v ክርስቶስ ከእኛ የነሣቸው ሦስት ነገሮች፤
v ሥጋ፣ ነፍስና ደመ ነፍስ ሆነው በየራሳቸው የፈጸሙት ስህተትና የተሰጣቸው ካሣ
v በዚህም ዕለት የተሻሩልን አራቱ ጠላቶቻን እና በኃጢአት ምክንያት ያጣናቸው በዚህ ዕለት መልሰን ያገኘናቸው አምስቱ ነገሮች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ
መልካም
ንባብ
ማልቀስ በጀመርንበት ዕለት መሳቅን፣ መሞት በጀመርንበት ጊዜ መነሣትን፣
መሰደድ በመርንበት ሰዓት መመለስን፣ መገፋት በጀመርንበት ወራት ማሸነፍን ጀምረናል፤ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በዚህ ዕለት ነበር የሰው ልጆች
ዕጣ ፋንታ መለወጥ የጀመረው፤ ይህ የሰው ልጆች የሕይወት ለውጥ የፍጡራንን ሁሉ አነዋወር የለወጠ ለውጥ ነበር፤ ጨለማ በነገሠበት
እግዚአብሔር በሌለበት ሕይወት ውስጥ መኖር ለሰው ግዴታው ሆነ የእጁ ሥራ ውጤት ነውና፡፡ በነባቢት ነፍሱ ያልተሰጠውን ክብር ሽቶ፣
በደማዊት ነፍሱ በእጸ በለስ ፍሬ ጎምጅቶ፣ በሥጋው እፀ በለስን በልቶ በሠራው ስሕተት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ሦስት ነገሮችን
ነሥቶ በእኛ አካል በእኛ ባሕርይ ወደ እኛ መጣ፤ እነሱም በኃጢአት የተበላሹት ነፍስና ሥጋም ደመ ነፍስም ናቸው፤ እነዚህን ከእኛ
ነሥቶ እነዚህኑ አነጻቸው፡፡
እነዚህን ነጻ ለማውጣት አራት ነገሮችን በዚህ ዕለት ሻረልን ኃጢአትን፣
ሞትን፣ ፍዳን እና ሰይጣንን ነው፡፡
Ø ኃጠአትን ይሽር ዘንድ ከኃጢአተኞች እንዳንዱ ተቆጠረ፤
ኃጢአት ከሰው ሁሉ እንዲወገድ ኃጢአተኞች ለፍርድ በሚቆሙበት ሥፍራ ቆሞ ታየ በኃጢአተኞች ላይ እንደሚያደርጉትም ቅጣቱን ሁሉ በእርሱ
ላይ ፈጸሙበት በርባን ነጻ መውጣቱ ኃጢአተኛው ዓለም ነጻ የሚለቀቅበት ጊዜ እንደደረሰ ሚያሳይ ነው፡፡
Ø ሞትን ያጠፋ ዘንድ በገዛ ፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ፤ሞት መጥፋቱ መቃብርም
ድል መነሣቱ ይታወቅ ዘንድ በሥጋ ሞትን በቀመሰበት ሰዓት ሙታን ከመቃብራቸው እየወጡ በዝማሬ ወደ ከተማይቱ ገቡ ኢየሩሳሌም ከሞት
እስራት ከመቃብር ግዞት በተፈቱ ሰዎች ተሞላች፤
የሚገርመው ነገር ሙታን ከመቃብር ወጥተው እያመሰገኑ ሳሉ
ኅያዋኑ አይሁድ ደግሞ ገና በተቃውሞ ላይ ነበሩ፤ እንድትይዙልኝ እምፈልገው ቁም ነገር የጌታችን ሞት ሙታንን ቀስቅሶ የሚያናግር
የሙታን ትንሣኤ መሆኑን ነው፤ ከሞትም በኋላ መናገር ጀምረናል፤ ነቢይ በመዝሙሩ ‹‹እስመ አልቦ በውስተ ሞት ዘይዜከረከ ወበሲኦልኒ
መኑ የአምነከ፤በሞት ውስጥ የሚያስብህ በመቃብርም ውስጥ የሚያመሰግንህ የለም››ብሎ ነበር ዛሬ በዚህ ዕለት የሙታን ዝማሬ ተሰምቷል በሲኦልም ያሉ ነፍሳት ሊቀ ካህናት
ኢየሱስ ክርስቶሰ ‹‹ሰላም ለኩልክሙ›› ሲላቸው ‹‹ምስለ መንፈስከ›› ብለው ተሰጥዎዉን መልሰዋል፡፡ አባቶቻችንን ሁሉ ዝም ያሰኘው
ሞት ዛሬ ቅጣቱን ተቀብሎ ዝም በማለቱ ቤቱ ሲኦል ተበረበረች፤ እሱ ግን አሁንም ዝም እንዳለ ነው፡፡
Ø ፍዳንም እንደሻረልን ለማስረዳት ስለ በጉነቱ ፋንታ
ክፉ ብድራትን ተቀበለ እሱም አስቀድሞ በነቢይ ‹‹ፈደዩኒ እኪተ ኅየንተ ሠናይት፤ በጎ ነገር ስላደረግሁላቸው ፋንታ ክፉ መለሱልኝ››
መዝ 108÷5 ብሎ እንዳናገረ መከራውን በፈቃዱ ተቀበለ፤ በፍዳ ስለተያዙ ነፍሳት ነውና የተያዘው የሚከሱበትን አንዳች ምክንያት
እንኳን ሊያገኙ አልቻሉም ዮሐ 18÷30 ነገር ግን በፍርዱ ፍርዳችን ይወገድልን ዘንድ አግባብ ነውና በነገሥታቱ ዘንድ ፍርድን ተቀበለ፤
እርሱ ግን ያደረገውን ሁሉ ስለዕኛ አድርጎታልና ከሞተም በኋላ በሥጋ ወደ መቃብር በነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ሂዶ በሥጋና በነፍስ
እስረኞችን ፈታ፡፡
ገና ከወዲሁ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ
አዘነች›› ማቴ 26÷38 ብሎ የነፍስን ፍዳ፣ ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ለአሥራ ስምንት ሰዓት በተቀበለው
መከራ የሥጋን ፍዳ ተቀብሎለታል፤ ኃዘን እና ጭንቀት የነፍስ መገረፍ እና መቁሰል የሥጋ ነውና፡፡
Ø ሰይጣን መሰደዱን ያወቅነው ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ
አደራ እሰጣለሁ›› ብሎ ሲጣራ ነው፤ ነፍስን በጭንቅ መስጠትና ወደሲኦልም መጓዝ የአባቶቻችን ዕጣ ፋንታ ነበር፤በጽድቁ የተመሰከረለት
አብርሃም ሳይቀር በሲኦል ከኃጥአን ጋር ታይቷል፡፡ ዛሬ እንደዚያ አይደለም ከፊታችን የሚቆመው የአባቶቻችን ከሳሽ ዲያብሎስ ተጥሏል
ኢዮ 1÷6 ስለዚህ ጉዟችን ወደ ገነት ሆነ ‹‹ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ›› ሉቃ 23÷43 ተባለ፤ከዚህ አስቀድሞ ‹‹እግዚአብሔርም
ከዔደን ገነት አዳምን አስወጣው›› ዘፍ 3÷23 ተብሎ እንደተጻፈ እንዳትረሱብኝ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ እንዲጠብቁ
የምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍን የጨበጡ ኪሩባውያን መላእክት እንደነበሩ ተጽፏል፡፡
ከዚያ ተመልሰናል በአዲሱ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ጀምረናል ዕብ 10÷19
ዛሬ ሰይጣን ስልጣን የለውም (ወደው ለሚገዙለት ካልሆነ በስተቀር) ምክንያቱም በዚህ ዕለት ከመስቀሉ ስር ተገኝቶ በሰጠው የኑዛዜ
ቃል መሠረት ‹‹ሰብአ ለቢሶ ሊተ ሞዓኒ፤ ሥጋ ለብሶ ድል አደረገኝ›› ሲል ሰምተነዋልና፡፡ በእውነት ያ ክፉ ገዥ አሁን ተሸሯል
ቅድስት ወንጌል ለዚህ ማስረጃ ምስክር ናት ዮሐ 12÷31
በደመ መስቀሉ የተቤዣችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሁላችሁ ለጻድቅ እንኳን ነፍሱን
የሚሰጥ ጭንቅ በሆነባት ዓለም ውስጥ ለኃጢአተኞች የሚሞት ክርስቶስ በአምስቱ ቅንዋት ተቸንክሮ አምስት ነገሮችን ማለትም፡- ልጅነትን፣
ሰማያዊ ርስትን፣ ክህነትን፣ መንግሥትን፣ ሥርየተ ኃጢአትን አሰጥቶናል፡፡
ስለሆነም በልጅነታችን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› በሰማያዊ ርስት ባለቤትነታችን
የሚበልጠውን ሰማያዊ ሀገር እንናፍቃለን ከተማን አዘጋጅቶልናልና ዕብ 11÷16፣ በክህነታችን ‹‹ዘወኀብከነ ዘንተ ሥልጣነ ከመ ንኪድ
ከይሴ ወአቃርብተ፤እባብና ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ ይህን ሥልጣን የሰጠኸን›› ማር 16÷18፣ ስለ መንግሥታችንም ‹‹የክብርና የምስጋና
ዘውድን ጫንህለት በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው›› ዕብ 2÷8 ኃጢአታችን ስለተሠረየልንም ‹‹አሁን በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ
አወጣን›› ገላ 5÷1 እያልን መናገር ጀምረናል ወገኖቼ ጠላታችን ተስፋ የሚያስቆርጥ እንጅ ተስፋ የማይቆርጥ ስለሆነ አሁንም ደግመን
በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል፡፡ በመወለዱ ሰማያዊ ልደትን ሰጥቶናል፣ በውኃ ተጠምቆ ኃጢአትን በውኃ አስጥሞልናል፣
ዛሬ ደግሞ ከሁሉም የሚበልጠውን አድርጎልናል በሞቱ ሞታችንን ገድሎልና፡፡
ሁላችሁንም
እንኳን አደረሳችሁ!
ከፍኖተ ሰላም
ሚያዝያ 2009 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment