>

Tuesday, 13 September 2016



አዲስነገርየለም
አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ሚመጣልን በተስፋ ሰምተናል፤ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረ ጊዜ አዲስ ያደረገው የሰውን ሕይወት እንጅ ምድርን አዲስ ማድረግ አልነበረም- የመምጣቱ  ዓላማ፡፡ ኃጢአት ያስረጀውን ዓለም ያለ ኃጢአት ተወልዶ በኃጢአት ያለውን የሰውን ልጅ ደግሞ በመስቀል ኃጢአትን አስወግዶ የሰውን ልጅ አዲስ አደረገው፡፡
አሁን ግን አዲስ ነገር የለም ያልኩት ሰው ወደ ጥንት ክፋቱ የተመለሰ ስለመሰለኝ ነው፤ እርግጥ ነው ዛሬ ያለንበት ቀን ባለፈው ዓመት በመምጣቱ ደስ ብሎን የተቀበልነውን ዓመት 2008ን አለቀብንና አሮጌ ብለን በአዲስ ልንተካው እየተዘጋጀን ያለንበት ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን ዓመታት አዲስ የሚሆኑት ሰው በሕይወቱ አዲስ ነገር ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡
ኃጢአትን በማይፀየፍ ሕይወት ውስጥ ሆኖ አዲስ ነገር እንዴት ይኖራል፤መጽሐፍ ‹‹ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም›› ብሎ የተናገረው ለምን ይመስላችኋል ያኔ በወቅቱ የሰውን ልጅ ኑሮውን አዲስ ማድረግ የሚችል ምንም አይነት ነገር እንደ ሌለ የሚያሳይ እኮ ነው፡፡
ክርስቶስ ሲመጣ ግን አዲስ ዘመን፣ አዲስ መሥዋዕት፣ አዲስ መንገድ፣ አዲ ስ ሰማይ አዲስ ምድር፣ አዲስ ትምህርት አዲስተስፋ ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ አዲስ ሰው ተፈጠረ፡፡ ሐዋርያት ‹‹ልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ፤ አዲሱን ሰው ልበሱት›› ቆላ 3÷10 ብለው መናገር ጀመሩ አዲስ ሆነዋልና በአዲስ ቋንቋ ተናገሩ አዲሱ ኪዳን ተጀምሯልና ሰውን ሁሉ አዲስ የሚያደርገው ሥልጣነ ክህነት ባለቤት ሆኑ፤
አዲስነታቸው አዲስ ነገርን እያስገኘላቸው ለብዙ ሰዎች መዳን ምክንያት የሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ነበራቸው፤ ክርስቶስ ወደ ዓለም ሲመጣ በአዲስ ልደት እንደ ሆነ የታወቀነው፤ በምድራችን ላይ ያለ አባት የተወለደ ኅጻን ያለ ወንድ ዘር የወለደች እና ከወለደችም በኋላ በድንግልና ጸንታ የኖረች ሴት ያን ጊዜ ብቻ ካልሆነ ከዚያ በፊት የት እናገኛለን፡፡ በዚያውም ላይ ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን  ያለ ሴት ሴትን ማስገኘት የሚችል ወንድ መኖሩን ነው እንጅ ያለ ወንድ ወንድን ማስገኘት የምትችል ሴት መኖሯን አይደለም፤ ዘፍ 2÷21 አሁን ግን ያ ሕግ ተሸሮ ያለ ወንድ ወንድን የምታስገኝ ሴት ድንግለeል ማርያም በምድራችን ተገኘች፡፡
በዚህ አዲስ ልደት የመጣው ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በቤተ መቅደስ በር ላይ የነበረውን አረጋዊ ስምዖንን አዲስ በማድረግ ነው፤ ዓላማውም ይህ ነበርና-ሰውን አዲስ ማድረግ፡፡
ሰው አዲስ ከሆነ ምን አሮጌ ነገር ሊኖር ይችላል፤ አዲስነታችን ሁሉን ነገር አዲስ ሊያደርገው እንደሚችል አታወቁም? አዲስ ልብ አዲስ መንፈስ ሊኖረን ይገባል፤ ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር የምንኖርበት፣በጨለማ ውስጥ ላሉት ብርሃን የምንሆንበት፣ያዘኑት የምናጽናናበት፣ስብራትን የምንጠግንበት፣ድካምን የምናበረታበት አዲስ ልብ ሊኖረን ይገባል፡፡
አዲስ ልብ ሳይኖረን ምን አዲስ ነገረeር ሊኖር ይችላል፤ እመኑኝ አዲስ ነገር ሊኖር የሚችለው አዲስ ልብ ሲኖረን ብቻነው፤ አዲስ ልብስ ገላን እንደ ማያጠራው ሁሉ አዲስ ዘመንም ሰውን  አዲስ ሊያደርገው አይችልም፤ የሰው አዲስነት ዘመኑን፣ ምድሩን፣ ነፋሱን፣ ውኃውን አዲስያደርገዋል፡፡
በሌላው ዓለም እንዳየነው ብዙ አንገት የሚያስደፉ ነገሮችን እየተመለከትን ምድር በሰው ደም እየታጠበች እናቶች ያለ ልጅ ሲቀሩ እያየን ይቅር ሳንባባል አንዳችን በአንዳችን ላይ ሰይፍ እየተማዘዝን የመዘዝነውን ሰይፍ ወደ ሰገባው ሳንመልሰው ምን አዲስ ነገር ሊኖር ይችላል፤ እውነት ነው እምላችሁ የሰው ደም የፈሰሰባት ምድር ራሷ እንደምትሞት ታውቃላችሁ፤ ሙት ባሕር የሚባል ሕይወት የሌለው ውኃ በዓለማችን እንዲኖር ምክንያቱ ምን እንደ ሆነ አታውቁም እንዴ፤ ወንድሙ ቃኤል በገደለው ጊዜ የጻድቁ የአቤል ደም የተጨመረበት ስለሆነ እኮ ነው፤
ደም እያፈሰስን ምድሩን ባሕሩን ነፋሱን ሌላውንም ነገር ለምን እንገለዋለን በሞ ተች ምድር ላይ ዘርተን በሞተ ውኃ አብቅለን የሞተ ዓየር ስበን እንዴት በሕይወት ልንኖር እንችላለን መጨረሻችን መተላለቅ ሳይሆን ነገሮችን ሁሉ ምክንያት ሳንሰጥ በይቅርታ ምድርን አዲስ ልናደርጋት ይገባናል፡፡ ሔሮድስም ሔሮድያዳም ወለተሔሮድያዳም በዮሐንስ ሞት ተሳትፈዋልና በንስሐ እስካልተመለሱ ድረስ እግዚአብሔር የሔሮድስን ቤት አንድ ቀን ያጠፋታል፡፡
ነገሥታት ለእግዚአብሔር የተገዙ እንደ ሆነ ከዙፋናቸው ዘር አይታጣም መዝ 131÷11 ይህ ካልሆነ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ለጨካኝ መንግሥት ሰጥቶ ዝም የሚል አምላክ አይደለምና ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ሊመለስ ይገባዋል፤ የዳዊት መንግሥት ለምን ተቀደደች? 1ነገ 12÷16፣ ግብጽ ንጉሷን አጥታ ለምን ባዶዋን ቀረች? ዘፀ14÷28 በጭካኔ ሕዝቡን የሚገዙ ነገሥታትን ማጥፋት የእግዚአብሔር ሥራነው፤ እኛ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እግዚአብሔርም ወደ እኛ ይመለሳል፡፡
አሁንም እንዘፍናለን፤ አሁንም እናመነዝራለን፤ አሁንም ያለ ልክ እንበላለን እንጠጣለን ማነው በሞት ፍርሃት ያልተከበበ፤ ማነው በኑሮ ክብደት ያልተንገዳገደ፤ ማነው የኃዘን የለቅሶ ድምጽ ሳይሰማ የዋለ፤ በከተሞቻን ሁሉ ሞት ና ግድያ አለ፤ በቀኖቻችን ሁሉ እነዚህ ነገሮች ነበሩ፤ አብረውን ተሻግረው ይሆን፡፡ በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ መጣፊያ መጨምር በአሮጌም አቀማዳ አዲስ የወይን ጠጅ መሾም ምን ያደርጋል፤ ልብሱም ይቀደዳል ወይኑም ይደፋል
እግዚአብሔር ዘመኑን ይባርክልን ያለፈው ክፉ ዘመን ደግሞ ወደ ዚህኛው አይምጣብን፡፡

No comments: