>

Friday, 26 July 2019


ሰይጣን ከፊት ነው ከኋላ?
በይሁዳ ምድር በቤተ ልሔም ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ጀምሮ ለመምጣቱ የምሥራችን ያወራለት ከእግዚአብሔር መላእክት በቀር ማንም የለም ሉቃ 2፥10 የነሣው ባሕርይ የዕኛን ቢሆንም ቅሉ ከእኛ ይልቅ ቅዱሳን መላእክት የነርሱን ባሕርይ የነሣ ያክል ደስ አላቸው፤ ኃጢአት እስኪወገድ ዲያብሎስም እስኪረታ ድረስ ሰዉን ጨምሮ ማንም በምንም ደስ ሊሰኝ አይችልም ጥንቱንም ቢሆን ደስታን ከልባችን አውጥቶ ጭንቀትን ያስጀመረን እርሱ ነውና- ኃጢት፡፡
ከመወለዱ ጀምሮ ወገኖቹ ሊያደርገን ቢመጣ እግዚአብሔርነቱን ለሰው ሰጥቶ ሰውን እግዚአብሔር ቢያደርገው ሰይጣን ተቀየመና በምድር ላይ ያሰማራቸውን ምልምሎች እያሰማራ ከዋለበት አላውል ካደረበት አላሳድር አለ፤ እርሱም የዋለብንን ያደረብንን ክፉ መንፈስ ለማሳደድ ከሀገር ወደ ሀገር በገዛ ፈቃዱ ተሰደደ፤ በዚህ ሁሉ ሲፈትነው የነበረ ዲያብሎስ በገዳመ ቆሮንቶስ ድል ተነሥቶ ‹‹ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፤ አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ›› ማቴ 4፥10፣ 16፥23 ተብሎ ከተባረረ በኋላ ጊዜውን ጠብቆ በሌላ መልኩ ራሱን ለውጦ በገዳም ባይሆንለት በከተማ ድል ይነሣው ዘንድ በአይሁድ ልብ ተሰውሮ መጣ፡፡
ከምድረ በዳ ሲያሳድደው በከተማ ገብቶ፣ ብቻውን መታገል ባለመቻሉ ሰዉን አሰልፎ ከፊት ቀድሞ ቆየ፡፡ ሰይጣን ቀድሞ ከገባበት ከተማ ፍትሕ ይጎላል፤ እውነትን የማያውቁ ገና እውነት ምንድነው ብለው ብለው የሚጠይቁ ጠይቀውም ያልተመለሰላቸው ሰዎች በከተማ ይሾማሉ፤ ጊዜው የወንበዴዎች ይሆናል፤ ከሰማይ ምልክትን ቢያሳይዋቸውም እንኳን የማያምኑ ክፉዎች በከተማው ይሞላሉ፤ ሕዝቡ ክርስቶስን እንዲሰቅሉ ካህናቱ ያባብላሉ ሕዝቡም ባላወቁት በክፉዎቹ መሪነት አብረው ይጮኻሉ፤
ብቻ ምኑን እነግራችኋለሁ ሰይጣን ቀድሞ ከገባበት ከተማ ንፁሐን ይሠዋሉ፤ ከእግዚአብሔር መልአክ ቁጣ የተነሣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ይቀደዳል፤ ቀኑ ይጨልማል፤ ዐለቶች ይሰነጣጠቃሉ፤ የሰማይ ኀይላት ይወድቃሉ፤ የምድር መሠረት ይነዋወጣል፡፡ ሰይጣን ሲቀድም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ እንገደዳለን፤
አሁን ባለንበት ዘመን ሰይጣን ከኋላ መሆኑ ቀርቶ ከፊት የቀደመ ይመስለኛል፤ እስኪ አስቡት እሱ ባይቀድም ኖሮ በሰው ኅሊና ሊታሰብ የማይችል ግፍ በምድር እንዲህ ይበዛ ነበር? ሰው ቁልቁል ይሰቀላል፣ እጅና እግሩን ታስሮ ወደ ገደል ይጣላል፣ በጨለማ ቤት ውስጥ አንዳች ብርሃን እንዳያሳዩ ተደርገው በተሠሩ ወፍራም ግድግዳዎች መካከል እንዲኖር ይደረጋል፣ ሰዉን ከአውሬ ጋር ማሳደር ጥንት በነበሩ ሰማዕታት ታሪክ እንደምንሰማው ዐይነት ይደረጋል፡፡ እና እስኪ ንገሩኝ ሰይጣን አልቀደመም ትላላችሁ? ከፊት ባይሆንማ ኖሮ በንፍር ውኃ አጥበን ያጠፋነውን በእሳት ያቃጠልነውን የሰብአ ትካትን የሰብአ ሰዶምና ገሞራን ኃጢአት ለዚህ ትውልድ ማን ያስተዋውቀው ነበር?
አትጠራጠሩ ሰይጣን ዕድሜው ብዙ ስለሆነ ያኔ የነበረውን ኃጢአት ለዚህ ትውልድ ያሻገረለት እርሱ ነው፡፡ በቃኤል አድሮ ወንድምን መግደል እንደሚቻል ያስተማረ፣ በዘካርያስ ጊዜ በቤተ መቅደስ መግደልን ያሳየ፣ ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን ሕጻናትን መግደልን ለነገሥታቱ ያስተማረ ሰይጣን ዛሬም ዕድሜው ረዝሞ በዓለማችን ውስጥ አለ፤ እሱ ያስተማራቸውን ይዘው ወንድሞቻቸውን የገደሉ፣ ሕጻናትን የደፈሩ፣ ወንዶችን እንደ ሴት ይዘው በመተኛት ያስነወሩ፣ ካህናትን በቤተ መቅደስ ደማቸውን ያፈሰሱ የጥንቱን የሰይጣን ጦር ይዘው ሰዉን እየወጉ ያሉ እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ከፊት ቀድሞናል፡፡

No comments: