ያልጠበቅናቸው ሦስቱ ቦታዎች
ባለፈው ክፍለ ትምህርታችን ነገረ ማኅሌትን አንስተን ቤተ ክርስቲያናችን በቅኔ ማኅሌት ውስጥ የክርስቶስን የእለተ ዓርብ ስቃይ በአገልግሎቷ እንዴት እንደምትገልጥ አይተን ነበር በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ከመስቀሉ በቀር ሌላ አጀንዳ እንደሌላት ግንዛቤ ወስዳችኋል ብየ አስባለሁ፡፡ ለዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ነገር ግን ያልጠበቅናቸው ሦስት ቦታዎችን እናያለን ረድኤተ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ትሁን፡፡
ሦስቱ ቦታዎች ያልናቸው የዘወትር አገልግሎታችን የሚፈፀምባቸው ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ደጅ የምንጠናባቸው ቦታዎች ናቸው እነርሱም፡-
Ø መካነ ጸሎት
Ø መካነ ተግሣጽ
Ø መካነ ምጽዋት ናቸው
፠ መካነ ጸሎት:- የምንለው ከቤተ መቅደስ እስከ ቅኔ ማኅሌት ያለውን ነው፡፡ በፍት. መን. አን. 13 እንደ ተደነገገው በቤተ መቅደስ ውስጥ ከዲቁና እስከ ፕትርክና ድረስ መዓርገ ክህነት ያላቸው አበው ለጸሎት ይቆሙበታል፡፡ ነገሥታቱም መዓርገ ክህነት ያላቸው ከሆኑ በዚህ ሥፍራ እንዲጸልዩ ተፈቅዷል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሥፍራ ለጸሎት ብቻ ካልሆነ ለሌላ ለምንም ነገር መግባት አልተፈቀደም ገብቶ መቀመጥ ዋዘዛ ፈዛዛ ማውራት እንዳይገባ ተጽፏል፡፡ ምክንያቱም ቦታው አትናቴዎስ በቅዳሴው እንደ ተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባበት በበጎ አገልግሎት ያገለገሉትን ካህናቱን እና ዲያቆናቱን በቀኝ እና በግራ አድርጎ ምሥጢር የሚያሳይበት የደብተራ ብርሃን ምሳሌ ነውና፡፡ ያን ጊዜ ዋዛ ፈዛዛ መች አለና! ያንጊዜ መቀመጥ ማንቀላፋት መቸ አለና! ስለዚህ በዚህ ሥፍራ የምንቆም ሁላችን መጠንቀቅ እና የቆምንበትን ቦታ ማስተዋል ይገባል፡፡
ከቤተ መቅደስ ቀጥሎ ባለው ክፍል ለሥጋው ለደሙ የተዘጋጁ ምዕመናን የሚቆሙበት ሲሆን ወንዶችም ሴቶችም በየነገዳቸው ለጊዜው የሥጋው የደሙን መድረስ ፍጻሜው ግን የክርስቶስን መምጣት ተስፋ እያደረጉ ደጅ የሚጠኑበት ቦታ ነው፡፡ እስከ ቅዳሴው መጀመር ድረስ የግል ጸሎታቸውን የሚያደርሱትም በዚህ ሥፍራ ነው፡፡
ከዚህ ሥፍራ በኋላ የምናገኘው ቅኔ ማኅሌቱን ሲሆን የዚህ ሥፍራ ባለቤት የለውም ማለትም እስካሁን ያልናቸው ካህናትና ምእመናን ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚቆሙበት አንጅ ከነዚህ የተለየ ፆታ ምእመናን ስለሌለ ነው፡፡
ፆታ ምእመናን ሦስት ናቸው።
-
ካህናት
-
ወንዶች ምእመናንና
-
ሴቶች ምእመናን ናቸው።
መግቢያ በሮችም ሦስት የሆኑበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ከነዚህ የወጣ ምእመን የለምና፡፡ ለነዚሀ ደግሞ በቤተ መቅደስ እና በቅድስት ቦታ ሰጥተናል፡፡
ታዲያ በቅኔ ማኅሌት ማን ይቆምበታል? ነው ጥያቄው፤ በቅኔ ማኅሌት ከህናቱ ከቤተ መቅደስ የተረፈውን አገልግሎት ለመፈጸም የሚቆሙበት ስፍራ ነው በቤተ መቅደስ ሥጋውን ደሙን በማከበር ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሌላውን አገልግሎት በዚሁ ቦታ ነው የሚያገለግሉት፡፡
ሥጋውና ደሙን ለመቀበል ሥጋን ማድከም ይገባልና ብለው አባቶቻችን ሌሊቱን በዚህ ቦታ ሰውነታቸውን በአገልግሎት ሲተጋ እንዲያድር ያደርጉትና ሲነጋ አገልግሎታቸውን በሥጋው በደሙ ለማተም ወደ ቤተ መቅደሱ ይመለሳሉ፡፡
ታዲያ በቅኔ ማኅሌት ማን ይቆምበታል? ነው ጥያቄው፤ በቅኔ ማኅሌት ከህናቱ ከቤተ መቅደስ የተረፈውን አገልግሎት ለመፈጸም የሚቆሙበት ስፍራ ነው በቤተ መቅደስ ሥጋውን ደሙን በማከበር ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሌላውን አገልግሎት በዚሁ ቦታ ነው የሚያገለግሉት፡፡
ሥጋውና ደሙን ለመቀበል ሥጋን ማድከም ይገባልና ብለው አባቶቻችን ሌሊቱን በዚህ ቦታ ሰውነታቸውን በአገልግሎት ሲተጋ እንዲያድር ያደርጉትና ሲነጋ አገልግሎታቸውን በሥጋው በደሙ ለማተም ወደ ቤተ መቅደሱ ይመለሳሉ፡፡
በዚህ ዓይነት አገልግሎት የማይሳተፍ ማንኛውም አገልጋይ ቢኖር በፍት. መን. አን. 22 በተደነገገው መሠረት ለሙታን ስንብት እንድናደርግ የታዘዝነው በሕይወት ሳሉ ሥጋውን ደሙን በተቀበሉበት ስፍራ ላይ ነውና በቅኔ ማኅሌት ስንብት አይደረግ! የት ላይ አድርገን ልናሰናብተው እንችላለን፡፡
ምእመናኑ የሆኑ እንደሆነ ሥጋውን ደሙን መቀበል ባልተዘጋጁበት እለት በዚህ በቅኔ ማኅሌቱ ቆመው ሥጋውን ደሙን ለሚቀበሉት ይጸልዩላቸዋል፡፡ ከዚህ ያለፈ በባለቤትነት እዚህ ቦታ እንዲቆም የተፈቀደለት ማንም የለም፡፡ መካነ ጸሎት እንግዲህ ይህን ይመስላል፤ ሦስቱንም ፆታ ምእናን የሚያሳትፍ እና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ቦታ ነው በዚህ ቦታ አንዳንድ ጊዜ በቅዳሴ ጊዜ ከሚደረጉ ዐዋጆች እና በቅዳሴ ጊዜ የሚነበበውን ወንጌል ከማብራራት በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት ብቻ ቦታውን ትጠቀምበታለች፡፡ እኛም ታዲያ በነውር ምክንያት ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ካልከለከለን በስተቀር ጸሎታችን እንድናደርስ የታዘዝነው በዚህ ቦታ ነውና ቦታውን ጠብቀን ልናደርስ ይገባናል፡፡
፠ መካነ ተግሣጽ:- የምንለው ዐውደ ምሕረቱን ነው፡፡ በመካነ ጸሎቱ ምእመናን ከእግዚአብሔ ጋር ይነጋገራሉ እንዳልን ሁሉ በዐውደ ምሕረት ደግሞ የእግዚአብሔርን ምክርና ተግሣጽ ይሰማሉ
፠መካነ ምጽዋት:- የምንለው ከቅጥሩ መግቢያ ላይ ያለውና ቤተ ክርስቲያን ሙዳዬ ምጽዋቷን የምታስቀምጥበት ነዳያንም ምጽዋትን የሚቀበሉበት ምእመናንም መብዓቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡ ጥንቱን ሙዳዬ ምጽዋትን ሲያዘጋጁት ‹‹ሰው ወደ እግዚአብሔረ ቤት በሚገባበት መግቢያ በስተቀኝ አኖረው›› 2ነገ 12÷9 ተብሎ ነውና የተጻፈው በልዩ ልዩ ምክንያት መግባት ያልቻሉ ሁሉ ሊደርሱት በሚችሉበት ቦታ ሊቀመጥ ይገባዋል፡፡
አሁን አሁን ግን እንደምናየው እነዚህ ሦስት መካናት ተደበላልቀው አንዱ ካንዱ ላይ ሲደረብ እየተመለከትን ነው በዚህ ምክንያት አገልግሎቱ መጉላላት ገጥሞታል፡፡ በተለይ መካነ ምጽዋቱ ቦታውን ለቆ ከቤተ መቅደሱ በር ጀምሮ ዐውደ ምሕረቱን ሳይቀር ተቆጣጥሮ ቤተ ክርስቲያን ለልመና እና ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቋቋመች እስክትመስል ድረስ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ቤተ መቅደስ ማለት እኮ ምእመናን የልባቸውን መባዕ ለእግዚአብሔር አቅርበው የሚባረኩበት የሐና ጸሎት የተሰማበት የዘካርያስ መሥዋዕት ያረገበት የአሮን ዕጣን እግዚአብሔርን ያስደሰተበት ቦታ ነው፡፡ እንዴት ልባችሁን አኑራችሁ ውጡ በሚባልበት ሥፍራ ገንዘብ ጥላችሁ ሂዱ ይባላል፤ ይህ ሕገ ወጥ ሰዎች ያስገቡት ሕገ ወጥ ተግባር ነው፡፡
አንዳንዴማ ታቦት አቁሞም ልመና ነው ወንጌል በሚሰበክበት ቦታና ጊዜም ልመና ነው፤ ሲጀመር ቤተ ክርስቲያን ሰው ራሱን እንዲሰጥ እንጅ ገንዘቡን እንዲሰጥ መጠየቅ የለባትም፡፡ ራሱን ሳይሰጥ የሰጠውን ገንዘብ ራሳቸውን ያልሰጡ አገልጋዮች ይቀበሉትና ለግል ጥቅማቸው ያውሉታል፡፡ ሰው ራሱን ከሰጠ ለእግዚአብሔር ያልሆነ ምን አለ፡፡ አሁን አሁን የምናየው ግን እንደዚያ አይደለም ለአገልጋዮች ከሚከፈላቸው በላይ በኮሚሽን የሚከፈላቸው ለማኞች በቤተ ክርስቲያን መድረክ መታየት ጀምረዋል በአጭሩ ካልተቀጨ ቤተ ክርስቲያኒቱ አትራፊ ተቋም ወደ መሆን መለወጧ አይቀርም፡፡ አባቶቻችን የሠሩልን አሉን የምንላቸው ቅርሶቻችን የተሠሩት አቀላጥፈው በሚናገሩ ለማኞች ውትወታ ይመስላችኋል? ላሊበላን ማን ሠራው? የአክሱምን ቤተ መቅደስ ማን አዘጋጀው? የደብረ ሊባኖስን ግራኝ ያቃጠለውን ባለ አሥራ ስምንት ጉልላት ቤተ ክርስቲያን ማን ሠራው? የነ መርጡለ ማርያምን መንግሥቶ ኪዳነ ምሕረትን ዲማ ጊዮርጊስን ሌሎችንም ማን የሠራቸው ይመስላችኋል? መቼም እነዚህ ኮሚሽን የሚታሰብላቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሳይሆን የሚያገኙት ገንዘብ ትዝ እያላቸው የሚያለቅሱ ለማኞች ናቸው እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ ነገሥታትና መኳንንት ናቸው እንጅ፡፡ አሁን አሁንም ራሳቸውን ችለው አንድ ቤተ ክርስቲያን የሚሠሩ ሰዎችን ማየት ጀምረናል ተመስገን ነው፡፡
አሁንም እላችኋለሁ በተለይ ዐውደ ምሕረቱን መካነ ምጽዋት ማድረጉን እናቁም ዐውደ ምሕረቱ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ቃሉን የሚናገርበት ቦታ ነው፡፡ ምእመናኑን እንንገራቸው ምጽዋታቸውን በሚገባው ሥፍራ ያስቀምጡ ለወንጌል አገልግሎት ሊሆን የሚገባውን ጊዜ በልመና ቤተ ክርስቲያን ልታጠፋ አይገባትም ሁሉም ነገር በወንጌል ስለ ወንጌል ሊሆን ይገባል፡፡ ገንዘብ ተከፍሏችሁ የምትለምኑ ሰዎች እባካችሁ ገንዘብ ያስገኘ ነገር ሁሉ ሥራ አይደለምና ራሳችሁን መርምሩ እነዚህን ሦስቱንም ቦታዎች እየራሳቸው መጠበቅ ካልቻልን የአንዱን ወደ አንዱ የምንወስድ ከሆነ አገልግሎታችን ቅጡ የጠፋው ይሆንና እግዚአብሔርን ደሰ የማያሰኝ ይሆንብናል፡፡
2 comments:
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ሠላምና ጸጋ በእግዚአብሔር ስም ይብዛሎት፡፡፡ብሎግዎ እጎበኘዋለሁ በጣም ደስ የሚሉ በመንፈስ የሚያሳድጉ በእውቀትም
የሚያበለፅጉ ትምህርቶች ነው የሚሰጡት ነገር ግን active ሁነው ወቅታዊ ትምህርቶችን ቶሎ ቶሎ ቢለቁልን መልካም
ነው፡፡፡፡እናም ወደ ጥያቄዬ ስገባ
ብዙ ወንድሞችና እህቶች "ሐጢአት ሰርተን ሲኦል እንደምንገባ እግዚአብሔር እያወቀ ለምን ይፈጥረናል?፡" ብለው
ይጠይቃሉ።ለነዚህ ምን መልስ አለ?
መልእክትዎን በጉጉት እጠብቃለሁ
Post a Comment