>

Thursday, 18 August 2016



ሙሴና ኤልያስ በደብረ ታቦር
ደብረ ታቦር ከደብረ ሲና የሚበልጠውን ምሥጢር ያየንበት ተራራ ነው፤ በደብረ ሲና በሁለቱ ጽላት ላይ የተጻፉ ቃላትን ተቀብለናል፤ በደብር ታቦር ግን አካላዊ ቃል ተገልጦ ታየልን፤ በደብረ ሲና ሙሴ ብቻውን ቆሞ ነበር በደብረ ታቦር ግን ነቢያት ከሐዋርያት አንድ ሆነው ተስማምተው ክርስቶስን መካከል አድርገው ታዩ፡፡ እነዚህ ሁለቱን ከነቢያት ለይቶ ለምን ይጠራቸዋል፤ ከነሱ በላይ የሚጠራቸው አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ያሉ አይደለምን! ሙሴና ኤልያስ ለምን ለዚህ ምሥጢር የተለዩ ሆኑ?
ቅዱስ ወንጌል ‹‹ወናሁ አስተርአዩ ሙሴ ወኤልያስ እንዘ ይትናገሩ ምስሌሁ፤ እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር እየተነጋገሩ ታዩ›› ማቴ 17÷4 ብሎ በስም የጠራቸው እነዚህ ነቢያት ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ሁሉ የሚያመሳስላቸው ታሪክ ያላቸው ነቢያት ናቸው፤

1.  ሁለቱም ነቢያት አሻጋሪ ነቢያት ናቸው
ሙሴ ከስድስት መቶ ሺህ የሚበዛውን ሕዝብ እየመራ መሻገሪያ በሌለው መንገድ በደረሰ ጊዜ ውኃውን ከፍሎ ሕዝቡን አሻገረ፤ ኢያሪኮ ለመድረስ ዮርዳኖስን ማሻገር ነበረበት ነገር ግን ሙሴ ዮርዳኖስን ሊያሻግር ያልተፈቀደለት ነቢይ ነበረና ዮርዳኖስ ሳይደርስ ሞት ቀደመው፤ ባሕር በመክፈል ታሪክ ኢያሱም ተሳታፊ ነው ነገር ኢያሱ ዮርዳኖስን ከፍሎ ሕዝቡን ሲያሻግር ከሙሴ ከኤልያስ የተለየ የሚያደርገው ታሪክ አለው ሙሴ በበትሩ ኤልያስ በመጎናጸፊያው ባሕር የከፈሉ ሲሆን በኢያሱ ጊዜ ግን ዮርዳኖስ የተከፈለው ሕዝቡም የተሻገረው የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮቻቸው ውኃውን በረገጡት ጊዜ ነው ስለዚህ አሻጋሪነቱ ከሙሴና ከኤልያስ የተለየ ነበር፡፡
ይህ የኤልያስና የሙሴ ማሻገር ክርስቶስ ሕዝቡን የሚያሻግርበት ዘመን እንደሚመጣ የሚያሳይ ነበር እንጅ ሕዝቡን የትም የሚያደርስ ማሻገር አልነበረም፡፡ ኤልያስም ሆነ ሙሴ ሕዝቡን አሻገሩት እንጅ የት አደረሱት ከመንገድ ነው የተለዩት፡፡ አማናዊው መሻገር በክርስቶስ የሚደረግ ነውና ዛሬ እነዚህ ነቢያት መመረጣቸው ይህ እነሱ የጀመሩት የማሻገር ሥራ የሚፈጸምበት ቀን ስለደረሰ ይህን ያዩ ዘንድ ተመርጠዋል፡፡
2.  ከሰማይ መናን ያወረዱ ነቢያት ናቸው፡፡
   ሙሴና ኤልያስ ከሰማይ መና የተላከላቸው ነቢያት ናቸው፤ ሁለቱም በመንገድ ላይ ነበሩ ከመናው መውረድም በፊት በሙሴ ላይ ሕዝቡ በረሃብ ምክንያት ያንጎራጉሩበት ነበር ‹‹የእስራኤልም ልጆች ማኅበር በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ ይህን ጉባኤ ሁሉ በረሀብ ልትገድሉ እኛን ወደ ምድረ በዳ አውጥታችኋል በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠገብ ሳለን በግብጽ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን›› እያሉ ያንጎራጉሩ ነበር፡፡ ነቢዩ ኤልያስም በእንጉርጉሮ ላይ ነበር፤ ‹‹ይበቃኛል እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ›› ብሎ ሞትን በመመኘት ላይ ነበር ዘጸ 16÷3፣ 1ነገ 19÷5
ሁለቱም ነቢያት እንዲህ ባለ ጭንቀት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር መናን ከሰማይ አወረደላቸው በዚህ መና ሙሴ ለአርባ ዘመናት ሕዝቡን የመገበ ሲሆን ኤልያስ ደግሞ በዚህ መና ምክንያት አርባ ቀናት ያለ ምንም መብልና መጠጥ ተጓዘ፡፡ የዚህ መና ፍጻሜ የሆነው አማናዊው መና እንደ ቀድሞው በልተውት የአርባ ዓመትና የአርባ ቀን ስንቅ መሆን ሳይሆን የዘለዓለም ስንቅ የሚሆነው መና ክርስቶስ የተገለጠበት ዘመን ስለሆነ እነዚህ ነቢያት ተጠርተው መጥተዋል፤ ‹‹ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰጣችሁ መና ይህ ነው እንካችሁ ብሉ›› ብለው ሊነግሩን መጥተዋል ዘጸ 16÷15-17
3.  ካሰቡት ሳይደርሱ መንገድ ላይ የተጠሩ ነቢያት ናቸው፤
እነዚህ ነቢያት የምድረ በዳ ነቢያት ናቸው፤ ራሳቸውን የሚያስጠጉበት ቤት የሌላቸው መንገደኛ ነቢያት ናቸው፤ ሁለቱም ከኋላ ከኋላ ጠላት የሆኑ ኃያላን ነገሥታት የሚያሳድዷቸው ከጠላት ሸሽተው እግዚአብሔርን ወደ ሚያገለግሉበት ከተማ ሲጓዙ አንዳች ማረፊያ ስፍራ ሳይኖራቸው እግዚአብሔር ከመንገድ የተቀበላቸው ነቢያት ናቸው፡፡ ሁለቱም አባቶቻችን ደቀ መዛሙርቶቻቸውን እየባረኩ ወደ እግዚአብሔር የሔዱት ከመንገድ ነው ዘዳ 33 እና 34፣ 2ነገ 2÷11
ሁለቱም ነቢያት ከዚያ በኋላ የደረሱበትን ከተከታዮቻቸው መካከል ያወቀ የለም እግዚአብሔር ባወቀ አስቀምጧቸዋል እንጅ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ሦስት ዳስን ለመሥራት ለምን አሰበ፤ ለሙሴና ለኤልያስ አንዳንድ ዳስ ለመምህሩ ለክርስቶስም እንዲሁ አንድ ዳስ ሊሠራ አሰበ፤ ሙሴና ኤልያስ በምድረ በዳ በዋሻና በፍርኩታ በመኖር ክርስቶስን ይመስሉታል ራሳቸውን የሚያስጠጉበት ቤት አልባዎች ሆነው በማገልገላቸው ከሚያሳድዳቸው ጠላት ለማምለጥ በሚያደርጉት ጥረት ከጎዳና እግዚአብሔር የተቀበላቸው ሰዎች ናቸው
 ዛሬ ግን ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ቤት የሚሠራላቸው ክርስቶስ መጥቷልና የቅዱስ ጴጥሮስን ዳስ ሳይሆን ‹‹ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ በአባቴ ቤት ብዙ ማረፊያ አለና›› ዮሐ 14÷2 የሚለውን የተስፋ ድምጽ ለመስማት ተጠርተው መጥተዋል፡፡
4.  ሁለቱም ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀናዕያን ነቢያት ናቸው
እግዚአብሔርን ማምለክ በማይፈልግ ሕዝብ መካከል ይኖሩ የነበሩ ነቢያት ናቸው - ሙሴና ኤልያስ፡፡ ነገር ግን በሚያደርጓቸው ተዓምራት በሕዝቡ ዘንድ እግዚአብሔር ሞገስን የሰጣቸው፡፡ በኤልያስ ዘመን የነበረው ንጉሥ አክዓብ እግዚአብሔርን የሚያሰቆጣ ነገርን አብዝቶ በማድረግ የሚተካከለው የሌለ ንጉሥ ነበር 1ነገ 16÷33 በሙሴ ዘመን የነበረውንም ተመልከቱት እግዚአብሔርን ያስቆጣ ሕዝብ ነው፤ ዘጸ 32÷10
ጣዖቱን በመስበር መሰዊያውን በመሥራት ሙሴና ኤልያስ ለአምልኮተ እገዚአብሔር ይቀኑ የነበሩ ነቢያት መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክርላቸዋል ዘጸ 32÷19፣ 1ነገ 19÷10 እንዲያውም ሁለቱን ነቢያት በጣም የሚያመሳስላቸው ዋናው ነገር በሁለቱም ነቢያት ዘመን ለሕዝቡ አምልኮ ጣዖት ያስተማሩ የጣዖት አገልጋዮች እንዲገደሉ ማድረጋቸው ነው ዘጸ 32÷27-28፣ 1ነገ 18÷40
ለመዳን እንዲበቃ የተጠነቀቁለት ሕዝብ ራስን እስከ መስጠት ደርሰው ሁለቱም ከሕዝቡ ጥፋት ይልቅ ለራሳቸው ሞትን ተመኝተው ነበር፤ ራስን እስከ መስጠት ድረስ ደርሰው ያገለገሉትን ሕዝብ የሚያድነው እውነተኛው አዳኝ መምጣቱ ሲጠብቁት የነበረው ተስፋቸው ነውና ይህ ተስፋ መፈጸሙን ለማስረዳት መጥተዋል፡፡     
5.  ሕዝቡ ርስት ይቀኑ የነበሩ ነቢያት ናቸው
ሙሴ ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ ርስት ለከነዓን ሲል ከፈርዖን ጋር ተዋቀሰ ሕዝቡን አስከትሎ አርባ ዘመን ተጓዘ ኤልያስ ደግሞ ለናቡቴ ርስት ሲል አክአብን ገሰጸ፡፡ ሁለቱም ነቢያት ርስት ያለውን ሕዝብ ርስት አልባ ሲያደርጉ ቢያዩ ስለ ሕዝቡ ርስት ነገሥታቱን ገሰጹ፡፡ ርስተ ምድር ለሰማያዊ ርስት አንጻር ስለሆነ ለምድራዊ ርስት አጥብቀው ይሟገቱ ነበር፡፡
አጥብቀው የተሟገቱለት ርስታችን የሚመለስለት ዘመን ስለሆነ ለዚህ ተጠርተው መጥተዋል፡፡


No comments: