>

Monday, 6 January 2020


ታናሿ ቤተ ልሔም
እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያት በኩል ታላቁን የአምላክን ሰው የመሆን ምሥጢር ለሰው ልጆች ስለመግለጡ የተወደደው የቤተ ክርስቲያንቻን ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል ዕብ 1፥1 ለሰው ከተገለጠው ከዚህ የሚበልጥ ምሥጢር ለማንም የለውም፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያ ‹‹ የተሰወረ ምሥጢር›› ሮሜ 16፥25-26፣ ኤፌ 3፥8-9 ብሎ የሚገልጠው ከዚህ አስቀድሞ ከተገለጠው ከዚህም በኋላ ከሚገለጠው ዐይን ካላየው፣ ሕሊና አስቦ ከማይደርሰው ታላቅ ምሥጢር ይልቅ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፡፡
ምሥጢሩ ታላቅ ስለሆነ ነው በስም የታወቀ እና ተርታ መልአክ ሳይሆን ሊቀ መላእክት ገብርኤል የተላከው፡- በተላከም ጊዜ እንደ ነቢያት በሕልም ወይም በራዕይ አይደለም ዳን 9፥21፣ እንደ እነ ማኑሔ በሰው አምሳል ሁኖ አይደለም መሳ 13፥6፣ እንደ ዘካርያስ ተቆጥቶ እንደ ኢያሱ ሰይፍ መዞ ኢያ 5፥15፣ ሉቃ 1፥11 ያይደለ ብሩኅ ገጽ ያለው የደስታ የምሥራች መልአክ ወደ እርሷ መጥቶ የጌታን ሰው የመሆን ምሥጢር እናቱ ትሆን ዘንድ ለመረጣት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ገለፀላት፡፡ ዓለም ሲጠብቀው የነበረውን ይህን ምሥጢር በማንኛውም ቦታ ሆነው ሊሰሙት አይገባምና እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታ ከመልአኩ ጋር ተነጋግራ ተረዳችው፡፡ ምሥጢሩ ታላቅ ነውና በእምነት ተቀበለችው፡፡
እመቤታችን በእምነት ‹‹እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› ብላ ስትቀበለው ጀምሮ ሰማይና ምድር በማኅፀነ ማርያም ተዋሓዱ፤
§  ዕርቅ በዚህ ጊዜ ተጀመረ፤ የላይኛውን የመለኮት ባሕርይ ታችኛው ሰው ወረሰ፤
§  የታችኛውን የሰው ባሕርይ የላይኛው መለኮት በተዋሕዶ ገንዘብ አደረገ፤
§  የዓለም ስፋት ለሥጋ አልሰፋበትም፤
§  የማኅፀነ ማርያምም ጥበት ለመለኮት አልጠበበትም፤
 የፍቅር ወግ እንዲህ ነውና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ የመለኮት ባሕርይ ራሱን ዝቅ አድርጎ የባሪያውን የሰውን ባሕርይ ለበሰ፤ ባሪያ የነበረው የሰው ባሕርይም የጌታን ባሕርይ የጌታን አካል በተዋሕዶ አገኘ፡፡
ይህ ቀን የጠፋው ሰው ተፈልጎ የተገኘበት ቀን ነው፤ የሚሞትበት ምክንያተ ኃጢአት በሰውነቱ የሌለበት፣ ኃጢአት ያልያዘው፣ ሰይጣን ያልተቆራኘው አዲሱ ሰው ዛሬ ተወለደ፡፡
ኃጢአት ከክብር ያሳነሰው ሰው ነገሥታት ያሳነሷት (የረሷት) ታናሿ ቤተ ልሔም የመጎብኘታቸው ቀን ዛሬ ነው፡፡
የይሁዳ ነገሥታት ከሚነግሡባቸው አህጉር ብትበልጥ እንጅ አታንስም ተብሎ  በነቢይ የተመሰከረላት ሚክ 5፥2 ቀድሞ ዘሩባቤል ስደተኞችን እስራኤልን ወደ ርስታቸው ሲመልሳቸው ዜና መንግሥቱን ያስነገረባት፣ እስራኤል ከፋርስ እና ከባቢሎን ተመልሰው ያረፉባት ምድር ናት - የኤፍራታ ዕጻ ቤተ ልሔም፡፡ ዛሬም የዳዊት ልጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደባት፡፡ ለይሁዳ የተገባለት የመንግሥት ቃል ኪዳን ዘፍ 49፥8-12 በቤተ ልሔማዊው ሰው በዳዊት ከ600 ዓመታት በኋላ ይፈፀም ዘንድ ንጉሡ ዳዊት የተቀባው በዚህች ከተማ ነበር 1 ሳሙ 16፥13 ነገር ግን የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም ማንም ጠብቆ ያቆያት የለም፡፡ ለዚያውም ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱርም ተጥሎ አገኘነው›› ተብሎ ተስፋ ተነግሮላት ነበር፡፡
ልቡ በተስፋ የሚፀና ትውልድ ከሌለ ተስፋ ምን ያርጋል፤ እነሆ የተናቀች እና የጠፋች ከተማ ሆና ሳለ ነው ጌታ በቤተ ልሔም የተወለደ፡፡ ታናሿ ቤተ ልሔም የይሁዳ ነገሥታት ከሚነግሡባቸው አህጉር በለጠች፤ እንደ ዳዊት የአዳምን መንግሥት የሚመልስ የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደባት፤ እስራኤል ከስደት ተመልሰው መንግሥት የጀመሩባት ቤተ ልሔም ዛሬም የአይሁድ ንጉሥ ተወለደባት፤ በኃጢአቱ ምክንያት ከፍጥረታት ሁሉ አንሶ እና ተዋርዶ የነበረው የሰው ባሕርይ ነገሥታት ገበሩለት መላእክት ዘመሩለት እንስሳት የተቻላቸውን እጅ መንሻ አቀረቡለት ከዋክብት ሰውን እየመሩ አመጡለት፡፡ ታናሿ ቤተ ልሔም በዓለመ ሰማይ በዓለመ ምድር ያሉ ፍጥረታት ተሰብስበው ዘመሩባት፡፡  
ዛሬም ታናሿ ቤተ ልሔም ቤተ ክርስቲያን እንደ ተናቀች አትቀርም፤ በቤተ መንግሥት ሆነው የሚመክሩባት ያልፋሉ፤ ሰይፍ መዝዘው በየበረሃው የሚያንከራትቷት በሰይፍ ይጠፋሉ፤ ይሄን እናምናለን! በረሃው ቢጠበንም አሸዋው ቢያቃጥለንም ሔሮድሳውያን ቢከተሉንም ከሔሮድስ ቀድማ የምትሞት ቤተ ክርስያን የለችንም፡፡
ሔሮድሳውያን ሆይ!   
የቤተ ክርስቲያን አምላክ በግርግም ተጥሎ ብታዩት አትናቁት በሰማይ የብርሃን ቤተ መቅደስ አለውና፡፡ ቅጠል ቢለብስ በጨርቅ ቢጠቀለል ምንም አይደለም፤ ይህን ያደረገው ስለ ፍቅር ነውና፡፡ ከነገሥታት እጅ መንሻ ስለተቀበለ እንደ እናንተ አማልክት ድሀ እንዳይመስላችሁ ስለ ድህነቱ ሊያለብሱት ሳይሆን ስለ አምላክነቱ ሊከብሩበት ሁለት ዓመት ደጅ ጠንተው እንዳቀረቡለት እንዳትረሱ፡፡
ነገሥታት ሆይ! የማታድኑትን ሕዝብ ትገዛላችሁ፤ ላትጠቅሙት ታስገብሩታላችሁ፤ ከጠላት ሰይጣን ነጻ ላታደርጉት ሰራዊት ትሰብስባላችሁ፤ ሞትና መቃብርን መግደል ላይቻላችሁ በከንቱ ትዘምታላችሁ፤ በክንድ በምትለካ መቃብር ውስጥ ማደር ላይቀርላችሁ ሀገር አልበቃ እስኪላችሁ ድረስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ እየዞራችሁ መንግሥት ታዳርሳላችሁ፡፡
ዛሬ ግን ወደ ልባችሁ ተመለሱ! ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ሰይጣንን የሚገድልላቸው ጽድቅን የሚያለብሳቸው ያለ ሰራዊት ብቻውን ሞትና መቃብርን ድል የሚነሣላቸው ጌታ ተወልዷል፤ ሕዝቡ እንዲገዙለት ፍቀዱላቸው፡፡ የሰይጣንን ምክር ሊያፈርስ ተገልጧልና በቤተ ምንግሥት ተቀምጣችሁ የምትመክሩትን ምክራችሁን ተዉ ይበቃል! አሁን መላእክት ተልከዋል ድሆች የምሥራቹን ሰምተዋል፤ አትጠራጠሩ እግዚአብሔር ከዋክብትንም ቢሆን ልኮ ሕዝቡን ነጻ ማውጣቱ የማይቀር ነው እግዚአብሔር ባሕርዩን የወደደለትን ሰዉን ያኽል ታላቅ ፍጡር ሊኮንነው የሚገባ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ሊኖር አይገባም፡፡

ጌታ ሆይ! ጥንትም ቢሆን ያለ ነገሥታት ፈቃድ ሰው ሆነህ ሕዝብህን አዳንህ አሁንም ቢሆን ሕዝብህን ተመልከት፤ ነገሥታቶቻችንን ገሥጻቸው ለሕዝቡ የማይጠቅሙትን እንደ ሔሮድስ ቅጣቸው፤      
እንኳን አደረሳችሁ

No comments: