ጥምቀት
ዛሬ አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፤ እስከ
ሠላሳ ዓመት ድረስ በሕዝቡ መካከል ሕጉ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገ ኖረ ይህም ማለት በሕግ መጽሐፋዊ በሕግ ፍጥረታዊ የተፈቀደውን
ሁሉ ከኃጢአት በቀር ለእኛ የሚስማማውን ማንኛውንም ያላደረገው አንዳች ነገር የለም፤ የዕለት ፅንስ መሆን፣ ዘጠኝ ወር ተፀንሶ መወለድ፣
እንደ እኛ በየጥቂቱ ማደግ፣ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት መግባት፣ ለእናቱና ለዘመዶቹ እየታዘዙ ማደግ እና የመሳሰሉትን
ሁሉ እያደረገ አደገ፡፡ ምክንያቱም ዓላማው አዳም በገባበት ሁሉ ገብቶ፣ አዳም የተቀበለውን ሁሉ ተቀብሎ አዳምን መፈለግ ስለነበረ በሄድንበት ሁሉ እየሄደ ፈለገን፡፡
ዛሬ ደግሞ የመጀመሪያው
ሰው አዳም ከኃጢአት በፊት የነበረበትን ዘመን ሲደርስ አዳም በኃጢአቱ ያጠፋትን ልጅነቱን የሚመልስለት በጥምቀት ስለሆነ ሊጠመቅ
ወደ ዮርዳኖስ ምድረ በዳ ባሕታዊው አጥማቂ ቃለ ዓዋዲ ዮሐንስ ወደሚያስተምርበት በረሃ ወረደ፤ ጊዜው የመጣበትን የመምህርነት የማዳን
ሥራውን የሚጀምርበት ጊዜ ነውና የአብ የባሕርይ ልጁ የሆነ ከአምላክ የተወለደ የባሕርይ አምላክ መሆኑን አስመስክሮ ሥራውን ሊጀምር
ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡
ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ለምን ሄደ
1. አብነት ለመሆን
ጌታ የመጣው
በትህትና ሊያገልግል ነው እንጅ እንዲያገለግሉት አለመሆኑን በዘመነ ትምህርቱ ነግሮናል ማቴ 20፥28 አዳምን የጣለችው ከዲያብሎስ
የወረሳት ትዕቢት ናት፤ ሰው አድርጎ ቢፈጥረው እግዚአብሔር እሆናለሁ ብሎ ተዋርዶ ነበርና የተዋረደባትን ትዕቢትን አርቆ ትህትናን
ለሰው ልጆች ሊያስተምር ጌታ ወደ ዮሐንስ የመምህርነት ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ በረሃ ሄደ፡፡ ሰይጣንን ድል ከሚነሣባቸው መንገዶች አንዱ
ትሕትና ነው፤ በደሙ ለሚሠራት ቤተ ክርስቲያን ዲያብሎስን ድል የምትነሣበትን የትሕትናን ትምህርት ሊያስተምራት ወደ አገልጋዩ ወደ
ዮሐንስ መገኛ ስፍራ ሂዶ መጠመቅን መረጠ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹እኔ ካንተ ልጠመቅ ይገባል እንጅ አንተ በእኔ ልትጠመቅ አይገባም››
ቢለውም ጽድቅን ያለ ትህትና መፈፀም አይቻልምና ‹‹ተው እንድ ጊዜስ ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል›› ማቴ 3፥14 ብሎ ስለ ጽድቅ
አስተማረው፡፡
እኛም እሱን
አብነት አድርገን ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ከክብራቸው የተነሣ መጥታችሁ አጥምቁን ብለው ወደ ካህናት ወደ ጳጳሳት አይልኩባቸውም እነሱ
እራሳቸው ወደ መጠመቂያው ስፍራ ሂደው ይጠመቃሉ እንጅ፡፡ ለዚህ አብነት ሊሆነን ጌታ ዮሐንስን ሂዶ አጥምቀኝ ብሎ ተጠመቀ፡፡ ዛሬም
ቤተ ክርስቲያናችን ትህትና ግብረ ክርስቶስ ስለሆነ ራስን ዝቅ በማድረግ ክርስቶስን ይመስሉት ዘንድ ምዕመናንን ታስተምራለች በመንግሥተ
ሰማያት ታላቁ ሰው ማነው ከተባለ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና የሚመላስ ሰው ነውና፡፡ ማቴ 11፥11
2. አባቶቹ እስራኤላውያን ተማርከው
የሄዱበት መንገድ ስለሆነ ነው
ናቡከደነፆር
እስራኤልን ማርኮ የወሰዳቸው በዚህ ጌታ በተጠመቀበት መንገድ በኩል ነበር፤ ተማርከው ሲወሰዱ ያስቀመጧቸው ቅዱሳት መጻሕፍትና ሌሎችም
የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ያስቀመጧቸው የቁምራን ዋሻዎችም የሚገኙት በዚህ ምድረ በዳ አካባቢ ነው፤ እንደ ሰዶም እና ገሞራ ሌሎችም በመጽሐፍ
ቅዱስ በኃጢአተኝነታቸው ጎልተው የሚታወቁ ከተሞች የሚገኙትም በዚህ አካባቢ ነው ሰይጣን ያሸነፈውን ለመርዳት የመጣው ጌታ ኃጢአት
ወደ ፀናባቸው ግፍ ወደ በዛበት መሄድ ፈቃዱ ነውና ኃጢአት ወደ በዛባቸው በኃጢአታቸውም ብዛት ሞት ወደ ተፈረደባቸው አስቀድሞ መሄድ
እና እነሱን መጎብኘትን መረጠ፤ ትምህርት የጀመረባቸውን ከተሞች እነ ኮራዚን እነ ቤተ ሳይዳን ለምን አስቀድሞ እንደ ጎበኛቸው ታላላቅ
ተዓምራትንም ለምን እንዳደረገባቸው ማሰብ ይገባናል ምክንያቱ ሌላ አይደለም ደዌ ነፍስ ፀንቶባቸው ስለነበረ ነው፡፡ ምድራውያን ሀኪሞች
ደዌ የፀናባቸውን አስቀድመው ቢያክሟቸው
ማን ይቃወማቸዋል፤ እንደዚሁም ሁሉ ግፍ የተፈፀመበትን አባቶቹ እስራኤላውያንም ተማርከው እያለቀሱ መሰንቆዎቻቸውን እየጣሉ መጻሕፍቶቻቸውን
እየቀበሩ በተጓዙበት በዚህ መንገድ ዛሬ ሰይጣን የማረከውን ዓለም ወደ ቀደመ ክብሩ የሚመልሰው ጌታ በዚህ መንገድ ተጓዘበት፡፡ ዓላማው
የተሰደደዱትን ወደ ቤታቸው መመለስ አይደለምን? ስለዚህም ስደተኞችን ተከትሎ ወረደ፡
3. ትንቢተ ነቢያትን ለመፈፀም
ነቢያት ጌታ
የሚወለድበትን ቦታ በትንቢት እንደተናገሩ ሁሉ የሚጠመቅበትንም ቦታ ነግረውናል እሱም ዮርዳኖስ ነው፤ ነቢዩ ዳዊት ዮርዳኖስን እንዲህ
ብሏታል ‹‹አቤቱ ዉኆች አዩህ ፈሩህ፣ አንችም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የሸሸሽ ምን ሆነሻል›› መዝ 114፥3-5 ብሎ የተናገረው ትንቢት የሚፈፀመው ዛሬ በዚህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በሚያደርጋት ታላቅ ሥራ ነው፡፡
4. ምሳሌው እንዲፈፀም
ምሳሌ ማለት
አካሉ እስኪመጣ ድረስ ጥላ ሁኖ ያገለገለውን የብሉይ ኪዳኑን ክንውን ማለታችን ነው፤ ያንጊዜ የተፈፀመው በሐዲስ ኪዳን ለሚፈጸመው የእግዚአብሔር ፍፁም የሆነ ማዳን ጥላ ነበረ ስለዚህም አስቀድሞ
በዚህ በዮርዳኖስ ውኃ ታጥበው ደዌ የፀናባቸው ኢዮብና ንዕማን ተፈውሰውበታል 2ነገ 5፥14 አዳምና ልጆቹም ደዌ ኃጢአት ፀንቶባቸው
ሲኖሩ ሳለ ሊያድናቸው የመጣው ክርስቶስ በየርዳኖስ መጠመቁ ሰውን ሁሉ የሚያድንባትን ጥምቀትን ሊያስጀምርን ስለሆነ ታላቅ ፈውስ
በተደረገበት በዚህ ቅዱስ ስፍራ ተጠመቀባት፡፡
በዓሉን ለምን እናከብረዋለን?
1. የጌታ ጥምቀት ለእኛ ጥምቀት በር
ከፋች ስለሆነ
ጌታ በመጠመቁ
የሚጨመርለት ክብር ኖሮት የተጠመቀ አይደለም ቅዱስ ሳዊሮስ በሃይማተ አበው ‹‹አኮ ዘነሥዐ ፀጋ በተጠምቆቱ፤ በመጠመቁ ፀጋ ያገኘበት
አይደለም›› ማለቱም ስለዚህ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ተጠመቀ ቢሉ የአይሁድን ጥምቀት ዘግቶ የእኛን አዲሲቱን ጥምቀት ሊከፍትልን ነው
ወንጌሉን የተረጎሙልን አባቶቻችንም ይህንኑ ነግረውናል፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስም ‹‹ጥምቀት የሚያስፈልገው ሆኖ የተጠመቀ አይደለም አምላክ
በሥጋ ተገልጦ ዳግመኛ መወለድን በጥምቀት ሊሰጠን ነው እንጅ እሱስ ከእኛ ከሰዎች የሚሻው ነገር የለውም›› ሳዊ. ክፍ. 9፥15
ብሎ አሁን የምንቀበላትን ጥምቀት በመጠመቁ ባርኮ የሰጠን ስጦታ እንደሆነች ይናገራል፡፡
2. ማያትን የቀደሰበት ዕለት ስለሆነ
‹‹ከውኃና ከመንፈስ
ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም›› ዮሐ 3፥6 ብሎ የሚያስተምረን ነውና እኛ የምንወለድባትን ውኃ በመጠመቁ ባረካት፤
ከዚህ በኋላ ውኃ ዕድፋችን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንም ከኃጢአቷ የምትነጻበት መንጽሒ ሆነ፤ ዛሬ የተጠመቀበትን ዮርዳኖስን በዕለተ ዐርብ
ከቀኝ ጎኑ አፍልቆ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ ከኃጢአት የሚነፁበት ከእግዚአብሔር በመንፈስ የሚወለዱበት አደረገው፤
ከዚህ አስቀድሞ
እስራኤል በዚህ በዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስትን የወረሱ ቢሆንም ሰማያዊት ርስታቸውን መውረስ አልተቻላቸውም ነበር ምክንያቱም
እስራኤልን የሚያሻግራቸው ኢያሱ ውኃውን መክፈል እንጅ ውኃውን መቀደስ የማይቻለው ስለነበረ ነው፤ ስለዚህም የተሻገረው ሕዝብ አሕዛብን
እንጅ አጋንንትን ድል መንሣት ሳይቻላቸው ቀረ፤ ከግብጽ ባርነት ተላቀው የአባቶቻቸውን ምድር ቢወርሱም ከኃጢአት ባርነት ተላቀው
ከዲያብሎስም አገዛዝ መውጣት ሳይችሉ ቀሩ፤ እኛን የሚያሻግረን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሁሉ የሚያድናቸው ስለሆነ
አስቀድሞ ሕዝቡ ሳይሻገሩ ገና ውኃውን ሊቀድስ ወደ ውኃው ወረደ፡፡
3. ምሥጢረ መለኮትን የተረዳንበት ቀን
ነው፡፡
ተሰውሮብን ከነበረው
ነገር አንዱ የመለኮት ምሥጢር ነው፤ የአምላካችን ሰው መሆን የእኛን ባሕርይ አምላክ ወደ መሆን አደረሰው አምላክም ሰው ወደ መሆን
መጥቷልና እንደ ቀደመው ሰው እንደ ሙሴ በሩቅ ከተራራ ራስ ላይ ሆኖ የምናየው ምሥጢር አይደለም አሁን የሕይወታችን ምሥጢር ክርስቶስ
በመካከላችን አለ፤ ይልቁንም በዚህ በዕለተ ጥምቀት ጌታ የጌትነቱነን ምሥጢር ፈጽሞ አጉልቶ ገለጠልን፤ የሙሴ የነቢያ መጻሕፍት ሊገልጠው
ያልተቻለው የሥላሴ የአንድነት እና የሦስትነት ምሥጢር በዮርዳኖስ ተገለጠ፤ አብ በደመና ሁኖ ሲመሰክርሰ ወልድም በክበበ ትስብእት
ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስም በርግነብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመት ተመለከትነው፡፡
አብ በደመና
ሁኖ ‹‹የምወደው ልጄ›› ባለ ጊዜ ‹‹ወልደ ዮሴፍ›› የሚሉት አይሁድ አፈሩ፤ ቅድመ ዓለም የተደረገች ከፍጥረታት አዕምሮም የራቀች
ሰማያዊ ልደቱም ተገለጠች፤ በዚህ ምክንያ በቤተ ክርስቲያናችን በዓሉ ‹‹ኢጲፋኒ›› ተብሎ ይጠራል የመገለጥ በዓል ነው፤ በምስክሩ
በዮሐንስ ፊት የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወትነት የአብ አባትነት ተገለጠ፤ ያየው ምስክሩ ዮሐንስም ‹‹እኔም አይቻለሁ እርሱም
የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ›› ዮሐ 1፥34 ብሎ መሰከረ፡፡
4. መንፈስ ቅዱስ ለሰውነታችን የተሰጠበት
ቀን ነው
አዳም ዕፀ በለስን
በበላ ጊዜ የልጅነት መንፈሱን፣ ‹‹እርሱ ሥጋ ነውና መንፈሴ ለዘለዓለም አድሮበት አይኖርም›› ዘፍ 6፥3 ባለ ጊዜ መንፈሰ ረድኤቱን
ከልክሎታል ዛሬ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት እንደሚሰጠን ለማስረዳት ይሆን ዘንድ ሰማዩን ከፍቶ በርግብ አምሳል ሲወርድ ታየ በጥንተ
ፍጥረትም ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ክንፉን ዘርግቶ አሰይፎ ይታይ ነበር ዛሬም ክንፉን ዘርግቶ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ
ላይ ሲያርፍ ታየ፡፡
በርግብ አምሳል
መሆኑም የዕርቅ ምልክት ነው፤ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ እባብ ክንፏን እየነደፋት እንቁላሏን እየበላባት ጎጆዋን ካላፈረሱባት ታግሣ
ትኖራች መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ነው ይቅር ይላል፣ ይራራል፡፡ ጌታ ለባሕርይ ልጅነቱ መጠመቅ የሚያስፈልገው ሆኖ የተጠመቀ ነው ብላ
ቤተ ክርስቲያናችን አታስተምርም በጥምቀት ከመንፈስ ቀዱስ መወለድን ይሰጠን ዘንድ ጥምቀትን ተጠምቆ አክብሯታል እንጅ፡፡ መንፈስ
ቅዱስ ለእርሱ በጥምቀት የሚሰጠው ሀብቱም አይደለም ጥንቱንም የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ሳዊሮስ ዘአንፆኪያ ‹‹እስመ መንፈስ ቅዱስ
ዚአሁ ውእቱ፤ ምንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወቱ ነውና›› ብሏል ሳዊ ክፍ. 9፥18 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ በፀጋ የሚሰጥባት
በሥላሴ ስም አምነን የምንቀበላትን ጥምቀት በጥምቀተ ክርስቶስ የተባረከች ከጥምቀተ አይሁድም የተለየች ናትና ይህን ዕለት እንዲህ
እናከብራለን፡፡