>

Wednesday, 10 August 2016

ሱባኤ



ሱባኤ
·        ---- --------------- የሱባኤ ጥቅሙ ምንድነው?
·      , ------------   ------እመቤታችን የሞተችው በጥር ከሆነ ሐዋርያት እስከ ነሐሴ ሱባኤ ያልገቡት ለምነድነው?
·         ---------------ትንሣኤዋ በሦስተኛው ሱባኤ ተገለጠላቸው ሱባኤውን ያልጨረሱት ለምንድነው?
--------እነዚህን እና ሌሎችን ጥያቄዎችን በዚህ ጽሑፍ ለመመለስ እንሞክራለን
ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዲደረግልን ስንሻ ሱባኤ መግባት በአባቶቻችን ሕይወት የተማርነው የጥያቄ ማቅረቢያ መንገድ ነው፤ በሱባኤ ምሥጢር ይገለጣል፤ በሱባኤ በረከት ይገኛል፤ በሱባኤ ዕጣ ፋንታን ማስተካከል ይቻላል፤ ሁሉም በጎ ነገሮች የሱባኤ ውጤቶች ናቸው፤ የሔዋን መፈጠር በሱባኤ ነው የእስራኤል ከፋርስ ባቢሎን መውጣት በሱባኤ ነው፤ የክርስቶስ ልደት በአበው ሱባኤ ነው፤ የሰው ልጆች ከሲኦል መውጣት በሱባኤ ነው፤ በመጨረሻም የታላቁ ዓለም የመንግሥተ ሰማያት መምጣት በሱባኤ ነው፤

አባቶቻችን ሐዋርያት የነቢያት ሱባኤ በተፈጸመበት ወራት የተገኙ ናቸው፤ የነቢያት ሱባኤ በክርስቶስ ተፈጽሟል፤ ሐዋርያት ሱባኤ ሚገቡት ከዚህ በኋላ ክርስቶስ የሚወርድበትን የሚወለድበትን ዘመን ፍለጋ አይደለም፤ የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር መምጣቱ ለሱባኤ እንደ መሆኑ መጠን የሐዋርያት ሱባኤ ደግሞ ሌላ ያልተገለጠ ምሥጢር ፍለጋ የመንግሥተ ሰማያት ነገር፣ የክርስቶሰ ዳግም ምጽዓት፣ የሰው ልጆች የተስፋ ፍጻሜ ማለትም ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ጠቅለል ባለ ትርጉም ስንገልጠው ሱባኤ ማለት የሰው ልጅ ተስፋ ያደረገውን ነገር የሚያገኝበት እንደመሆኑ መጠን አሁን ቤተ ክርስቲያን ተስፋ የምታደርጋቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡
ለጊዜው ሐዋርያትን ዛሬ ሱባኤ እንዲገቡ ያደረጋቸው ነገር የእመቤታችን ጉዳይ ነው፤ እመቤታችን ያረፈችው በጥር 21 ቀን መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፤ ከጥር እስከ ነሐሴ በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ቆይታለች ይህን ከዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር የሚያውቅ ማንም አልነበረም፤ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቀን ቀን በሀገረ ስብከቱ ሲያስተምር ውሎ ማታ በደመና ተነጥቆ የእመቤታችን በድነ ሥጋ ወዳለበት ገነት ሂዶ ሲያጥን ያድር ነበር፤ ይህን ምሥጢር ዮሐንስ ለወንድሞቹ ሐዋርያት ከነገራቸው በኋላ ሱባኤ ነሐሴ አንድ ቀን እንደ ጀመሩ በቤተ ክርስቲያናችን የሚነገረው ትውፊታዊ ታሪክ ያስረዳናል፡፡
ሐዋርያት እመቤታችን ከዐይናቸው ከተሰወረችበት ጊዜ ጀምሮ ሱባኤ ያልገቡ እስከ ነሐሴ የቆዩት ለምንድነው የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል፤
መንፈስ ቅዱስ ባወቀ በዚህ ሱባኤ ማስተላለፍ የሚፈልገው ምሥጢራዊ መልእክት ያለው ስለሆነ ነው
1.   ይህ ወር በእብራውያን ዘንድ አምስተኛ ወር ነው እመቤታችንም የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን መፈፀም ምክንያት መሆኗን እና የአበው ነቢያትም ሱባኤ እስከ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ድረስ መሆኑን ሊያስረዳ
2.    ናቡዛርዳን ቤተ መቅደስን ያፈረሰበት ወር ነው ታለቁ ቤተ መቅደስ በዚህ ወር ፈረሰ የሚገርመው ነገር ግን ዘሩባቤል ቤተ መቅደስን መሥራት የጀመረውም በዚህ ወር ነበር፤ ኃጢአት ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን ካፈረሰው በኋላ ለእግዚአብሔር የክብር ስፍራ ሆኖ መገኘት የቻለ ከሰው ወገን ማንም አልነበረም፤ እስከ እመቤታችን መምጣት ድረስ፡፡ ለዚህ ነው አባ ሕርያቆስ ‹‹…ወኢረከበ ዘከማኪ፤…እንዳንች ያለ አላገኘም›› ሲል ያመሰገናት፡፡ የሰው ልጅ ቤተ መቅደስ ሆኖ ዳግም ይሠራ ዘንድ ለመንፈስ ቅዱስ በሥጋዊና በደማዊ ፍጡር ላይ ማደር ምክንያት መሆኗን ለመግለጥ፡፡
3.   ከጥር 21 እስከ ነሐሴ መባቻ ድረስ ብትቆጥሩት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ቀናትን እናገኛለን፤ ይህን በሱባኤ ብንገባው (ብንቆጥረው) 27 ሱባኤ እለት እናገኛለን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባወቀ እስከዚህ ቀን ድረስ ሱባኤ እንዳይገቡ ከለከላቸው፤ ምክንያቱም አሁን ሐዋርያት እመቤታችንን የሚቀበሏት በሁለት ሱባኤ ነው ማለትም እስከ ነሐሴ 14 ቀን ድረስ በሚያደርጉት ሱባኤ፤ ይህን ከቅድሙ ጋር ብንደምረው 29 ሱባኤ ይሆናል ሱባኤው ፍጹም ሊሆን አንድ ይቀረዋል ሰላሳ ከሞላ የሁሉም ነገር ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው፤ ስለዚህ ለቀሪው ትውልድ አንድ ሱባኤ ትቶ በሃያ ዘጠነኛው ሱባኤ የእመቤታችንን መገለጥ ለሐዋርያት አደረገላቸው
ይህ በሚገባ ግልጥ እንዲሆንላችሁ በቀጣዩ ዓመትም ሐዋርያት የገቡትን ሱባኤ ተመልከቱ በዚሁ ወር በነሐሴ አንድ ሱባኤ ጀምረዋል የመጀመሪያው ሱባኤ እመቤታችንን ለማግኘት ነበር ሁለተኛው ነሐሴ ላይ የገቡት ሱባኤ ትንሣኤዋን ለማየት ነው ነገር ግን እንደ ቀድሞው ሁለተኛው ሱባኤ ሲያበቃ ትንሣኤዋን ማየት አልቻሉም ሦስተኛውን ሱባኤ ጀምረው ሁለት ቀን ካስቆጠሩ በኋላ ነው በ16 ቀን ትንሣኤዋን ያዩት፡፡ ይህ ለምን ይመስላችኋል? በሱባኤ መሀል ምሥጢር መግለጥ ለመንፈስ ቅዱስ ልማዱ ቢሆንም የፈለግሁት ምሥጢር ከተገለጠልኝ ብሎ ሱባኤን ማቆም ግን ልማደ አበው አይደለም ታዲያ የሐዋርያት ሱባኤ እዚህ ላይ የሚያቆመው ለምንድነው? ከተባለ የመንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩ ሐዋርያት የጀመሩትን ሱባኤ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ እንድትፈጽመው ነው፤
እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ድረስ ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ የምታደርገው ሱባኤ እንደ አንድ ሱባኤ ይቆጠራል ይህም የሐዋርያት ጅምር ሱባኤ ነው ሱባኤያችን ሠላሳ ሲሞላ የእመቤታችን ምሳሌ የሆነች መንግሥተ ሰማያት ትገለጣለች በእመቤታችን ጌታ ሰው በመሆኑ ምክንያት የሰው ልጆች ትንሣኤ እንደተረጋገጠ በሠላሳኛው ሱባኤ ደግሞ የሰው ልጅ ለዘለዓለም ላይሞት ይነሣል ላይሻር ይነግሣል ላይሰደድ ወደ ቤቱ ይመለሳል፤
ይሄኛውን ሰላሣ ሱባኤ ከዳንኤል ሰባ ሱባኤ ጋር ስንደምረው መቶ ሱባኤ ይሆንልናል፤ መቶ ሱባኤ ሲሞላ የእግዚአብሔር ሰራዊት መቶ ነገድ ይሆናል ማለትም ፍጹም ይሆናል ማለት ነው፤
ታስታውሱ ከሆነ አባታችን አዳም ሲሞት ሺህ ዓመት ሊሞላው ሰባ ሲቀር ነበር የሞተው እናታችን ሔዋን ደግሞ ሰላሣ ሲቀራት ሞተች አዳም ከክርስቶስ በፊት የነበረውን የመጀመሪያውን ትውልድ የሚወክል ሲሆን ሔዋን ደግሞ ከክርስቶስ በኋላ ያለች ቤተ ክርስቲያንን ትወክላለች ስለዚህ የመጀመሪያው ትውልድ እንደ አዳም ወደ ሕይወት ጫፍ ለመድረስ ሰባ ሱባኤ መቆየት ነበረበት የሐዲስ ኪዳኑ ትውልድ ደግሞ እስከ ሰላሣ ሱባኤ ድረስ ‹‹ወንሴፎ ትንሣኤ ሙታን ወሕይወተ ዘይመጽእ፤ የሙታንን መነሣና የሚመጣውን ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን›› ስትል በተስፋ ትኖራለች፡፡
አበቅቴና መጥቅዕ ከሰላሣ አይወርዱም ከሰላሣም አይበልጡም ቤተ ክርስቲያን ዕድሜዋን ስታሰላ የምትኖረው ከሰላሣ እንዳይበልጡ ከዚያም እንዳያንሱ በተመጠኑ ቁጥሮች ነው ይህ ለምን ሆነ መሰላችሁ? የቀረው ሱባኤ ሰላሣ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹መጥቅዕ ወአበቅቴ ኢየዐርጉ እምሰላሣ ወኢይወርዱ እምሰላሣ ወትረ ይከውኑ ሰላሣ›› እንዲል
                        ይቆየን

1 comment:

Unknown said...

ሱባኤ
…ታስታውሱ ከሆነ አባታችን አዳም ሲሞት ሺህ ዓመት ሊሞላው ሰባ ሲቀር ነበር የሞተው እናታችን ሔዋን ደግሞ ሰላሣ ሲቀራት ሞተች አዳም ከክርስቶስ በፊት የነበረውን የመጀመሪያውን ትውልድ የሚወክል ሲሆን ሔዋን ደግሞ ከክርስቶስ በኋላ ያለች ቤተ ክርስቲያንን ትወክላለች ስለዚህ የመጀመሪያው ትውልድ እንደ አዳም ወደ ሕይወት ጫፍ ለመድረስ ሰባ ሱባኤ መቆየት ነበረበት የሐዲስ ኪዳኑ ትውልድ ደግሞ እስከ ሰላሣ ሱባኤ ድረስ…..
 ይህን ሐሳብ ሱባኤ ከሚለዉ አጭር ጽሑፍ ነዉ እስከሁን ድረስ የእናታችንን ሔዋን ዕድሜ ስንት ነዉ የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሣል መልስም አላገኘሁም ነበር ከዚህ ጽሑፍ መነሻ ግን ማወቅ የሚቻል ስለመሰለኝ መምህር ማብራረያና የመጽሐፍትም ጥቆማ ካለም ብጠቅሱልኝ እያልኩ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡