አሥሩ ደናግል
የምትመጣው የእግዚአብሔር
መንግሥት በቅዱስ ወንጌል በአሥር ደናግል ተመስላለች እነዚህ ደናግል መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡ ናቸው፤ ከአሥሩ
መካከል አምስቱ ሰነፎች አምስቱ ጠባባት ናቸው፤ ጠባባቱ ደናግል ከመብራታቸው ጋራ ዘይታቸውን በማሰሯቸው የያዙ ናቸው ሰነፎቹ ደግሞ
መብራታቸውን ይዘዋል ነገር ግን ማሰሯቸው ባዶ ነበር፤ ሙሽራውን በመጠበቅ ላይ ሳሉ ሁሉንም እንቅልፍ ጣላቸው ተኝተው ሳሉ ሙሽራው
መጣ ውጡና ተቀበሉ ተባለ፤ ይህን ዐዋጅ ሲሰሙ ሁሉም መብራታቸውን አብርተው ለመቀበል ሲዘጋጁ ሰነፎቹ ዘይት አለቆብናልና ከዘይታችሁ
ስጡን ብለው ጠባባቱን ደናግል ጠየቋቸው እነሱም ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንምና ወደ ሚሸጡት ሂዳችሁ ግዙ አሏቸው እንገዛለን
ብለው እንደሄዱ ሙሽራው መጣና የተዘጋጁትን ይዞ ወደ ጫጉላው ገባ በሩም ተዘጋ ማቴ 25፥11
በዚህ ታሪክ
ውስጥ የሰው ልጆችን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ አስተምሯል፤ አሥሩ ደናግል እነማን ናቸው፤
ለምን አሥር ሆኑ አምስቱ ጠባባት አምስቱ ደግሞ ሰነፎች መሆናቸውስ ስለምን ነው? (በዚህ ርዕስ እስከ ትንሣኤ ድረስ የሚቆይ ተከታታይ
ትምህርቶችን እንሰጥበታለን)
ደናግል የተባሉ
ቅዱሳን ናቸው፤ ለድንግሉ ሙሽራ ለክርስቶስ የታጨ ሕይወት ያላቸው ስለሆኑ ደናግል አላቸው፤ በሥጋ የክርስቶስ አባቱ የሆነው ሰሎሞን
‹‹በእንተዝ ደናግል አፍቀራከ ወሰሀባከ ድሕሬከ፤ ስለዚህ ደናግለ ነፍስ ምዕመናን ወደዱህ ወደኋላም ጎተቱህ›› መኃ 1፥4 ገና ከአብራከ
ወንጌል የሚወለዱ ምዕመናን አጥብቀው ስለወደዱት፣ ልብን በሚያራራ ልመና አድነን ብለው ስለለመኑት ቀዳማዊውን አምላክ ደሀራዊ አደረጉት፤
ከዘመን መቆጠር አስቀድሞ የነበረውን ጌታ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ሕጻን ሁኖ እንዲታይ አደረጉት፤ የአረጋውያን አባት
እግዚአብሔር በሥጋ አንድ ብሎ ዘመንን ማስቆጠር ጀመረ፤ ሁሉን ቀድሞ በመጀመሪያ የነበረውን አምላክ ፍጥረት ቀድሞት በሥጋ እንዲወለድ
አደረጉት፤ የምዕመናን ፍቅር ኋለኛ አድርጎታልና ‹‹ወሰሃባከ ድሕሬከ፤ ወደኋላ መለሱህ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ ቀዳማዊውን መለኮት
በሥጋ ደሐራዊ ያረገው፣ ደሐራዊውንም ሥጋ በመለኮት ቀዳማዊ ያደረገው ከፍቅር በቀር ሌላ ምንም የለም፤
‹‹እንደ ንጽሕት
ድንግል እናንተን ለአንድ ንጹሕ ወንድ ለክርስቶስ ላቀርባችሁ አጭቻችኋለሁና›› እንዲል 2ቆሮ 11፥2 ድንግሉ ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስ
በመጣ ጊዜ በድንግልና የምትጠብቀው ምዕመን (ቤተ ክርስቲያን) ጋር በክብር ሰማያዊ የብርሃን መጋረጃ በተዘረጋበት በብርሃን ድንኳን
ሰርጉን ያደርጋል አትናቴዎስ እንደተናረው ያጊዜ የብርሃን ድንኳን ተተክሎ በቅዱስ ቁርባን ድግስነት ጋብቻውን ይፈጸማል ራዕ 19፥7
‹‹የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሙሽሪትም ራሷን ስላዘጋጀች ደስ ይበላችሁ›› ይሄ በመላእክት መካከል የተሰማ ድምጽ ነው፡፡
ይህ ሰርግ የማን
ነው? በጉ የተባለው ክርስቶስ ነው የእርሱ የጌታችን ሰርግ ነው እንጅ ሌላ የማን ነው፤ የተዘጋጀችውስ ሙሽሪት ማን ናት? የክርስቶስ ሙሽራው ቤተ ክርስቲያ ናት፡፡
የድንግልና ሕይወት እንኳን በሥጋ በነፍስም ቢሆን አይፀናልንምና ብሎ እግዚአብሔር ንስሀን አዘጋጀልን፤ ንስሐ ሰው በኃጢአት ምክንያት
ያጣውን የነፍስ ድንግልና መልሶ የሚያገኝበት ነውና፡፡
ለዚህ ነው በማር
ይስሐቅ መጽሐፍ ላይ ‹‹ንስሐሰ ትሬስዮ ለዘአበሰ ከመ ዘኢአበሰ ለዘማኒ ከመ ድንግል…. ንስሐ ምንድነው ትለኝ እንደሆነ ንስሐስ
በደለኛውን እንዳልበደለ ዘማዊውን እንደ ድንግል … ታደርገዋለች›› ተብሎ የተጻፈው፡፡ አባቶቻችን መኃልይ 1፥4ን በተረጎሙበት ስፍራ
በእንተዝ ደናግል አፍቀራከ ወሰሐባከ ድኅሬከ፤ ስለዚህም ደናግለ ልቡና እነ ረዐብ ዘማ እነሩት ወደዱህ በኋላህም ተከተሉህ›› ብለው
ተርጉመውታል፤ እነ ረዓብ ዘማ ከዓለመ ዝሙት ኢያ 2፥1 ወጥተው ደናግለ ልቡና ተብለው መጠራታቸው በንስሐ ምክንያት ነው፡፡
በወዲያኛውም
ዓለም እንደ እግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉና ደናግል ተብለው መጠራታቸው የሚገባ ስም ነው፤ በምድር ላይ ለሚደረገው ቅዱስ ጋብቻ
በሥጋ ደናግል ሁነው የተገኙ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ካባ ደርባ አክሊል ደፍታ ታጋቸዋለች፤ የሰማዩም እንዲሁ ነው የልቡና ድንግልናን
ይጠይቃል ምክንያም ከክርስቶስ ጋ ተዋሕዶ ለመኖር ቃል ኪዳን የምንጋባበት ቀን ስለሆነ፡፡ የድንግልና አይነቶቹ ሦሰት ናቸው
v ድንጋሌ ሥጋ
v ድንጋሌ ነፍስ
v ድንጋሌ ልቡና ናቸው
ድንጋሌ ልቡና ከሁሉም ይበልጣል
ማን ይደርስበታል፤ ድንጋሌ ነፍስ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ለተወለዱ ሁሉ የሚሰጥ ስለሆነ በልጅነት የምናገኘው ነው ድንጋሌ ሥጋም
ሰው በመሆናችን ብቻ የምናገኘው ፀጋ ነው፡፡ ድንጋሌ ልቡና ግን ክፉ ኅሊናን ፈጽሞ ድል መንሣት ነው፤ በተዘክሮ (እግዚአብሔርን
በማሰብ) ፀንተው ለሚኖሩ ብቻ የሚሰጥ ነው እንጅ ማንም ክርስቲያን የሚደርስበት አይደለም፡፡
ድንጋሌ ሥጋ የማይገኝባን ሴት ምሥጢረ
ተክሊል የሚፈፅምላት እንደሌለ ሁሉ ድንጋሌ ነፍስ የሌላትም ነፍስ ከክርስቶስ ጋር የመዋሐድ ዕድል የላትም፤ ድንጋሌ ልቡና ሲኖራት
ደግሞ በምድርም ሳለች ክርስቶስን ተዋሕዳ ስለምትኖር የወደደችውን ታደርግ ዘንድ ሥልጣን አላት ፡፡ ይህ ሁሉ ስለተሰጣት መንግሥተ
ሰማያትን በደናግል መስሎ ተናገረ፡፡
No comments:
Post a Comment