>

Tuesday, 21 January 2020


ጥምቀት
ዛሬ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፤ እስከ ሠላሳ ዓመት ድረስ በሕዝቡ መካከል ሕጉ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገ ኖረ ይህም ማለት በሕግ መጽሐፋዊ በሕግ ፍጥረታዊ የተፈቀደውን ሁሉ ከኃጢአት በቀር ለእኛ የሚስማማውን ማንኛውንም ያላደረገው አንዳች ነገር የለም፤ የዕለት ፅንስ መሆን፣ ዘጠኝ ወር ተፀንሶ መወለድ፣ እንደ እኛ በየጥቂቱ ማደግ፣ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት መግባት፣ ለእናቱና ለዘመዶቹ እየታዘዙ ማደግ እና የመሳሰሉትን ሁሉ እያደረገ አደገ፡፡ ምክንያቱም ዓላማው አዳም በገባበት ሁሉ ገብቶ፣ አዳም የተቀበለውን ሁሉ ተቀብሎ አዳምን መፈለግ ስለነበረ  በሄድንበት ሁሉ እየሄደ ፈለገን፡፡
ዛሬ ደግሞ የመጀመሪያው ሰው አዳም ከኃጢአት በፊት የነበረበትን ዘመን ሲደርስ አዳም በኃጢአቱ ያጠፋትን ልጅነቱን የሚመልስለት በጥምቀት ስለሆነ ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ምድረ በዳ ባሕታዊው አጥማቂ ቃለ ዓዋዲ ዮሐንስ ወደሚያስተምርበት በረሃ ወረደ፤ ጊዜው የመጣበትን የመምህርነት የማዳን ሥራውን የሚጀምርበት ጊዜ ነውና የአብ የባሕርይ ልጁ የሆነ ከአምላክ የተወለደ የባሕርይ አምላክ መሆኑን አስመስክሮ ሥራውን ሊጀምር ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡
ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ለምን ሄደ
1.      አብነት ለመሆን
ጌታ የመጣው በትህትና ሊያገልግል ነው እንጅ እንዲያገለግሉት አለመሆኑን በዘመነ ትምህርቱ ነግሮናል ማቴ 20፥28 አዳምን የጣለችው ከዲያብሎስ የወረሳት ትዕቢት ናት፤ ሰው አድርጎ ቢፈጥረው እግዚአብሔር እሆናለሁ ብሎ ተዋርዶ ነበርና የተዋረደባትን ትዕቢትን አርቆ ትህትናን ለሰው ልጆች ሊያስተምር ጌታ ወደ ዮሐንስ የመምህርነት ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ በረሃ ሄደ፡፡ ሰይጣንን ድል ከሚነሣባቸው መንገዶች አንዱ ትሕትና ነው፤ በደሙ ለሚሠራት ቤተ ክርስቲያን ዲያብሎስን ድል የምትነሣበትን የትሕትናን ትምህርት ሊያስተምራት ወደ አገልጋዩ ወደ ዮሐንስ መገኛ ስፍራ ሂዶ መጠመቅን መረጠ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹እኔ ካንተ ልጠመቅ ይገባል እንጅ አንተ በእኔ ልትጠመቅ አይገባም›› ቢለውም ጽድቅን ያለ ትህትና መፈፀም አይቻልምና ‹‹ተው እንድ ጊዜስ ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል›› ማቴ 3፥14 ብሎ ስለ ጽድቅ አስተማረው፡፡
እኛም እሱን አብነት አድርገን ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ከክብራቸው የተነሣ መጥታችሁ አጥምቁን ብለው ወደ ካህናት ወደ ጳጳሳት አይልኩባቸውም እነሱ እራሳቸው ወደ መጠመቂያው ስፍራ ሂደው ይጠመቃሉ እንጅ፡፡ ለዚህ አብነት ሊሆነን ጌታ ዮሐንስን ሂዶ አጥምቀኝ ብሎ ተጠመቀ፡፡ ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን ትህትና ግብረ ክርስቶስ ስለሆነ ራስን ዝቅ በማድረግ ክርስቶስን ይመስሉት ዘንድ ምዕመናንን ታስተምራለች በመንግሥተ ሰማያት ታላቁ ሰው ማነው ከተባለ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና የሚመላስ ሰው ነውና፡፡ ማቴ 11፥11
2.     አባቶቹ እስራኤላውያን ተማርከው የሄዱበት መንገድ ስለሆነ ነው
ናቡከደነፆር እስራኤልን ማርኮ የወሰዳቸው በዚህ ጌታ በተጠመቀበት መንገድ በኩል ነበር፤ ተማርከው ሲወሰዱ ያስቀመጧቸው ቅዱሳት መጻሕፍትና ሌሎችም የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ያስቀመጧቸው የቁምራን ዋሻዎችም የሚገኙት በዚህ ምድረ በዳ አካባቢ ነው፤ እንደ ሰዶም እና ገሞራ ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ በኃጢአተኝነታቸው ጎልተው የሚታወቁ ከተሞች የሚገኙትም በዚህ አካባቢ ነው ሰይጣን ያሸነፈውን ለመርዳት የመጣው ጌታ ኃጢአት ወደ ፀናባቸው ግፍ ወደ በዛበት መሄድ ፈቃዱ ነውና ኃጢአት ወደ በዛባቸው በኃጢአታቸውም ብዛት ሞት ወደ ተፈረደባቸው አስቀድሞ መሄድ እና እነሱን መጎብኘትን መረጠ፤ ትምህርት የጀመረባቸውን ከተሞች እነ ኮራዚን እነ ቤተ ሳይዳን ለምን አስቀድሞ እንደ ጎበኛቸው ታላላቅ ተዓምራትንም ለምን እንዳደረገባቸው ማሰብ ይገባናል ምክንያቱ ሌላ አይደለም ደዌ ነፍስ ፀንቶባቸው ስለነበረ ነው፡፡ ምድራውያን ሀኪሞች ደዌ የፀናባቸውን አስቀድመው ቢያክሟቸው ማን ይቃወማቸዋል፤ እንደዚሁም ሁሉ ግፍ የተፈፀመበትን አባቶቹ እስራኤላውያንም ተማርከው እያለቀሱ መሰንቆዎቻቸውን እየጣሉ መጻሕፍቶቻቸውን እየቀበሩ በተጓዙበት በዚህ መንገድ ዛሬ ሰይጣን የማረከውን ዓለም ወደ ቀደመ ክብሩ የሚመልሰው ጌታ በዚህ መንገድ ተጓዘበት፡፡ ዓላማው የተሰደደዱትን ወደ ቤታቸው መመለስ አይደለምን? ስለዚህም ስደተኞችን ተከትሎ ወረደ፡
3.     ትንቢተ ነቢያትን ለመፈፀም
ነቢያት ጌታ የሚወለድበትን ቦታ በትንቢት እንደተናገሩ ሁሉ የሚጠመቅበትንም ቦታ ነግረውናል እሱም ዮርዳኖስ ነው፤ ነቢዩ ዳዊት ዮርዳኖስን እንዲህ ብሏታል ‹‹አቤቱ ዉኆች አዩህ ፈሩህ፣ አንችም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የሸሸሽ ምን ሆነሻል›› መዝ 114፥3-5  ብሎ የተናገረው ትንቢት የሚፈፀመው ዛሬ በዚህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያደርጋት ታላቅ ሥራ ነው፡፡
4.     ምሳሌው እንዲፈፀም
ምሳሌ ማለት አካሉ እስኪመጣ ድረስ ጥላ ሁኖ ያገለገለውን የብሉይ ኪዳኑን ክንውን ማለታችን ነው፤ ያንጊዜ የተፈፀመው በሐዲስ ኪዳን  ለሚፈጸመው የእግዚአብሔር ፍፁም የሆነ ማዳን ጥላ ነበረ ስለዚህም አስቀድሞ በዚህ በዮርዳኖስ ውኃ ታጥበው ደዌ የፀናባቸው ኢዮብና ንዕማን ተፈውሰውበታል 2ነገ 5፥14 አዳምና ልጆቹም ደዌ ኃጢአት ፀንቶባቸው ሲኖሩ ሳለ ሊያድናቸው የመጣው ክርስቶስ በየርዳኖስ መጠመቁ ሰውን ሁሉ የሚያድንባትን ጥምቀትን ሊያስጀምርን ስለሆነ ታላቅ ፈውስ በተደረገበት በዚህ ቅዱስ ስፍራ ተጠመቀባት፡፡
በዓሉን ለምን እናከብረዋለን?
1.      የጌታ ጥምቀት ለእኛ ጥምቀት በር ከፋች ስለሆነ
ጌታ በመጠመቁ የሚጨመርለት ክብር ኖሮት የተጠመቀ አይደለም ቅዱስ ሳዊሮስ በሃይማተ አበው ‹‹አኮ ዘነሥዐ ፀጋ በተጠምቆቱ፤ በመጠመቁ ፀጋ ያገኘበት አይደለም›› ማለቱም ስለዚህ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ተጠመቀ ቢሉ የአይሁድን ጥምቀት ዘግቶ የእኛን አዲሲቱን ጥምቀት ሊከፍትልን ነው ወንጌሉን የተረጎሙልን አባቶቻችንም ይህንኑ ነግረውናል፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስም ‹‹ጥምቀት የሚያስፈልገው ሆኖ የተጠመቀ አይደለም አምላክ በሥጋ ተገልጦ ዳግመኛ መወለድን በጥምቀት ሊሰጠን ነው እንጅ እሱስ ከእኛ ከሰዎች የሚሻው ነገር የለውም›› ሳዊ. ክፍ. 9፥15 ብሎ አሁን የምንቀበላትን ጥምቀት በመጠመቁ ባርኮ የሰጠን ስጦታ እንደሆነች ይናገራል፡፡
2.     ማያትን የቀደሰበት ዕለት ስለሆነ
‹‹ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም›› ዮሐ 3፥6 ብሎ የሚያስተምረን ነውና እኛ የምንወለድባትን ውኃ በመጠመቁ ባረካት፤ ከዚህ በኋላ ውኃ ዕድፋችን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንም ከኃጢአቷ የምትነጻበት መንጽሒ ሆነ፤ ዛሬ የተጠመቀበትን ዮርዳኖስን በዕለተ ዐርብ ከቀኝ ጎኑ አፍልቆ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ ከኃጢአት የሚነፁበት ከእግዚአብሔር በመንፈስ የሚወለዱበት አደረገው፤
ከዚህ አስቀድሞ እስራኤል በዚህ በዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስትን የወረሱ ቢሆንም ሰማያዊት ርስታቸውን መውረስ አልተቻላቸውም ነበር ምክንያቱም እስራኤልን የሚያሻግራቸው ኢያሱ ውኃውን መክፈል እንጅ ውኃውን መቀደስ የማይቻለው ስለነበረ ነው፤ ስለዚህም የተሻገረው ሕዝብ አሕዛብን እንጅ አጋንንትን ድል መንሣት ሳይቻላቸው ቀረ፤ ከግብጽ ባርነት ተላቀው የአባቶቻቸውን ምድር ቢወርሱም ከኃጢአት ባርነት ተላቀው ከዲያብሎስም አገዛዝ መውጣት ሳይችሉ ቀሩ፤ እኛን የሚያሻግረን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሁሉ የሚያድናቸው ስለሆነ አስቀድሞ ሕዝቡ ሳይሻገሩ ገና ውኃውን ሊቀድስ ወደ ውኃው ወረደ፡፡
3.     ምሥጢረ መለኮትን የተረዳንበት ቀን ነው፡፡
ተሰውሮብን ከነበረው ነገር አንዱ የመለኮት ምሥጢር ነው፤ የአምላካችን ሰው መሆን የእኛን ባሕርይ አምላክ ወደ መሆን አደረሰው አምላክም ሰው ወደ መሆን መጥቷልና እንደ ቀደመው ሰው እንደ ሙሴ በሩቅ ከተራራ ራስ ላይ ሆኖ የምናየው ምሥጢር አይደለም አሁን የሕይወታችን ምሥጢር ክርስቶስ በመካከላችን አለ፤ ይልቁንም በዚህ በዕለተ ጥምቀት ጌታ የጌትነቱነን ምሥጢር ፈጽሞ አጉልቶ ገለጠልን፤ የሙሴ የነቢያ መጻሕፍት ሊገልጠው ያልተቻለው የሥላሴ የአንድነት እና የሦስትነት ምሥጢር በዮርዳኖስ ተገለጠ፤ አብ በደመና ሁኖ ሲመሰክርሰ ወልድም በክበበ ትስብእት ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስም በርግነብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመት ተመለከትነው፡፡
አብ በደመና ሁኖ ‹‹የምወደው ልጄ›› ባለ ጊዜ ‹‹ወልደ ዮሴፍ›› የሚሉት አይሁድ አፈሩ፤ ቅድመ ዓለም የተደረገች ከፍጥረታት አዕምሮም የራቀች ሰማያዊ ልደቱም ተገለጠች፤ በዚህ ምክንያ በቤተ ክርስቲያናችን በዓሉ ‹‹ኢጲፋኒ›› ተብሎ ይጠራል የመገለጥ በዓል ነው፤ በምስክሩ በዮሐንስ ፊት የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወትነት የአብ አባትነት ተገለጠ፤ ያየው ምስክሩ ዮሐንስም ‹‹እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ›› ዮሐ 1፥34 ብሎ መሰከረ፡፡
4.     መንፈስ ቅዱስ ለሰውነታችን የተሰጠበት ቀን ነው
አዳም ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የልጅነት መንፈሱን፣ ‹‹እርሱ ሥጋ ነውና መንፈሴ ለዘለዓለም አድሮበት አይኖርም›› ዘፍ 6፥3 ባለ ጊዜ መንፈሰ ረድኤቱን ከልክሎታል ዛሬ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት እንደሚሰጠን ለማስረዳት ይሆን ዘንድ ሰማዩን ከፍቶ በርግብ አምሳል ሲወርድ ታየ በጥንተ ፍጥረትም ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ክንፉን ዘርግቶ አሰይፎ ይታይ ነበር ዛሬም ክንፉን ዘርግቶ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ ሲያርፍ ታየ፡፡
በርግብ አምሳል መሆኑም የዕርቅ ምልክት ነው፤ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ እባብ ክንፏን እየነደፋት እንቁላሏን እየበላባት ጎጆዋን ካላፈረሱባት ታግሣ ትኖራች መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ነው ይቅር ይላል፣ ይራራል፡፡ ጌታ ለባሕርይ ልጅነቱ መጠመቅ የሚያስፈልገው ሆኖ የተጠመቀ ነው ብላ ቤተ ክርስቲያናችን አታስተምርም በጥምቀት ከመንፈስ ቀዱስ መወለድን ይሰጠን ዘንድ ጥምቀትን ተጠምቆ አክብሯታል እንጅ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለእርሱ በጥምቀት የሚሰጠው ሀብቱም አይደለም ጥንቱንም የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ሳዊሮስ ዘአንፆኪያ ‹‹እስመ መንፈስ ቅዱስ ዚአሁ ውእቱ፤ ምንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወቱ ነውና›› ብሏል ሳዊ ክፍ. 9፥18 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ በፀጋ የሚሰጥባት በሥላሴ ስም አምነን የምንቀበላትን ጥምቀት በጥምቀተ ክርስቶስ የተባረከች ከጥምቀተ አይሁድም የተለየች ናትና ይህን ዕለት እንዲህ እናከብራለን፡፡ 

Sunday, 19 January 2020



የከተራን በዓል በከተራ
በመጀመሪያ እግዚአብሔር በምድር ላይ ካስቀመጠው ነገር አንዱ ውኃ እንደነበረ የመጀመሪያው መጽሐፍ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ተጽፎ እናነበዋለን፤ ‹‹ወጽልመት መልዕልተ ቀላይ፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ›› ይላል፡፡ በትምህርተ ሃይማኖት በጥልቁ ላይ የነበረው የጨለማው ምሥጢር ፍጡራን ተመራምረው ስለማይደርሱበት የእግዚአብሔር ባሕርይ ምሳሌ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ ›› መዝ 1711 ብሎ የዘመረው መዝሙር ባሕርዩን የማይመረመር አደረገው ተብሎ በሊቃውንት እንደ ተተረጎመ፡፡ በውኃ ስለሚሰጠን የእግዚአብሔር ፀጋ ብንመረምር ስንቱን እንጨርሰዋለን? በጥምቀት የሚሰጠንን የማይታይ ፀጋ አስቀድሞ በዕለተ ፍጥረት በጥልቁ ላይ በነበረው ጨለማ ገልፀልን፤ የማይመረመር ይህን ጥልቅ ባሕርዩን በጥምቀት ስንካፈል እንኖራለን 2 ጴጥ 14
ደግሞ ነገሩን ግልጽ የሚያደርግልን ከዚህ ቀጥሎ ያለው ንባብ ነው፤ ‹‹ወመንፈሰ እግዚአብሔር ይጼልል መልዕልተ ውዕቱ ማይ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ሰፍፎ ነበር›› ዘፍ 12 ሲል ፀጋ መንፈስ ቅዱስ በውኃው ላይ እንዳረፈ ለምዕመናንም እደሚሰጥ ያመላክታል ይህን የኦሪት ቃል የብሉይ ኪዳን መምህራን በጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ዓለም በተፈጠረችበት በመጀመሪያው ቀን መንፈስ ቅዱስ በፀጋው ጋርዶት ይታይ የነበረው ውኃ በኋላም ጠፈር ተብሎ ለምድር አክሊል የሆናት እርሱ ነው፤ ጠፈር ማለት የፀና ውኃ ማለት ነውና፤
ዛሬ አምላካችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ዓለም ውስጥ የእኛን ሥጋ ለብሶ ከተወለደ ሠላሳ ዓመት ሞላው፤ እስከ ሠላሳኛ ዓመቱ ሕገ ኦሪትን እየፈፀመ፣ በሰዎች ሥርዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲወጡ እየወጣ፣ በዓላትን ሲያከብሩ አብሮ እያከበረ በሊቃውንቶቻቸው ዘንድ እየተገኘ፣ እየጠየቃቸው፣ እያዳመጣቸው ከኃጢአት በቀር ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ እያደረገ አብሯቸው ተመላለሰ፡፡ መላእክት የሚያገለግሉት ጌታ ለእናቱ እና ለዘመዶቹ ሁሉ ሲያገለግላቸው ኖረ፤ አሁን ግን አዳም ሲፈጠር የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ስለነበረ ጌታም ፍፁም አዳምን ሲያኽል የመምህርነት ሥራውን የሚጀምርበት ዘመን ደረሰ፤ ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ያስመሰክር ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
በዚያ ዘመን ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ያጠምቅ ስለነበረ ሕዝቡ እየወጡ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀትን ከዮሐንስ ይጠመቁ ነበር፤ ጌታም ወደ ዮርዳኖስ የመጣው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ያንጊዜ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ መምጣት ይመሰክር ነበር፤ የዮሐንስ መምጣት ዓላማው ሕዝቡን ከክርስቶስ ጋር ለማገናኘት እንጅ እርሱ ክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ካህን አልነበረምና ሕዝቡን ለንስሐ ጥምቀት እያጠመቀ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣው፣ ነገር ግን አምላክ ነውና ከእርሱ በፊት ስለነበረው አምላክ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይነግራቸው ነበር፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ትዕቢት ምክንያት የገባውን ኃጢአት በእርሱ ትህትና ያጠፋልን ዘንድ በትህትና ወደ ዮሐንስ ሊጠመቅ ሄደ፤ ይህ ለዮሐንስ ልዕልና ለጌታ ደግሞ ትህትና ነው፤ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ሲባል ይኖራል ጌታም በባሪያው እጅ ተጠመቀ እየተባለ ሲነገርለት ይኖራል፤
ዮሐንስ ከዮርዳኖስ ማዶ ባለች በሔኖን ወንዝ የንስሐ ጥምቀት በሚሰጥበት ቀራጮችና ጭፍሮች በሚጠመቁበት ጉባኤ ጌታ አብሮ ሌሊቱን ተራ ሲጠብቅ አደረ፤ በኃጢአታችን ምክንያት በተጣልንበት ዓለም ኃጢአት የነገሠበት ባሕርያችንን ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኗልና ጻድቃን ነን ብለው የሚያስቡ የአይሁድ ካህናት ከሚገኙበት ጉባኤ ይልቅ ኃጢአታቸውን አምነው ለንስሐ የቀረቡት ቀራጨችና ጭፍሮች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ ጌታ ተገኘ፡፡  የጌታ ሰው መሆን ዓላማው ከኃጢአተኞች እንደ አንዱ ተቆጥሮ እኛን ኃጢአት ከሌለባቸው መላእክት ጋር እንድንቆጠር ማድረግ ነውና በኃጢአታቸው ምክንያት ንስሐ ግቡ እየተባሉ ከሚገሠፁት ሕዝብ መካከል እንዳንዱ ሆኖ አደረ፤ ዮሐንስ ‹‹እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ አለ›› ዮሐ 16 ብሎ ነገራቸው እሱ ያውቀዋል እነሱ ግን አያውቁትምና፡፡
ሕዝቡ ተጠምቀው ሲጨርሱ ጌታ ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው ዮሐንስም ወንጌላዊ እንደተናገረው ‹‹እኔ ባንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጅ አንተ በእኔ እጅ ልትጠመቅ አይገባም›› ማቴ 314 ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን ‹‹ተው አንድ ጊዜስ ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል›› ቢለው እሺ ብሎ ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ ወረዱ፤ ትንቢቱ የተነገረው በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ስለነበረ ነቢያት ትንቢት ወደተናገሩለት ዮርዳኖስ ሄዱ፡፡   
በዚያውም ላይ ኢዮብ የተፈወሰበት፣ ንዕማን ከለምፁ የነጻበት ይህ የፈውስ ውኃ ዛሬም ዓለሙን ከኃጢአቱ የሚያድነው ጌታ በዚህ ውኃ ተጠምቆ ውኃን ለሰው ልጆች የመዳን መንገድ መጀመሪያ ሊያደርጋት ዮርዳኖስን መረጠ፡፡ አባቶቹ እስራኤል በዚህ መንገድ አልፈው ነው የቃልኪዳኗን ምድር ከነዓንን የወረሱት፤ የእስራኤሉ ኢያሱ ይህን ባደረገበት በዚህ ውኃ የእኛ ኢያሱ ኢየሱስ ክርስስ የሰማዩን ርስት በጥምቀት  ሊያካፍለን ወደ ዮርዳኖስ መጣ፤
ያንጊዜ ዮርዳኖስ በእሳትና በሰማያውያን ሰራዊት በቅዱሳን መላእክት ተከበበች በዓሉ ከተራ የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው፤ ከተረ ማለት በግእዙ ከበበ ማለት ነውና፡፡
የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሆይ!
ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ከተራ ላይ ናት፤ እንደ ዮርዳኖስ በሚዘምሩ መላእክት፣ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ በሆነው እሳት እንዳይመስላችሁ ነፍስን በሚያጠፉ ሰዎች ተከባለች፤ ሕዝቡን ከዘለዓለም እሳት ሊያድናቸው የመጣው ጌታ ዛሬ ዮርዳኖስን በእሳት እንድትከበብ አድርጓታል ቅዱስ ያሬድ ‹‹ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ ማይ ኀበ የሐውር ፀበቦ፤ እሳቱ ውኃውን ከበበው ውኃውም የሚሄድበት ጠበበው›› ይላል በሰውኛ ግስ ሲገለጽ በእርግጥም ዮርዳኖስ እግዚአብሔር በሥጋ ሊጠመቅ ሲመጣ መንገዱን ከመሄድ ተከለከለ፡፡ እንዲህ ውኆች በሚፈሩት ግርማ ተገልጦ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በነፍሰ በላዎች ተከባለች፤ የከተራን በዓል በከተራ እያከበርን ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች በዚህ የነጻት በዓላችን ነጻነታቸውን አጥተው የጥምቀተ ባሕር ቦታቸውን ተነጥቀው በበዓሉን ማክበር ከማይችሉት ጋር አብረን እንዳለን ሆነን በኃዘን ልናስባቸው ይገባል፡፡