ዜና ፍልሰታ ፪
እንዲህ ነበር፡-
ከገነት ወደ ምድር የተደረገውን ስደት፣ ከምድር ወደ ሰማይ የሚደረገውን ደግሞ ፍልሰት እንለዋለን፡፡ የእስራኤል ከግብጽ
መውጣት ፍልሰት ሲሆን የአሕዛብ ከተስፋይቱ ምድር ከኢያሪኮ መውጣት ግን ስደት ነው፡፡ ዛሬ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ከሚያረጀው
ዓለም ወደ ማያረጀው ዓለም የፈለሰችበትን ቀን እናስታውሳለን፡፡
አባቶቻን ሐዋርያት በገቡት ሱባኤ መሠረት የእመቤታንን በድነ ሥጋዋን መልአከ እግዚአብሔር አምጥቶ ሰጥቷቸው በጌቴሴማኒ
ቀብረዋታል የእናትና የአባቷ እንዲሁም የጠባቂዋ የቅዱስ ዮሴፍ መቃብርም በዚሁ ስፍራ ይገኛል፡፡ ሱባኤ የገቡበት የጸለዩበት ጉዳይ
ሥጋዋን አግኝተው እንደ ልጇ መቃብር መቃብሯን መሳለም ነበር እንጅ ትንሣኤዋን ማየት ስላልነበረ - የሱባኤው ዓላማ ፤ ቀብረዋት
ወደየሀገረ ስብከታቸው ተበታትነዋል፡፡
ቶማስ ከመቃብሯ ላይ አልተገኘም ነበርና ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደመና ሲመለስ እሷን መላእክት ሲያሳርጓት በዐየር
አግኝቷታል፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢሩን ተመልከቱት! ሐዋርያት ሱባኤ የገቡት ለመቃብሯ እንጅ ለትንሣኤዋ ስላልነበረ ትንሣኤዋን አላሳያቸውም፤
ነገር ግን የእመቤታች ትንሣኤ ከቤተ ክርስቲያን ተደብቆ እንዳይቀር በቶማስ በኩል እንዲገለጥ አደረገው፡፡ እኛስ ሐዋርያት ያላስተማሩንን
ምን ብለን ተነሣች ዐረገች እያልን እናስተምር ነበር፤ እግዚአብሔር የልጇን ትንሣኤ ዘግይቶ ያመነውን ቶማስን የእሷን ትንሣኤ ቀድሞ
እንዲያምን አደረገው፡፡
ቶማስ መጥቶ በነገራቸው መሠረት ትንሣኤዋን ለማየት ለሁለተኛ ጊዜ በዓመቱ ሱባኤ ገቡ እንደ ቀድሞው በሁለተኛው ሱባኤ
መጨረሻ ላይ ትንሣኤዋን አልገለጠላቸውም አሥራ አራተኛውን ቀን አሳልፎ በአሥራ ስድስተኛው ቀን ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችንን
አስከትሎ በሐዋርያት መካከል ተገልጦ አሳያቸው፡፡
ነሐሴ አሥራ አራት ተቀብራ የተነሣቸውም በዚያው ቀን ነሐሴ አሥራ አራት ዕለቱም እሑድ ነው ነገር ግን ዛሬ እኛ ትንሣኤዋን
የምናከብረው በነሐሴ አሥራ ስድስት ነው ለሐዋርያት የተገለጠበት ቀን ነውና፡፡ በሌላ መንገድ ሐዋርያት ማለት ቤተ ክርስቲያን ናትና
ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤዋን ባየችበት ቀን ነው እያከበርን ያለነው ማለት ነው፡፡
እመቤታችን በተነሣችበት እለት ነሐሴ አሥራ አራት በእለተ እሑድ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በገነት ያለውን ምሥጢር ያሳያት
ዘንድ ወሰዳት፤ በገነት ውስጥ መዐዛቸው ልብን የሚመስጥ ዕፀዋትን አየች፤ ጌታችንም ከሁሉም የሚበልጥ መዓዛ ያለው ርሔ ከሚባለው
የሽቱ ዛፍ ቆርጦ ሰጣት፡፡ በዚያም የንፁሐን ደናግልን የቅዱሳንን ሁሉ ማደሪያ አየች፤ ዳግመኛ የሰማዕታትን ማረፊያና የተሰጣቸውንም
ክብር ታይ ዘንድ ሰማዕታት ወዳሉበት ስፍራ ወሰዳት፤ አይታም አደነቀች፡፡
ከዚህም በኋላ ‹‹ዕርጊ ውስተ ሰማይ ከመ ትርአዪ ምሥጢረ በህየ፤ በሰማይ ያለውን ምሥጢር ትመለከች ዘንድ ወደ ሰማይ
ውጭ አላት›› በዚያም የእግዚአብሔር የሀብቱን መዛግብት ተመለከተች፤ የበረዱን፣ የዝናሙን ፣የቁርን፣ የጠልን፣ የውኃውን የእሳቱን፣
የነፋሱን መዛግብት ተመለከተች ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስም በብርሃን ሠረገላ ተቀምጦ ይታይ ነበር፡፡
ኤልያስ ሔኖክ ቆመው የሚጸልዩበትን ስፍራ በመጀመሪያው ሰማይ ላይ ተመለከተች፡፡ በሁለተኛውና በሦስተኛው ሰማይ መላእክት
ክንፎቻቸውን ዘርግተው በማያቋርጥ ቅዳሴ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሲሉ ሰማቻቸው፡፡
በዐራተኛው ሰማይ እንደ እንቊ የሚያበራ በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት
ስም የተሰየመ አሥራ ሁለት በር ያለው አዳራሽ ተመለከተች፤ በእያንዳንዱ በር አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቁመው ምስጋና ሲያቀርቡ ከኋላቸውም
12ቱ ሊቃነ መላእክት በየበሮቹ ቁመውበታል ፡፡ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በታላቁ በር በኩልም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ዳዊት
ቆመው ለንጉሠ ሰማይ ወምድር ምስጋና ሲያቀርቡ አየቻቸው፡፡
ወደ ውስጥም በገባች ጊዜ ከመጀመሪያው በር ላይ ስትደርስ ነገደ መላእክት ሰገዱላት፤ ከሁለተኛው በር ስትደርስ ሱራፌል
አመሰገኗት፤ ከሦስተኛው በር ኪሩቤል ዘመሩላት፤ ከአራተኛው በር ስትገባ ሥልጣናት፣ ከአምስተኛው ሊቃናት፣ ከስድስተኛው ሚካኤልና
ገብርኤል ሰገዱላት፤ ከሰባተኛው በር ሠራዊተ መላእክት ጩኸው ሲያመሰግኑ ሰማች፡፡ ከስምንተኛውም ከዘጠነኛውም ከአሥረኛውም ከአሥራ
አንደኛውም ከአሥራ ሁለተኛውም በር ገባች ፍጥረታት ሁሉ ዝናም፣ መብረቅ፣ ነፋስ፣ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት አመሰገኗት፡፡ በዚያ የነበሩ
መላእክት ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡
የእመቤታችን ወደ ሰማይ የገባችው መግባት እንዲህ ነበረ፡፡ በኋላም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ
ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚመሰገንበትን ጽርሐ አርያምን አሳያት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚመሰገኑትን ምስጋናም ሰማች፡፡ የእመቤታችን የምድር ላይ የመከራ ጊዜ አብቅቶ ወደ ዘለዓለማዊው ተድላ ደስታ
የፈለሰቸው እንዲህ ነበር፡፡
ይቅርታ! በበዓሉ ዕለት እንዲለቀቅ ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆንም internet ወደሚገኝበት ስፍራ ለመሄድ ጊዜ
በማጣቴ የዘገየ ነው፡፡