አንተ ዘወሰንኮ ወዘኃለይኮ ኢይተርፍ; አንተ ያልኸው ይደረጋል፡፡
አጼ ዮሐንስ ሁለተኛ ናቸው የአባታቸውን የአጼ ኢያሱ አድያም ሰገድን መንግሥት እንዳይረከቡ
አጼ ኢዮአስ ብዙ ደባ ሰርተውባቸዋል ይባላል የነገሥታት ልጆች ከሚታሠሩበት አንባ አስገብተዋቸው ብዙ ዓመታን ታሥረዋል ያም አልበቃ
ብሏቸው አንድ እጃቸውን ቆረጧቸው ምክንያቱም አካሉ የጎደለ ሰው አይሾምምና ያለ ስጋት ለመኖር ነበር ነገር ግን እግዚአብሔር የወሰነው
አይቀርምና አጼ ዮአስን ራስ ሚካኤል በሻሽ አንቀው በቤተ መንግሥታቸው ገደሏቸውና መንግሥት እንደ ዋዛ ባዶ ስትቀር ራስ ሚካኤል
ከነገሥታት ልጆች ደጉን ሹመው እንዳሻቸው አዛዥ ናዛዥ ሁነው መኖር ፈለጉና በሰባ ዓመት ዕድሜአቸው ዙፋን ላይ አስቀመጧቸው፤ ለአንድ
ዓመት ዙፋን ላይ በቆዩበት ዕድሜአቸው የኅዳር ሚካኤል በዓል ላይ አጣጣሚ ሚካኤል ተገኝተው ቅኔ እንዲቀኙ ቢጋበዙ ‹‹አዕላፈሂ ጊዜያተ
እመ መከሩ አዕላፍ አንተ ዘወሰንኮ ወዘ ኃለይኮ ኢይተርፍ፤ ሰዎች ሺኽ ጊዜ ሺኽ ሆነው ሺኽ ጊዜ ሺኽ ቢመክሩም አንተ ያሰብከውና
ይሁን ያልኸው አይቀርም›› ብለው ተቀኙ ይባላል፡፡
ዛሬም ይህን ያነሣሁላችሁ በዓለም የመላውን ግፍ አይተን እግዚአብሔር ደግሞ የተገፉትን እንዴት
እንደሚያድናቸው ግፈኞችንም እንደሚቀጣቸው የምናይበት የእግዚአብሔር ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ቀን እግዚአብሔር ባሕራን የተባለውን
ወጣትና አፎምያ የተባለቸውን ድሀ መበለት ያዳነበት ቀን ነው፤ ባሕራን ሃይማኖት ካላት ገንዘብ ግን ከሌላት ሴት ማኅፀን ወጥቶ ወደዚህች
ምድር የመጣ ሰው ነው፤ የዚህ ሰው እናት ባላት ሃይማኖት ትጽናናለች እንጅ በሌላት ገንዘብ ምክንያት አትጨነቅም ስለዚህም ያላትን
ጥቂት ገንዘብ ከድሆች ጋር ተካፍላ በመብላት ለራሷ ደስታን ገንዘብ ታደርጋለች፤ ባለጠጎችን በጭንቅ ቀን ማዳን የማይችለውን ገንዘቧን ትበትናለች በጭንቅ ቀን
የሚያድናትን የእግዚአብሔር ምሕረት ትሰበስባለች፤ እንዲህ ሆና ስትኖር ነው የተፀነሰው ልጇ የተፈጥሮ ሥርዓቱን አድርሶ ከእናቱ ማኅጸን
ወደዚህ ምድር የሚመጣበት ጊዜ ደረሰ፤ ቅድም እንደ ነገርኋችሁ ሃይማኖት እንጅ ሌላ ምን አላት! ከገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከዘመድም
ድሀ ነበረች፤ በሚያስጨንቀው የምጥ ጊዜ ካጠገቧ ሊቆም የሚችል ያዘጋጀችው ሰው አልነበራትም ባጠገቧ ያለ አንድ ክፉ ባለጠጋ ጎረቤት
ብቻ ነው የነበራት፤ ባጠገቡ እንድትኖር አይፈቅድም በሚታየው ሀብት ምንም አልነበራትምና፡፡
ስለዚህ ምጥ እንደተያዘች በሰገነት ላይ ሆኖ እየተመለከታት ቢሆንም ብቻዋን ለነበረችው ሴት
ከአሽከሮቹ አንዱን ሊያዝዝላት ፈቃደኛ አልነበረም በዚያ ምጥ ተይዛ እንደምትሞትና እሷን ከማየት የሚያርፍ መስሎት ነበርና፡፡ ነገር
ግን የሰው ዘመድ የላትም ብለናል እንጅ ይህች ሴት ብቻዋን እንዳትኖር አብረዋት የሚኖሩ ቅዱሳን መላእክትን ሰጥቷት ስለነበረ ሚካኤልና
ገብርኤል በጭንቁ ሰዓት በቀኝና በግራ ሆነው ሲያገላግሏት፣ የወለደችውንም ልጅ ሲባርኩት፣ የዚያንም ባለጠጋ ሀብት እንደሚወርስ ትንቢት
ሲናገሩለት እንዲሰማ የጆሮውን መስኮት እግዚአብሔር ከፍቶለት እንዲሰማ አደረገው፡፡
ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች በሥጋ የሚሆን መጽናናትን ያገኛሉ፤ በሥጋዊ ዘመዶቻቸው፣ በሥጋዊ
ምቾታቸው፣ በሥጋዊ ገንዘባቸው በጠቅላላው የሥጋ በሆኑ ስጦታዎቻቸው ይጽናናሉ፤ በሃይማኖት ለሚኖሩት ደግሞ መጽናናት በማየታየው ሰማያዊ
ስጦታ ነው፤ የክርስትና ትርጉሙ ሲገባን ከሚታየው ይልቅ ለማይታየው ቦታ እንሰጣለን፤ ከሚታየው ካራን ይልቅ የማይታየው ከነዓን እንደሚበልጥ
መቀበል ለአብርሃም ካልሆነ ለማን ይቻላል፤ ከሚፍለቀለቀው የተሰሎንቄ ከተማ ኢየሩሳሌምን ማስቀደም ለዴማስ እንዴት ይሆናል፤ መንፈሳዊ
ስጦታዎች ሁሉ የሥጋ የሆነውን ሁሉ መልቀቅ ይፈልጋሉ፤ ያንጊዜ መንፈሳዊውን ገንዘብ ማድረግ ይቻላል፤
የዚህችም ሴት አነዋወር እንዲሁ ነው የነበረው፤ ምንም የኔ እምትለው ሥጋዊ ነገር በእጇ
የላትም፤ ከሰው ስትርቅ መላእክትን አጽናኝ ተቀብላለች በገንዘብ ድሀ ስትሆን በሃይማኖት ከብራለች፤ ባለጠጋው ግን ብቸኝነቷን እንጅ
ያላትን መንፈሳዊ ሰራዊት አያውቅም ነበርና የተወለደውን ኅጻን ሊገለው ወዶ እንድትሰጠው ጠየቃት ሃብቱን እንደሚወርስ ከአዋላጆቹ
ከመላእክት አንደበት ሰምቶ ነበርና አስቀድሞ በሞት ሊያስወግደው ሀብቱንም እንዳይወርስ ሊያደርገው ነው እንጅ ሊያሳድገው አልነበረም፡፡
እንዳሰበው ከእናቱ ተቀበለ ኅጻኑን በሳጥን አድርጎ ከእናቱ በተቀበለ ማግስት በባህር እንዲጥሉት አደረገ፤ እግዚአብሔር ግን ከኅጻኑ
ጋር ነበረ፤ ሙሴን በግብጽ ምድር በወንዝ ዳርቻ የጠበቀው አምላክ ይህንንም ኅጻን ይጠብቀው ነበር፤ እግዚአብሔር ውኃውን መርከብ
አደረገውና አድርስ ወደ ተባለበት ቦታ አደረሰው ልጁንም በሕይወት ሳለ ወደ ዳርቻው አስወጥቶ አስቀመጠው፤ በዚህ ጊዜ ነው ስሟ በመጽሐፍ
ባልተገለጠ አንዲት መንደር ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ባለጠጋ ሳጥኑን ከፍቶ ቢያይ መልኩ ያማረ ደም ግባቱ የሠመረ ኅጻን አገኘና
ደስ ቢለው ስሙን ባሕራን ብሎ ሰይሞ ወደ ቤቱ ወስዶ አሳደገው ከዚህች ቀን ጀምሮ የባለጠጋው ቤት ተባርኮለታል ስለዚህም ልጁ እያደገ
ሲሄድ በገንዘቡ ሁሉ ላይ ሾመው የግብጹ ንጉሥ ዮሴፍን ስለ በረከቱ በገንዘቡና በሀገሩ ሁሉ ላይ ሾሞት እንደነበረው ዘፍ 39÷4፣
41÷40
ከብዙ ዘመን በኋላ ኅጻኑ
አደገና ወራሽ መሆን የሚችልበት ዘመን ሲደርስ ይህ ኅጻን ወዳለበት ቤት አስቀድሞ ይገድለው ዘንድ ወደ ባሕር የወረወረው ሰው በንግድ
ምክንያት እንግዳ ሆኖ ባሕራን ወደ ነበረበት ቤት መጣ፤ ባሕራን የሚለውን ስሙን ትርጓሜ ሲጠይቅ ከባሕር የተገኘ ማለት መሆኑን ሰማ
ዘመኑን ሲያሰላ እሱ የጣለው ኅጻን እንደሆነ ቢገባው በልቡ የሞተውን፣ በእግዚአብሔር ጥበብ ደግሞ ሕያው የሆነ ይህን ሰው የሚያጠፋበትን
ሌላ የሞት መንገድ ይፈልግ ጀመረ እንጅ ንስሐ መግባትን አላሰበም፤ በምን እንደሚገድለው ሲያስብ የመጨረሻውን እንዲያስብ አደረገው፤
የባሕራን የተስፋው ፍጻሜ፣ የስደቱ መደምደሚያ፣ ያልታወቀ ሆኖ በሰው ሀገር የመኖሩ ማብቂያ፣ ለባለጠጋው ደግሞ የሕይወቱ መጨረሻ
ሃሳብ መሆኑን ልብ በሉ! የኅጻኑን አባት ጠርቶ ወደ ቤቴ እልከው
ዘንድ ልጅህን ፍቀድልኝ የምትሻውን ገንዘብ እከፍልሀለሁ አለው እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ኅጻኑን ያሳደገበትን ዋጋ ሊከፍለው ፈልጎ
ነው ይህን እንዲል ያደረገው፤ ምክንያቱም ባሕራን እስከዚህ ቀን ድረስ በዚህ ሰው እጅ አደራ የተቀመጠ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ
ነበርና እስካሁን የጠበቀበት ደመወዙ ነው፡፡ ባሕራንን ከዚህ ቀን ጀምሮ ለሌላ ለተሸለ ተልዕኮ እግዚአብሔር ይፈልገዋልና ተመልሶ
በዚህ ቤት ሊኖር አይችልም በባሕር ውስጥ የጠበቀው አምላክ ሊሾመው ይፈልገዋል ስለዚህ ለአሳዳጊው የድካሙን ዋጋ ከዚያ ንፉግ ባለጠጋ
እጅ አዘዘለት፡፡ ባለጠጋው በተለመደ ተንኮሉ ለባሕራን የሞቱን ደብዳቤ በስውር ጽፎ ለሚስቱ እንዲሰጥ አዘዘው፤ ባሕራን በደግነት
የራሱን ሞት የምትናገረውን ደብዳቤ ይዞ ሲጓዝ ወዳጆቹን አሳልፎ የማይሰጥ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ እርሱ ላከ፤
በሙሴ መንገድ ላይ ያን ሁሉ ሕዝብ በደኅና የመራ በሕዝቅያስ መንገድ ላይ ቆሞ ሰናክሬምን የቀጣ ይህ ታላቅ መልአክ የሰው ልጆችን
መንገድ የሚያበላሽ ሰይጣንን መቅጣ ልማዱ ነውና ለሞት የተጻፈውን ለሕይወት አድርጎ ሞት የሚገባው ለክፉዎቹ ስለሆነ የባሕራንን ሞት
በሞተ ሀሳብ ውስጥ የሚኖረው ክፉ ባለጠጋ እንዲሞተው ከእግዚአብሔር ዘንድ ተወሰነ የባሕራንን ደብዳቤ እንደደረሰ ግደሉት የሚለውን
እንደደረሰ ልጄን አጋቡት በውስጥና በውጭ ያለውን ሀብቴን አውርሱት የሚል እንዲሆን አድርጎ ሲወለድ የተነገረለትን፣ ሳይፀነስ ገና
በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነለትን ዕድል ፈንታውን ወርሶ እንዲኖር አደረገው፡፡
በዚህ ሰው ሕይወት ውስጥ አግዚአብሔር ምን እንደሠራ በግልጽ ያያችሁ ይመስለኛል፤ ለባሕራን
መዳን የመጀመሪያ ምክንያት የሆነው የእናቱ ሃይመኖት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ እናትና አባት ለልጆቻቸው ከገንዘብ ይልቅ ሃይማትን
ቢያወርሱ ኖሮ ትውልድ ምን ያክል እንደሚባረክ ተመልከቱ ከእኛ በኋላ የሚነሣውን ትውልድ የእግዚአብሔር ምሕረት ያልተለየው ለማድረግ
ሃይማኖትን ልናተርፍለት ይገባናል፤ በሃይማኖት ሰው እንደ ባሕራን የጠላቶቹን ምድር ሳይቀር ይወርሳል ያለ ሃይማኖት ደግሞ እንደ
ሰናክሬም የእጁን ይነጠቃል፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሰው መንገዱ በእግዚአብሔር የተወሰነ ስለሆነ ጎዳናው ላይ የሚቀመጡ ሰዎችን የሚያነሣለት
እግዚአብሔር ነው ይሄ ኅጻን ምንም ሳያውቅ ገና ሰውየው ለሞት አጨው የሚጠብቀው ማን እንደሆነ ባያውቅ እኮ ነው፤ ሲጀመር ጀምሮ
ወደ ባሕር ሲጥለው ለምን ዝም ያለው ይመስላችኋል? እግዚአብሔር በዝምታው ውስጥ ያለውን ዓላማ ተመልከቱ! በዚህ ክፉ ሰው ቤት ውስጥ
የዚህ ክፉ ሰው ልጅ እየተባለ እንዲያድግ አልፈለገም ይሄ ክፉ ሰው በባሕራን በረከት እንዳይባረክ ባሕራንም ከዚህ ክፉ ሰው ክፋት
እንዳይሳተፍ ነበር እግዚአብሔር ይህን ያደረገው፤ በሚደርስብን ፈተና ውስጥ አልፎ የሚመጣውን የእግዚአብሔር ስጦታ መመልከት ብንችል
ኖሮ ስንት በጎ ነገር በመከራ ውስጥ አልፎ ወደኛ በመጣ ነበር፡፡
እግዚአብሔር በክፉዎች ዘንድ እንደ ሬሳ የተቆጠረውን በፈሰሽም ወንዝ የተወሰደውን አንሥቶ
ሞትን ለሰው እያደሉ በሕይወት መኖር የሚፈልጉ ክፉዎችን በሞት ቀጥቶ ሰውን ከጭንቅ ከመከራ ያድናል፡፡ በሰው መንገድ ውስጥ የምናውቀውም
ሆነ የማናውቀው ብዙ መሰናክል አለ ነገር ግን ሰው በሃይማኖት ቢኖር የተፈቀደለት መንገድ ላይ እንዲደርስ የእግዚአብሔር ቀኝ ትረዳዋለች፡፡
ሰዎችም ይምከሩ፤ ጎበዞችና ጉልበታሞችም ይወርውሩ፤ አለቆችና ባለ ሥልጣናትም ይወስኑ፤ የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ
ነውና በሃይማኖት ጸንተን ድል ልናደርግ ይገባናል በዛሬው ዕለት እግዚአብሔር በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አፎምያን ከተጣለው ዘንዶ
ከዲያብሎስ አፍ ባሕራንን ከሞት መዳፍ ከመቃብር ደጃፍ አድኗቸዋል፡፡
የባሕራንም ደብዳቤው ተጽፎ ወጥቷል፤ በሰው ልብ ውስጥ የሞተ እንጅ በሕይወት ያለ ሰው አይደለም፤
አፎምያም አጠገቧ የቆመው አፉን የከፈተ የሚያገሳ አንበሳ ነው፤ በሥጋ ብቻ ብናየው ምን ያክል ከባድ እንደሆነ በኅሊናችሁ አስቡ፤
ፊት ለፊት ከሚታየው ሞት በኋላ የማይታይ ሕይወት አለ ብሎ በተስፋ መቆምስ እንዴት ይቻላል! ነገር ግን ሐዋርያው እንዳስተማረን
ሁለቱም በማመን እንጅ በማየት የሚመላለሱ ሰዎች አልነበሩምና በእምነታቸው የፀኑ ነበሩ 2ቆሮ 5÷7
ባሕራን በጎዳና ብዙ ሰራዊት ባስከተለ ንጉሥ አምሳል ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለትና የያዝኸውን
ደብዳቤ አሳየኝ ቢለው አድርስ እንጅ አሳይ አልተባልሁም ብሎ መለሰ፤ ቅድስት አፎምያም ባሏ ከሞተ በኋላ ብቻዋን ሆና የዓለምን ጣዕማ
ንቃ በፆም በጸሎት በምጽዋት ስታገለግል ለመኖር መወሰኗን ያልወደደላት ሰይጣን በአረጋዊ መነኩሴ አምሳል ተገልጦ እነድታገባ መጻሕፍትን
እየጠቃቀሰ ቢመክራት ከእግዚአብሔር ይልቅ አንተን ልሰማ አልችልም ምንኩስናህ መልካም ነበር ንግግርህ ግን ክፉ ነው አለችው በዚህ
ጊዜ መልኩን ለውጦ በምክር ያልተሳካለትን በኃይል ለማምጣት በሰኔ በ12 ቀን የመላኩን በዓል እያከበረች ሳለች አፉን ከፍቶ ሊውጣ
የመጣው፤ እሷ ግን አሁንም ወደ እግዚአብሔር አመለከተች እንጅ ክፉ ምክሩን ተቀብላ ለጥቂት ጊዜ በሕይወት ቆይታ ለዘለዓለም መሞትን
አልፈለገችም በእምነቷ ፀናች፤
የሁለቱንም ሰዎች እምነታቸውን አስተውሉ! የያዙትን መንገድ በመታመን መዝለቅ ነው የሚፈልጉት፤
ለማይገባው ሰው የማይገባውን ምሥጢር የማይናገረው ባሕራን፣ አነጋገሩ ለሥጋ መልካም ቢሆንም ለነፍስ ግን የሚኮሰኩሰውን በአምሳለ
መነኮስ የመጣ የሰይጣን ምክር የናቀች አፎምያ የሁለቱም መንገዳቸው በእግዚአብሔር እጅ የተያዘ ነው፤ ለዚህም ነው እግዚአብሔር መንገዳቸውን
የሠራላቸው፤ የባሕራንን ደብዳቤ እንደ ተጠቀለለ በእስትንፋሱ ብቻ ወደ ሕይወት ለወጠለት፤ የአፎምያን ደግሞ ሰይጣን እንደሚገላት
እየዛተ ሲመጣባት መላኩ ደርሶ ሰይጣን እንደ ጉም አተነነላት፤ ሁለቱም ሰዎች ሞታቸውን አይተውታል ግን አልተቀበሉትም ሁል ጊዜ የሚያምን
ሰው ከሚያየው መከራ ይልው የማያየው እግዚአብሔር በእምነት ጎልቶ ይታየዋል፤ ስለዚህ በእውነት በነገር ሁሉ ብንታመን እግዚአብሔር
ክፉውን ሳይቀር ወደ በጎ እንደሚለውጠው አያችሁ አይደል!? እመኑ! የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች በደጋግ ሰዎች ዘንድ ክፉ መንገድ የለም
እግዚአብሔር ከፊታቸው ይጓዝላቸዋልና፡፡ እሱ በሄደበት እርሱን ተከትለው ይሄዳሉና መንገዳቸው የቀና ይሆናል፡፡
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሆይ! በነፍስና በሥጋችን ላይ ሥልጣንን ለእርሱ ሰጥተን
‹‹ወይኩን ፈቃድከ›› ማለትን በዘመናችን ሁሉ ልንለማመድ ይገባናል፤ የሰማያት ውበታቸው፣ የሥነ ፍጥረት ደም ግባታቸው፣ የሰማያውያንና
የምድራውያን ፍጥረታት መግባባታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ጥበብ ነውና ሁሉን ባዘጋጀበት ጥበቡ መንገዳችንን ያሳምር ዘንድ ለእግዚአብሔር
በሕይወታችን ስፍራ ልንሰጥ ይገባናል
እንኳን አደረሳችሁ