>

Monday, 4 July 2016



አሮን ለራሱ ሙሴ ለመቅደሱ




Ø  የቤተ መቅደስ አገልግሎት ራስን በመካድ ይጀምራል፤ ራሱን ያልካደ አገልጋይ እግዚአብሔርን ማገልገል የማይችል የራሱ አገልጋይ ነው፡፡ ለአንድ አገልጋይ ወደ አገልግሎት ከመግባት በፊት
Ø  ጥዎተ ርእስ
Ø  ጋህ
Ø  ሎት
Ø  እግሥት
እነነዚህ አምስት ነገሮች ያልተሟሉለት አገልጋይ ውኃ በሌለበት ምንጭ ይመሰላል፤ዝናም ያልቋጠረ ደመና ምድሩን ሲዞር ቢውል ምን ያደርጋል ከማኅፀኑ አውጥቶ ምድርን የሚያረካበት አንዳች ጠብ የሚል ውኃን አልቋጠረምና፡፡
ከእነዚህ ነገሮች የተለየ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋይም እንዲሁ ነው፤ ያለጸሎት እንዴት የሚያስተምረው ትምህርት በምእመናን ልቡና ተዘርቶ ይበቅልለታል፤ ያለ ትእግሥት በሃይማኖት የሚመጣበትን ፈተና እንዴት ድል መንሳት ይችላል? ያለ ትጋት መንጋውን እንዴት መጠበቅ መመገብ ይችላል? ራስን ሳይሰጡ እንደምን አድርጎ ምእመናንን ያለጥቅም መውደድ ይቻላል? ያለ መሠረታዊ እውቀትስ ወንጌልን እንዴት ይኖሩታል?
የዘራነው አልበቅል አለ የተከልነው አልጸድቅ አለ ወይን ዘርተን እሾህ፣ ስንዴ ዘርተን እንክርዳድ እየሆነብን ነው፤ እየጸለይን እንዝራው እየዘመርን እንሰበስበዋለን፤ አባቶቻችን ለሥራ ሲነሡ አስቀድመው ጾምና ጸሎትን ይይዙ እንደነበረ መጽሐፍ ምስክር ነው ሥራ 13÷4 ለወንጌል አገልግሎት ከመጠራት በላይ የሆነ ምንም አይነት ሥራ የለም፤ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነውና፡፡ ለዚህ ሥራ ራሳቸውን ለሰጡ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ ቀጥሎ በሚደረግ ተዓምር ሥራቸውን ያከናውናላቸዋል ማር 16÷17 የዓይናችን ብሌን ከጸሐይ ብርሃን ጋር ካልተዋሐደ የዚህን ዓለም ብርሃን ማየት አንችልም የልባችንም ዓይን ከመንፈስ ቅዱስ ጸዳል ጋር ካልተዋሐደ እግዚአብሔርን ማየት አንችልም አባቶቻችን ለሕዝቡ የሚሆነውን ፀሐይ የሚያወጡ ንጋቶች ናቸው፤ ፀሐይን እናይባቸዋለን፡፡
የሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ለሕዝቡ ካልጠቀመ ምን ያደርጋል፤ ስድት መቶ ሺህ ሕዝብ አብነት የሚያደርገው ሰው አጥቶ እየተጨነቀ የሙሴ ወደ ተራራው መውጣት ምን ጥቅም አለው፤ አሮን ራሱን ያልካደ አገልጋይ ነው ለመቅደሱ ሥራ እስከ ልጅ ልጆቹ ድረስ የተለየ የእግዚአብሔር ካህን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም ዘፀ 40÷12 የበፍታ ኤፉዱን ሲለብስ ያምርበታል፤ በወርቅ ማዕጠንቱ ድውያን ይፈወሱለታል፤ በሚሠዋው መሥዋዕት የኃጢአት ሥርየት ይሰጥለታል እግዚአብሔር በጠላት ፊት ሊናገርበት አንደበቱን ባርኮለታል ከሙሴ ይልቅ ተናግሮ እንዲያሳምን ጥሩ አንደበት ተሰጥቶታል፤ ግን ምን ያደርጋል አሮን ሕዝቡን ግብጻዊነት ሲያጠቃው እያየ ያቀረቡለትን የጆሯቸውን ጌጥ እንደ ግብጽ ልማድ የጥጃ ምስል አድርጎ ሠርቶ ለሕዝቡ እንቅፋትን ፈጥሮባቸዋል፤
አሮን ከሕዝቡ የሚመጣበትን መከራ እንዳይቀበል ትእግሥት አጣ እውነቱን እንዳይናገር ራሱን አልካደም ራሱን ያልካደ አገልጋይ እንደምን አድርጎ እውነትን በምትጠላ ዓለም ፊት እውነትን መመስከር ይችላል በዓለም ላይ እውነትን ከመናገር በላይ ምን የሚያስፈራ ነገር አለ፤ ዓለምም እንደ እውነት የምትጠላው ምንም አይነት ነገር የላትም፤ ስለዚህ ራሳቸውን ላልካዱ አገልጋዮች ዓለም ክንደ ብርቱ ናት፡፡ አሮን በዚያ አንደበቱ ለሕዝቡ እውነት ቢናገር ኖሮ ተራራው ላይ ካለው ከሙሴ ይልቅ የተሻለ ጽድቅ በተገኘበት ነበር፤ በእርግጥ ከተራራው ግርጌ ላሉ ሰዎች ይሄ ነገር ከባድ መሆኑን አውቃለሁ፤
ከተራራው ግርጌ ያለ ሕዝብስ እንዴት ለእግዚአብሔር ሕግ ሊገዛ ይችላል፤ የእውቀት የንጽሕና የቅድስና የምንኩስና ተራራን መውጣት የቻሉ እነ ሙሴ ካልደረሱለት ከተራራው እግር ሥር ሁከት ዘፈን ጭፈራ መቸም አይወገድም፤ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ይመለስ ግብጻዊነት ይጥፋ አምልኮተ እግዚአብሔር ይስፋ ካላችሁ አሮንን ተውትና ሙሴን ከተራራው ላይ እንዲልከው ጸልዩ የሚገሥጸው ሙሴ ካልመጣ የአሮን ዝምታ አልጠቀመንም፤
አባቶቻችን እንደ ሙሴ ካልሆኑ ጣዖቱ አይሰበርም፤ ሕዝቡ ይቅርታ አያገኝም፤ የቃል ኪዳኑን ምድር አይወርስም፤ ተስፋው አይፈጸምም፤ ጉዞው አይቀጥልም፤ ጠላት አይሸነፍም፤ ስለዚህ ይህን እንደ ወይን ስካር ባለ ኑሮ ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ የሚያወጣ ሙሴ ከተራራው ሊወርድልን ይገባል፤ አሮን ዝም ባይል የጥጃው ምስል የወርቁ እንክብል ባልገዛንም ነበር፤ ግና ምን ይሆናል አሮን ለራሱ ክብር ሲል ሕዝቡን ከክብር አጎደለው፤ ሙሴ ስለመቅደሱ ሥርዓት ለመነጋገር ከእግዚአብሔር ጋር ቆሟል አሮን ለራሱ ሙሴ ለመቅደሱ ይተጋሉ፡፡ ዘፀ 32÷1-35   
በዚህ ዘመን ሊሾሙ የሚገባቸው አባቶችም እንደ ሙሴ ተራራው ላይ ወጥተው የሚዘገዩ እንደ አሮን ራሳቸውን የሚጠብቁ ሊሆኑ አይገባም፤ ሕዝቡ ጠንካራ መንፈሳዊ መሪ ከሌለው ከአርባ ቀን በላይ አይቆይም፤ ታሪክ ያበላሻል፤ እግዚአብሔርን የሚያስቀይም ሥራ ይሠራል፤ ስለዚህ አባቶቻችን ሕዝቡ የጠየቃቸውን አድርገው በሕይወት ከሚኖሩ ይልቅ ከፊት ቀድመው ‹‹የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ›› ዘፀ 32÷26 ቢሉ ሁሉም ይከተላቸዋል፤
ወደ ፊት የሚሾሙልን አባቶችም ከተራራው ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚነግሩን እንጅ ከግብጽ በወረስነው ክፉ ልማድ ስንጎዳ ዝም የሚሉን እንዳይሆኑ በታቦቱ የዓለምን ጣዖት የሚሰብሩ ለምድሩ ሳይሆን ለሰማዩ መንግሥት የሚሠሩ እንዲሆኑ ሁላችንም ልንጸልይ ይገባናል፡፡
አባቶቻችን ሆይ! አርባ ቀንም ታሪክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እናንተን በመንጋው ላይሾሟችኋልና ሕዝቡን ከሙሴ በተረከባችሁት መንፈስ ልትመሩት ይገባል፤ እናምናለን እናንተ በሙሴ መንገድ ከተጓዛችሁ የአባቶቻችን አምላ ከእናንተ ጋር እንደሚሠራ፡፡ በአበው መንፈስ ካልሆነ ግን ሙሴ አርባ ዓመት የመራውን ሕዝብ ከአርባ ቀን በላይ እድሜ እንዳይኖረውና የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቡ ላይ እንዲነድ ታደርጉታላችሁ፡፡



No comments: