>

Saturday, 10 August 2019


በፍልሰታ እንፍለስ
ይህ ጾም ጾመ ማርያም ወይም ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ጾም እመቤታችንን, አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትን እናስታውስበታለን እነዚያ መከረኞች የጌታ ሐዋርያት በምድር ላይ ያለዉን መከራ ሁሉ ቀምሰውታል፤ ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ ምሥጢር የሚጠይቁት መከራቸውን የሚረሱት፣ ከድካም የሚያርፉት ወደ እመቤታችን  ቅድስት ማርያም ዘንድ እየሄዱ ነው፡፡ ከየሀገረ ስብከታቸው ወደ ኢየሩሳሌም በደመና ተጭነው መጥተው ኀይል መንፈሳዊ በረከት ሰማያዊ ከእሷ ተቀብለው ይመለሳሉ መለኮትን በዳሰሱ እጆቿ ትዳስሳቸዋለች፤ ከሰባቱ የእሳት መጋረጃ ውስጥ ያለውን የመለኮት ምሥጢር ባዩ ዐይኖቿ ታያቸዋለች ቁስላቸው ድኖ ስብራታቸው ተጠግኖ ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ፡፡
አሁን ግን ነገሩ እንደዛ አይደለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአፀደ ሥጋ ከእነርሱ ከተለየች ከቤተ ዮሐንስ ከወጣች ወራት ተቆጥረዋል፤
ያውም የድካም ጊዜ ምርኩዛቸውን እመቤታችንን ቀብረው መቃብሯን አለማወቃቸው ልባቸውን በኃዘን የሚሰብር ሆኖባቸዋል በዚህ ምክንያት ነው ሱባኤ በነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው የገቡት፡፡
§  ሱባኤው በድነ ሥጋዋን ለማግኘት ነበር ነገር ግን ያልጠበቁትን ትንሣኤዋን አሳያቸው፡፡
አግኝተው ይቀብሯት ዘንድ በመሻት ሱባኤ ገቡ እግዚአብሔር ጥቂት ሲሹ ብዙ መስጠት ልማዱ ነውና አግኝተው እንዲቀብሯት ሳይሆን አግኝተው ወደ ሰማይ ስታርግ እንዲያይዋት ፈቀደላቸው፤
§  ነፍስ የተለየውን ሥጋዋን ብቻ ሳይሆን ነፍስ ከሥጋዋ ተዋሕደው እንዲያይዋት ዳግመኛ ቀርበው ከእጇ እንዲባረኩ አደረጋቸው፤
v  ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከፍልሰታ አስቀድመው መፍለሳቸው ነበር ሰውነታቸውን በጾም ከመብል ከመጠጥ፣ ደስታቸውን በኃዘን፣ ዕረፍታቸውን በትጋት፣ ሳቃቸውን በለቅሶ፣ እንቅልፋቸውን በአገልግሎት አፈለሱት ይህን ዓለም እረሱት እሷ ከእነርሱ ስትወሰድ እነሱም ያለ ጊዜአቸው ይህን ዓለም ጥለውት ተሰደዱ፤ ወንጌል ሲሰብኩ ይውላሉ ሌሊቱን እንቅልፍ በማጣት በትጋሓ ሌሊት  ያድራሉ፡፡
እግዚአብሔር የልባቸውን መሻት እስኪያደርግላቸው ድረስ እስከ መንበረ ፀባኦት ድረስ እየገሰገሱ ደጅ ጠኑ፡፡ አስቀድመው ፈልሰው ፍልሰቷን ተመለከቱ፡፡
v  እስኪ እኛም እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ በፍልሰታ እንፍለስ፤ በዚህ ወራት ኃዘን እና ለቅሶ ጸሎትና ምኅላ ጎን ለጎን የሚሠራ ሥራ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያን ወገቧን ታጥቃ ልትሠራው የሚገባ ዋና ተግባሯ ነው፤ ጠላት ሳያፈልሰን እኛ በፍልሰታ እንፍለስ አብያተ መቃድሳቶቻችን በእሳት የተተኮሱብን፣ መምህራኑ ወምበራቸውን እያጠፉ ወደ ከተማ የፈለሱብን፣ ምዕመናኑ ማተባቸውን የበጠሱብን ካህናት በአለባበሳቸው በአኗኗራቸው ቅጥ ያጡብን፣ ጳጳሳቱ እውነትን መድፈር አቅቷቸው አፍረው የተመለሱብን እኛ የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ነን፡፡
ግብረ ክርስትናውን ትተነው ስንፈልስ እነሱ ደግሞ በዚያው ገቡና ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሀገር ትፍለስ አወ! ድሮ አገር ነበረች አሁን ግን ትፍረስ፤
አወ! ድሮ ንጉሥ ንግሥት ነበረች አሁን ግን ጵጵስናዋም ይርከስ፤
 አወ! ድሮ የሕግ መምህር ነበረች አሁን ግን ያለ ሕግ ትወቀስ! ትከሰስ! እያሉ ዘበቱባት፡፡ እጃቸውን ይዛ ለጣቶቻቸው ጥበብን፣ ጽሕፈትን፣ ድጉሰትን ያስተማረቻቸው ኢትዮጵያውያኑ እራሳቸው እጃውን አወጡባት፡፡ ለአንደበታቸው ፊደልን ቋንቋን ያስጠናቻቸው አንደበታቸውን ከፈቱባት፡፡ በቀረጸችው ፊደል ዜና ሞቷን ጻፉላት፡፡ አያችሁት እኛ አስቀድመን ከትምህርተ ክርስትና መፍለሳችን ቤተ ክርስቲያንችንን አፈለሳት፤ አሁንም እላችኋለሁ በፍልሰታዋ እንፍለስ፡፡ ያንጊዜ አጋንንት ከሀገራችን ይፈልሳሉ፤ ጠቢባን ጥበብን ይናገራሉ ሰነፎቹ ዝም ይላሉ፤ ኢትዮጵያ ዐዋቂዎች የሚናገሩባት አርዮስፋጎስ ትሆናለች፡፡

እግዚአብሔር ከረዳኝ ዜና ፍልሰታን ጾሙ ሳያበቃ አንድ ቀን እጽፍላችኋለሁ

No comments: