የከተራን በዓል በከተራ
በመጀመሪያ እግዚአብሔር በምድር ላይ ካስቀመጠው ነገር አንዱ ውኃ እንደነበረ የመጀመሪያው መጽሐፍ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ተጽፎ እናነበዋለን፤ ‹‹ወጽልመት መልዕልተ ቀላይ፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ›› ይላል፡፡ በትምህርተ ሃይማኖት በጥልቁ ላይ የነበረው የጨለማው ምሥጢር ፍጡራን ተመራምረው ስለማይደርሱበት የእግዚአብሔር ባሕርይ ምሳሌ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ ›› መዝ 17፥11 ብሎ የዘመረው መዝሙር ባሕርዩን የማይመረመር አደረገው ተብሎ በሊቃውንት እንደ ተተረጎመ፡፡ በውኃ ስለሚሰጠን የእግዚአብሔር ፀጋ ብንመረምር ስንቱን እንጨርሰዋለን? በጥምቀት የሚሰጠንን የማይታይ ፀጋ አስቀድሞ በዕለተ ፍጥረት በጥልቁ ላይ በነበረው ጨለማ ገልፀልን፤ የማይመረመር ይህን ጥልቅ ባሕርዩን በጥምቀት ስንካፈል እንኖራለን 2 ጴጥ 1፥4
ደግሞ ነገሩን ግልጽ የሚያደርግልን ከዚህ ቀጥሎ ያለው ንባብ ነው፤ ‹‹ወመንፈሰ እግዚአብሔር ይጼልል መልዕልተ ውዕቱ ማይ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ሰፍፎ ነበር›› ዘፍ 1፥2 ሲል ፀጋ መንፈስ ቅዱስ በውኃው ላይ እንዳረፈ ለምዕመናንም እደሚሰጥ ያመላክታል ይህን የኦሪት ቃል የብሉይ ኪዳን መምህራን በጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ዓለም በተፈጠረችበት በመጀመሪያው ቀን መንፈስ ቅዱስ በፀጋው ጋርዶት ይታይ የነበረው ውኃ በኋላም ጠፈር ተብሎ ለምድር አክሊል የሆናት እርሱ ነው፤ ጠፈር ማለት የፀና ውኃ ማለት ነውና፤
ዛሬ አምላካችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ዓለም ውስጥ የእኛን ሥጋ ለብሶ ከተወለደ ሠላሳ ዓመት ሞላው፤ እስከ ሠላሳኛ ዓመቱ ሕገ ኦሪትን እየፈፀመ፣ በሰዎች ሥርዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲወጡ እየወጣ፣ በዓላትን ሲያከብሩ አብሮ እያከበረ በሊቃውንቶቻቸው ዘንድ እየተገኘ፣ እየጠየቃቸው፣ እያዳመጣቸው ከኃጢአት በቀር ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ እያደረገ አብሯቸው ተመላለሰ፡፡ መላእክት የሚያገለግሉት ጌታ ለእናቱ እና ለዘመዶቹ ሁሉ ሲያገለግላቸው ኖረ፤ አሁን ግን አዳም ሲፈጠር የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ስለነበረ ጌታም ፍፁም አዳምን ሲያኽል የመምህርነት ሥራውን የሚጀምርበት ዘመን ደረሰ፤ ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ያስመሰክር ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
በዚያ ዘመን ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ያጠምቅ ስለነበረ ሕዝቡ እየወጡ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀትን ከዮሐንስ ይጠመቁ ነበር፤ ጌታም ወደ ዮርዳኖስ የመጣው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ያንጊዜ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ መምጣት ይመሰክር ነበር፤ የዮሐንስ መምጣት ዓላማው ሕዝቡን ከክርስቶስ ጋር ለማገናኘት እንጅ እርሱ ክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ካህን አልነበረምና ሕዝቡን ለንስሐ ጥምቀት እያጠመቀ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣው፣ ነገር ግን አምላክ ነውና ከእርሱ በፊት ስለነበረው አምላክ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይነግራቸው ነበር፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ትዕቢት ምክንያት የገባውን ኃጢአት በእርሱ ትህትና ያጠፋልን ዘንድ በትህትና ወደ ዮሐንስ ሊጠመቅ ሄደ፤ ይህ ለዮሐንስ ልዕልና ለጌታ ደግሞ ትህትና ነው፤ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ሲባል ይኖራል ጌታም በባሪያው እጅ ተጠመቀ እየተባለ ሲነገርለት ይኖራል፤
ዮሐንስ ከዮርዳኖስ ማዶ ባለች በሔኖን ወንዝ የንስሐ ጥምቀት በሚሰጥበት ቀራጮችና ጭፍሮች በሚጠመቁበት ጉባኤ ጌታ አብሮ ሌሊቱን ተራ ሲጠብቅ አደረ፤ በኃጢአታችን ምክንያት በተጣልንበት ዓለም ኃጢአት የነገሠበት ባሕርያችንን ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኗልና ጻድቃን ነን ብለው የሚያስቡ የአይሁድ ካህናት ከሚገኙበት ጉባኤ ይልቅ ኃጢአታቸውን አምነው ለንስሐ የቀረቡት ቀራጨችና ጭፍሮች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ ጌታ ተገኘ፡፡
የጌታ ሰው መሆን ዓላማው ከኃጢአተኞች እንደ አንዱ ተቆጥሮ እኛን ኃጢአት ከሌለባቸው መላእክት ጋር እንድንቆጠር ማድረግ ነውና በኃጢአታቸው ምክንያት ንስሐ ግቡ እየተባሉ ከሚገሠፁት ሕዝብ መካከል እንዳንዱ ሆኖ አደረ፤ ዮሐንስ ‹‹እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ አለ›› ዮሐ 1፥6 ብሎ ነገራቸው እሱ ያውቀዋል እነሱ ግን አያውቁትምና፡፡
ሕዝቡ ተጠምቀው ሲጨርሱ ጌታ ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው ዮሐንስም ወንጌላዊ እንደተናገረው ‹‹እኔ ባንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጅ አንተ በእኔ እጅ ልትጠመቅ አይገባም›› ማቴ 3፥14 ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን ‹‹ተው አንድ ጊዜስ ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል›› ቢለው እሺ ብሎ ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ ወረዱ፤ ትንቢቱ የተነገረው በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ስለነበረ ነቢያት ትንቢት ወደተናገሩለት ዮርዳኖስ ሄዱ፡፡
በዚያውም ላይ ኢዮብ የተፈወሰበት፣ ንዕማን ከለምፁ የነጻበት ይህ የፈውስ ውኃ ዛሬም ዓለሙን ከኃጢአቱ የሚያድነው ጌታ በዚህ ውኃ ተጠምቆ ውኃን ለሰው ልጆች የመዳን መንገድ መጀመሪያ ሊያደርጋት ዮርዳኖስን መረጠ፡፡ አባቶቹ እስራኤል በዚህ መንገድ አልፈው ነው የቃልኪዳኗን ምድር ከነዓንን የወረሱት፤ የእስራኤሉ ኢያሱ ይህን ባደረገበት በዚህ ውኃ የእኛ ኢያሱ ኢየሱስ ክርስስ የሰማዩን ርስት በጥምቀት
ሊያካፍለን ወደ ዮርዳኖስ መጣ፤
ያንጊዜ ዮርዳኖስ በእሳትና በሰማያውያን ሰራዊት በቅዱሳን መላእክት ተከበበች በዓሉ ከተራ የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው፤ ከተረ ማለት በግእዙ ከበበ ማለት ነውና፡፡
የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሆይ!
ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ከተራ ላይ ናት፤ እንደ ዮርዳኖስ በሚዘምሩ መላእክት፣ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ በሆነው እሳት እንዳይመስላችሁ ነፍስን በሚያጠፉ ሰዎች ተከባለች፤ ሕዝቡን ከዘለዓለም እሳት ሊያድናቸው የመጣው ጌታ ዛሬ ዮርዳኖስን በእሳት እንድትከበብ አድርጓታል ቅዱስ ያሬድ ‹‹ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ ማይ ኀበ የሐውር ፀበቦ፤ እሳቱ ውኃውን ከበበው ውኃውም የሚሄድበት ጠበበው›› ይላል በሰውኛ ግስ ሲገለጽ በእርግጥም ዮርዳኖስ እግዚአብሔር በሥጋ ሊጠመቅ ሲመጣ መንገዱን ከመሄድ ተከለከለ፡፡ እንዲህ ውኆች በሚፈሩት ግርማ ተገልጦ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በነፍሰ በላዎች ተከባለች፤ የከተራን በዓል በከተራ እያከበርን ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች በዚህ የነጻት በዓላችን ነጻነታቸውን አጥተው የጥምቀተ ባሕር ቦታቸውን ተነጥቀው በበዓሉን ማክበር ከማይችሉት ጋር አብረን እንዳለን ሆነን በኃዘን ልናስባቸው ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment