ በኋላ የአጠቃቀም መመሪያ አለው ያንን ሳያሟሉ ቢወስዱት ሌላ ጉዳት ሌላ በሽታ
ሊያስከትል ይችላል፡፡
በሐኪሙ ትዕዛዝ የማይስማማ ሰው
ከበሽታው ጋር ተስማምቶ መተኛት ይገባዋል እንጅ እሱም ሰው እኔም ሰው ብሎ ያለ አግባብ የወሰደው እንደሆነ ያለ ፈቃዱ ለመታከም
የሚያስችል ከባድ ደዌ ያድርበትና አንደበቱን ዘግቶ ዐይኑን ጨፍኖ በሰዎች እርዳታ ውስጥ እንዲወድቅ ያስገድደዋል፡፡
በመንፈሳዊውም እንዲሁ ነው፤ በቤተ
ክርስቲያኒቱ የተሾሙ መምህራን ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን መድኃኒት እያዘጋጁ የሚያቀብሉ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ቁርባኑ ያድናል፤ ፆሙ
ጸሎቱ ይታደጋል፤ ጠበሉ ይፈውሳል፤ መስቀሉ አጋንንትን ያርቃል፤ የቤተ ክርስቲያኑ መዓዛ ዕጣን የነፍሳችንን መዓዛ ብቻ ሳይሆን የዓለማችንንም
መዓዛ መለወጥ የሚችል ሱራፊ መልአክ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር የሚያሳርገው መሥዋዕት ነው ራዕ 8፥3 ነገር ግን ከመቀበላችን አስቀድሞ ከዚያም በኋላ ልናከብረው የሚገባ ትዕዛዝ
አለው እንዲሁ አይደለም ያድናል ያልነው፡፡ አሁን ስለ ፆም ስለሆነ ያነሣነው እሱን ለይተን እናያለን እንድንበት ዘንድ የሚያስችለን
ፆም የትኛው ነው?
1. ፍቅር ያለው ፆም ሲሆን ነው
ለማንኛውም መንፈሳዊ ነገር ሕይወቱ
ፍቅር ነው፤ ፍቅር የሌበት መንፈሳዊ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመድረስ ዐቅም የለውም፤ በተለይ ደግሞ ፆም ያለ ፍቅር እንዳይቀርብ
ተከልክሏል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወሶበሂ ትጸውሙ ቅብዑ ርዕሰክሙ፤ በምትፆሙበት ጊዜ ራሳችሁን ተቀቡ›› ማቴ 6፥17ብሎ
አስተምሯልና፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ‹‹ተቀቡ›› የተባለው ፍቅርን እንጅ ሌላ ቅብዓት አይደለም በትርጓሜ ወንጌልም የተቀመጠው
‹‹ቅብዕ ኢይርሀቀ ቅብዕሰ ፍቅረ ደቂቀ እጓለ እመሕያው፤ ቅቤ አይራቅህ ቅቤም የተባለው የሰው ልጅ ፍቅር ነው›› ተብሎ ተተርጉሟል፡፡
መኪና ያለው ሰው ያለ ዘይት እንዴት
ሊነዳው ይችላል? ነገሥታቱስ ያለ ቅብዓ ዘይት እንዴት ሊነግሡ ይችላሉ? 1ሳሙ 15፥13 ነፍሳችንም እንዲሁ ናት በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር
ትደርስ ዘንድ ሰማያዊት መንግሥትንም ትቀበል ዘንድ ቅብዓ ዘይቱ ፍቅር ነው፡፡ ሴት በባሏ ዘንድ የተወደደች ትሆን ዘንድ የምትቀባ
ከሆነ ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ መወደድን እንድታገኝ ልትቀባ አይገባትምን? ያለ ፍቅር ፆም የለም፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው
‹‹እነሆ ለጥልና ለክርክር ትፆማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ…… እኔ የመረጥሁት ፆም ይህ ነውን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ
የቀንበርንስ ጠፍር ትለቁ ዘንድ የተገፉትንስ ነጻነት ትሰጡ ዘንድ አይደለምን? እንጀራን ለተራበ ትቆርሱ ዘንድ ስደተኛዎቹን ድሀውን
ብታገኝ ወደ ቤትህ ታስገባው ዘንድ እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ የተራቆተውንም ታለብሰው ዘንድ አይደለምን?›› ኢሳ 58፥4-7
በዚህ ንባብ ውስጥ ሁሉም የፍቅር መልዕክት ያላቸው ናቸው ስለዚህ ጾም ያለ ፍቅር ከንቱ ነው ማለት ነው፡፡
አስተውሉ! አሞራ ክንፉን አጥፎ መብረር አያምረውም፤ ፍቅር የሌላት ነፍስም
ይህን ዓለም ለቆ ወደ ሰማይ የሚመሰጥ ልብ ሊኖራ አይችልም እና ማስተካከል ይገባናል፡፡
2. ግብዝነት የሌለበት ፆም መሆን አለበት
የግብዞች ፆም
በሰዎች ዘንድ እንዲታወቅ እንጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ምንም ይሁን ምን የማይጨነቁለት ፆም ነው፡፡ ፊታቸውን ቋጥረው አጠውልገው ይታያሉ፤
ራሳቸውን አጽድቀው ሌላውን ይነቅፋሉ፤ ሕግ መፈጸማቸውን እንጅ ለእግዚአብሔር የተመቸ ፆም መሆኑን አያዩትም እየሰረቁ እያጭበረበሩ
ግብር እንደሚከፍሉ ነጋዴዎች ያሉ ናቸው፤ ግብር በመክፈል በመንግሥት ዘንድ የሚወደሱ የማይገባ ዕቃ ለሕዝብ የሚያቀርቡ ሰዎች እንዳሉ
ሁሉ የተጭበረበረ የፆም ግብር ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ፡፡ ይሄ ግብዝነት ነው፤
ቅዱስ ሉቃስ
እንደመዘገበው ግብዝ ፈሪሳዊ ያለ ፆመኛ ሰው በሚፆመው ፆም አንዳች የሚያተርፍ እንዳይመስለው ይልቁንም ባልእንጀራው ጸድቆ ሲመለስ
ባዶውን ይመለሳል እንጅ ሉቃ 18፥10-14 በሥውር ለሚያየን አባት ሰማያዊ ዋጋ እንድንቀበልበት ሁነን መፆም ያስፈልገናል፤ ፆም
ምድራዊ ዋጋ ሊያሰጥ የሚችለው እንደ አስቴር አስ 4፥13 እንደ ነነዌ ሰዎች ዮና 3፥1-9 አደጋ በታዘዘበት ወቅት ሊሆን ይችላል
እንጅ የምንፆመው በባሕርያቸው መብል መጠጥ የማይስማማቸው መላዕክትን መስለን መንግሥቱን ለመውረስ ነው፡፡ ለምድራዊ ሀሳባችን መሳካት
ብቻ ፆምን የምንጠቀምበት ከሆነ ወደ ግብዝነት ሕይወት ተሸጋግረናል ማለት ነው፡፡
3. ንስሐ፣ ትሕትና፣ ፈቃደ ሥጋን መተው
በፆማችን ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው፤ የነነዌ ሰዎች ንስሐ ዮና 3፥1-9 የነቢዩ ዳንኤል ኑዛዜ ዳን 9፥1 የሠለስቱ ደቂቅ ፈቃደ ሥጋን መተው ዳን 1፥8-16 እነሱንም ሕዝቡንም ለመዳን
አብቅቷቸዋል፤ እኛም ስንፆም በተሰበረ ልብ፣ በተዋረደ መንፈስ ሁነን ልንፆም ይገባናል፡፡
እንዲህ ያደረግን እንደሆነ ፆማችን
በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ይሆናል፤ ምድራችንን ያድናታል፣ ጠበብቶቻችን ጥበብን ያፈልቃሉ ገዥዎቻችን ሁሉን በሰላም ይመራሉ ሕዝቡ
ከሚያስገብሩት ክፉ መሪዎች እጅ ነጻ ይወጣል ቤተ ክርስቲያን ክብሯን እንደ ጠበቀች ትኖራለች መንፈስ ቅዱስ በሚፆምና በሚጸልይ ሰውነት
እንጅ ለመብል ለመጠጥ በሚጎመጁ ሰዎች ላይ አያድርም፡፡
No comments:
Post a Comment