>

Wednesday, 15 November 2017



ደብረ ቁስቋም
ደብረ ቁስቋም ማለት ደብረ ምዕራፍ ማለት ነው፤ ከእመቤታችን ክብረ በዓላት መካከል አንዱ በዚህ ስም ይጠራል፤ ለቤተ ክርስቲያን ከሚደረግላት የመዳን ታሪክ ጋር ስለተገናኘ እንጅ ከግብፅ ተራሮች አንዱን መጥራት ስላስፈለገን አይደለም፤ ዛሬ አግዚአብሔር ታላቅ የሆነውን ፍርዱን በምድር ላይ ማድረጉን ለዮሴፍ በሕልም የታየው መላክ አስረድቶታል፤ ‹‹እስመ ሞቱ እለ የሐስስዋ ለነፍሰዝ ሕጻን፤ የዚህን ሕጻን ነፍስ ሊገሏት የሚሷት ሁሉ ሞተዋልና›› ማቴ 2 20 ከዚህ በፊት የተደረገው እንዲህ አልነበረም በልደተ ክርስቶስ ያልተደሰተው ሰይጣን በሔሮድሳውያን አድሮ ስደት የሚገባቸው ግፈኞች አርፈው ተቀምጠው ስደት የማይገኝባት እመ አምላክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ተሰደደች የእግዚአብሔር መላክ የቀኑን ልክ ሳይናገር ‹‹እስክነግርህ ድረስ በዚያ ተቀመጥ›› ብሎ ዮሴፍን ወደ ግብፅ እንዲወርድ አዘዘው፡፡ የመከራ ጫፉ አይነገርም የእስራኤልን የግብጽ ኑሮ መጀመሪያውን እንጅ መጨረሻውን ከእግዚአብሔር በቀር ማን ያውቀው ነበር፤ የዚህ ዓለምም ጉዞ መጨረሻው በኛ ዘንድ አልተነገረንም
ነገር ግን እግዚአብሔር ማንንም በስደት ምድር አይረሳምና ከሦስት ዓመት ከስድስት ወራት በኋላ ዛሬ ስደተኞችን በምሕረት አሰበ ይህ አርባ ሁለት ወር ለእመቤታችን የስደት ወቅት ይሁን እንጅ ለሔሮድሳውያን ደሞ የንሥሐ ጊዜ ነበር ታዲያ ሔሮድስ ንስሐ ባለመግባቱ ዛሬ ተቀስፎ ሞተ፤ ስደተኛዋእመቤታችን ወደ ናዝሬት ስትመለስ አሳዳጁ ሔሮድስ ከእግዚአብሔር መንግሥት ለዘለዓለም ተሰደደ፤ ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ሽሽ ብሎ ስደቱን የነገረው መላክ ዛሬ ደግሞ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ ብሎ ነገረው፤ በዚሁ ዕለት ደብረ ቁስቋም ገብተው አድረዋልና ደብረ ምዕራፍ ተብሎ ተተረጎመ፡፡
የምድረ በዳው ጉዞ፣ የበረኃው ስቃይ፣ የግብፅ ዋዕይ፣ የሽፍቶቹ ማንገላታት፣ የሔሮድስ ሰራዊት ከበባ፣ የሦስት ዓመት ረሀብና ጥም፣ የነኮቲባ ክፉ ወሬ፣ ይሄ ሁሉ መከራ ዛሬ ተጠናቀቀ፤ ማደሪያ የሌላት ዖፍ ብሎ ቅዱስ ዳዊት የዘመረላት ፀዓዳ ዖፍ ድንግል ማርያም ዛሬ ማረፊያ አገኘች ይህችውም ደብረ ቁስቋም ናት፡፡ እንዴት ደስ ይላል ከረጅም የመከራ ወራት በኋላ የተሰማ የምሥራች ነው ደሞ የምሥራቹን ታላቅ የሚያደርገው የሕጻኑን ነፍስ የሚሹት መሞታቸው ነው፡፡ የገደላቸው ሕጻናት ብዙ ናቸው በእናታቸው እቅፍ ላይ እያሉ አንቀው የገደሏቸው አሉ ጡት እየጠቡ ሳሉ ነጥቀው በሰይፍ የቀሏቸው አሉ፤ ተኝተው ሳሉ ከእናቶቻቸው ጀርባ እያወረዱ የጨፈጨፏቸውም ብዙ ናቸው፤ የእናቶቻቸው ልብስ በደም ተነከረ ዓይናቸው በእንባ ተሞላ ቤተ ልሔምና አካባቢዋ በጩኸት ተሞላች፤ አስቀድሞ በነቢይ እንደተባለ ‹‹ራሔል ስለልጆቿ አለቀሰች›› በራሔል ልጆች ርስት ላይ የተፈፀመ ጭፍጨፋ ስለሆነና የራሔልም መቃብር በገሊላ አውራጃ ውስጥ ስለነበረ ነው ከአራቱ የእስራኤል ልጆች እናቶች መካከል ራሔልን ለይቶ ይጠራታል፡፡
ሞትን በሰው ልጆች ላይ የፈረደው ንጉሡ ሔሮድስ እሱም በሰማዩ ንጉሥ ሞት ተፈርዶበት መቃብር ወረደ፡፡  እገለዋለሁ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በኃጢአት የሞተውን ዓለም ለማዳን ኃጢአት ወደ በዛባቸው ሰዎች ሂዶ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ጎበኛቸው፤ ከዚህም በኋላ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ለመግባት ያሰበ አይደለም፤ ኃጢአት ወደፀናባት ከተማ ወደ ናዝሬት ተመለሰ፡፡
በእርግጥ የመጨረሻ ድል አይደለምና በክፉው ሔሮድስ ፋንታ ልጁ ነው የነገሠው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ኃጥዕ ሔሮድስን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም›› መዝ 36÷35 የሚለውን የአባቷን መዝሙር እየዘመረች ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
ደብረ ቁስቋም የመንግሥተ ሰማይ ምሳሌ ነው፡፡ እመቤታችንና አብረዋት የተሰደዱት ሰዎች የምዕመናን ምሳሌዎች ናቸው፤ ምዕመናን የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከነእርሱ ጋር እያለ በክፉዎች ምክንያት ይሰደዳሉ፤ እውነትን ይዘው ከሀገር ሀገር ይንገላታሉ፤ በምድረ በዳ ማደሪያ በማጣት፣ በረሀብ በጥምና በእርዛት ይፈተናሉ ነገር ግን ለነፍሳቸው የሚሆን ማረፊያን ፍለጋ እየተጓዙ እንደሆኑ በማሰብ ይፀናሉ፤ በመጨረሻም የጠላታቸውን የዲያብሎስን መሞት ይሰማሉ፤ ለቤተ ክርስቲያን ታላቁ የምሥራች የዲያብሎስ ድል መነሣት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዲያብሎስን በሃይማትና በምግባር ገድላ ራሷን ወደ ማረፊያው ተራራ ወደ ደብረ ጽዮን ታስጠጋለች፡፡
የዛሬው በዓል ቤት አልባ የነበረችው የሰው ልጆች ሕይወት ማረፊያ ያገኘችበት ቀን ነው፤ ስደቱ ቤተ ክርስቲያን በሐሳዊ መሢህ ዘመን የሚደርስባት ስደት መነሻ ነውና የተደረገውም ዕረፍት ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር መንግሥት ለምታገኘው ዕረፍት ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ እኮነው መላዕክትም በልጇና በእርሷ ላይ ክንፋቸውን እየጋረዱ ምስጋን ያቀረቡት ቅዱስ ያሬድም ‹‹ዮም ፀለሉ መላዕክት ላዕለ ማርያም ወላዕለ ወልዳ ክርስቶስ በደብረ ቁስቋም፤ መላዕክት በልጇና በእርሷ ላይ ክንፋቸውን እየጋረዱ አመሰገኑ›› ብሎ ይናገራል፡፡ መላዕክትን ሳይቀር ያስደሰተ ታላቅ ዕረፍት፡፡
እግዚአብሔር ዕረፍት በሌለባት ዓለም ውስጥ ስንኖር ዕረፍትን ለሁላንም ያድለን፡፡

Wednesday, 25 October 2017



ክብራችን ወዴት ሄደ?
ከስደት ለተመለሰ ሕዝብ፣ በፈርዖናዊ አገዛዝ ወገቡ ለጎበጠ ወገን ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ምንኛ ከባድ ነው!? ዳታን እና አቤሮንን ምድር እንድትከዳቸው፣ ደቂቀ ቆሬን እሳት ከሰማይ ወርዳ እንድታቃጥላቸው፣ የሰማርያን ሰዎች ረሀብ እንዲፈጃቸው ምክንያት የሆነው የእግዚአብሔር ቅያሞት ነው፤ እግዚአብሔር ሲቀየም ሥነ ፍጥረት ሁሉ ሰውን ይቀየመዋል፤ እንኳን ሌላው ፍጥረት ይቅርና ሰው በራሱ የተፈጥሮ ሕጉን ጠብቆ መሄድ አይችልም፡፡
እስራኤል ከፈጣሪው ጋራ በተጣላበት ወራት ለተወለደው ኅጻን እናቱ ስም ስታወጣለት ‹‹ኢካቦድ›› አለችው፡፡ በወቅቱ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለች፤ ካህናቱም አብረው ተማርከዋል፤ የእስራኤል ጎበዛዝቶች በጦርነቱ ድል ሆነው አፍረው ተመልሰዋል፤ እስራኤልን ለዓርባ ዓመታት የመገበው ካህን ዔሊ ከመንበሩ ወድቆ ተንቆጫቁጮ ሞቷል፤ የሊቀ ካህናቱ መንበር ያለ ሰው ቀርቷል፤ ስለዚህ ልጁን ከዚህ የተሻለ ሌላ ስም ምን ብላ ልታወጣለት ትችላለች?
በእኛስ ሀገር ዛሬ ለሚወለድ ኅጻን ስም አውጡ ብትባሉ ማን ልትሉት ትችላላችሁ?? በውኑ ክብር ከእኛ አልራቀም? በረከትስ አልጎደለንም? ኃያላኖቻችን በመንፈሳዊ ሰልፍ ቢሰለፉ ድል መንሣት ይችላሉ? የትኛው ሕዝብ ነው በሀዘን ያልተዋጠ በእውነት ምንድነው እየሆነ ያለው በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ማነው የእግዚአብሔር ክብር እንዲጎድለን እየሠራ ያለው? ሲጀመር አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ክብር ሊርቀው የሚችለው ክብር ከቤተ መቅደሱ ሲጠፋ ነው፡፡ የሀገርም ሆነ የሕዝብ ክብር የሚመነጨው ከቤተ መቅደሱ ነውና፡፡
እስራኤልን ‹‹ኢካቦድ›› ያሰኘው ክብር በካህናቱ ምክንያት ከቤተ መቅደሱ በመጥፋቱ ነው፡፡
ቤተ መቅደሱ ካልተፈራ ሀገር አትፈራም ካህናቱ ካልከበሩ የሀገር ሽማግሌዎቹ አይከብሩም፤ ካህናቱ ጽድቅን ለብሰው ኃጢአትን አሸንፈው ካልነገሡ ንጉሥ በሀገሪቱ አይነግሥም የንጉሡ ሰራዊት አያሸንፍም፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር ከጎደላት ሀገሪቱ ክብር ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም መፈራትና መወደድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሹማምንት ዘንድ ሲኖር በሀገሪቱም ሹማምንት ዘንድ ሊኖር ይችላል፡፡
ትውልዱ የሚቀበለው ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት የሚችል አባት አጣን እኮ! ምንድነው እንደዚህ በሰው ድርቅ እንድንመታ ያደረገን?
በየመንገዱ ድንጋይ መወራወር በዝቶ ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያዊው ደምቶ እያየን ስናዝን በዓየር ካልሆነ በምድር መጓዝ አልችል ብለን እየተቸገርን ሰንብተን የዚህን መፍትሔ አምጣልን ብለን ጸሎታችንን ሳንጨርስ ቅዱሱ ጉባኤያችን ድንጋይ መወራወር በዝቶበት ስናየው በጣም ያሳዝናል፡፡
አንድ ሲኖዶስ መፈራትን፣ መወደድን፣ ባለሟልነትን ገንዘብ ማድረግ አለበት፤ በመናፍቃን ዘንድ መፈራትን፣ በምዕመናን ዘንድ መወደድን፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት አለበት፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን እውነት እውነቱን ስንነጋገር ማኅበረ ቅዱሳንን እንጅ ሲኖዶሱን የሚፈራ መናፍቅ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ታላቁ የሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሊቃውንት ጉባኤ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ ያላገኘውን መፈራት እና መወደድ አንድ የወጣት ጉባኤ ሲያገኝ ክብራችን ወዴት ሄደ ተብሎ ክብራችንን ፍለጋ መሄድ ያለብን ይመስለኛል እንጅ አሁን ያለንን ጉልበትና ሥልጣን ተጠቅመን ክብራችንን ማስመለስ የምንችል አይመስለኝም፤ ክብር ከሰማይ ነውና፡፡  
ብፁዓን አባቶቻችን ሆይ! ይሄን ትውልድ ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት መርታችሁ የምታስገቡበት ቁልፉ ያለው በእጃችሁ ነው፤ መግቢያው ጠፍቶበት የሚባዝነውን ሕዝባችሁን እናንተው ራሳችሁን ሳታጠሩ ቀርታችሁ መግቢያ ብታሳጡት ፍርድ ከሰማይ ይጠብቃችኋል፡፡ እናንተ የረገጣችሁትን መሬት ስሞ የጨበጣችሁትን መስቀል ተሳልሞ በደስታ የሚኖር ሕዝብ ነበራችሁ አሁን ግን ነገሩ እየተለወጠ ነው፤ በየቦታው በእናንተ ላይ ምሬት የሚያሰማ፣ በየቤቱ እናንተን የሚያማ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡
እውነት የሚነግረው፣ ክርስትናን በተግባር የሚያሳየው፣ ተሻግሮ የሚያሻግረው መሪ ይፈልጋል፡፡ እንደምታዩት መሻገሪያው ሁሉ ታጥሮ በብዙ ነገሮች ተከቦ ነው የሚኖረው ቀድማችሁ ስለሕዝቡ መጸለይ ያስፈልጋል፤ ሁሉም በእናንተ ጸሎት እንደሚከናወንለት ያምናል፡፡
የሊቃነ ጳጳሳት የኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ ማለት የኒቅያ የኤፌሶን ጉባኤ ነው፤ ርዕዮተ ዓለም በተቀየረ ቁጥር የማይቀየር ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ ጉባኤ በመሆኑ በሽህ የሚቆጠሩ ዓመታትን በሕያውነት መቆየት ይችላል፡፡
እኔ አሁንም እኛ እናንተን እንናገር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራውም ጉባኤ ሀሳብ እንሰጥ ዘንድ አግባብ አይደለም፤ ነገር ግን ሕዝቡ ከመንሾካሾክ አልፎ ስለእናንተ በጩኸት እያወራ ነው እናንተ ግን በዓመት ሁለት ጊዜ የምታነሡት አጀንዳ ሁልጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ ነው፤ እናንተ ሙሴ ለመሆን ከበቃችሁ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እጃችሁን የሚደግፍ እንደ አሮንና ሖር ያለ ትውልድ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ወቅታዊ ጉዳዮች እያሉባት ከሃይማኖት የወጡ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ፣ የምዕመኑ ቁጥር እየተመናመነ፣ በአንድ በኩል አክራሪ እስልምና በሌላ በኩል ፕሮቴስታንት ተሐድሶ በሚል ስም ገብቶ እየገዘገዛት አሁንም የቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡
 የእናንተን ውሳኔ የሚሹ ብዙ ዘመኑ የወለዳቸው ችግሮች አሉ እኮ! ስደተኛና መደበኛ የሚባል ሲኖዶስ የተፈጠረው፣ በቦርድ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት የተፈጠሩ፣ አብነት ትምህርት ቤቶች የተመናመኑ፣ ገዳማቱ የመናንንያን እጥረት ገጥሟቸው ራሳቸው ከሰው ተለይተው የመነኑ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ በብዛት የተሰረቁ፣ ምዕመናን ከሥጋው ከደሙ የራቁ በዚሁ እናንተ ቤተ ክርስቲያኒቱን በኃላፊነት በተረከባችሁበት ዘመን ነው፡፡
ብፁዓን አባቶቻችን ሆይ! ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በእጃችሁ ነው ያለው አንድ ሁኑና ትውልዱን አድኑት የቅዱስ ሲኖዶስ አለመስማማት በሀገር ላይ አለመስማማትን ያመጣል፤ የአባቶቻችን ክብር በትውልዱ ልብ ውስጥ መቀነስ የሀገርን ክብር ይቀንሳል፡፡
መናፍቃንን ስትገሥፁ እንጅ እርስ በእርሳችሁ መሰዳደባችሁን ልጆቻችሁ መስማት የለብንም፤ ነውርና ነቀፋ የሌለባት ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን መትጋት ያስፈልጋችኋል፡፡
                                             ክብራችን ይመለስልን!፡፡   

Saturday, 15 July 2017

ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ



ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ
በዘመነ ክርስቶስ ከዘመነ ነቢያት ይልቅ ስለ ክርስቶስ ብዙ ጥያቄዎች ይቀርቡበት የነበረው ዘመን ነው፤ ተዓምራቱን ያዩ፣ ትምህርቱን የሰሙ፣ በመልኩ የተማረኩ፤ በቃሉ የረኩ ሁሉም የየራሳቸውን ጥያቄ አንሥተው ለራሳቸው መልስ ሰጥተው ያልፋሉ፤ በተዓምራቱ የተደነቁት ሙሴ ነው ይሉታል፤ ንጽሕናውን ድንግልናውን ያወቁ፣ ሕብስት ሲያበረክት ያዩት ደግሞ ኤልያስ ነው ይሉታል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጠሯቸው ነቢያት ሁሉ የሚበልጠውን ተዓምራት ሲያደርግ ያዩት እንደሆነ የሚሉትን ያጡና ብቻ ከነቢያት አንዱ ነው ብለው ያልፉት ነበር ማቴ 16÷14

 እንደ ሚያውቋቸው መምሕራን ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና ለዚህ መልስ ቢያጡ አድንቀው ዝም ይሉ ነበሩ እንጅ አንዱም እንኳን ከነሳቸው ማን እንደሆነ ጠይቆ ሊያውቅ የደፈረ ሰው የለም ማቴ 13÷54 ምን አልባትም ከዮሐንስ መጥምቅ በቀር አንተ ማን ነህ ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ ሰው ላይኖር ይችላል፤

ከሦስት ዓመት ከሦስት ወር ባስተማረባቸውም ጊዜያት ከሰማይ ተልኮ ስለ መምጣቱ ቢነግራቸው ‹‹ዘለሊነ ነአምር አባሁ ወእሞ እፎ እንከ ይብለነ እምሰማይ ወረድኩ፤ እኛ አባትና እናቱን እያወቅናቸው እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል›› ዮሐ 6÷42 ብለው ይነቅፉት ነበር እንጅ ትምህርቱን ሊቀበሉት አልተቻላቸውም፤ እንዲያውም መነቀፍና መሰደብ በሚገባው ሥጋ ከመምጣቱም በላይ ከነገሥታቱ ቤት ሳይሆን ንቀው አጥቅተው በሚመለከቱት በድሀው በዮሴፍ ቤት በመወለዱ ምክንያት ‹‹አኮኑ ዝንቱ ወልዱ ለፀራቢ ይህ የእንጨት ጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን!?›› ማቴ 13÷55 ብለው ይጠይቁም ነበር፡፡

 የዮሴፍ ድህነቱ የዳዊት ልጅነቱን በአይሁድ ዘንድ አስረስቶበት ነው እንጅ በዘር ሐረጉ ቢቆጠር የዳዊት ልጅ ሆኖ ባገኙት ነበር፤ አይሁድ ግን ይህን አላወቁም፤ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ማቴዎስ ተናዶ ተነሥቶ ወንጌሉን ወልደ ዳዊት ብሎ የሚጀምረው የዳዊትን አባትነት በዮሴፍ በኩል አድርጎ ወደ እመቤታችን ወደ ክርስቶስ ለማድረስ፡፡ 

አይሁድ ባለማወቃቸው ሲሳለቁ ‹‹የጠራቢው ልጅ አይደለምን!›› ብለዋል እንጅ እሱስ እውነት ነው ሰማይና ምድሩን ጠርቦ ያስማማ የአብ የባሕርይ ልጁ ነው እንደ እግዚአብሔር ጠራቢ ማነው? የጠራቢ ግብሩ ያልተስማማውን ማስማማት የማይዋሐደውን ጠርቦ አስተካክሎ ማስማማት አይደለምን!? እንኪያስ ሰማይን ከምድርጋር በአድማስ ያስማማ አባቱ ነውና ‹‹የጠራቢው ልጅ›› ማለታቸው እውነታቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከስላቅ ውስጥ ቁም ነገርን ለሚድኑ ሰዎች ያዘጋጃል በእመቤታችን ፊት ውኃ ሲቀዱ የነበሩ ሴቶች አስቧቸው  ‹‹…እኛስ ለባሎቻችን ስራ አለብን እንዳንች ሥራ ፈት አይደለንም ወይም እንጅ ክርስቶስ ይወለዳል እሚባለው ካንች ይሆናል›› ብለው የዘበቱባትን መዘባበት ለእመቤታችን እውነት አድርጎላት ወላዲተ አምላክ ሆነች፤ እውነታቸውን ነው እሷ ለሰማዩ ንጉሥ የታጨች ሙሽራ ናት ከእርሱ ‹‹ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና›› ከተባለችለት ከእርሱ በቀር ለማንም ሥራ ሊኖርባት አይችልም፡፡ 

ይሄም እንደዚያ ያለ ነው እነሱ ሊሳለቁ የተናገሩትን መንፈስ ቅዱስ በአባቶቻችን ላይ አድሮ እንዲህ አስተረጎመ፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ እንዴት የዮሴፍን ስም ሳይጠሩ የቀሩ ይመስላችኋል? መንፈስ ቅዱስ ከልክሏቸው እኮ ነው፡፡
ታዲያ የሚንቁት ስለሚንቁት የሚጠሉትም ስለሚጠሉት ስለ ክርስቶስ መልስ አጥተው ለሚጨነቁት አይሁድ እነሱ መልስ ለማግኘት በቅንነት አልጠየቁምና እሱ ‹‹ምንተ ትብሉ በእንተ ክርስቶስ ወልደ መኑ ውዕቱ፤ ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡
 ይህ ጥያቄ ለተራው አይሁዳዊ ሕዝብ የቀረበ እንዳይመስላችሁ! አወቅን መጠቅን ለሚሉትና መዓርጋችን ረቂቅ አእምሯችን ምጡቅ ለሚሉ ፈሪሳውያን ነው- ጥያቄው የቀረበው፡፡ እነ ገማልያልን ያኽል ምሁር የሚገኝበት ጉባኤ ነው - የፈሪሳውያን ጉባኤ፡፡ በወቅቱ የታወቀው አንጋፋ የብሉይ ትርጓሜ ትምህርት ቤትም ያለው በነሱ እጅ ነበር- እንደነ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ንቁ ደቀ መዛሙርትን የያዘው ጉባኤ፡፡

 ግን ምን ይሆናል! የነቢያት ልጆች መሆናቸው የነቢያትን ሱባኤ ማወቃቸው ትንቢተ ነቢያትን ሲሰሙ ማደጋቸው ክርስቶስን ይመጣ ዘንድ ያለው መሢሕ እንደሆነ ሊያውቁ አላስቻላቸውም፤ በፊደል እንጅ በመንፈስ የሚመሩ አልነበሩምና፡፡ ለዚህም ነው ‹‹የዳዊት ልጅ ነው›› ማቴ 22÷41 ብለው የሰጡት መልስ በሌላ ምዕራፍ ስለ እርሱ ማንነት ጠይቆ ማቴ 16÷16 ደቀ መዛሙርቱ ለመለሱለት መልስ የሰጠውን ብፅዓን ሳይሰጣቸው የቀረው፡፡ መልሳቸው ከፊደል እንጅ ከመንፈስ ቅዱስ ያልተገኘ ነውና ‹‹ዘለሊሁ እንከ ዳዊት እግዚእየ ይብሎ እፎ እንከ ይከውን ወልዶ፤ እሱ ራሱ ዳዊት ጌታየ እያለው እንደምን ልጁ ይሆናል›› የሚለውን ጥያቄ አስከተለባቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ክርስቶስ አሁን ዓለማችን ምን ትላለች? የዓለም ጥበበኞች (ፈላስፎች ሳይንቲስቶች..) ምን ይላሉ? መናፍቃንስ? በተለይም በኛ አውደ ምሕረት ሳንዘራቸው የበቀሉት የተሐድሶ መናፍቃን ኢየሱስ ኢየሱስ ብሎ ያልዘመረ ያልሰበከ ሁሉ አልዳነም እያሉ በማሸማቀቅ አባቶቻችን ከተጓዙበት መንገድ ሊያወጡን እየታገሉን ነውና ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክርስቶስ ምን ትላለች? በተከታታይ እናያለን፡፡  

Friday, 14 April 2017

ጀምረናል

v ርስቶስ ከእኛ የነሣቸው ሦስት ነገሮች፤
v ሥጋ፣ ነፍስና ደመ ነፍስ ሆነው በየራሳቸው የፈጸሙት ስህተትና የተሰጣቸው ካሣ
v በዚህም ዕለት የተሻሩልን አራቱ ጠላቶቻን እና በኃጢአት ምክንያት ያጣናቸው በዚህ ዕለት መልሰን ያገኘናቸው አምስቱ ነገሮች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ
                                            መልካም ንባብ
ማልቀስ በጀመርንበት ዕለት መሳቅን፣ መሞት በጀመርንበት ጊዜ መነሣትን፣ መሰደድ በመርንበት ሰዓት መመለስን፣ መገፋት በጀመርንበት ወራት ማሸነፍን ጀምረናል፤  ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በዚህ ዕለት ነበር የሰው ልጆች ዕጣ ፋንታ መለወጥ የጀመረው፤ ይህ የሰው ልጆች የሕይወት ለውጥ የፍጡራንን ሁሉ አነዋወር የለወጠ ለውጥ ነበር፤ ጨለማ በነገሠበት እግዚአብሔር በሌለበት ሕይወት ውስጥ መኖር ለሰው ግዴታው ሆነ የእጁ ሥራ ውጤት ነውና፡፡ በነባቢት ነፍሱ ያልተሰጠውን ክብር ሽቶ፣ በደማዊት ነፍሱ በእጸ በለስ ፍሬ ጎምጅቶ፣ በሥጋው እፀ በለስን በልቶ በሠራው ስሕተት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ሦስት ነገሮችን ነሥቶ በእኛ አካል በእኛ ባሕርይ ወደ እኛ መጣ፤ እነሱም በኃጢአት የተበላሹት ነፍስና ሥጋም ደመ ነፍስም ናቸው፤ እነዚህን ከእኛ ነሥቶ እነዚህኑ አነጻቸው፡፡
እነዚህን ነጻ ለማውጣት አራት ነገሮችን በዚህ ዕለት ሻረልን ኃጢአትን፣ ሞትን፣ ፍዳን እና ሰይጣንን ነው፡፡

Ø  ኃጠአትን ይሽር ዘንድ ከኃጢአተኞች እንዳንዱ ተቆጠረ፤ ኃጢአት ከሰው ሁሉ እንዲወገድ ኃጢአተኞች ለፍርድ በሚቆሙበት ሥፍራ ቆሞ ታየ በኃጢአተኞች ላይ እንደሚያደርጉትም ቅጣቱን ሁሉ በእርሱ ላይ ፈጸሙበት በርባን ነጻ መውጣቱ ኃጢአተኛው ዓለም ነጻ የሚለቀቅበት ጊዜ እንደደረሰ ሚያሳይ ነው፡፡
Ø  ሞትን ያጠፋ ዘንድ በገዛ ፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ፤ሞት መጥፋቱ መቃብርም ድል መነሣቱ ይታወቅ ዘንድ በሥጋ ሞትን በቀመሰበት ሰዓት ሙታን ከመቃብራቸው እየወጡ በዝማሬ ወደ ከተማይቱ ገቡ ኢየሩሳሌም ከሞት እስራት ከመቃብር ግዞት በተፈቱ ሰዎች ተሞላች፤

የሚገርመው ነገር ሙታን ከመቃብር ወጥተው እያመሰገኑ ሳሉ ኅያዋኑ አይሁድ ደግሞ ገና በተቃውሞ ላይ ነበሩ፤ እንድትይዙልኝ እምፈልገው ቁም ነገር የጌታችን ሞት ሙታንን ቀስቅሶ የሚያናግር የሙታን ትንሣኤ መሆኑን ነው፤ ከሞትም በኋላ መናገር ጀምረናል፤ ነቢይ በመዝሙሩ ‹‹እስመ አልቦ በውስተ ሞት ዘይዜከረከ ወበሲኦልኒ መኑ የአምነከ፤በሞት ውስጥ የሚያስብህ በመቃብርም ውስጥ የሚያመሰግንህ የለም››ብሎ ነበር  ዛሬ በዚህ ዕለት የሙታን ዝማሬ ተሰምቷል በሲኦልም ያሉ ነፍሳት ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶሰ ‹‹ሰላም ለኩልክሙ›› ሲላቸው ‹‹ምስለ መንፈስከ›› ብለው ተሰጥዎዉን መልሰዋል፡፡ አባቶቻችንን ሁሉ ዝም ያሰኘው ሞት ዛሬ ቅጣቱን ተቀብሎ ዝም በማለቱ ቤቱ ሲኦል ተበረበረች፤ እሱ ግን አሁንም ዝም እንዳለ ነው፡፡

Ø  ፍዳንም እንደሻረልን ለማስረዳት ስለ በጉነቱ ፋንታ ክፉ ብድራትን ተቀበለ እሱም አስቀድሞ በነቢይ ‹‹ፈደዩኒ እኪተ ኅየንተ ሠናይት፤ በጎ ነገር ስላደረግሁላቸው ፋንታ ክፉ መለሱልኝ›› መዝ 108÷5 ብሎ እንዳናገረ መከራውን በፈቃዱ ተቀበለ፤ በፍዳ ስለተያዙ ነፍሳት ነውና የተያዘው የሚከሱበትን አንዳች ምክንያት እንኳን ሊያገኙ አልቻሉም ዮሐ 18÷30 ነገር ግን በፍርዱ ፍርዳችን ይወገድልን ዘንድ አግባብ ነውና በነገሥታቱ ዘንድ ፍርድን ተቀበለ፤ እርሱ ግን ያደረገውን ሁሉ ስለዕኛ አድርጎታልና ከሞተም በኋላ በሥጋ ወደ መቃብር በነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ሂዶ በሥጋና በነፍስ እስረኞችን ፈታ፡፡

ገና ከወዲሁ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች›› ማቴ 26÷38 ብሎ የነፍስን ፍዳ፣ ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ለአሥራ ስምንት ሰዓት በተቀበለው መከራ የሥጋን ፍዳ ተቀብሎለታል፤ ኃዘን እና ጭንቀት የነፍስ መገረፍ እና መቁሰል የሥጋ ነውና፡፡

Ø  ሰይጣን መሰደዱን ያወቅነው ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ብሎ ሲጣራ ነው፤ ነፍስን በጭንቅ መስጠትና ወደሲኦልም መጓዝ የአባቶቻችን ዕጣ ፋንታ ነበር፤በጽድቁ የተመሰከረለት አብርሃም ሳይቀር በሲኦል ከኃጥአን ጋር ታይቷል፡፡ ዛሬ እንደዚያ አይደለም ከፊታችን የሚቆመው የአባቶቻችን ከሳሽ ዲያብሎስ ተጥሏል ኢዮ 1÷6 ስለዚህ ጉዟችን ወደ ገነት ሆነ ‹‹ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ›› ሉቃ 23÷43 ተባለ፤ከዚህ አስቀድሞ ‹‹እግዚአብሔርም ከዔደን ገነት አዳምን አስወጣው›› ዘፍ 3÷23 ተብሎ እንደተጻፈ እንዳትረሱብኝ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ እንዲጠብቁ የምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍን የጨበጡ ኪሩባውያን መላእክት እንደነበሩ ተጽፏል፡፡
ከዚያ ተመልሰናል በአዲሱ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ጀምረናል ዕብ 10÷19 ዛሬ ሰይጣን ስልጣን የለውም (ወደው ለሚገዙለት ካልሆነ በስተቀር) ምክንያቱም በዚህ ዕለት ከመስቀሉ ስር ተገኝቶ በሰጠው የኑዛዜ ቃል መሠረት ‹‹ሰብአ ለቢሶ ሊተ ሞዓኒ፤ ሥጋ ለብሶ ድል አደረገኝ›› ሲል ሰምተነዋልና፡፡ በእውነት ያ ክፉ ገዥ አሁን ተሸሯል ቅድስት ወንጌል ለዚህ ማስረጃ ምስክር ናት ዮሐ 12÷31

በደመ መስቀሉ የተቤዣችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሁላችሁ ለጻድቅ እንኳን ነፍሱን የሚሰጥ ጭንቅ በሆነባት ዓለም ውስጥ ለኃጢአተኞች የሚሞት ክርስቶስ በአምስቱ ቅንዋት ተቸንክሮ አምስት ነገሮችን ማለትም፡- ልጅነትን፣ ሰማያዊ ርስትን፣ ክህነትን፣ መንግሥትን፣ ሥርየተ ኃጢአትን አሰጥቶናል፡፡

ስለሆነም በልጅነታችን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› በሰማያዊ ርስት ባለቤትነታችን የሚበልጠውን ሰማያዊ ሀገር እንናፍቃለን ከተማን አዘጋጅቶልናልና ዕብ 11÷16፣ በክህነታችን ‹‹ዘወኀብከነ ዘንተ ሥልጣነ ከመ ንኪድ ከይሴ ወአቃርብተ፤እባብና ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ ይህን ሥልጣን የሰጠኸን›› ማር 16÷18፣ ስለ መንግሥታችንም ‹‹የክብርና የምስጋና ዘውድን ጫንህለት በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው›› ዕብ 2÷8 ኃጢአታችን ስለተሠረየልንም ‹‹አሁን በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ገላ 5÷1 እያልን መናገር ጀምረናል ወገኖቼ ጠላታችን ተስፋ የሚያስቆርጥ እንጅ ተስፋ የማይቆርጥ ስለሆነ አሁንም ደግመን በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል፡፡ በመወለዱ ሰማያዊ ልደትን ሰጥቶናል፣ በውኃ ተጠምቆ ኃጢአትን በውኃ አስጥሞልናል፣ ዛሬ ደግሞ ከሁሉም የሚበልጠውን አድርጎልናል በሞቱ ሞታችንን ገድሎልና፡፡
                                 
     ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ!
                                                  ከፍኖተ ሰላም   

                                  ሚያዝያ 2009 ዓ.ም