ሐሽማል፤ ሐሽማል፤ ሐሽማል
ስሙን ስሰማ በቁሜ ፈዘዝሁ፡፡ መጽሐፉን ገልጬ ሳነበው ትንሽ ተሻለኝ፡፡
ሐሽማል በማዕበል ፈጠነ የተዘጋጀ መጽሐፍ ሲሆን በሀገራዊ ጥበብ ላይ
ያጠነጥናል፡፡ የጠቢባኑንና የባለቅኔዎችን በደመና የመጫን ጥበብ በአቡሻክር
ቀመር ቀምሮ ቁጭ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በፊት በደመና የሚሄዱ ጠቢባን መኖራቸውን ሲሰሙ አንዳንዶቹ በአስማት ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚያስቡ
አልጠራጠርም እኔም ቢሆን ጥልቀት ያለው ዕውቀት በዚህ ዘርፍ ስላልነበረኝ ዕፁብ ዕፁብ ብዬ አልፈው ነበር፡፡ የሐሽማል ደራሲ ማዕበል
ፈጠነ ግን በአስማት ሳይሆን በአቡሻክር ቀመር ነው ሲል የውስጤን ጥርጣሬ አውጥቶ ጥሎ አቡሻክሩን ቀምሮ አሳየኝ፡፡ እናም ለጥበብ
ልቤን ሰጠሁ፡፡ ከዚህ ዐልፎ የጠቢቡ ሖረን በጥበብ የሕይወትን ውኃ ፍለጋ የሊቅ ዐፅቁን በድቅድቅ ጨለማ ቀይ ብርሃን የሚተፋ መጽሐፍ
አምጥቶ አስደመመኝ፡፡ በተለይ በጎንጅ ደብረ ጥበብ ተዋነይ በጥበቡ የሰወራትን ውኃ ለጠጣ ሰው ቅኔ መዝረፍ ቀላል እንደሆነ ከአፈ ታሪክ አልፎ አማናዊ መሆኑን ሊያሳምነኝ
ዳዳው፡፡
‹‹በእርግጥ ጥበብ ኅብረ ብዙ
እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ለጥበብ እንደ ኪሩቤል አይኖቿ ብዙ ናቸው፡፡
እንደ ሱራፌልም መላ አካሏ በክንፍ የተሞላ ነው፡፡ ወደ ወደደችውም ትበራለች፡፡ የምታርፍበትን ካገኘች በልቡ ላይ ታርፋለች፡፡ ሰባት
ምሰሶዋችን አቁማ ቤቷን ሠርታ ወዳጆቿን ሁሉ ወደ ቤቷ ትጠራለች፡፡ ማዕዱ ከቀረበ በኋላ ራሷ የወይን ጠጅ ሆና ብቅ ትላለች፡፡ ሲጠጧት
ከወይን ይልቅ ትበረታለች፡፡ጠቢባንን ታሰክራለች፡፡ ለዚህም ምስክሬ ራሱ የመጽሐፉ ደረሲ ማዕበል ፈጠነ ነው፡፡ መምህር ማዕበል ፈጠነ
ጥበብ ካሰከረቻቸው ወጣት ባለ ቅኔዎች ዋናው ሲሆን በቅኔው ዘረፋ ጊዜ የምር ሊወድቅ ሲንገዳገድ ብዙ ቀን ዐይቻለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ
ሐሽማል የሚባል መጽሐፍ ጽፎ እኔንም አስክሮኛል፡፡ እናንተም ከጥበቡ ተቋደሱ፡፡
No comments:
Post a Comment