ክፍል 3
ለምን ጠባባት ተባሉ?
ኃጢአትን ዳስሰው
የማያውቋት፣ በምላሳቸው ያልቀመሷት፣ በዐይናቸው ያላዩአት፣ በጆሯቸው ያልሰሟት፣ በአፍንጫቸው ያላሸተቷት እነዚህ ቅዱሳን ምንኛ የተወደዱ
ናቸው!? ጠባባት ያሰኛቸው ቅሉ ይህ ነው፤ ኃጢአትን ከማምለጥ በላይ ምን አይነት ጥበብ ሊኖር ይችላል! ኃጢአትን ማምለጥ ማለት
በምድር ሳሉ በሰማይ ስፍራ ማዘጋጀት እኮ ነው! ከዚህ በላይ ጥበብ የለም፤ ሁሉንም ኅዋሳት አስተባብሮ አንዱም ሳያፈነግጥ ተገዝቶላቸው
እስከ መንግሥተ ሰማያት ድረስ መጓዝን የሚያክል ጥበብ የለም ስለዚህም ጠባባት አላቸው፡፡
በአንጻሩ ሰነፎች
የተባሉት ይህ ሁሉ ነገር ያልተከናወነላቸው ናቸው እንደምታዩት ሁለቱም ዕኩል አምስት አምስት ናቸው የጻድቃንና የኃጥአን ቁጥራቸው
ዕኩል ስለሆነ አይደለም፤ በቁጥር ከሆነ ኃጥአን ይበዛሉ ነገር ግን በዚህ መጽሐፍ ሊገለጥ የታሰበው ነገር ሌላ ነው፤ ለሁለቱም ዕኩል
ኅዋሳት የተሰጣቸው መሆኑን ለማስረዳት ነው፤ መጻሕፍትን የሚመለከቱበት ዐይን፣ መምህራንን የሚሰሙበት ጆሮ፣ የሚመጸውቱበት እጅ፣
ሥጋውን ደሙን ቀምሰው ሕይወታቸውን የሚያጣፍጡበት አንደበት፣ መዐዛ መንፈስ ቅዱስን የሚያሸቱበት አፍንጫ ለሁሉም ዕኩል ነው የተሰጠው፤
ነገር ግን ኃጥአን በእንቢታቸው ሰነፎች ሆኑ፤ ስለዚህም ዘይት የሌላቸው፣ ነገር ግን ሙሽራውን ከሚጠብቁት እንዳንዱ ሁነው የተቀመጡ
ሆኑ፡፡
የመጠበቂያው
ስፍራ ላይ ያሉ ሲያዩአቸው ሙሽራውን እንደሚጠብቁ የሚመስሉ ብዙ ናቸው፤ ዘይት ግዙ ብለው እንዳይመክሯቸው ማሰሯቸውን መብራታቸውን
ይዘው ሲሰለፉ የሚቀድማቸው የለ ዘይት አለመያዛቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? ሁሉ ነገር ላይ ተመሳስሎ ማለፍ የሚቻል ስለሚመስላቸው
ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም መግባት የሚፈልጉት ከሰው ተጠግተው ነው፤ የራሳቸው ምንም የላቸውም እጃቸው ላይ ላለው መብራት እንኳን
የሚሆን ምንም ዘይት የላቸውም፡፡ የሚገርመው ነገር ሙሽራው እንደማይቀር ያውቃሉ ነገር ግን ሙሽራውን ለመቀበል መያዝ ያለባቸውን
ሁሉ አልያዙም፤ ሙሽራው መጣ ውጡና ተቀበሉ ሲባሉ የጎደለ ነገር እንዳላቸው አወቁ፡፡
ሙሽራውን ነቅቶና
ተግቶ መጠበቅ ትልቅ ጥበብ ነበር ነገር ግን ለሙሽራው ክብር የሚገባ ነገር ሳያዘጋጁ መጠበቅ ምንድነው? እነዚህ የእግዚአብሔር ዳግም
ምጽዓት ተነግሯቸው ነግህ ሠለስት ሲሉ በሕይወታቸው ሳይዘጋጁ የሚኖሩ ነፍሳት ናቸው፤ የእግዚአብሔርን የቸርነቱን ነገር ተመልከቱ!
እስከ ሙሽራው መምጣት ሁሉም ደናግል በአንድነት ሲጠብቁት እንዲቆዩ ፈቀደላቸው፤ አንዱ የሌላውን ማሰሮ አያውቅም ሁሉም የየራሳቸውን
ብቻ ያውቃሉ እንጅ፡፡
በዚህ ዓለም
ስንኖር ሁላችንም በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ እንኖራለን፤ በሁላችንም ዘንድ የክርስቶስ ዳግም የመምጣቱ ነገር ታውቋል፤ ጻድቃንን
ከኃጥአን ሳይለይ በቤተ መቅደሱ ያኖራል፤ አንድ ሁነው ይጠብቁት ዘንድ ፈቃዱ ነው ማንም ቢሆን በገዛ ራሱ እጅ ከመንግሥተ ሰማያት
ውጭ የሚጣል እንደሌለ ያስረዳል፡፡ የጻድቃን ትሩፋታቸው የኃጥአንም ክፋታቸው በየራሳቸው እንጅ የአንዱን አንዱ እንዲያውቅ አልተፈቀደም፤
በዚህ ምክንያት ኃጥአንም ከጻድቃን ጋራ ባዶ ማሰሯቸውን ይዘው በመቅደሱ ውስጥ ይገባሉ ይወጣሉ ሃይማኖት አላቸው ምግባራቸውን ግን
በልዩ ልዩ መንገድ አባክነው የጨረሱ ናቸው፤ ጥቂት እንኳን በማሰሯቸው ውስጥ ዘይት ብትገኝ ሙሽራው ሳይደርስ አብርተው ይጨርሷታል
ማለትም ጥቂት ለክብር እምታበቃ ሥራ ብትኖራቸው በከንቱ ውዳሴ በሰው ፊት አብርተው ይጨርሱታል ማለት ነው፡፡ ለነዚህ ሰዎች ወዮላቸው
ሙሽራው ሲመጣ የሚያበሩትን መብራታቸውን በከንቱ በዓለም ውስጥ ሳሉ ጨርሰውታል እና፡፡
በቅዱስ ወንጌል
እንደተጻፈ ሙሽራው ክርስቶስ ከመጣ በኋላ መብራት ለመግዛት ይሯሯጣሉ ማለትም ከምጽዓት በኋላ ንስሐ መግባት ይመኛሉ፤ ሰነፎች ያሰኛቸውም
ቅሉ ይህ ነው፤ ባዷቸውን ሁነው ሳለ ዘይታቸውን ከያዙት ጋር አብረው ማንቀላፋታቸው ነው፡፡ ማንቀላፋት የተፈጥሮ ሕግ ነውና ሙሽራው
በመዘግየቱ ምክንያት ሁሉም በጋራ አንቀላፉ ማለትም ጻድቃን እና ኃጥአን ሁሉም በሞት ይወሰዳሉ፡፡ ነገር ግን ጠባባት ደናግል ሲሞቱም
በሃይማኖት በምግባር አጊጠው ይሞታሉ ኃጥአን ደግሞ ሃይማኖት እንጅ ምግባር ፈጽሞ አንዳች የሌላቸው ናቸው፤ በዓለም ሳሉ ሃይማኖታቸውን
ይወዳሉ፤ በሃይማኖት መኖር ግን ይሳናቸዋል፤ ለቤተ ክርስቲያን ይቆረቆራሉ ቤተ ክርስቲያንን በሕይወታቸው መምሰል ግን አይችሉም፤
ከንቱ ቅንዓት ከንቱ ፍቅር ያላቸው ናቸው፤ ዘይት ግዙ ብሎ እንዳይመክሯቸው ያላቸው ይመስላሉ ስለ ድንግልና እየሰበኩ ድንግልና የላቸውም
ብሎ እንዴት ይታሰባሉ? የሃይማኖት መሪዎች አገልጋዮች ሆነው ሃይማኖት የላቸውም ተብለው እንዴት ይጠረጠራሉ? ከንስሐ አባቶቻቸው
ጋር ያላቸውን ቅርበት ያየ ሰው እንደምን ንስሐ አይገቡም ብሎ ማሰብ ይችላል? ብቻ ሁሉም ነገራቸው ሁሉ ነገር ያላቸው ያስመስላል
ሁሉም የሚታወቀው ሙሽራው ሲመጣ ነው የሚያበሩት አጥተው ይቅበዘበዛሉ ዘይት አበድሩን ይላሉ የሚሰጣቸው ሲያጡ ደግሞ በዚህ ዓለም
ሳሉ እንዳስለመዱት ሁሉን በገንዘባቸው መግዛት ስለሆነ ልማዳቸው በገንዘባቸው ሊገዙ ይወጣሉ ነገር ግን ሲመለሱ በሩ ተዘግቶ ለጻድቃን
መንግሥተ ሰማያት ተሰጥታ ትቆያቸዋለች አንደ ወጡ ይቀራሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ተግተው ለሚጠብቋት ትሰጣለች እንጅ በሰው ገንዘብ
አትገዛም እና፡፡
ጠባባት ደናግል
በማሰሮ ዘይት ከሙሽራው ጋር አብረው ሊኖሩ ወደ ውስጥ ገቡ፤
ሃይማኖት እና ምግባር የተዋሐዱለት ሰው ጠቢብ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment